ሀገራዊ ምክክሩ እውን እንዲሆንየሁላችንም ኃላፊነት ከፍያለ ነው

 ኢትዮጵያዊ ባህሎቻችንና እሴቶቻችን እየደበዘዙና እየተሸረሸሩ መምጣታቸው እንደሀገር ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል። ‹‹በእጅ የያዙት ወርቅ…›› እንደሚባለው አይነት ሆኖ የኛ የሆኑት የመከባበር፣ የመደማመጥ፣ የመቻቻል፣ የመተራረምና የመገሳሰጽ እሴቶቻችና ማኅበራዊ መስተጋብሮቻችን ወደኋላ እየተተውና እየተዘነጉ መሄዳቸው በብዙ ችግሮችና መከራዎች ውስጥ እንድናልፍ የግድ እያሉን እስካሁን ድረስ ከገባንበት ችግሮች መላቀቅ ሳንችል ቀርተናል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች እያጋጠሙን ያሉ ፈተናዎችና ችግሮች ለመሻገር አቅም የሚሆኑንን ማህበራዊ ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶቻችን አክብረን በእለት ተእለት ህይወታችን መኖር አለመቻላችን እስካዛሬዋ ቀን ድረስ ከፈተናዎቹና ከችግሮቹ ጋር ያልተገባ ዋጋ እየከፈልን አብረን ለመኖር ተገደናል።

እርስ በእርስ መከባበር፣ ሌሎችን ማክበር ፣ መቻቻል ፣ አንዱ ሲያወራ ሌላው የማዳመጥ ፣ ነገሮች በጥሞናና በተረጋጋ መንፈስ በማስተዋል ከራስ ባለፈ ለጋራ ተጠቃሚነት መመርመር ፤ ከዚህ ከፍ ያሉ ሀገራዊ ችግሮች ሲያጋጥሙ ደግሞ የሀገርን ገበና በሚሸፍኑ መንገድ ተነጋግሮ መፍትሄ ማፈላለግ ከቀደሙት አባቶቻችን የወረስናቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያሳውቁን እሴቶቻችን ናቸው።

ከዚህ ሁሉ ማህበራዊ ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶቻችን ባለቤት ሆነን ፤በነዚህም ዓለም አቀፍ እውቅና እያለን ምንም እንደሌለን፤እራሳችን በፈጠርናቸው ችግሮች እየዳከርን መገኘታችን የሚያሳዝን ከሁሉም በላይ የሚያስቆጭ ነው ፤ ቆም ብለን በኃላፊነት መንፈስ እንድናስብ የሚያስገድደን ነው።

በተለይም ወደ ቀልባችን ተመልሰን ቀደም ባሉት ጊዜያት እነዚህን እሴቶቻችንን አባቶቻችን እንዴት እንደኖሩባቸውና ምን እንዳተረፉባቸው ልናሰላስል ይገባል። ለነዚህ እሴቶች በተገዛ ህይወት መኖር አለመቻላችን የቱን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለንና ወደፊትም ሊያስከፍለን እንደሚችል መገንዘብ ይጠበቅብናል።

ጤነኛ አእምሮ ላለው ዜጋ በሀገራችን እየሆነ ያለው ያልተገባ ነገር፤በብዙ መልኩ ከራስ አልፎ ስለመጪው ትውልድ ለማሰብ የሚያስገድድ፤በሰላም ተኝቶ ማደር የሚያስችል አይደለም ።እኔ አይመለከተኝም አያገባኝም በሚል መንፈስ እጅ አጣምሮ መቀመጥን የሚያበረታታ አይደለም።

ከዚህ ይልቅ ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሄ የሚሆኑ እና በእጃችን ያሉ ማህበራዊ ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶቻችን አውቆና ተረድቶ፤ አምኖ እና የህይወት መርህ አድርጎ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል። ከዚህ ውጪ ለችግሮቻችን የሆነ መፍትሄ መሻት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ያህል ነው።

ይልቁን ወደራሳችንን በጥልቀት መመልከት፣ ማስተዋል፣በተለይ ደግሞ ችግሮቻችን እና ምንጮቻቸው ፤ያስከፈሉን እያስከፈሉን ያለውና ወደ ፊት ሊያስከፍሉን የሚችሉትን በዋጋ በአግባቡ መገንዘብ ተገቢ ነው። ለዚህ ደግሞ የዘገየነውን ያህል መፍጠን፣ መሯሯጥ ይጠበቅብናል። ይህ ደግሞ የአንድ አካል ወይም ቡድን ኃላፊነት ሳይሆን የሁላችንም የቤት ሥራ ነው።

ለዚህ ደግሞ ዛሬ ላይ ዋንኛ አጀንዳችን መሆን ያለበት ሰላምና የሰላም ጉዳይ ነው። ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት ሀገር እንድትረጋጋ፤ ሰላም እንዲሰፍን የማድረግ ሂደት የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው። ይህንኑ ተልዕኮ ከግብ ለማድረስ ታሰቦ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋሙም ከፍ ያለ እውቅና የሚሰጠው፤ ለሀገራችን መጻኢ እድል የተስፋ ብርሃን የሚያፈነጥቅ ነው።

ኮሚሽኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ ብሄራዊ መግባባትን በውይይት ለመፍጠር ታስቦ የተቋቋመ ነው። በውይይት መተማመን እና ተቀራርቦ የመሥራት ባህል በማጎልበት የተሸረሸሩ እሴቶችን የማደስ፤ ለእሴቶቹ አዲስ ህይወት የመዝራት ተልእኮን ያነገበና ለዚሁ ብቻ የተገዛ ነው።

ኮሚሽኑ ይህንኑ ተልእኮውን በስኬት ለመወጣት የሚያስችለውን ስራ እያከናወነ ይገኛል። እስካሁንም ለሀገራዊ ምክክር ሂደቱ አስፈላጊ የሆኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲሰራ ቆይቷል።

በቅርቡም እያከናወናቸው ባሉ ስራዎች ዙሪያ ለተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት እንዳመለከተው፤ በቅድመ ዝግጅት፣ በዝግጅት፣ በትግበራ እና ክትትል ምዕራፎች ከፋፍሎ በርካታ ስራዎችን ሰርቷል። በቅድመ ዝግጅት ስራዎች አጠቃላይ ቢሮ ማደራጀት፣ የሰው ኃይል ማሟላት፣ ለስራው የሚያስፈልጉ ከአዋጁ በመነሳት ድንጋጌዎችን ማዘጋጀትና በየክልሉና ከተማ አስተዳደሩ በመሄድ የወደፊቱ ባለድርሻ አካላት የሚሆኑትን የመለየት ስራዎችን አከናውኗል።

በዝግጅት ምዕራፉ፤ወደ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እስከ ወረዳ ድረስ በመሄድ ባለድርሻ አካላትን በማግኘት የመለየት ስራ ሰርቷል። በቀጣይ የሀገራዊ ምክር ሂደት ተሳታፊዎችን በመለየት አጀንዳ የመሰብሰብ ሥራዎቹ ይሰራል።

ለውይይት የሚቀርቡት አጀንዳዎች ፤ በመሰረታዊነት ላያግባቡን የቻሉ፣ ፈታኝ የሆኑ፣ ለግጭት የዳረጉን ምክንያቶች ተብለው የሚታሰቡ/ የሚገመ፤ከህዝቡ ጋር በሚደረግ ውይይት ነጥረው የሚወጡ ናቸው። በዚህ ሂደት ውስጥ የማይጠቅም እና የሚጣል አጀንዳ ስለማይኖር የሚመጡ አጀንዳዎች ተሰብስበው፤ኮሚሽኑ ባስቀመጣቸው አሰራሮች መሰረት የሚጣሩ ይሆናሉ ።

ኮሚሽኑ እስካሁን የመጣበትንና አሁን እየሄደበት ያለውን መንገድ ስንመለከት ይበል የሚያሰኝ ነው። የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ፤ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱም ስኬታማ እንዲሆን እያንዳንዱ ዜጋ ከፍያለ ኃላፊነት እንዳለበት ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም ።

ውይይት ተቀራርቦ በመነጋገር ልዩነቶች በማጥበብ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚያስችል ሁነኛ መፍትሔ ነው። ውለው ስላደሩ የጠጠሩ፤ የማይፈቱ የሚመስሉት ችግሮቻችን ተቀራርበን ስንመካከር በቀላሉ ሊፈቱ እንደሚችሉ ለመገመጥ አይከብዱም። አሁን ላይ በሚደረገው ምክክርና ውይይት የማይፈቱ ችግሮች እንኳን ቢሞሩ ከውይይቱ የምናገናቸው ተሞክሮዋች በቀጣይ የመፍትሄዎቻቸው አቅም እንደሚሆኑ ይታመናል።

አሁን ላይ ዋንኛ አጀንጃችን መሆን ያለበት ሰላማችንን ለመመለስና ዘላቂ ለማድረግ ፤መነጋገር፣ መወያየት፣መመካከርና መደማመጥ ነው። ለዚህ ደግሞ በኮሚሽኑ በኩል በተከፈተው በር እየታየ ያለው የተስፋ ጭላንጭል በደንብ ሊታይ የሚችልበትን መንገድ መከተል ፤ ተስፋችን ደምቆ ብርሃን እንዲበራ እና እውን እንዲሆን እንቅፍት የሆኑ እና ሊሆኑ የሚችሉ ጋሬጣዎች ከመንገዳችን ማስወገድ ነው ።

ይህን ማድረግ ስንችል በባለፉት ተከታታይ ዓመታት የነበረው የእርስ በእርስ ግጭትና አለመግባባት ተወግዶ ያጣነው ሰላም ተመልሶ ፣ በሰላም ወጥተን በሰላም በመግባት የሰላም አየር መተንፈስ እንችላለን። ሀገራችንን ከድህነት አረንቋ በማውጣት ከፍ በማድረግ የብልጽግና ማማ የማድረስ ህልማችን እውን ይሆናል። ቸር እንሰንብት።

ትንሳኤ አበራ

አዲስ ዘመን ኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You