ሀገራችን በማዕድን ሀብት ከታደሉ ሀገራት አንዷ ናት፡፡ ከከበሩ ማዕድናት ጀምሮ ከፍተኛ የእምነበረድ፣ የድንጋይ ከሰል፣ የተፈጥሮ ጋዝ ፣ የታንታለም ፣ የጂብሰም፣ የኖራ ድንጋይ… ወዘተ ማዕድናት እምቅ ሀብቶች ባለቤት ነች፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ እንደ ሊቲየም ያሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊነታቸው ከፍተኛ የሆኑ ማዕድናት እየተገኙ ነው፡፡
አብዛኛዎቹ የሀገሪቱ የማዕድን ሀብቶች በጥናት ያልተለዩ ፤ የተለዩትንም ቢሆን አልምቶ ጥቅም ላይ በማዋል በተገቢው መልኩ ተጠቃሚ የመሆናችንም እውነታ ብዙ ክፍተቶች እንዳሉ ይታመናል። በተለይም የማዕድን ልማቱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂና የአመራረት ሥርዓት አለመታገዙ ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን እንዳታገኝ ተግዳሮት ሆኖባታል።
መንግሥት ዘርፉን እየተፈታተኑ የሚገኙ ችግሮችን ለዘለቄታው ለመፍታት ባለፉት አምስት ዓመታት ለሀብቱ የተለየ ትኩረት በመስጠት፤ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። ተግባራዊ እያደረገው ባለው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የአስር ዓመት መሪ ዕቅድ ውስጥም የሀገር ኢኮኖሚ ምሰሶዎች ተደርገው ከተያዙት አምስት ዘርፎች አንዱ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የማዕድን ሚኒስቴር ራሱን ችሎ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮም ዘርፉን በማነቃቃት ሀገሪቱ ያላትን እምቅ የማዕድን ሀብት በአግባቡ እንድትጠቀም የሚያስችሉ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ይታመናል። ዘርፉን በማስተዋወቅ፣ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በማስፋትና በዘርፉ ለተሰማሩ አካላት የገበያ ትስስር ለመፍጠር ተስፋ ሰጪ ሥራዎችን እየሰራ ነው፡፡
በዚህም በተጨባጭ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች፤ በርግጥም የማዕድን ዘርፉ የሀገሪቱ ዋነኛ የልማት ምሰሶ የሚሆንበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን አመላካች ነው። በተለይም ዘርፉን ለማዘመን ሆነ በስፋት ለማስተዋወቅ የሚደረጉ ጥረቶች በሚመለከታቸው አካላት ሁለንተናዊ ድጋፍ የሚያገኙበት ዕድል ከተፈጠረ ዘርፉ የዜጎች የነገ ተስፋ ስንቅ መሆኑ የማይቀር ነው።
ይህም ሆኖ ግን አሁን ላይ ዘርፉን በከፍተኛ ደረጃ እየተፈታተነ ያለው ሕገወጥ የማዕድን ዝውውር የሁሉንም ትኩረት የሚሻ ፤የመላው ሕዝባችንን ንቁ ተሳትፎ የሚጠይቅ ደረጃ ላይ ከደረሰ ውሎ አድሯል። እንደ ሀገርም እያሳጣን ያለው ሀብት በቀላሉ የሚሰላ እንዳልሆነ ሲገለጽ ቆይቷል።
ችግሩ በርግጥ እንደ ሀገር እያሳጣን ካለው ሀብት አንጻር የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግምት በማስገባት ሕገወጥ የማዕድን ዝውውርን መቆጣጠር የሚያስችል ብሄራዊ ግብረ ኃይል ባለፈው አመት መቋቋሙ ይታወሳል። በዚህም እየተመዘገበ ያለው ውጤት ዘርፉ የቱን ያህል ለሕገወጦች የተጋለጠ እንደሆነ እያመላከተ ይገኛል።
በቅርቡ የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ ችግሩን በማስመልከት እንዳስታወቁት፤ ሕገወጥ የማዕድን ዝውውርን ለመቆጣጠር የተቋቋመው ግብረ ኃይል በሕገወጥ የማዕድን ዝውውር የተሳተፉ ከ100 በላይ የውጭ ሀገር ዜጎች በሕግ እንዲጠየቁና በአስገዳጅ ሁኔታ ከሀገር እንዲወጡ ተደርጓል ብለዋል።
በሕገወጥ የማዕድን ማውጣትና ንግድ ተሠማርተው የተገኙት ሕገወጦች አብዛኞቹ የውጪ ሀገር ዜግነት ያላቸው መሆኑ ፤ትኩረታቸውም በሀገሪቱ የወርቅ ሀብት ላይ የመሆኑ ጉዳይ፤ ችግሩን ለመቆጣጠር የሚደረገው ሀገራዊ ጥረት በጠንካራ ዲሲፕሊን መመራት እንዳለበት የሚያመላክት ሆኗል።
በተለይም ሀብቱ የሚገኝባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የአስተዳደርና የጸጥታ አካላት ፤ሕገወጥ የማዕድን ዝውውር ሀገርና ሕዝብን የቱን ያህል ሊጎዳ እንደሚችል ፤ ለጀመርነው ድህነትን ታሪክ የማድረግ ጥረት ትልቅ ተግዳሮት መሆንን በአግባቡ ተረድተው ፤ ኃላፊነት በሚሰማው መንገድ ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ፤ ችግሩ ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎችን በስፋት ማስተማር እንደሚያስፈልግ ያመላከተ ነው።
ሀብቱ እንደ ሀገር ዘላቂ ልማት ለማካሄድ ካለው ስትራቴጂካዊ አስተዋጽኦ አንጻር ፤ ከምርት አንስቶ እስከ ገበያ ያለው ትስስር በሕግና ሥርዓት የሚመራበትን አሰራር መፍጠር ፤በዘርፉ ያለውን የተጠያቂነት ሥርዓት ማጠናከር ያስፈልጋል፤ለዚህ ደግሞ ከሁሉም በላይ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኃላፊነት ከፍያለ እንደሆነ ይታመናል።
የፌዴራል እና የክልል የፀጥታ መዋቅሮች በጋራ ተቀናጅተው የሚሠሩበትን አሠራር መዘርጋት ፤አሠራሩ በራሱ ሊመራበት የሚገባውን ጠንካራ ዲሲፕሊንና ተጠያቂነት መፍጠር እና ተግባራዊ ማድረግ ፤ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነትና ቁርጠኝነት ያስፈልጋል።
በተለይም ሕገወጥ የማዕድን ዝውውር በስፋት በሚስተዋልባቸው የቤንሻንጉል ጉሙዝ፤ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች እና በኦሮሚያ ክልል ጉጂ አካባቢዎች የተለየ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል። በአካባቢዎቹ የሚካሄዱ የማዕድን ማልማት ሥራዎች በዘመናዊ መንገድ የሚከናወኑበት አሰራር እና ሥርዓትም መፍጠር ተገቢ ነው!
አዲስ ዘመን ህዳር 8/2016