የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ጥሩ ስም የለውም፤ ፕሮጀክት የሚጓተትበት፣ ጥራት ጥያቄ ውስጥ ያለበት፣ ሙስና ስር የሰደደበት፣ በአጠቃላይ በፕሮጀክት ማኔጅመንት ችግር የተተበተበ መሆኑ ይገለጻል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የፋይናንስ፣ የግብዓት፣ የአቅም፣ ወዘተ… ክፍተቶች እንዳሉበትም በተለያዩ መድረኮች ይጠቆማል። ይህን ሀቅ መንግሥትም፣ የዘርፉ ተዋንያንም በሚገባ ያውቁታል፡፡
በዛሬው የስኬት ዓምዳችን የምንዳሰሰው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽንም ይህን የዘርፉን ችግር ያውቀዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ከዓመታት በፊት በፕሮጀክት ማኔጅመንት፣ በአመለካከት፣ በአቅም ውስንነትና በመሳሰሉት ችግሮች በእጀጉ ተፈትኗል። በአሁኑ ወቅት ግን በሀገሪቱ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በመገንባት የሚታወቅ ሲሆን፣ 55 ነጥብ ሰባት ቢሊየን ብር ኮንትራት ያላቸውን ፕሮጀክቶች እየገነባ ይገኛል፡፡
ድርጅቱ ቀደም ሲል ፕሮጀክት ከአምስት እስከ አስር ዓመት በእጁ ላይ የሚቆይበት፣ ሠራተኛውም ሆነ አመራሩ ለፕሮጀክት ያለው አመለካከት በእጅጉ የተዛባበት ነበር፤ በሠራተኛውና በአመራሩ መካከል ያለው የግንኙነት ክፍተትና የሀብት ብክነት እንዲሁም በደንበኞች ዘንድ እስከ አለመታመን የደረሰ ችግሮች ነበሩበት፡፡
በ2011 ዓ.ም ሂሳብ ሲዘጋ ከ500 ሚሊየን ብር በላይ ኪሳራ ነበረበት፤ በ2010 ዓ.ም ላይም እንዲሁ ከ600 ሚሊየን ብር በላይ ኪሳራ ታይቶበታል፡፡ ኪሳራው ደግሞ በዓለም አቀፍ ሁኔታም የኮንስትራክሽን ዘርፉ ችግር ባልነበረበት ወቅት የተፈጠረ ኪሳራ ነበር፡፡ ኮርፖሬሽኑ ባካሄዳቸው የሪፎርም ሥራዎች ግን በጥቂት ዓመታት ውስጥ እነዚህን ችግሮች በመፍታት ወደ አትራፊነት መመለስ መቻሉን የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው ይጠቅሳሉ። ለውጡ ከተተገበረ በኋላ በ2012 ማትረፍ መጀመሩን ያስታውሳሉ፡፡
ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ በማድረግ ለሀገሪቱ ኢንዱሰትሪያላይዜሽን የሚጠቅም ተግባር እያከናወነ እንደሚገኝም ይገልጻሉ፡፡ ኮርፖሬሽኑ መድረስ ያለበት ቦታ ለመድረስ ባከናወናቸው ተግባራት ብዙ ለውጦች ማስመዝገቡን ጠቅሰው፤ ለውጦቹ ግን ጅምር ናቸው ብሎ ኮርፖሬሽኑ እንደሚያምን ተናግረዋል፡፡‹‹ወደ ለውጥ ሥራዎች ለመግባት መነሻዎቻችን አጠቃላይ የሀገሪቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ችግሮች ናቸው›› ያሉት ዋና ሥራ አስፈጸሚው፣ እንደዚህ ዓይነት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ችግሮችን ለመፍታት ለሀገሪቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለውጥ መሠረት መሆን የሚያስችል ተቋም መገንባት ላይ መሥራት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡
‹‹ሌላው የሪፎርሙ መነሻ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክቶች ናቸው፤ ፕሮጀክቶቹን እሳቸው እየመሩ እኛ መሥራታችን እሳቸው የሚመሩበትን ሥርዓት ወደ ተቋሙ ለማምጣት አስችሏል›› ይላሉ፡፡ እሳቸው ፕሮጀክቶች በሚመሩበት መንገድ ሌሎች ፕሮጀክቶችን መምራትና ማስተዳደር ቢቻል ትልቅ ስኬት ማስመዝገብ እንደሚቻል መረዳታቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከለውጡ በፊት ተቋሙ እንደ ማንኛውም የመንግሥት ተቋም መሠረታዊ ችግሮች ነበሩበት›› ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ኮርፖሬሽኑ ሰው ሳይቀየር፣ ተቋም ሳይቀየር ሪፎርምን ማስተግበር አይቻልም ብሎ የመጀመሪያ ሥራ ያደረገው ተቋማዊ ሪፎርም መሆኑን ገልጸዋል፡፡
‹‹የሰው ኃይሉ አመለካከት፣ የተቋሙ ችግሮች ሳይፈቱ ወደ ሌላ መሄድ አይቻልም ብሎ ተቋምና የሰው አመለካከት መለወጥ ላይ ሠራ፡፡ ለሠራተኛ ምቹ የሥራ አካባቢ መፍጠር፣ በሠራተኛውና አመራሩ መካከል ጥሩ ግንኙነት እንዲኖር ማድረግ ላይም መሥራት ተጀመረ። ተልእኮዎችን መፈጸም የሚያስችል አደረጃጀት መፍጠር፣ ሀብት እንዳይባክን ማድረግ፣ ገቢ ማግኛ ሥራዎችን መሥራት፣ ተቋሙ እምነት የሚጣልበት እንዲሆን ማድረግ ላይ ተሰራ፤ በዚህ ሁሉ መቶ በመቶ ስኬት ተመዘገበ›› በማለት ያስረዳሉ፡፡
ቀጣዩ ሥራ በፕሮጀክት አስተዳደር ላይ መሥራት ሆነ፡፡ ተቋሙ ፕሮጀክት በባህላዊ መንገድ የሚመራበት ነበር፡፡ ይሄ የሀገሪቱም ችግር ነው፡፡ ‹‹ዓለም አቀፍ ተቋም ለመሆን ይህን ችግር መፍታት አለብን ብለን ተነሳን፡፡ ለእዚህም ዓለም አቀፍ ከሆነው የፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ጋር በጥምረት ሠራን፤ ከዚያም የኛን የፕሮጀክት ማኔጅመንት ሪፎርም ሎጎ አዘጋጅተንለት በ2013 ተገበርነው›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡ ቀደም ሲል የአንድ ቢሊየን ብር ፕሮጀክት ሲመጣ መሥሪያ ቤቱ አንድ ቢሊየን ብር የሚያገኝ የሚመሰለው ብዙ ነበር፡፡ ፕሮጀክት ጨርሼ ይህን ያህል አትርፌ… ወጪውን ሸፍኜ አስረክባለሁ የሚል አስተሳሰብ ውስን ነበር፤ ፕሮጀክቶች አምስት፣ ስድስት፣ ሰባት፣ አስር ዓመት ይዘገዩ ነበር ሲሉም ይገልጸሉ፡፡
በሪፎርሙ እነዚህን ፕሮጀክቶች መምራት ይገባል በሚል ለማጠናቀቅ ጥረት ማድረግ ተጀመረ፡፡ በዚህም የተቋሙ ሪፎርም እንዲቀጥል ተደረገ፡፡ በዚህ ሥራም የኮርፖሬሽኑ የፕሮጀክት ማኔጅመንት አቅም ከ80 በመቶ በላይ ደረሰ፡፡ ይህን ሥራ የሚመራ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንትና ዴቨሎፕመንት ማዕክል በማቋቋም ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉንም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቅሰው፣ በዚህም ፕሮጀክት በየቀኑ የሚገመገምበት ሥርዓት እንደተፈጠረም ይገልጻሉ፡፡
ከፕሮጀክት ማኔጅመንት አቅሙ 20 በመቶው ክፍተት ከግብዓት አቅርቦት ጋር የተያያዘ መሆኑን በመለየት ይህን ችግር የሚፈታ የዲጂታላይዜሽንና ኢንደስትሪያላይዜሽን ሪፎርም ማድረግ ውስጥ ተገባ፡፡ ‹‹ይህንንም ከምን እንጀምር ብለን ተነሳን፤ የተገጣጣሚ ፕሮጀክት መምሪያችንን ማሽኖች ከተጣሉት አንስተን መሥራት ጀመርን፤ አንድ ምርት ለማውጣት ብዙ ጊዜ ይወስድበት የነበረውን ይህን ተቋም በቀናትና በወራት ሥራዎች የሚጨርስበትን መንገድ ፈጠርን›› ሲሉም የዚህ ሪፎርም ስኬት መጀመሩን ገለጹልን፡፡ በዚህም ራሳችን አልሙኒየም እየቆራረጥን መገጣጠም ውስጥ ገባን፤ ቀን ከሌት የሚሰሩ ሠራተኞችና ወርክሾፖች አሉን፤ ይህንንም በአምስት ሺ ፕሮጀክት ላይ ተገበርን፤ በአንድ ቀን ብዙ በርና መስኮት መሥራትና መግጠም ቻልን›› ብለዋል፡፡
ከግብዓትና ከውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር በተያያዘ በፕሮጀክቶች ላይ የሚደርሰውን መጓተት ለመቀነስ ደግሞ እንደ አልሙኒየምም፣ እምነበረድ፣ ሴራሚክ የመሳሰሉትን ከውጭ ሀገር የሚመጡ የማጠናቀቂያ ግብዓቶች በሀገር ውስጥ ማምረት አለብኝ፤ ብሎ እየሰራ ነው፤ የጂብሰም ፋብሪካ ተክሏል፤ የማርብል ፋብሪካ እየገነባ ነው። በሲሚንቶ ኢንቨስትመንት ለመሰማራትም ከሌሎች ኩባንያዎች ጋር እየሰራ ይገኛል፤ ለተገጣጣሚ ቤቶች አካላት ሥራ በራሱ ባለሙያዎች ሞልዶችን በማምረትና ከውጭ የሚመጣውን በማስቀረት በአንድ ቀን የአንድ ጂ+4 ህንጻ ተገጣጣሚ አካላት ማምረት ችሏል፡፡
ሥራዎቹን ዲጂታላይዝ ማድረግ አለብኝ ብሎም በመነሳት ለሥራው የሚያስፈልገውን ሶፍትዌር ከውጭ ከማስመጣት ይልቅ በራስ አቅም ማልማት ውስጥ ገባ። ይህንንም እውን አድርጎ ፕሮጀክቶቹን ከቢሮ ሆኖ መከታተል፣ ሀብትን በሚገባ ማስተዳደር የሚቻልበትን ሁኔታ ፈጠረ፡፡ ‹‹በዚህም የነዳጅ ብክነትን በግማሽ ቀነሰ፡፡ ከ2012 ጋር ሲነጻጸር በ2015 በጣም ብዙ ሚሊየን ብር መቆጠብ ቻለ፤ 12 ሚሊየን ሊትር ይጠቀም የነበረውን ነዳጅ ወደ 6 ሚሊየን አወረደ፡፡ የሥራ አፈጻጸሙም በአራትና አምስት እጅ አደገ›› ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጸሚው ጠቅሰዋል፡፡
ይህን ሲጨርስ ደግሞ ሌላ ክፍተት ማየቱን ገለጸ፤ እንደ ሀገር የፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ቢኖርም፤ ኮርፖሬሽኑም የራሱ የማኔጅመንት ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ያስፈልገኛል ብሎ ተነሳ፡፡ ለእዚህም የስልጠና ማዕከል ከፍቷል፡፡ በፕሮጀክቶች የሚደረግ ክትትል ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቅሰዋል፡፡ እኛ የጠቅላይ ሚኒስትሩንና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሮጀክቶችን ብንሰራ እንመርጣለን ሲሉም ገልጸው፣ አዲስ አበባ ላይ ከንቲባዋ የጠቅላይ ሚኒስትሩን መንገድ ተከትለው ፕሮጀክት እየተከታተሉ ናቸው፤ የክልል መንግሥታትም ይህን ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ሌሎች ተቋማትም ይህን ማድረግ አለባቸው ሲሉ ያስገንዝባሉ።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከኢትዮጵያ ወጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ በማመንም ወደ ሥራ መገባቱን ጠቅሰዋል፡፡ ለእዚህና የተቋሙን የኢንዱስትሪ ሪፎርም ለመሥራት በጣም ብዙ የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፣ ሀገር ቅድሚያ የምትሰጠው ለሌላ ጉዳይ ነው›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹እኛ መሥራት እየቻልን ዶላር ሰርተን ማግኘት የሚያስችለን አቅም እያለን ለምን ዶላር እንጠይቃለን ብለን በአፍሪካ ጅቡቲ ላይ ቅርንጫፍ ከፍተናል፤ ከዚህ በምናገኘው ዶላር ኢንዱስትሪያችንን ማስፋፋት ጀምረናል፤ ለእዚህም ከመንግሥት የውጭ ምንዛሬ አልጠየቅንም፤ ላለፉት ሁለት ሶስት ዓመታት ከመንግሥት ምንም የውጭ ምንዛሬ አልወሰድንም›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በጅቡቲ የጀመረውን ቅርንጫፍ የመክፈት ሥራ በኬንያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ መቀጠል አለብኝ ብሎ እየሰራ ነው፤ ደቡብ አፍሪካና ሌሎችም ጥያቄ እያቀረቡለት መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ ኮርፖሬሽኑ የውጭ ምንዛሬ የሚያገኝበትን መንገድ ለመጨመር መሥራቱን ቀጥሏል፤ በኦሞ ኩራዝ ፕሮጀክት እያካሄደ ያለውን የግብርና ሥራ ትራክተርና የመሳሰሉትን በመግዛት ባለሙያዎች ቀጥሮ በሌላ በ600 ሄክታር ማሳ ላይ ሩዝ እያለማ ይገኛል፤ ምርቱንም ከውጭ ባለሀብቶች ጋር በመሆን ለውጭ ገበያ ወደሚሆን ምርት ለመቀየር እየሰራ ይገኛል፡፡
ለእነዚህ ሁሉ ስኬቶቹ የመጀመሪያው መሠረት የአመራሩና የሠራተኛው ቁርጠኝነት ነው ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ይጠቅሳሉ፤ በርካታ የተቋሙ ሠራተኞች በቁጭት ውስጥ ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ፤ አዳዲስ አመራሮችን ከውስጥም ከውጭም ማምጣቱ፣ የመንግሥት ቅንነት የተሞላበት ድጋፍ ሌሎች መሠረቶች ናቸው፡፡ ተቋሙ ይህን ሁሉ ውጤት አሳይቶም ‹‹እኛ ተሳክቶልናል ብለን አንናገርም፤ መስመር ውስጥ ገብተናል ነው የምንለው፡፡ ስኬት የሚባለውን ነገር ገና አልቀመስነውም›› ሲሉ ነው ዋና ሥራ አስፈጻሚው የሚናገሩት፡፡ ‹‹ስኬት የሚባለው አንደ ሀገርም አንደ ዓለምም እኛ ከውጭ ተቋም በተሻለ መፈጸም ከሚያስችለን እንዲሁም መንግሥት እና ሕዝብ ዛሬ የሚፈልጉትን ዛሬ መፈጸም ደረጃ ስንደርስ ስኬታማ ሆነናል እንላለን›› ብለዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ማህበራዊ ኃላፊነትን እየተወጣም ነው፡፡ ይህንን ሥራ ብሎ የጀመረው በተቋሙ ውስጥ ነው፡፡ ‹‹የኛ ሠራተኞች ደመወዝ ዝቅተኛ ነው፡፡ ሠራተኞቹን ለማነቃቃት ተቋሙ ምን ማድረግ አለበት፤ ከደመወዝ ውጭ ምን ልንደግፋቸው እንችላለን ብለን እንደ ማኔጅመንት ተወያይተናል›› ይላሉ፡፡ ‹‹ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ሠራተኞቻችን መካከል አንዳንዶቹ ምሳ አይበሉም ነበር፤ ምሳ ይዞ የሚመጣውም ቢሆን ምግቡ ለመሥራትና ሰውነቱን ለመገንባት አቅም የሚፈጥርለት ዓይነት አልነበረም፡፡ ልጆቹን ሳያበላ ቢሮ ለማጽዳትና ለማስተካከል ሌሊት ቢሮ የሚገባ ነበር›› ሲሉ ያስታውሳሉ።
ይህን ሁኔታ በመቀየር ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው 400 ሠራተኞች ላለፉት ሶስት ዓመታት ምሳ በነጻ እንዲመገቡ ተደርጓል፡፡ ስለዚህ ሠራተኛው ቢሮ ይዞ የሚመጣውን ምግብ ለልጁ መተው ይችላል፡፡ ከፈለጉም ምሳ በምሳ እቃ ስለሚሰጣቸው ይህንንም ወደ ቤታቸው መውሰድ ይችላሉ፡፡ ሌላው ሠራተኛም በካፍቴሪያ ትንሽ ከፍሎ የሚደገፍበት ሥርዓት ተፈጥሯል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ከዚያም ወደ አካባቢው ወጣ፡፡ ወደ ግቢው የሚወስደውን መንገድ አሳመረ፡፡ በአቅራቢያው ያለውን የወረዳ አስተዳደር ህንጻ አደሰ፤ የወረዳውን አመራር በጥራት ሽልማት ድርጅት እንዲሰለጥን አደረገ፤ በዚህም ጥራት ያለው አገልገሎት መስጠት እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ ሌሎች በአካባቢው የሚገኙ የተቸገሩ ሰዎችን ማገዝ አለብን የሚል አቋም በመያዝ የምገባ ማዕክል አቋቁሟል፤ በዚህም አመራሩና ሠራተኛው ገንዘብ እያዋጣ በየቀኑ ወደ ሁለት መቶ አካባቢ የሚሆኑ ችግረኞች ምገባ እየተካሄደ፣ ቡና እንዲጠጡ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በፕሮጀክቶቹ አካባቢዎችም እንዲሁ ለማህበረሰቡ መሠረተ ልማቶችን ይገነባል፡፡ በቅርቡ መገጭ ግድብ አካባቢ ከሃያ ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ ሰርቶ የሕብረተሰቡን የመንገድ ጥያቄ መልሷል ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቅሰዋል። ላለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ተመሳሳይ መሠረተ ልማቶችን በመገንባት ሕዝብን ተጠቃሚ አድርጓል ብለዋል፡፡
ሁሉም የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራ በእቅድ እንደሚመራም አመልክተው፣ ከገቢያችን ከትርፋችን የተወሰነውን መቶኛ ለእዚህ አላማ በመመደብ ብዙ የተቸገሩ ሰዎችን ቤቶች ሰርተናል፤ የከተማ አስተዳደሮችና ክልሎችን ደግፈናል ሲሉ ጠቅሰዋል፡፡ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚያስተዳድረውን የሰው ሰራሽ የአካል ድጋፍ ማምረቻ ማዕከል ብዙ ሚሊየን ብር በማውጣት በነጻ ሙሉ ጥገና ማድረጉንና አንዳንድ ግንባታዎችን ማካሄዱን፣ የፌዴራል ፖሊስ የጀግኖች ማዕከል ግንባታንም እንዲሁ ሙሉ ወጪ ሸፍኖ መገንባቱን ጠቅሰዋል፡፡
ተቋሙ አቅሙን እያሳደገ አስፈላጊ በሆኑት አካባቢዎች ላይ አተኩሮ መሥራት ይፈልጋል፤ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በሚገቡበት ላይ እያተኮረ፣ ከኢትዮጵያ ውጭ መሥራት አለብኝ ብሎ እየሰራ ይገኛል፡፡ አብዛኞቹ ሥራዎቹ ከኢትዮጵያ ውጭ መሆን አለባቸው የሚል አቋምም አለው፡፡ በአብዛኛው በኮንስትራክሽን ግብዓቶች ማምረት ሥራ መሳተፉን ጀማምሮታል፡፡
‹‹በጥራት፣ በዋጋ መወዳደር፣ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ዋጋ ማረጋጋት የሚችል ተቋም ለመገንባት ትልቅ ሥራ እንሰራለን›› ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ይገልጻሉ፡፡ ይሄን ተቋም አፍሪካዊ ማድረግ መቻሉን፤ ቀጥሎ ደግሞ ዓለም አቀፋዊ ለማድረግ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡ ደረጃችን ወርቅም ይሁን መዳብ አፍሪካ ላይ ተቋማችንን ለማሳየት ያደረግነው ሙከራ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ይላሉ፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን የተሰጠንን እድል ተጠቅመን ከሠራን ከዚህም በላይ መሥራት እንችላለን፡፡ ብዙ መሥራት የሚችል አእምሮ ያላቸው ባለሙያዎች፣ ይህን ማስፈጸም የሚችሉ አመራሮች እየተፈጠሩ ናቸው፤ መንግሥታችን በፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ ያለው እይታ እና እየተፈጠረ ያለው ንቅናቄ ቀላል አይደለም፤ ይህን ሁሉ ምቹ ሁኔታ ልንጠቀምበት ይገባል›› ሲሉም ያስረዳሉ፡፡
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ህዳር 8/2016