የነገይቱ ኢትዮጵያ መልክ  “ከዛሬ ጋር ሙግት!?”፤

ከዛሬ ይልቅ ስለ ነገ ማሰብ የሰው ልጆች ሁሉ ባህርይ መሆኑን የበርካታ የጥናት መስክ ምሁራን እውነታውን ያረጋግጡልናል። ለእኛ ለኢትዮጵያ ልጆችም እንዲሁ፡፡ ትናንት ለየትኛውም የአዳምና የሄዋን ዘር የትዝታ፣ የቁጭትና የነበር ወግ ማህደር ነው፡፡ “ትናንትን እንዴት ነበርክ?” በማለት ከታሪኩ ለመማርና ለመተራረም ተፈልጎ ካልሆነ በስተቀር “እንዴት ነህ?” ወይንም “እንዴት ትሆን ይሆን?” በማለት በዛሬና በነገ ወንጠፍት ለመፈተሽ እንሞክር ብንል ከኃላፊ ዘመን ጋር ለመኳረፍ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ፋይዳ አይኖረውም፡፡

“ጊዜ በረርክ በረርክ፣

ጊዜ በረርክ በረርክ፣

ግና ምን አተረፍክ፣

ግና ምን አጎደልክ?

ሞትን አላሸነፍክ፣

ሕይወትን አልገደልክ፡፡”

ብለን ብንፎትተውም ሆነ ብንገረምበት አለያም ብንፈላሰፍበት ምንም ጠብ የሚያደርግለን ነገር ስለሌ ድካማችን ከጉንጭ አልፋነት አያልፍም።

ነፍሰ ሄሩ የሀገራችን ብዕረኛ ከበደ ሚካኤል “አዝማሪና የውሃ ሙላት” በሚለው ዘመን ተሻጋሪ ግጥማቸው ስለ አንድ ማሲንቆ ገዝጋዥ አዝማሪ ድንቅ ቅኔ ተቀኝተዋል። የዋሁ አዝማሪ ከአፍ እስከ ገደፉ የሞላ ፈረሰኛ ወንዝ ራርቶለት ጎድሎ እንዲያሻግረው ለመለማመጥ ዳር ላይ ቆሞ አንጀት በሚያራራ ዜማ ወንዙን ሲያሞጋግሰው ያስተዋለ አንድ መንገደኛ ምስኪኑን መሲንቆኛ የመከረው እንዲህ በማለት ነበር፡፡

“እስኪ ተመለከተው ይህ አወራረድ፣

ያልሰማው ሲመጣ የሰማው ሲሄድ፤

ድምጡን እያውካካ መገስገሱን ትቶ፣

ማን ይሰማኝ ብለህ ትደክማለህ ከቶ፡፡”

ገጣሚው “ልብ ያለው ልብ ይበል” ብለው ሊመክሩን የፈለጉት “ጊዜንም” በአግባቡ ተጠቅመን ለውጤትና ለፍሬ ካላስገበርነው በስተቀር የነበር ወግ እያላመጥን ወይንም የነገን እለት እየጎመጀን ብቻ “ወይ ጊዜ! አይ ጊዜ!” እያልን በአራራይ ዜማ ብናሞጋግሰውም ሆነ በትዝታ ቅኝት ብናደናንቀው አለያም ብናማርረው ትርጉም አይኖረውም፡፡ ይልቅስ ጊዜን በጊዜ አሸንፈን ካልረታነው በስተቀር በጊዜያት ውስጥ ያከማቸነውን በጎ ትሩፋቶች ሁሉ አስረግፎንና ባዶ እጃችንን አስቀርቶ “ምርኮኛ” በማድረግ ለነገ ፍርድ እንዳያሸጋግረን አጥብቆ ማሰቡ ብልህነት ነው፡፡

“የግድግዳ ሰዓቴ የሴኮንድ ቆጣሪ ያለ እረፍት ቲክ! ቲክ! እያለ የመጓዙን ድምጽ የሚያሰማኝ ዛሬህ በከንቱ እንዳያመልጥህ እኩል በመራመድ በእጁ የያዘውን ዕንቁ አስጥለው እያለ ሊመክረኝ ፈልጎ ይመስለኛል።” እንዳለው ጠቢብ፤ ገስጋሹን ጊዜ በአግባቡ ጨምቀን አምቆ የታቀፈውን “ጣዝማ ማር” ከእጁ ካላስጣልነው በስተቀር (ጣዝማ ማር አንድም ለጥፍጥና አንድም ለመድኃኒትነት መዋሉን

 ልብ ይሏል) እኛን ወደ ኋላ እያስቀረ የያዘውን ሀብት ይዞ እንደ ወንዙ አወራረድ እያውካካና እየሳቀብን መገስገሱን አያቆምም፡፡ ሀገራዊ ብሂላችንስ ቢሆን፡ – “ጊዜ ወርቅ ነው፤ ግና ኃላፊም ነው፡፡” በማለት የሚያስተምረን ስለዚሁም አይደል፡፡

ከላይ የተጠቀሰውን “ጊዜ በረርክ በረርክ” ስንኞች ያዋቀረው ብዕረኛው ደበበ ሰይፉ በሌላ ግጥሙ ጊዜን በአግባቡ ተጠቅመን እንዴት ፍሬ እንደምናዘምርበት በ1967 ዓ.ም በጻፈውና “የምቾት ሱስ ለሌለባቸው ለሀገር ልማትና ዕድገት የትም መቼም ቀና ደፋ ለሚሉ” በሚል የግርጌ ማስታወሻ አስደግፎ “በትን ያሻራህን ዘር” በሚለው ግጥሙ የመከረን እንዲህ በማለት ነው፡፡

“በጓጥ በስርጓጉጡ፤ በማጥ በድጡ፤

እንደ ተንጋለልክ እንደ ዘመምክ፣

ትንፋሽህን እንደቋጠርክ፣

ልል ቀበቶህን እንዳጠበክ፣

የተልዕኮህን አባዜ፣

የሕይወትህን ቃለ-ኑዛዜ፣

ወርውር!

የእጅህን ዘገር፡፡

በትን! ያሻራህን ዘር፡፡

ይዘኸው እንዳትቀበር፡፡

ጊዜን ማሸነፍ የሚቻለው በሥራና በውጤት ብቻ እንጂ “ሀሳብ ሹሩሩ” በማለት ከንጋት እስከ ፀሐይ ግባት ብናንጎራጉሩ ትርፋችን ምንም፤ ድካማችንም ከንቱ መሆኑን ልብ ማለቱን ከቶውንም ልንዘነጋው አይገባም። ከሰማይ በታች ለሚከናወን ለማንኛውም ነገር ጊዜ አለው” እንዳለው የቅዱስ መጽሐፉ ጠቢብ፤ ጊዜን በአግባቡ ሥራ ላይ ከማዋል ይልቅ “እንደ ኦሪታዊው ኢያሱ ፀሐይን ካላቆምን ብለን ግብ ግብ ብንፈጥር” የጊዜን መብረር ለአፍታም ቢሆን ልንገታ ስለማንችል ጠቡ ከራስ ጋር፤ ኩሪፊያውም ከማንነት ጋር ይሆን ካልሆነ በስተቀር አንዳች ጠብ የሚል ፋይዳ አይኖረውም፡፡

“የአራት ሴናሪዮዎች” ግምገማ፤

ከሦስት ዓመታት በፊት ዴስቲኒ ኢትዮጵያ በተባለ ሀገር በቀል ተቋም አማካይነት ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ 50 ያህል በተለያየ ደረጃ የሚገኙ ፖለቲከኞች፣ መሪዎች፣ የማህበረሰብ አንቂዎችና በጎ ፈጣሪ እንደሆኑ የታመነባቸው ግለሰቦች ለሦስት ያህል ጊዜያት ተገናኝተው የነገይቱ ተናፋቂ ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ምን ሆኖ ለማየት እንደሚጓጉ የጋራ አግባቢ ሃሳብ ላይ ደርሰው ነበር፡፡

በተከታታይ መርሃ ግብሮችም በኢትዮጵያ የሃይማኖት ጉባዔና በሰላም ሚኒስቴር ጥምረት ከሀገሪቱ ቤተ እምነቶች የተውጣጡ መምህራንና ምሁራን ቀደሚዎቹ 50 ተሳታፊያን በነደፏቸው አራት ሴናሪዮዎች ላይ ጥልቅ ውይይቶችን በማድረግ የነገይቱን ኢትዮጵያ መልክና ውበት ላይ ምክክሮች አድርገው ነበር፡፡ የዚህን ምክክር ክራሞት በተመለከተ ይህ ጸሐፊ ጥር 27 ቀን 2013 ዓ.ም በዚሁ ገጽ ላይ ምልከታውን በዝርዝር ማጋራቱ አይዘነጋም፡፡

በተወያዮቹ የቀረቡት ሴናሪዮዎች በቁጥር አራት ሲሆኑ ኢትዮጵያን በ2032 ዓ.ም ሊገጥሟት ይችላሉ ብለው የገመቷቸው አማራጮች የተንጸባረቁባቸው ነበሩ። የመጀመሪያው በሠባራ ወንበር (Broken Cahir) የተወከለ ሴናሪዮ ሲሆን ዋነኛ ይዘቱም የሀገሪቱ ዜጎች በመነጋገር፣ በመመካከርና በመግባባት ችግሮችን እየፈቱ ካልሄዱ በስተቀር ሊያጋጥም የሚችለው የሥርዓት አደጋ የከፋ ሊሆን ይችላል የሚል መደምደሚያ የተደረሰበት ነበር፡፡

የዚህ አደጋ ምክንያቱ ደግሞ በሰነዱ ውስጥ የተገለጸው እንዲህ ተብሎ ነበር። “በሰባራ ወንበር ሴናሪዮ ጠንካራ በሚመስል፣ ነገር ግን ገና ሲነኩት እንደሚሽመደመድ፣ ቀላል ክብደትን እንኳን የማይሸከም ወንበር የተመሰለ ነው፡፡ የአቅም ማጣቱ በማሕበረሰቡ ውስጥ በየደረጃው ለሚነሱ የልማት ፍላጎቶች ተግባራዊ ድጋፍ ለመስጠት እንዳይቻል ያደርጋል…፡፡” ይላል፡፡

ሁለተኛው ሴናሪዮ የተወከለው አፄ በጉልበቱ (Hegemony) በሚል ስያሜ ሲሆን ሴናሪዮው የተብራራውም፤ “ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ የኢኮኖሚውን አካሄድ፣ የአካባቢ መጎሳቆልንና የሕዝብ እድገት ጫናዎችን ለመመከት ቁጥጥር ተኮር ሥርዓትን መከተል ወሳኝ መሆኑን ያምናል…።” በሚል ትንተና ነበር፡፡

ሦስተኛው ሴናሪዮ የፉክክር ቤት (Divided House) የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ በሰነዱ ውስጥ የተብራራውም እንደሚከተለው ነበር። “የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል እንደሚባለው የተለያዩ ቡድኖች እና ክልሎች ያገኙትን አዲስ ነፃነት እነርሱ እንደፈለጉትና እንደመሰላቸው መጠቀማቸውን የሚያሳይ ሲሆን ከመንግሥት አንስቶ እስከ ቤተሰብ ደረጃ በሁሉም የማሕበረሰብ ክፍሎች ውስጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶችንና ክፍፍሎችን የሚያሳይ ነው…” የሚል ነበር፡፡

አራተኛው ሴናሪዮ ንጋት (Dawn) በሚል ስያሜ የተለየ ሲሆን ማብራሪያውም እንደሚከተለው ይነበባል፡፡ “የንጋት ሴናሪዮ የኢትዮጵያ እድገት ደረጃ በደረጃ ዕውን የሚሆንበትን ተስፋ ያዘለ ነው፡፡ የሙሉ ቀን ብርሃን አልሆነም፡፡ ነገር ግን የአዲሱ ቀን ወገግታ ጀምሯል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ሕጋዊና ተቋማዊ ማሻሻያዎችን እና የዕርቅ ሂደቶችን አጠናክረው በመተባበር የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውን እያስቀጠሉ ነው፡፡

በሀገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ደረጃዎች ሥር የሰደዱ ማሕበራዊ ቅራኔዎች በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረጉ ውይይቶች እልባት ማግኘት ጀምረዋል። ከቅራኔና ከጥላቻ ይልቅ የይቅርታና እርቅ አስተሳሰቦች በማሕበረሰቡ ዘንድ እንዲሁም በመደበኛ እና ማሕበራዊ መገናኛዎች በየዕለቱ ተቀባይነታቸው እየጨመረ መጥቷል፡፡ የዴሞክራሲ ተቋማትና  ኢኮኖሚው ደረጃ በደረጃ እየተገነቡ፣ በጋራ ርእይ ላይ የተመሠረተ አንድነት በመፍጠር ላይ ይገኛል።” የሚል ነበር፡፡ በማጠቃለያው ላይም “ኢትዮጵያ ውስብስብ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማሕበራዊ ተግዳሮቶች ከፊቷ ተደቅነዋል፡፡ ምላሾቻችን ምን ይሆናሉ?” የሚል ጥያቄ ለተሳታፊያኑ ተሰንዝሮ ነበር፡፡

ጥቅምት 28 ቀን 2016 ዓ.ም የመጀመሪያውን ምክክር ያከናወኑ የቤተ እምነት መሪዎችና ምሁራን እንደገና ተሰባስበው የሦስቱን ዓመት ጉዞ ለመገምገም ዕድል አግኝተው ነበር፡፡ በዚሁ የምክክር መርሃ ግብር ላይ በርካታ ሃሳቦች የተንሸራሸሩ ሲሆን፣ በአጠቃላይ የተደረሰበት የጋራ መግባቢያ ድምዳሜ ዛሬም ኢትዮጵያ ወደምንመኘው ንጋት እንዳትቃረብ በበርካታ ተግዳሮቶች መከበቧን የሚጠቁሙ ነበሩ፡፡

ኢትዮጵያ በቀዳሚዎቹ ሥርዓተ መንግሥታት ያልተፈተነችባቸው ችግሮች ነበሩ ለማለት ያዳግታል። ችግሮቹም ብዙ ሀገራዊ ቀውስ አስተናግደው አልፈዋል። አንዳንዶችም “በደረታቸው እየተሳቡ” በመምጣት ዛሬም ድረስ ብሔራዊ ፈተናዎቻችን በመሆን እየተገዳደሩን ይገኛሉ፡፡

የብሔራዊ ችግሮቻችን መልኮችም ሆኑ ቅርጾች የተለያዩ ቢሆኑም “በንጋት” የሚመሰለውን የነገ ተስፋችንን ያዘገዩ ካልሆነ በስተቀር የውጋጋኑን በረከትና ትሩፋት ግን ማየታችን የሚቀር አይደልም። የከበቡን ተግዳሮቶች የበዙ ቢመስልም በንግግርና በምክክር፣ በውይይትና በስክነት፣ በመደማመጥና ተቀራርቦ በመተያየት የማይፈታ ምንም ችግር ሊኖር እንደማይችል ዜጎች በሙሉ ከልብ ልንቀበለው እንደሚገባ ወቅቱ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ጉጉት እየጠበቀን ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያን ንጋት የሚያደበዝዙ፣ ተስፋዋንም የሚፈታተኑ እጅግ በርካታ የፈተና ጋሬጣዎች ከውስጥም ሆነ ከውጭ ከፊታችን ቢጋረጡም ዜጎች በአንድ ልብና ሃሳብ ምህዋር ውስጥ የሚሰለፉ ከሆነ የነገይቱ ሀገራችን ተውባና ደምቃ በዓለም ፊት እንደምትታይ ጅምር ሀገራዊ ትሩፋቶቿ ምስክሮች ናቸው፡፡

በተለየ ሁኔታና በተደራጀ ዝግጅት ተልዕኮውን ለማካሄድ እየተንቀሳቀሰ ያለው የምክክር ኮሚሽን በሙሉ ኃይሉ ሥራውን ጀምሮ ሲፈጽም የምንመኘው የነጋችን የንጋት ተስፋ እውን እንደሚሆን መጠራጠር አይቻልም፡፡ ስለዚህም የነገይቱ ኢትዮጵያ መልክ ዛሬ እንደሚስተዋለው በጥልፍልፍ ፈተናዎች ወይቦ ብቻ አይቀርም፡፡

የተስፋዋ ወጋጋን ደምቆ የሚወጣበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ ዜጎቿም ከቁዘማ ወጥተው በደስታ ዜማ አድማሳችን መድመቁ አይቀርም፡፡ ይህቺን ኢትዮጵያ ነው ነገ ማየት የምንፈልገው፡፡ ዛሬንና ነገን ከማስዋብ ይልቅ በትናንት ቁጭት መብከንከኑ ወይንም “ለምን ሊሆን አልቻለም ነበር” በማለት ከታሪክ ጋር ግብግብ ለመፍጠር እልህ መያያዙ እጅግም ለዛሬያችን መፍትሔ ስለማይሆን የሚበጀው የነገ ተስፋችን ንጋት ደምቆ እንዲፈካ፣ ገጣሚው እንደመከረን፤ የእጃችንን መልካም ዘር በመዝራት የድርሻን መወጣት ብቻ ነው፡፡ ሰላም ለሕዝባችን፤ ለዜጎችም በጎ ፈቃድ፡፡

 (በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)

gechoseni@gmail.com

አዲስ ዘመን ህዳር 8/2016

Recommended For You