የሀገር መከላካያ ሠራዊት በየዘመኑ የተሰጠውን ሀገር እና ሕዝብን ከየትኛውም አደጋ የመታደግ ኃላፊነት በላቀ የሀገር ፍቅር ፣ ጀግንነት እና ሕዝባዊነት በመወጣት ከፍ ያለ ስምና ዝና ያተረፈ ነው ። በዓለም አቀፍ ደረጃም በተሰማራባቸው የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ስኬታማ ግዳጆችን በመወጣት ዓለም አቀፍ እውቅናው ከፍ ያለ ነው።
ከሕዝብ አብራክ የወጣው ይህ ሠራዊት ፤ በተሰማራባቸው የግዳጅ መስኮች ሁሉ በከፍተኛ ዲሲፕሊን እየተመራ ፤ ሕይወቱን ያለመሳሳት ለሀገርና ለሕዝብ እየከፈለ ያለ ፤ በዚህም በመላው ሕዝባችን ከፍተኛ ከበሬታን ያተረፈ ፤ የሀገር ምሽግ፣ የሉዓላዊነትና ደህንነት ጥግ ነው።
በሰላም ወቅትም የሕዝቡን ኑሮ እየኖረ ፤ ያለውን በማካፈል የሚታወቅ ፤ ሳይተርፈው ካለው እየቀነሰ የተለያዩ ሕዝባዊ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን ፣ ትምህርት ቤቶችን ፣ ጤና ጣቢያዎችን .. ወዘተ በመገንባት የሚታወቅ ፤ በሀገሪቱ የልማት ታሪክ ውስጥ የራሱን ዐሻራ እያስቀመጠ ያለ የተከበረ ሠራዊት ነው ።
የሀገር ዳር ድንበርም ሆነ የሕዝባችን ሰላምና መረጋጋት አደጋ ውስጥ በወደቀባቸው ጊዜያት ፤ ፈጥኖ በመገኘት በአኩሪ መስዋዕትነት የሀገርን ህልውና ከስጋት ፤ የሕዝባችንን ሰላምና መረጋጋት ከጥፋት ኃይሎች ከንቱ ሴራ በመታደግ ሀገር እንድ ሀገር ሉዓላዊነቷን ጠብቃ እንድትቀጥል ሕግንና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱ እንዲከበር ውድ ሕይወቱን እየሰዋ ሀገር ያቆመም ነው።
ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የሀገርን ህልውና ሆነ ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን ካጋጠሙ መልከ ብዙ ተግዳሮቶችን በቁርጠኝነት በመጋፈጥ ፤ ሀገር እንደ ሀገር የምጥቀጥልበትን አስቸጋሪ ግዳጆች ለሕይወቱ ሳይሳሳ በታላቅ ጀግንነት እና ገድል መጣት የቻለ ፣ በዚህም ሀገር እንደ ሀገር እንድትቀጠል ያስቻለ ነው።
ፋታ በሌለባቸው አስቸጋሪ ግዳጆች ውስጥ ራሱን እያበቃ፣ ለበለጡ ስኬታማ ግዳጆች የሚያበቁ አቅሞችን እያጎለበተ ያለው ይህ ሠራዊት ፣ እየተፈተነና በፈተናዎች ውስጥ እየጠነከረ በተከበረ ማንነቱ የውስጥም ሆነ የውጭ ጠላቶቻችን ሀገርና ሕዝብን እየጠበቀ ይገኛል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት የሠራዊቱን ኅብረ- ብሄራዊነትን በማስጠበቅ በሰው ኃይልና በትጥቅ ለማዘመን በተደረጉ መጠነ ሰፊ ሥራዎች ፤ ሠራዊቱ አሁን ላይ የሚወክለውን ታላቅ ሕዝብና ሀገር በሚመጥን ቁመና ላይ ነው። ለሀገሩ እና ለመላው ሕዝባችን የተጨማሪ ክብርና ሞገስ ምንጭ እየሆነም ይገኛል።
የዛሬዋን ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር ነገ ላይ ሆና ለማየት የምንሻትን ታላቂቱን ኢትዮጵያ እንዲመጥን ታስቦ እየተገነባ ያለው ይህ ሠራዊት ፤ በቀጣይ ሀገሪቱ በቀጣናው ያላትን ተደማጭነት ከማሳደግ ባለፈ፤ በቀጣናው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ለሚደረጉ ጥረቶች ትልቅ አቅም እንደሚሆን ይታመናል።
ይህ ሠራዊቱ ዛሬ የሆነውንም ሆነ፣ ነገ ሊላበሰው ያለው ቁመና ያሳሰባቸው የውስጥና የውጭ ጠላቶች፤ በሠራዊቱ ላይ ሰፊ ስም የማጠልሸት ዘመቻ ከጀመሩ ውለው አድረዋል። ሠራዊቱ በሕዝባችን ልብ ውስጥ ያለውን የገዘፈ ከበሬታ ለመሸርሸር በብዙ የፈጠራ ትርክቶች ሌት ተቀን ሲዳክሩ ይታያል።
ይህ ጥረታቸው ዕለት ተዕለት ከሚታየው የሠራዊቱ ተጨባጭ ማንነት አንጻር ፣ ከተራ አሉባልታ ባለፈ በሠራዊቱና በሕዝቡ መካከል ያለውን ጠንካራ መተማመን እና በመተማመን ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ስጋት ውስጥ ሊከተው አልቻለም። ከዚያ ይልቅ የሠራዊቱን ሕዝባዊነት የበለጠ እንዲጠናከር አቅም እየፈጠረለት ይገኛል ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ መከላከያ ሠራዊት የሀገር ምሽግ፣ የሉዓላዊነትና ደህንነት ጥግ መሆኑን በተጨባጭ ያየውና ምስክር የሆነበት ታሪካዊ ክስተት ከመሆኑ አንጻር ፤ በሠራዊቱ ላይ የሚካሄዱ የስም ማጥፋት ዘመቻዎች ትርጉም አልባ ከመሆን የዘለለ ዕድል አይኖራቸውም!
አዲስ ዘመን ህዳር 7/2016