የተለያዩ ሀገራት በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ ሀገራዊ ችግሮችንና መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ያጋጠሙ አለመግባባቶችን አካታች በሆነ ሀገራዊ ውይይት መፍታት ችለዋል። በዚህም ዘላቂ ሰላም በማስፈን የተሳካ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖላቲካዊ ለውጥ አምጥተዋል። ለአብነት ያህል ደቡብ አፍሪካን መጥቀስ ይቻላል። ዜጎቿ ሀገሪቱን እንደ ሀገር የኅልውና አደጋ ውስጥ ጥሎ የነበረውን ችግር ይቅርታ እና እርቅን መሠረት ባደረገ ሀገራዊ ውይይት በሀገራቸው ጉዳይ ተገልለው የነበሩ ቡድኖችን ጭምር እንዲደመጡ እድል በመስጠት ችግሮቻቸውን ፈትተዋል።
ይሄ ደግሞ ለኢትዮጵያ እንደ አንድ አብነት ሊወሰድ የሚችል ተግባር ነው። ምክንያቱም ሀገራዊ ውይይቶች ለዘመናት የነበሩ ቁርሾዎችንና አለመግባባቶችን ለመፍታት እንደሚያስችሉ ይታመናል። ሀገራዊ ውይይት በሚጠሩበት ጊዜ አላማው ብዙውን ጊዜ ፖለቲካ ተሳትፎን ማስፋት እና በሌለ መልኩ ለተገለሉ ቡድኖች ባለቤትነት መስጠት ነው፡፡ ይህ የበለጠ አካታች ሂደት እና የተሻለ ዘላቂ ውጤት ለማምጣት መንገድ ይከፍታል።
ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚደረግ ምክክር ዜጎች ከየትኛውም ዓይነት አሉታዊ ፍላጎት በጸዳ መልኩ በዕውነት ላይ በተመሠረተ ግንኙነት እና ስሜትን ተቆጣጥሮ ቁጭ ብሎ በጥሞና በመነጋገርና በመደማመጥ ሃሳብ የሚለዋወጡበት፤ እርስ በእርስ የሚነጋገሩበት፤ የሚመካከሩበት እና የጋራ መግባባት ላይ የሚደርሱበት ነው። ሀገራዊ ምክክር ደግሞ በዚህ መልኩ ሲከወን ከአሸናፊነትና ተሸናፊነት ስሜትና እልህ ነፃ በሆነ መንፈስ ሁሉም ሀገርና ሕዝብ አሸናፊ የሚሆኑበት የፖለቲካ ምህዳር መፍጠር የሚያስችል ነው። ዘላቂ ሰላምና መግባባትን በመፍጠር ዜጎችን ከግጭትና ግጭት ከሚፈጥረው ኪሳራ ለመታደግ ያስችላል ተብሎ ይታመናል፡፡
ሀገራዊ ምክክር በአንድ ሀገር ውስጥ የሚገኙ የተለያየ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ባሕል፣ ወግና ልማድ ወዘተ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን አካታች በሆነ ሥርዓት ቁጭ ብለው ላለመግባባታቸው ምክንያት በሆኑ ጉዳዮቻቸው ዙሪያ የሚመካከሩበትና ወደ መግባባት የሚሸጋገሩበት ሂደት ነው። ሀገራዊ ምክክር አለመግባባቶች ወደ ግጭት ከማምራታቸው በፊት መከላከል የሚያስችል ሲሆን፤ በዜጎች መካከል አዲስ ማህበራዊ ውል እስከ መፍጠር የሚደርስ ዓላማ ሊኖረው ይችላል።
በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ የፖለቲካ እና የሃሳብ መሪዎች መካከል እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሳይቀር የሃሳብ ልዩነት እና አለመግባባት እንዳለ ይታመናል። ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ በውይይት ለመፍታት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል። ተስፋ የተደረገበት ሀገራዊ ምክክሩ የተሻለ ሀገራዊ አንድነት ለመገንባት በሂደትም የመተማመን እና ተቀራርቦ የመሥራት ባህልን ለማጎልበት እንዲሁም የተሸረሸሩ ማህበራዊ ዕሴቶችን ለማደስ የሚጠቅም ነው፡፡
የቆዩ አለመግባባቶችን ጨምሮ አሁን ላይ የሚስተዋሉ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ በውይይት በመፍታት፣ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ለሚደረገው ጉዞ የውይይት ባህልን ማዳበር እና ወቅታዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ይረዳል። በዚህ ረገድ የተሳካ ብሔራዊ ውይይት ማድረግ ሀገሪቱ ለምታደርገው የልማትና የዴሞክራሲ ጉዞ መደላደልን ከመፍጠር በዘለለ ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ሚናው የጎላ እንደሆነ የሚተመን ነው። ሀገራዊ ውይይቱን ውጤታማ በማድረግ ደግሞ የወጣቶች ሚና መተኪያ የሌለው ነው፡፡
ይህንን በተመለከተ አዲስ ዘመን ከአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ዋና ፀሐፊ ወጣት ይሁነኝ መሃመድ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ ወጣት ይሁነኝ መሃመድ እንደሚናገረው፤ ሀገራዊ ምክክር እንደ ሀገር ያለንበት ሁኔታ የመጣንበት መንገድ ያለፍነው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ ታሪክና ማህበራዊ ጉዳዮቻችን ገፍተው ያመጡት ጉዳይ እንደሆነ ማሰብ ተገቢ ነው ይላል።
በአንድ ሀገር የትኛውም ችግር ቢመጣ ለዛ ሀገር መፍትሔ ለመምጣት የጦር መሣሪያ አንግቦ መነሣት ፋይዳ አልባ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥም ነፍጥ አንግቦ በኃይል ብቻ ጥያቄዬ ይመለስልኛ የሚል ግምት በስፋት የሚስተዋል ቢሆንም አዋጭ ያልሆነ አካሄድ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ተጉዘን የደረሰብን ዘርፈ ብዙ ኪሳራም የቅርብ ጊዜ ትዝታችን እንደሆነ ይናገራል።
ሀገራዊ ምክክርን ለብዙ ችግሮቻችን መፍትሔ ሊሰጥ የሚችልና እንደ ጥሩ አጋጣሚም የሚታይ ነው የሚለው ወጣት ይሁነኝ፤ በተለያየ ምክንያት የተፈጠሩ አለመግባባቶች፤ መራራቆችና ችግሮችን እንዴት መፍታት ይቻላል የሚለውን የሚያመለክት በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ ቁርሾዎችን እንደ ሕዝብ ቁጭ ብሎ ተነጋግሮ ለመፍታት የመጣ መልካም አማራጭ አድርጎ እንደሚወስድ ይገልጻል።
ወጣት ይሁነኝ እንደሚናገረው፣ ይህ ሀገራዊ ምክክር ጉዳዮቻችንን በሃይማኖት ያለን መገፋፋት፣ በፖለቲካ፣ በማህበራዊ መስተጋብር፣ የውክልና ማጣት፣ የዕውቅና ማጣት በታሪክ ሊኖረን የሚገባውን ደረጃ አለማግኘት የሕገ መንግሥትና አስተዳደር፣ የክልል አከላለል ጉዳዮችን ጨምሮ ሰፋፊ ጉዳዮችን በነፃነት የአሁኑንና የወደፊቱን አንስቶ ተወያይቶ ከመግባባት ለመድረስ ትልቅ ዕድል በመሆኑ ሁሉም ዜጋ በተለይም ወጣቱ ክፍል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ይናገራል፡፡
በሀገራዊ ምክክር የጥቂት ኤሊቶች ሃሳብ ብቻ አይደለም ለውይይት የሚቀርበው የሚለው ወጣቱ፤ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ሃሳቡን በተለያየ መንገድ መግለጽ የሚችልበት መድረክ ነው። በቤተሰብ፣ በጓደኛ መካከል እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያ የምናነሳቸው ሃሳቦች ወደ መድረክ የሚመጡበት ነው። ስለዚህ እንደ ሀገር በእውነት ከልብ መለወጥ፣ መስተካከል፣ መግባባት ይገባል የሚል ሰው እንደ ትልቅ ዕድል ወስዶ ንቁ ተሳታፊ ለመሆን መዘጋጀት እንዳለበት ያስረዳል።
በዚህ ሀገራዊ ምክክር በተለይ የወጣቶች ተሳትፎ በምን መልኩ መሆን እንዳለበት ወጣት ይሁነኝ ሲናገር፤ ወጣቶች የትናንቱን ሀገር ማሻገሪያ ድልድይ የዛሬውን ማፅኛ መሠረት፣ የነገው ሀገር ደግሞ ተረካቢ እንደመሆናቸው ወጣቶች በሀገራቸው ጉዳይ በንቃት ሊሳተፉ ይገባል፡፡ ወጣቶች የተሳተፉበት፤ መልካም አስተዋጽኦ ያኖሩበት ሀገር እንጂ ምንም ዓይነት አስተዋጽኦ ያላበረከቱበትን ሀገር መረከብ የለባቸውም፡፡
ስለዚህ የኢትዮጵያ ወጣት በአጠቃላይ በዚህ የሀገራዊ ምክክር መድረኩ ላይ ያያቸውን፣ ያጋጠማቸውን በቀጣይ ሊገጥሙ በቀጣይ ይችላሉ የሚላቸውን ችግሮች ብሎም መፍትሔም ይሆናል ያላቸውን ሃሳቦች በማንሳት በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
ወጣቱ የዚህን ሀገራዊ ምክክር የጎላ ጠቀሜታ ተገንዝቦ አስፈላጊ የሚላቸው ነጥቦች እንዲመዘገቡና ውይይቱ በስኬት እንዲካሄድ ያለው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ የሚገልጸው ወጣት ይሁነኝ፤ አሁን ባሉ አለመግባባቶች ተጎጂ የሆነው ወጣት ማንኛውም ጉዳይ ተነስቶ መነጋገር እንዲቻል ይቅርታ፣ ዕርቅ ወርዶ ልዩነት ወደ መሀል መጥቶ ሰላም የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለማየት ከምኞት ባለፈ ተግባራዊ ሥራ ለመሥራት ቆራጥ መሆን እንዳለበት ይናገራል።
ይህን የብሔራዊ መግባባት ጉዳይ እንደ ዕድል የመጣ አጋጣሚ አድርጌ እወስደዋለሁ የሚለው ወጣት ይሁነኝ፤ በአንዳንድ ሀገራት ተሞክሮ ውጤታማ ሆኖ ሀገራቱ ወደፊት እንዲጓዙ በር የከፈተ አጋጣሚ ሆኖ አልፏል፤ ስለዚህ በኢትዮጵያም የሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ እንዲሆን ከሁሉም ወገን የሚነሱ ሃሳቦች ተገቢ ቦታ ኖሯቸው ወደፊት የምናደርገው የጋራ ጉዞ ውጤታማ እንዲሆን በተለይ ወጣቶች ታሪካዊ ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው ያስረዳል።
እንደ ሀገር በግጭትና ጦርነት ውስጥ ለበርካታ ዘመናት ኖረናል፡፡ ሰላም ማጣትና ጦርነት የቅርብም የሩቅ ዘመን የታሪካችን አካል ነው የሚለው ወጣት ይሁነኝ፤ ሰላምን በዘላቂነት ለማምጣት ሀገራዊ ምክክሩ ትልቅ ተስፋ ይዞ መጥቷል። እንደ ሀገር ልዩነት በመፍጠር ለግጭት ሲዳርጉን የቆዩ ጉዳዮች ወደ ጠረጴዛ መጥተው በሰጥቶ መቀበል መርህ ሁሉንም አሸናፊ በሚያደርግ መልኩ ከስምምነት ለመድረስና ችግሮችን ለመፍታት ያስችለናል፤ ጠያቂው ህብረተሰብም ደግሞ በረዥምና በአጭር ጊዜ የሚመለሱ ጥያቄዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ በመገንዘብ ለዚህ ዝግጁ መሆን አለበት ይላል።
ከሁለት ዓመት በፊት በትግራይ ጦርነት አሁን ደግሞ በአንዳንድ ክልሎች ውስጥ ባሉ ግጭት በሁለቱም ወገን ተሳትፎ እየሞተ፣ እየደማ፣ አካሉን እያጣ ያለው ወጣቱ እንደሆነ የሚናገረው ይሁነኝ፤ ይህ ወጣት አሁን ወደተዘጋጀው ምክክር ቢገባ፣ ዕድሉን ቢያገኝ፣ ማዳመጥ ቢችል ጥያቄዎቹን ቢያነሳ ለመፍትሔው ደግሞ በጋራ ጥረት ቢያደርግ እንደ ሀገር እንተርፋለን እንደ ትውልድ ደግሞ እናተርፋለን ይላል።
ኢትዮጵያ ባለት አቀማመጥ፣ ባለት ሀብት፣ ባላት የሰው ኃይል ለራሳችን ብቻ ሰይሆን ለምሥራቅ አፍሪካ መብቃት የምንችልና በታሪክ ያለን ቦታም ከፍ ያለ እንደሆነ የሚገልጸው ወጣት ይሁነኝ፤ ይህንን ከፍ ያለ ታሪክ ለማስቀጠል የቀደመው ትውልድ የራሱ ውስንነቶች እንዳሉ ሆነው ያወረሰንን በጎ ነገር ይዘን ችግሩን ቀርፈን ወደፊት መሻገር የምንችለው ስንወያይ ስንነጋገር ብቻ ነው ይላል፡፡ ስለዚህ ይህንን ታሳቢ በማድረግ በየትኛውም አቅጣጫ ሰላም፣ ፍትህና ዕድገት የምንፈልግ ከሆነ ይሄንን ደግሞ በሰላማዊ መንገድ ለመምጣት ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይገልጻል።
በዚህ ሂደት ውስጥ የሃይማኖት አባቶች፣ የምሁራን፣ የሚዲያው፣ የመንግሥትና የአጠቃላይ ህብረተሰቡ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ሁሉም የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበት የሚገልጸው ወጣቱ፤ የሃይማኖት መሪ በፖለቲካና ብሔር ውስጥ የፖለቲካ መሪ በሃይማኖት ውስጥ የመግባት ምሁሩ ምሁርነቱን ትቶ የብሔር ተወካይ የሚሆንበት ሁኔታ በሀገራችን ይስተዋላል ይህ መስተካከል እንዳለበት ያስረዳል።
ምሁር ከተማረው ነገር ለህብረተሰቡ የሚጠቅም የመፍትሔ አማራጭ እያመጣ፣ ፖለቲካኛው እንደ ፖለቲካ ፓርቲ፣ መንግሥት እንደ መንግሥት፣ የሃይማኖት ተቋም እንደ ሃይማኖት ተቋም፣ ሚዲያው እንዲሁ ፍትሃዊ ሆኖ መነሳት የሚገባቸውን ነገሮች እያነሳ አለመግባባቶች በውይይት ብቻ የሚፈቱበት ሁኔታ እንዲፈጠር ቢያተኩር እንደ ሀገር ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ወጣት ይሁነኝ ይናገራል።
ወጣቱ እንደሚናገረው፤ የውስጥ ችግሮቻችንን ያለ ሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ተነጋግሮ የመፍታትን ባህል ልናዳብር ይገባል፡፡ ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገ ትውልድም ኃላፊነት በመውሰድ ችግሮቻችንን አራግፈን ሰላሟ የተረጋገጠ፤ በልማት የተራመደችና ዜጎች የሚኮሩባት ሀገር ለመፍጠር ሀገራዊ ምክክሩን ልንጠቀምበት ይገባል፡፡
ወጣት ይሁነኝ በመጨረሻ ባስተላለፈው መልዕክት ሰላም እንዲኖር፣ ሰላም እንዲከበር ለአንድ አካል ብቻ የሚሰጥ ጉዳይ አይደለም፡፡ መንግሥት ሺ ወታደር ቢያሰልፍም ሕዝብ ካልተባበረ ሰላም አይመጣም፡፡ ሰላም የወል እውነት ነው፡፡
የወል እውነት ደግሞ የጋራ ርብርብ ይጠይቃል፡፡ ሰላም ለመኖር፣ ለመሥራት፣ ሀብት ለማፍራት፣ ማህበራዊ ሕይወትን ለማስቀጠል ተገልጾ የማያልቅ ትሩፋት አለው፤ በተቃራኒው ደግሞ ሰላም በቸልተኝነት አንዴ ከእጅ ካመለጠ በቀላሉ አይመለስም፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያውን ዘላቂ ሰላማቸውን አስጠብቀውና የጋራ መግባባት ፈጥረው ወደፊት ለመጓዝ ይህንን ብሔራዊ ምክክር በአግባቡ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ህዳር 7/2016