ትብብር- የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኑሮ ውድነትን የሚያባብሱ ምክንያቶች በሀገራችን እያስተዋልን ነው። የገበያ ሥርዓቱን የሚረብሹ ሕገወጥ ድርጊቶች ለዚህ አለመረጋጋት ምክንያት ይሁኑ እንጂ ሌሎች አያሌ ምክንያቶችንም ማንሳት ይቻላል። ከእነዚህ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች፣ ፖለቲካዊ አሻጥር (sabotage) ፣ የዓለም የነዳጅ ዋና መናር፣ ሙስና እና ሌሎች በርካታ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። ከላይ ባነሳናቸውና በሌሎች በርካታ ምክንያቶች የተነሳ የዋጋ ግሽበት (inflation) በኢትዮጵያ እየጨመረ እንዲመጣና የኑሮ ውድነት እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል። ይህ ደግሞ የዜጎች የመግዛት አቅም እንዲዳከም ከማድረጉም በላይ የዝቅተኛው የማህበረሰብ ኑሮ ላይ ጫና እየፈጠረ ይገኛል።

ኢትዮጵያ በንግድ ሥርዓት ውስጥ “የነፃ ገበያ” ፖሊሲን እንደምትከተል ይታወቃል። ይሁን እንጂ ይህንን መርህ በተሳሳተ መልክ በመተርጎም የማህበረሰቡን የመግዛት አቅም ባላገናዘበ መንገድ ዋጋ ጣሪያ ላይ የሚሰቅሉ (የሚጨምሩ) በርካታ ነጋዴዎች እዚህም እዚያም እየታዩ ነው። እዚህ ጋር በኑሮ ጫና ፈተና ውስጥ የወደቁ አንድ አዛውንት “የኑሮ ውድነቱን መቋቋም አቅቶናል። በነፃ ገበያ ስም ነጋዴዎች ዋጋ እየቆለሉብን ነው። ወጣቱም ጭምር ያለ እድሜው በሽበት ተወረረ” በማለት ሲናገሩ ያደመጥኩት ጠንካራ ትችት እዚህ ጋር ማስታወስ እወዳለሁ።

በየጊዜው በሸቀጦች ላይ ዋጋ ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አይስተዋልም። ምርቱ በስፋት ቢኖር እንኳን ቀደም ሲል የተጨመረው ዋጋ እዚያው ነው የሚቀረው። ይህም የብር የመግዛት አቅም እንዲዳከምና ማህበረሰቡ በኑሮ ጫና ውስጥ እንዲቆይ እያስገደደው ነው። ቀደም ባሉት ዘመናት የኑሮ ውድነትን የሚያረጋጉ የህብረት ሱቆች የነበሩ ቢሆንም መንግሥት ይከተለው በነበረው የነፃ ገበያ ሥርዓት ምክንያት በብዛት እንዲዘጉ ተደርጓል። እንደ እኔ ሃሳብም የህብረት ሱቆቹ መዘጋት እና በሚፈለገው ልክ አለመኖር ለኑሮ ውድነቱ አስተዋጽኦ አድርጓል።

በዋናነት ትኩረት ሊሰጠውና እልባት ሊበጅለት የሚገባው ጉዳይ ባልተገባ የንግድ እንቅስቃሴ ሀብት የሚያካብቱ ሕገወጥ ነጋዴዎች ጉዳይ ነው። የእነዚህ ሕገወጦች ድርጊት አብዛኛውን ማህበረሰብ ለከፋ የኑሮ ፈተና አጋልጦታል። መንግሥትም ትክክለኛውን የነፃ ገበያ ሥርዓት ተግባራዊ እንዳያደርግ እንቅፋት እየሆኑና ሥርዓት አልበኝነትን እያባባሱ ይገኛሉ። በመሆኑም ሕዝብን ለምሬት የሚዳርገው የእነዚህ ጥቂት ጥቅም ፈላጊዎች ሰንሰለት ሊበጠስና ሥርዓት ሊበጅለት ይገባል።

በሚፈለገው ልክ ለውጥ አምጥቷል ተብሎ ባይታሰብም መንግሥት የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ እና የማህበረሰቡን ጫና ለማስተካከል ልዩ ልዩ ርምጃዎችን እየወሰደ ነው። አቅመ ደካሞችን በሴፍቲኔት እንዲታቀፉ ለማድረግ፣ የትምህርት ቤት ምገባ፣ የሥራ ፈጠራን ማበረታታት፣ ሕግና ሥርዓትን ማስከበር፣ በበዓላት ወቅት ምርቶችን በድጎማ ማስገባት እና ሌሎች መሰል ድጋፍና ድጎማዎችን ያደርጋል። ይህን መሰል ድጋፍና ርምጃም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

መንግሥት ቀደም ባሉት ሥርዓቶች ይተገበሩ እንደነበሩት አይነት የህብረት ሱቆች ባይሆንም የሸማች ማህበራትን በማቋቋምና ምርቶች እንዲያቀርቡ በማድረግ እየሠራ ይገኛል። ያለውን ችግር ለመፍታት እንደ አንድ መፍትሄ የሚወሰድ ነው። ይሁን እንጂ ማህበራቱ ልዩ ልዩ ሸቀጦችን አምጥተው ለነዋሪ ሳይዳረሱ “አልቋል” የሚባሉበባቸው ጊዜ እንዳለ መዘንጋት የለብንም። በመሆኑም “ምን ያህል ውጤታማ ናቸው” የሚለው ግን መፈተሽ ይኖርበታል። ይህ ሲሆን የተፈጠረውን የኑሮ ጫና ለመቀነስ ከሚወሰዱ አበረታች ርምጃዎች አንዱ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል።

ለኑሮ ውድነቱ መባባስ ሌላኛው ምክንያት በንግዱ ማኅበረሰብ ውስጥ ማኅበራዊ ኃላፊነትና አገልጋይነት የማይሰማቸው የዘልማድ ነጋዴዎች መኖር፤ ሥርዓተ አልበኝነት፣ ከትርፍ ህዳግ በላይ የሚፈልግ ለኑሮ ውድነቱ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ይታመናል። ለዚህም የምርት አቅርቦት ሰንሰለቱ በደላሎችና ሕገወጦች የተሳሰረ መሆኑ የራሱ ድርሻ እንዳለው እሙን ነው።

ሌላው የገበያ ሥርዓቱ ኋላቀር መሆን፣ ሕገወጥ ደላሎዎች እንዳሻቸው የሚያሽከረክሩት መሆኑ እንደ ምክንያት ሊነሳ ይችላል። ይህንን ስር የሰደደ ችግር ለመፍታትና ሕገወጦችን ከዚህ ሰንሰለት ውስጥ ቆርጦ ለማውጣት ጠንካራ ርምጃ ሊወሰድ ይገባል። ከቀናት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ለህዝብ እንደራሴዎች ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኑሮ ውድነትን የሚፈጥሩ ጉዳዮች ላይ መንግሥታቸው እየወሰደው ያለው ርምጃና ሊወስዳቸው ያሰባቸው እቅዶችም ተጠናክረው ተግባራዊ ሊደረጉ ይገባል።

ለኑሮ ውድነቱ መባባስ ምክንያት ከሚሆኑ ጉዳዮች መካከል የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ነው። ይህንን ችግር ለመፍታት ከላይ ባነሳነው ጊዜ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ቀጥታ አርሶ አደሩ ገበያ ላይ ምርቱን የሚያቀርብበት እድል እየፈጠርን ነው” በማለት ያቀረቡት መፍትሄ ሊበረታታ ይገባል። ምርት ገበያ ላይ በፍላጎት ልክ እንዲኖር ከተሠራም ይህን ችግር መፍታት ይቻላል። ይሁን እንጂ ምርት ሲጨምር ዋጋ ሲቀንስ አለመታየቱ አሁንም ሕገወጥነት ለመኖሩ ማሳያ ስለሚሆን ማስተካከያ ሊደረግ ይገባል።

‹‹ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ ›› እንደሚባለው ሕገ ወጥነትንና ሕገወጦችን ለመከላከል የጋራ ርብርብ ያስፈልጋል። በተለይ በገበያ ሥርዓት ውስጥ የሚታየውን ውስብስብ ችግር መንግሥት ብቻውን ሆኖ ሊከላከለው ስለማይችል በአንድነት መቆም ያስፈልጋል። በመሆኑም ከወረቀት ላይ እቅድ በዘለለ መሬት ላይ የወረደ ሥራዎች ሊተገበሩ ይገባል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ገዝቶ የሚያስገባቸውን ምርቶች ለመተካት እቅዶች ነድፎ እየሠራ መሆኑ ይታወቃል። ከእነዚህ ውስጥ ስንዴና መሰል የግብርና ምርቶች ይገኙበታል። በኩታ ገጠም እርሻዎች እየለሙ ያሉ ልዩ ልዩ ሰብሎችና በበጋ መስኖ እየተመረቱ ያሉ የስንዴ ሰብሎችን ማየታችን አርሶ አደሩን ፣ሀገሪቱንና አመራሩን የሚያስደስት ፤ተስፋ ሰጪ ጅማሬ ነው። ይህ ርምጃ ከውጭ የምናስገባውን ምርትና ወጪ በመቀነስ ለኑሮ መረጋጋቱ ተስፋ ሰጪ አበርክቶ እንደሚኖረው ይታመናል።

የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት ረገድ በርካታ የመፍትሄ ርምጃዎችን መውሰድ ይቻላል። ከእነዚህ መካከል በከተማ ያሉ የሸማቾች ማኅበራትን ማጠናከር ቀዳሚው ነው። በመሆኑም ማህበራቱ ምርቶችን ከአርሶ አደሩ በቀጥታ በተመጣጣኝ ዋጋ ለከተማ ነዋሪዎች ሊያከፋፍሉ የሚችሉበትን ወጥ የገበያ ሥርዓት እንዲፈጠር ሊጠናከሩ ይገባል።

በአጠቃላይ መንግሥት እና ዜጎች ተረባርበው ሀገራዊ የገበያ ሥርዓቱን “ሥርዓት” ማስያዝ ይጠበቅባቸዋል። ይህ በየትኛውም መመዘኛ ለድርድር የሚቀርብ መሆን የለበትም። ነጋዴው “በረባ ባልረባው” ምክንያት ዋጋ እንዲጨምርና የኑሮ ጫና እንዲፈጥር ሊፈቀድለት አይገባም። በፖሊሲ፣ በሕግና በሌሎች ማሻሻያዎች ሊስተካከሉ የሚገባቸው የኑሮ ውድነትን የሚያባብሱ ምክንያቶችም ስለሚኖሩ እንደየ ፈርጃቸው እልባት ሊበጅላቸው ይገባል፡፡

ይቤ ከደጃች ውቤ

አዲስ ዘመን ህዳር 7/2016

Recommended For You