የቆዳው ዘርፍ ስትራቴጂ አስቀድሞ መጥቶ ቢሆን መልካም፣አሁን መምጣቱም መልካም!

ኢትዮጵያ በዓለም በከብት ሀብቶቻቸው ከሚታወቁ አስር ሀገሮች ተርታ እንዲሁም ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ብትሆንም፣ ከዘርፉ ተጠቃሚ በመሆን በኩል ግን ተጠቃሽ መሆን አልቻለችም። ሀገሪቱ በተለይ በቆዳና ስጋ ሀብቷ የሚገባትን ያህል ተጠቃሚ አለመሆኗን በዘርፎቹ የተሰማሩ አካላትም፣ መንግስትም በተደጋጋሚ ያረጋገጡት ሀቅ ነው፡፡ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ሊያስገኝ የሚችለው ቆዳ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደ ዋዛ እየተጣለ ያለበት ሁኔታ ብቻውን ሌላው ትኩስ ማረጋገጫ ነው፡፡

በቅርቡ የተካሄደ መድረክም ይህንኑ ቆዳ በሚገባ ጥቅም ላይ አለመዋሉን አረጋግጧል፡፡ የቆዳው ዘርፍ ባለድርሻ አካላት በዘርፉ ችግሮችና መፍትሄዎች ላይ በመከሩበት በዚህ መድረክ ላይ በሀገሪቱ በዓመት ከሚመረተው የቆዳና ሌጦ ምርት ግማሽ ያህሉ አገልግሎት ላይ እንደማይውል የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በመድረኩ ላይ ከ2016 እስከ 2025 ዓ.ም የሚተገበርና የቆዳውን ዘርፍ ችግሮች በመፍታት ልማቱን ለማጠናከር የሚረዳ የስትራቴጂ ሰነድ ለውይይት በቀረበበት ወቅት እንደተጠቆመው፤ የቆዳ ዘርፉ ባሉበት ውስብስብ ችግሮች ምክንያት በሀገር አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከሚመረተው ከ41 ሚሊየን በላይ የቆዳና ሌጦ ምርት ግማሽ ያህሉ ብቻ ነው አገልግሎት ላይ የሚውለው፡፡ በዚህ የተነሳም ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትም ጥቅም አጥታለች፡፡

ሀገሪቱ ከ165 ሚሊየን በላይ የቀንድ ከብት ሀብት እንዳላት ሚኒስቴሩ ጠቅሶ፣ ከዚህ የሚገኘው የቆዳና ሌጦ ምርት ግን ዝቅተኛ ነው ብሏል፤ ችግሩን ለመፍታት ይህ የአስር ዓመት ስትራቴጂ መነደፉን አመልክቷል፡፡ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም አናሳ መሆን፣ የዓለም የቆዳ ምርቶች ገበያ መቀዛቀዝ፣ የመጓጓዣ እጥረት፣ የጥሬ ቆዳ አሰባሰብ ችግር፣ ምርቶች የሚቀርቡበት ሰፊ ገበያ አለመኖርና የግብአት አቅርቦት እጥረት ዋነኛ የዘርፉ ማነቆዎች መሆናቸውን አመልክቷል፡፡

በመድረኩ የስትራቴጂው ፋይዳዎችም ተጠቁመዋል፡፡ ስትራቴጂው ምክንያት ሆኖ ባለድርሻ አካላት በጉዳዩ ላይ በጋራ መምከራቸው በራሱ ብቻ ዘርፉን ለመታደግ ይጠቅማል። በቆዳና ሌጦ ምርት ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት በእጅጉ የሚያም መሆኑን እዚህ ላይ መግለጽ ይገባል። የዘርፉ ችግሮች አያሌና ውስብስብ ናቸው፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት ርብርብ ማድረግ መጀመር የነበረበት ዛሬ አልነበረም፡፡ አስቀድሞ ይህን ማድረግ ባለመቻሉ የሀገር ሀብት የሆነው ቆዳ መጣል ላይ ከተደረሰ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

የቆዳውን ዘርፍ ችግሮች ለመፍታት መጮህ ሲገባ ዓመት በአላት በመጡ ቁጥር ዘርፉ የሚመለከታቸውን አካላት ዋቢ ያደረጉ ዘገባዎች ይዘዋቸው የሚወጡ መረጃዎች ግራ የሚያጋቡ የሚባሉ ናቸው፡፡ ቆዳ እየተጣለ ባለበት ሀገር ‹‹በዓሉን በማስመልከት እርድ በሚፈጸምበት ወቅት ለቆዳ ጥንቃቄ ይደረግ›› የሚሉ አይነት ዘገባዎች ናቸው ሲቀርቡ የቆዩት፡፡ ከአንዴም ሁለቴ፣ ሶስቴ፣ ቆዳ ለጣለ ማሕበረሰብ ይህ ዜና ምን ይረባዋል? ለሚጣል ቆዳ ጥንቃቄ አድርጉ የሚል መልዕክት ማስተላለፍስ ራስን ለመሳለቂያ አይዳርግም ወይ? ቆዳ ጠያቂ አጥቶ እየተጣለ ባለበት ወቅት ይህን አይነት ዜና መስማት በእርግጥም ይገርማል፡፡

በአንድ ወቅት ከቡና ቀጥሎ ሁለተኛው የውጭ ምንዛሬ ምንጭ የነበረው ቆዳ እንደ ዋዛ እየተጣለ ነው፤ መፍትሄ ይፈለግለት የሚል መረጃ ነጋ ጠባ መስራት ሲገባ በእርድ ወቅት ቆዳ እንዳይቀደድ ጥንቃቄ ይደረግ ብሎ መረጃ መስጠት ወቅታዊም ምጣኔ ሀብታዊ ፋይደም የለውም፡፡

ሁሉም ማሕበረሰብ ባለፉት ዓመታት የታዘበው ቆዳ የሚሰበስበው በመጥፋቱ የተነሳ እንደ ሌሎች የእርድ ተረፈ ምርቶች በየቆሻሻ መጠያው፣ በየስርቻውና በየወንዙ እየተጣለ መሆኑን ነው፡፡ የአራጆች ድምጽ እንጂ የቆዳ ገዥዎች ድምጽ ከተሰማ ቆይቷል፡፡ የአራጅ ሂሳብን ይችል የነበረው ወይም የአራጅ ወጪን በከፊልም ቢሆን ይችል የነበረው ቆዳ ሲጣል ምን ያህል ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት እየተጣለ መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም፡፡

በአንድ ወቅት በዘርፉ ላይ ዘገባ ለመስራት ከጥቂት ዓመታት በፊት ከሚመለከታቸው ክፍሎች አንዱን አነጋግሬ ነበር፡፡ መረጃውን የሰጡኝ አካላት የቆዳና ሌጦን ጉዳይ በቁጭት ነው ያነሱልኝ፡፡ ከቡና ቀጥሎ ሁለተኛው የውጭ ምንዛሬ ምንጭ የነበረበትን ዘመን የጠቀሱት እነዚህ ምንጮች፣ የቆዳ ጉዳይ በእጅጉ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ነገሩኝ፡፡

የዘርፉ ችግሮች በርካታ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በተለይ ቆዳ ሰብሳቢዎች ለከፍተኛ ኪሳራ መዳረጋቸውን፣ ቆዳ ተረካቢዎች / ኢንዱስትሪዎች/ በሚሰጧቸው ዝቅተኛ ዋጋ የተነሳ ቆዳ ክፉኛ መጎዳታቸውን፣ በርካታ ቆዳ ሰብሳቢዎች ከስራ ውጪም መሆናቸውንም ገልጸውልኝ ነበር፡፡

እውነታው ፍንትው ብሎ የሚታይ ቢሆንም፣ ምክንያቱ ይህ ይሁን ሌላ ቆዳ ለመሰብሰቢያ በየአደባባዩ የተገነቡ ማዕካላት በአሁኑ ወቅት በቦታቸው የሉም፡፡ ይህም ቆዳ መሰብሰብ ላይ እየተሰራ ስላለመሆኑ እንደ አንድ አመላካች ሊወሰድ ይችላል፡፡

ኢንዱስትሪዎቹ የሚያነሷቸው ችግሮች ስለመኖራቸውም ይገለጻል፡፡ ከጥንት ጀምሮ በእርድ ወቅት በሚከሰት የጥንቃቄ ጉድለት ሳቢያ በቆዳ ላይ ጉዳት እንደሚደርስ ይገለጻል፤ አዎን ሊደርስ ይችላል፤ ጥንቃቄም መደረግ አለበት፡፡ ባለኢንዱስትሪዎቹ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደጋጋሚ የሚያነሱት ችግር ለዘርፉ የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ከውጭ ለማስመጣት የሚያጋጥመው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ነው፡፡

ልብ በሉ እንግዲህ፤ ዘርፉ የውጭ ምንዛሬ አመንጪ ሆኖ እያለ ነው የውጭ ምንዛሬ እጦት ፈተና የሆነበት፡፡ በእዚህ ጉዳይ ላይ ከመንግስት አካላት ጋር ብዙ ቢመከርም፣ የመጣ ለውጥ ግን ሳይመጣ ብዙ ጊዜ ቆይቷል፡፡ ኢንዱስትሪዎቹ ቆዳና የቆዳ ውጤቶችን ለውጭ ገበያ ልከው ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሬ እጅግ የተወሰነውን ነበር እንዲጠቀሙ የሚፈቀድላቸው፡፡ ቢያንስ 50 በመቶው እንዲፈቀድላቸው ሲጠይቁም ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ምን ያህል የኢንዱስትሪዎቹን ጥያቄ የመለሰ እንደሆነ ባላውቅም መንግስት ለእዚህ ችግር መፍትሄ ያስቀመጠ መሰለኝ፡፡

ሌሎች አካላት ደግሞ የኢንዱስትሪዎች አለመዘመንና እርጅና የዘርፉ ሌላው ችግር መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በእርድ ወቅት በቆዳ ላይ ጉዳት መድረስ እንደሌለበት የሚጠቁሙት እነዚህ አካላት፣ በኢንዱስትሪዎች ማሽነሪዎች እርጃና የተነሳ እዚያው ፋብሪካ ውስጥም ቆዳ የሚቀደድበት ሁኔታ እንዳለም ያመለክታሉ። ኢንዱስትሪዎች ዘመኑን የዋጁ አይደሉም፤ በሌላ ሀገር አገልግሎታቸውን ጨርሰው እንደገና ኢትዮጵያ ውስጥ የተተከሉ ናቸው፤ በዚህ ምክንያት በቆዳ ላይ ጉዳት ያደርሳሉ የሚሉ አስተያየቶችም ይሰነዘራሉ፡፡

መንግስት በዘርፉ ላይ ያለውን ችግር በመመልከት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጥሬ ቆዳ ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ ያደረገበት ሁኔታ መኖሩን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ደረቅ ቆዳ ወደ ናይጄሪያ እንደሚላክ ነው የሚገለጸው፡፡ ቆዳ የትም ከሚጣል ጥሬ ቆዳ ወደ ውጪ መላኩ አንድ መፍትሄ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ቀደም ሲል ያነሳሁት ለአጠቃላይ ላኪዎች የወጣው አዲስ አሰራር የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ላኪዎችም ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሬ እስከ አሁን ከሚጠቀሙት በላይ ሊጠቀሙ የሚችሉበት እድል መመቻቸቱም አንድ ለውጥ ሊሆን ይችላል፡፡ ችግሩ ግን ከዚህም በላይ መስራትን የግድ ይላል፡፡

መንግስት የዘርፉን ማነቆዎች በመፍታት ልማቱን ለማሳለጥ ይጠቀማል የተባለ ከ2016 ጀምሮ ለአስር ዓመት የሚተገበር ስትራቴጂ ይዞ መምጣቱን ደግሞ እንደ አንድ ለውጥ መመልከት ይገባል፡፡ ስትራቴጂው ቀደም ብሎ መጥቶ ቢሆን ኖር መልካም ነበር፤ አሁን መምጣቱም መልካም ነው፡፡ ስትራቴጂው መያዝ ያለበትን ሁሉ እንዲይዝ ማድረግ ላይ ግን በሚገባ መስራት ያስፈልጋል፡፡ በስትራቴጂው ላይ ባለድርሻ አካላት እንዲመክሩበት መደረጉ አንድ ጥሩ ነገር ነው፡፡ ምክክሩ ግን ሰፊ መሆን አለበት ፤ ብልጭ ብሎ ወደ መጽደቅ የሚሄድ መሆን የለበትም፡፡ በየደረጃው ውይይት ሊደረግበት ይገባል፡፡

በዓለም ገበያ የቆዳ ግብይት መቀዛቀዙን የሚገልጹ አካላት ቢኖሩም፣ ሌሎች በዘርፉ ላይ የሚሰሩ አካላት ገበያው አሁንም እንዳለ ነው የሚጠቁሙት፡፡ ዛሬም ቢሆን የሀገሪቱ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች በዓለም ገበያ ተፈላጊ መሆናቸውን በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾችና ላኪዎች ይገልጻሉ፡፡

የኢትዮጵያ ቆዳ በተለይ የደጋ በጎች /የሀይላንድ ሺፕ/ ቆዳ በውጭው ዓለም በከፍተኛ ሁኔታ ተፈላጊ መሆኑን እነዚሁ አካላት አሁንም ይጠቁማሉ። በፋሽን ኢንዱስትሪውም በኩል ቢሆን የቆዳ ምርቶች ተላጊነት እየጨመረ መጥቷል፡፡ በሀገር ውስጥም ቢሆን ዋጋቸው እየተወደደ እንጂ የቆዳ ውጤቶቹ በእጅጉ ተፈላጊ ናቸው፡፡

ይህ በሆነበት ሁኔታ የሀገሪቱ የቆዳና ሌጦ ምርት ሲጣል ማየት/ ለዚያውም ለዓመታት/ በእጅጉ ያማል፡፡ በዘርፉ ላይ ለዓመታት የሰሩና አሁን በሌሎች ዘርፎች ላይ ያሉ አካላት ጭምር ዘርፉ በዚህ ደረጃ መሰበሩ በእጅጉ እያሳዘናቸው ይገኛል፡፡

የቀደሞው መንግስት ከቆዳና ቆዳ ውጤቶች የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን ጥሬ ቆዳ ለውጭ ገበያ እንዳይቀርብ ክልከላ ጥሎ ነበር፤ በምትኩ እሴት የተጨመረበት ቆዳ ብቻ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ አቅጣጫ አስቀምጦ መስራት ውስጥ ገብቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በተለይ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመናት በዚህ ላይ ለመስራት እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል፤ ይሁንና ከቆዳ የሚገኘው ተጠቃሚነት ማደግ ሲገባው ቁልቁል እየወረደ ሄዶ ቆዳ የሚጣልበት ዘመን ላይ ከተደረሰ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

የሀገሪቱን የቆዳ ዘርፍ ተዋንያን ከገጠሟቸው ተግዳሮቶች በማውጣት እንደ ዋዛ እየተጣለ ያለው የሀገሪቱ ቆዳ ለኢንዱስትሪዎች የሚቀርብበትን መንገድ መፈለግ ወቅቱ የሚጠይቀው ተግባር ነው። ለእዚህ ስኬት ደግሞ የስትራቴጂውን መምጣት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም አሁንም በዘርፉ ላይ በሚገባ መምከርና መካተት ያለባቸው ካሉ ማካተት ያስፈልጋል፡፡

በስትራቴጂው መሰረት በዘርፉ ቀጣይነት ያለው ኢንቨስትመንት ለመሳብ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ለማሻሻል፣ የጥሬ ቆዳ አቅርቦትንና ጥራትን ለማሳደግና ሌሎች ሀገሮቶች በቆዳ ውጤቶች ያደጉባቸውን መንገዶች ለመቅሰም ጥረት ይደረጋል ተብሏል፡፡ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች መዳረሻ ሀገሮችን ማሳደግ፣ የሀገር ውስጥ ገበያን መጠቀም፣ ከውጭ የሚገቡ ኬሚካሎችን በሀገር ውስጥ ማምረት የሚሉትና ሌሎች መፍትሄዎች እንደሚተገበሩም ተመልክቷል፡፡

ሁሉም መልካም ናቸው፡፡ ምክከሩ በሌሎች መድረኮችም የሚቀጥል ከሆነ እንዲሁም ሰነዱ እስከሚፀድቅና ስራ ላይ አስከሚውል ድረስ ችግሮቹን ስኬቶቹንም በዝርዝር በመዳሰስ መካተት ያለባቸውን ማካተት ይገባል፡፡

ከዘርፉ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመኑ ጥሬ ቆዳ ለውጭ ገበያ ከማቅረብ በመውጣት እሴት ጨምሮ ብቻ መላክ ላይ ለመስራት የተሄደበት ርቀት ለምን ውጤታማ ላይሆን እንደቻለም መመልከት ያስፈልጋል፡፡

ቆዳ በዚህ ልክ እየተጣለ ባለበት ሁኔታ ኢንዱስትሪዎች ቆዳና ሌጦ ከየት እያገኙ ነው በመስራት ላይ የሚገኙት? የሚለው ጥያቄም በአግባቡ መመለስ ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ የዘርፉ አካል እየተዳሰሰ ችግሩ የት ላይ እንደሆነ ታይቶ መፍትሄውም ምን መሆን እንዳለበት መመላከት አለበት፡፡

ስትራቴጂው ሊተገብራቸው ይዟቸው የመጣ ተግባሮች አንድ ነገር ሆነው በሀገሪቱ ታሪክ ቆዳ እስከመጣል ያደረሰ ኪሳራ ላይ ለምን እንደተደረሰ በሚገባ አጥንቶ በአስቸኳይ ለችግሩ መፍትሄ በመስጠት ዘርፉ የሚያገግምበት መንገድ መቀየስ ይኖርበታል፡፡

ዘካርያስ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You