ቃልኪዳን ሽመልስ ውልደቷና እድገቷ አዲስ አበባ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የትምህርት ዘርፍ ተመርቃለች፡፡ ትምህርቱን ፈልጋው እና መርጣው ነው የተማረችው፡፡ ቃልኪዳን በከፊል የማየት ችግር አለባት፡፡ ከርቀት ማየት አትችልም፡፡ የጨለማ ፍርሃት እንዳለባትም ትናገራለች፡፡ ይሁን እንጂ ማንበብም ይሁን መጻፍ በሚገባ ትችላለች፡፡
የፖለቲካ ሳይንስ ምሩቋ ቃልኪዳን ከልጅነቷ ጀምሮ ከርቀት ማየት ስለምትቸገር በክፍል ውስጥ ሰሌዳ ላይ የሚጻፍን ነገር ወደ ደብተሯ መገልበጥ ለእሷ አዳጋች ነበር፡፡ በዚህም ከክፍል ተማሪዎቿ ደብተር በመዋስ ክፍል የተማረችውን እቤቷ ወስዳ ለመገልበጥ ትገደድ ነበር፡፡ ይህ በየቀኑ የክፍል ተማሪዎቿን ፊት እንድታይ አድርጓታል፣ ‹‹ደስ አይልም፡፡ ይህ ነገር እኔን በሚገባ ፈትኖኛል፡፡ አንዳንዴም ከርቀት ያለማየቱ ነገር ወደ ኋላ ያስቀራል፡፡›› ስትል የገጠማትን ነገር ታስታውሳለች፡፡
ይህ ዓይነቱ ችግር በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ጭምር መኖሩን የምትናገረው ቃልኪዳን ምንም እንኳን መጻፍ እና ማንበብ ብትችልም ፈታኝ ተዘጋጅቶላት ፈተናዎችን ትወስድ ነበር። እርሷ የፈተና ወረቀቶችን ለማንበብ ወደ ፊቷ አቅርባ (አስጠግታ) ስትመለከት ብዙ ሰዎች ይጨነቃሉ፡፡ ለምን አርቀሽ አታይም? እና መሰል ጥያቄዎች ይቀጥላሉ፡፡ ‹‹እንደዚህ ዓይነቱ ነገር ስለሚገጥመኝ በፈታኝ እንድፈተን ይደረጋል፡፡›› የምትለው ቃልኪዳን በዚህ ሂደት አልፋ በጥረተ ለምርቃት በቅታለች፡፡
ቃልኪዳን ፖለቲካል ሳይንስ እና ኢንተርናሽናል ሪሌሽንን ፈልጋ ያጠናችበት ምክንያት የምለውጠው ነገር እዚህ ዘርፍ ላይ ነው የሚል ዕምነት ስላላት ነው፡፡ እምነት ብቻ ሳይሆን ከልጅነቷ ጀምሮ ታሪክ እና ፖለቲካ ሲወራ በተለየ መልኩ እንደሚገባት እንዲሁም ልዩ ፍቅር እንዳላት ትናገራለች፡፡ ‹‹ታሪክ በጣም እወዳለሁ፡፡ እናም ብዙ መፍትሔ ያጡ ነገሮችን የመፍታት ብቃት ውስጤ ያለ ይመስለኛል፡፡ ለዚያ ነው ፖለቲካን የመረጥኩት። ያልተፈቱ ነገሮችን የመፍታት አቅም አለኝ ብዬ ነው የማምነውም፡፡›› ትላለች፡፡
ቃልኪዳን ከምርቃት በኋላ ተቀጥራ ሥራ ለመሥራት አንዳንድ ቢሮዎችን ታንኳኳ እንጂ በቀላሉ ሊሳካላት ግን አልቻለም፡፡ ‹‹በፖለቲካል ሳይንስ የሥራ ማስታወቂያ ማውጣት አስቸጋሪ ነው፡፡›› የምትለው ቃልኪዳን ከተቻለ ለምን መምህር አልሆንም? በማለት በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች የሥነ ዜጋ ወይም የታሪክ መምህር ለመሆን ተወዳድራለች፡፡ ይሁን እንጂ በታሪክ እና በሥነ ዜጋ (ሲቪክስ) የተመረቁ መምህራን በመኖራቸው በተመረቀችበት የትምህርት ዘርፍ ሥራ እንድትፈልግ አስተያየት እየሰጡ ይመልሷታል፡፡
ቃልኪዳን አሁን ላይ ሥራ የመቀጠሩ ነገር ተስፋ ያስቆረጣት ትመስላለች፡፡ ስለዚህም ለምን ቁጭ ብዬ እጠብቃለሁ? በማለት ሥልጠናዎችን ለመከታተል ወሰነች፡፡ በዚህም መሠረት ስለ ሊደርሺፕ (አመራር)፣ ስለ ማኔጅመንት እና የሥራ ፈጠራ ሂደትን ያካተቱ ጉዳዮች ላይ ሥልጠናዎችን እየተከታተለች ትገኛለች፡፡ አሁን ሥልጠና በምትወስድበት ቦታም በበጎ ፈቃደኝነት ለማገልገል ይሁንታን አግኝታለች፡፡ በተጨማሪም ብራይት ሳይድ የተባለ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በበጎ ፈቃድ እንድታገለግል አጋጣሚውን አግኝታለች፡፡
ቃልኪዳን ለወደፊት መገናኛ ብዙኃን ላይ ጎበዝ ጋዜጠኛ ሆና የመሥራት ፍላጎቱ አላት፡፡ እንደ እርሷ ብዙ ነገሮች ይቀየራሉ ብለው ከሚያምኑ ሰዎች ጋር በጋራ ለመሥራት ያላት ፍላጎትም ከፍተኛ ነው፡፡
ከምርቃት በኋላ ሥራ አለማግኘት የበርካታ ኢትዮጵያውያን ችግር ነው፡፡ አካል ጉዳተኛዋ ሞዴል እና ዲዛይነር ሳቤላ ከድርን በአርአያነት የምታነሳት ቃልኪዳን፤ በሁለት ቦታ ላይ በበጎፈቃደኝነት እየሠራች ትገኛለች፡፡ ዛሬ ላይ መቀጠር ብቻ አማራጭ ነው የሚል አመለካከቷም ተቀይሯል፡፡ ‹‹የሰው ልጅ አዕምሮውን መጠቀም መቻል አለበት፡፡ አቅሙ የፈቀደውን ነገር በበጎፈቃደኝነትም ሆነ በሌሎች አማራጮች ራሱን የሚቀይርበት መንገድ ማመቻቸት አለበት፡፡›› በማለት ቁጭ ከማለት የተለያዩ አማራጮችን መሞከሩ ከጭንቀት ለመገላገል አንዱ አማራጭ መሆኑን ታመላክታለች፡፡
ያምሆኖ በመንግሥት በኩል ብዙ ሥራዎች መሠራት እንዳለበት ታስረዳለች፡፡ ‹‹በመንግሥት በኩል አስፈላጊ የሆኑ እና አካታች የሆነ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅበታል። አካል ጉዳተኛውንም ጉዳት አልባውንም በእኩል ማስተናገድ ቢቻል መልካም ነው፡፡›› በማለት መፍትሄ የምትጠቁመው ቃልኪዳን፤ አንዳንድ ሰው በገንዘብ እጥረት ምክንያት በጎ ፈቃደኛ ሆኖ እንኳን ማገልገል እንዳልቻለ ትናገራለች፡፡ ስለዚህም እነዚህ ነገሮች በጣም ታስበው መሠራት ይኖርባቸዋል ባይ ናት፡፡ አካል ጉዳተኛው በቀላሉ ሥራዎችን መከወን እንዲቻለውም የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት እንዲቻልም ጥረቶች መደረግ እንዳለባቸው ጠቁማለች፡፡
እንደ ቃልኪዳን ማብራሪያ ሁሉም ሰው ተስፋ መቁረጥ የለበትም፡፡ ‹‹ከምንም ነገር በላይ ፈጣሪ ሰውን ፈጥሮ ብቻውን አይተወውም፡፡ ሰው ከጣረ የእጁን ፍሬ ያገኛል። ከሠራም ብር ያገኛል፡፡ እና ማንም ሰው እከሌ እንዲህ አለኝ፣ እከሌ እኮ ፊት ነሳኝ ብሎ ቤቱ ከመቀመጥ እንደነ ሳቤላ ጠንካራ ሆኖ መውጣቱ የተሻለ አማራጭ ነው፡፡›› በማለትም ትመክራለች፡፡
‹‹ይህች ዓለም ለጠንካሮች ነው የምትሆነው፡፡ ደካማ ከሆንን ችግሮች እየጨመሩ እንጂ እየቀነሱ አይመጡም፡፡ አንዳንድ ጊዜም ስሜትን ዋጥ አድርጎ ወደፊት መራመዱ ያዋጣል›› ባይ ናት፡፡ በቀጣይ ምን ልስራ በሚለው ጉዳይ ላይ በብዙ እያሰበች የምትገኘው ቃልኪዳን፤ ለወደፊቱ ለብዙዎች መፍትሄ የሚሆን ሥራ ለመሥራት እና ለራሷ የምትለው ነገር እንዲኖራት ጥረት ማድረጓን ቀጥላለች፡፡
ቃልኪዳን እንደ እርሷ ብዙ ወጣቶች ከምርቃት በኋላ በሥራ ማጣት ራሳቸውን ለጭንቀት መዳረግ እንደማይገባቸው ትልቅ ምሳሌ ናት፡፡ እርሷ ይህንን በማድረጓ ከጭንቀት ተገላግላለች፡፡ ነፃ አገልግሎት እየሰጠች በበጎ ተግባራት የመንፈስ እርካታን ታገኝበታለች። የትናንት ጭንቀቷ ሥራ ተቀጥሬ ብሠራ የሚል ነበር፣ ዛሬ ግን ምን ሥራ ልፍጠር? የሚል ሆኗል፡፡ ሕይወት ብዙ መንገዶች እና ብዙ መልኮች አሏት፡፡ እርሱን መፈለግ፣ መጣር እና ለስኬት ለመብቃት ተግቶ መሥራት ከወጣቶች የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ኅዳር 6 ቀን 2016 ዓ.ም