የጠልሰም ጥበብ – በመጥፋት ጎዳና

ኅዳር ሲታጠን…ጠልሰም ሲጠለሰም፤ ሁለቱም ውሃ ጥም ሲቆርጡ አንጀትን ያረሰርሳሉ ነብስንም ያለመልማሉ። ከጥበብ ጋራ ከሚፈስሱ የሸንተረር ምንጮች መካከል እንደ ጠልሰም ያለ ኩልል ያለ ውሃስ ከወዴት ይገኛል…ጠልሰም ጥበብ…ጠልሰም ባህረ ምስጢር…ጠልሰም ጸጋ…ጠልሰም የፈጣሪ እጆች…ጠልሰም የእውቀት ሰማይ…ጠልሰም ስዕል…ጠልሰም ቀለማት…ጠልሰም…ሞት ያደፈጠበት የሕይወት መንገድ ነው። በተፈጥሮ ውስጥ የተገለጡ ምድርና ሰማይ፤ በቀለማት ጠብታ ከሰው ልጆች እውቀትና ጥበብ ጋር ተዋህደው የሚፈጥሩት ይሄ ለአዕምሮ የሚከብድ ምስለ አምሳል…የጠልሰም ጥበብ ወይንም ጥበበ ጠልሰም ይባላል። የአባቶቻችንን የአዕምሮና የመንፈስ ምጥቀትን የሚያሳይ የጥበብ ሥራ ነው። ጠልሰምን ስዕል ብቻ ነው እንዳንል…በስዕል ጥበብ ላይ ያረፈ፤ ምድርንና መላውን ተፈጥሮ የምናንቀሳቅስበት እንዲሁም በቀመራዊ ስሌት የተቀረጸ ቁልፍ ነው። ይሄ ጥበብ አባቶቻችን ዘንድ ነበር። ዛሬ ግን…በነበር ልናልፈው ጥቂት ርዝራዥ ቀርቶታል። ‘ጠልሰም አስማትና ምትሀታዊ የሰይጣን ሥራ ነው’ የሚል አስተሳሰብን በወለደ ትውልድ ተረግጦ፤ ከአፈር እንዲደባለቅ ተፈርዶበታል።

ጠልሰም አስማት ወይንስ ጥበብ? የጠልሰምን እውነተኛ ማንነት አግኝቶ መጨበጥ ለተማረውም ለተመራመረውም አልገባህ ያለ ቅኔ አዘል ምስጢር ሆኖበታል። በቀለማት ጠብታ እየተሰባጠረ፤ በቃላት ምሰሶ እየቆመ የሰውን ልጅ የሕይወት መስመር የሚያቀና ምን ዓይነቱ ተዓምራዊ ጥበብ ነው ብለን ሳንጨርስ፤ ደግሞ ከወዲህ ማዶ አስማታዊ ክንፉን ዘርግቶ የሰውን ልጅ ነብስ እስከመንጠቅ ያደርሳል። ለወትሮ ከአባቶቻችን ዘንድ ሳለ የምንመለከተው ጥበባዊ የእውቀት ዳርቻው ሰፍቶ ለታመመው ፈውስ መድኃኒት፤ ለከፋው የነብስ ምግብ ተስፋው ነበር። ዘግየት ብሎ ደግሞ ጠልሰምን በመጠቀም የጠሉትን የሚያደቁ፤ ያልተገባቸውን የሚነጥቁ ግለሰቦች ብቅ ማለት ጀመሩ። ጠልሰም አስማት ነው ወይ? ጠልሰም አስማት አይደለም። ለሰው ልጆች የጦር መሣሪያ ያስፈልጋል፤ ወይንስ አያስፈልግም? ብሎ እንደመጠየቅ ነው። አዎን ያስፈልጋል በማለት ጠቀሜታውን የሚያስረዱ እንዳሉ ሁሉ ኧረ በጭራሽ…በማለት ጎጂነቱን ለማሳየት የሚሞክሩም አሉ። በሁለቱም ወገን የማይካድ ሀቅ መኖሩ ግልጽ ነው። የመሣሪያ አጠቃቀማችን እነዚህን ሁለት ጽንፍ የያዙ አስተሳሰቦችን ፈጥሯል። በጠልሰም ባሕረ ሃሳብ ውስጥ ያለው ጉዳይም መልኩ ይህንኑ ይመስላል። የጠልሰም ጥበባዊነትም ሆነ አስማታዊነት በእኛ አጠቃቀም ላይ የተመሠረተ ነው። መድኃኒት ያድናል ደግሞም ይገድላል። በእውቀትና በጥበብ ብርሃን እየተመራን ያለውን ኃይል ከተጠቀምንበት የገነትን ምድራዊ በር እንደርስበታለን። በተቃራኒው በስውር የጨለማ ጉድጓድ ውስጥ ደብቀን ካደፈጥንበት ወደ ጥልቁ የሲኦል ወለል ተሽቀንጥረን እንወድቅበታለን። በጠልሰም ጥበብ የነበረው የአባቶቻችን ራዕይ እጅግ በጣም ግዙፍ ነበር። ዛሬ ግን ይህን የሀገር ሀብት ወድቆ አገኙትና አንዳንዶች ለጥንቆላቸው ውቃቢ መቀስቀሻ አደረጉት።

ጠልሰም የሚለው ቃል በጥሬው ውክል፣ አምሳል እንዲሁም በልዩ ሁኔታ ማስዋብ ማለት ነው። በጠልሰም ውክልና ማለት እንደ አስፈላጊነቱ ከእጽዋት፣ ከእንስሳት፣ ከአፈርም ሆነ ከየትኛው ተፈጥሮ የምንወስደው የተፈጥሮ ናሙና በትክክልም ለጉዳዩ የሚሆን ኃይል አለው ተብሎ ስለሚታሰብ ነው። ለምሳሌ እጽዋት ከበሽታ የማዳን ኃይል አላቸው። ከሰው ልጆች አንደበት የሚወጣው ቃልም የራሱ የሆነ ኃይል አለው፤ ተፈጥሮን ማዘዝ ይችላል። አንድ ሰው ታሞ ወደ ጠልሳሚ አባቶች ዘንድ ሲመጣ፤ የበሽታውን ዓይነት በመመርመር ከእጽዋቱም ሆነ ከሌላ አስፈላጊውን ሁሉ በመሰብሰብ ወካይ ቀለማትን አዘጋጅተው ከበሽታው እስከ መድኃኒቱ በስዕል ይጠለስሙታል። ከዚህ የበሽታ ዓይነት ሊያድኑት የሚችሉና ኃይል የተሞሉ ቃላትን ከዚሁ ስዕል ላይ በመከተብ ጠልሰምን በጥበብ እፍታ ያዘጋጁታል። በሕክምናው ብቻም ሳይሆን በተለያዩ ዘርፎች ለእያንዳንዱ ጉዳይ ተዓምራዊ መፍትሄን ሲሰጡበት ኖረዋል። በጠልሰም ጥበብ የተነደፉ አባቶቻችን ጂኦግራፊ አልተማሩም፤ ጂኦግራፊ ከእነርሱ ተማረ እንጂ… እራስዋ ተፈጥሮ እንጂ ባዮሎጂንም ጠመኔ ይዞ በጥቁር ሰሌዳ ያስተማራቸው የለም። የዚህን ጥበብ ምስጢራዊ እውቀቶችን በብዙ የብራና መጽሐፍቶቻቸው ላይ ያስቀመጡት ቢሆንም፤ የተሰረቁት ተሰርቀው የጠፉትም ጠፍተው ዛሬ በጥቂት ገዳማትና አድባራት ላይ ብቻ ይገኛሉ። የዚህ ጥበብ የምስጢር ተካፋይ የሆኑት ጠልሳሚዎቹም ቢሆኑ በትውልድ ቅብብሎሽ መሃል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመኑ ወደመጥፋቱ ተቃርበዋል። የጥበቡ ምንጮች በጉልህ ከወዴት እንዳሉ ባይታወቅም፤ የመፈወስ ኃይል እንዳለው የሚያምኑ አንዳንድ ሰዎች፤ ዛሬም ጠልሰምን በክታብ መልክ አስረውት እንመለከታለን። ጠልሰም ሃይማኖታዊ ቢመስልም፤ ነገር ግን ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ ይዘት የሌለው ግዙፍ የሆነ ሳይንሳዊ ጥበብ ስለመሆኑ በምርምር ጠልሰምን ፍለጋ የወጡ ሁሉ ይመሰክራሉ።

ጠልሰም መቼና እንዴትስ ተጀመረ?..የጠልሰም የስዕል ጥበብ በሀገራችን በረዥም የታሪክ መስመር ላይ ተጉዟል። የመነሻ ታሪኩ ወደ ሁለተኛው ክፍለ ዘመን ይወስደናል። ያኔ የጀመረው የአባቶች ጥበብ በስዕል አቡጊዳ አሊያም በሳይንሳዊ ምርምር የመጣ አልነበረም። ዛሬ ሳይንስ የቱንም ያህል ቢመጥቅ ያለ መርፌና ኪኒን ሊያድን አይችልም። የእኛ አባቶች ግን ከሳይንስ ቀድመው ተወልደው በእኛ ጉራማይሌ ሳይንስ ሞተዋል። ተፈጥራዊ ሰውነታቸውን በተፈጥሮ ብቻ በማከም በሕክምናው ዘርፍ ያገኟቸውን ግኝቶች ዛሬ ላይ ሳይንሱ ከላይ እያጣጣለ ከስር ቢያነፈንፈውም ሊደርስበት ግን አልቻለም። ጠልሰም የራሱ የሆኑ የተለዩ አላባውያን አሉት፡፡ ከእነዚህም ዕጽዋት፣ ኃይልን የታመቁ ቃላትና ልዩ ልዩ ምልክቶች ተጠቃሾች ናቸው። የጥንት አባቶቻችን ጥበብን ከእውቀትና እረቂቅ ከሆነው መንፈሳቸው ጋር አዋህደው የሚፈጥሩት ምልክታዊ እምቅ ኃይል ነው። በዚህም ምክንያት የአስማት ስዕል በማለት ብዙዎች ይፈሩታል። በጠልሰም አዋቂዎች ዘንድ ሁሉም የሚስማሙበት አንድ ፍልስፍና አለ። ይህም የሰው ልጅ የፈጣሪ ጠልሰም ነው። ጠልሰም ማለት የአንድ ነገር መልክ በመሆኑ፤ ፈጣሪም የሰውን ልጅ በአምሳሉ ፈጥሯልና የእርሱ መልክ ነው። ፈጣሪ በሰማይና በምድር ሁሉ ሙሉ ሥልጣንና ኃይል አለው። የሰው ልጅ ደግሞ የእርሱ አምሳል በመሆኑ ለሰው ልጅ በምድር ላይ የተሰጠው ኃይልና ሥልጣን አለ። ምድርን እንዲገዛ በምድር ያለውን ሁሉ ሰጥቶታል። ስለዚህ ጠልሰም ማለት ፈጣሪ የሰጠንን ነገር በጥበብ የምንጠቀምበት መክፈቻ ነው። በጠልሰምም የምናገኘው ይህንኑ ምድራዊ ኃይል ነው። የምድርን ቁልፍ ፍለጋ በተደረገ ጥበባዊ አሰሳ ጠልሰም ተወለደ፡፡

የጠልሰም ጥበብ ከምን ይወለዳል? ከስዕል ጥበብ ወይንስ ከመንፈስ ሃሳብ?… አንድ ጎበዝ ጠልሳሚ ለመሆን ጥሩ የስዕል ተሰጥኦ ሊኖር የግድ ነው። እንደማንኛውም ሰዓሊ ይህ ብቻ ጠልሳሚ አያስብለንም። ከሀገር ከርሰ ምድር እስከ ሕዝቦቿ ያለውን ውስጣዊ ማንነት ማወቅ ያስፈልጋል። ከእጽዋቱ እስከ አራዊቱ መመርመርን ይጠይቃል። ከአፈርና ድንጋዩ ጋር ማውጋት፤ እየዳሰሱ በመጫወት እያሸተቱ በመለየት ተፈጥሮን ጥንቅቅ አድርጎ ማወቅ ወሳኙ ነገር ነው። ጠልሰም የሚከወነው በስዕል ጥበብ ውስጥ ቢሆንም ከመደበኛ የስዕል ጥበብ የሚለይባቸው በርካታ ነገሮች አሉ። ሁለቱን አንድ የሚያደርጋቸው ደግሞ ስዕል የምናብ ፈጠራ እንዳለበት ሆኖ እውነተኛና ያለን፤ የሚኖር ነገርን መወከሉ ነው። ሁለቱም የተለየ ችሎታን የሚጠይቁና የአንድ ነገር ውክልና ያላቸው መሆናቸውም ጭምር። ከዚህ በተለየ ጠልሰም መሠረታዊና ሁሉም የጠልሰም ሊህቃን የሚግባቡት የራሱ የሆነ ቋንቋ አለው። እንደ ስዕል በራሳችን ፍልስፍና እንደገባን ብቻ የምናስቀምጠው አይደለም። አሐዛዊ ስሌቶችም የተካተቱበት ነው። አንድ ጠልሰም፤ ጠልሰም ለመሆን መልክ፣ ቁጥር፣ አሥራ ሦስቱ ወራት፣ ምልክት እና ሐረጎች ወይም ቃላት በአንድ ሊሰደሩ የግድ ነው።

ይህ ጥበብ በዓለማችን በተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ውስጥ የሚገኝ ቢሆንም ረቂቅነቱም ሆነ የግዝፈት ደረጃው በእኛ ሀገር የነበረውን ግን አይስተካከልም። ለዚያም ነው የእኛን ብራና መጽሐፍት አጥብቀው የሚሹት። ኢትዮጵያዊ የሆኑ ልዩ ልዩ ምልክቶችን የራሳቸው እንደሆነ ነገር አድርገው በኩራት ሲጠቀሙባቸው እናያለን። ለምሳሌ ያህል በላሊበላ ውቅር አቢያተ ክርስቲያን አናት ላይ የሚገኘውን ዞዲያክ፤ የጀርመን ናዚዎች ወስደው አቀማመጡን ብቻ በተቃራኒው በመገልበጥ የወታደሮቻቸው አርማ አድርገውታል። ይህም በደንብ ልብሶቻቸው ላይ ሳይቀር ይጠቀሙበታል። በአሜሪካን የኮንግረስ ምክር ቤቱ መግቢያ ላይ ከሚገኘው የንስር አሞራን ጨምሮ በርካታ ምልክቶቻችንን ተነጥቀን እኛም እንደዋዛ ረስተናቸዋል። በጠልሰም ጥበብ ውስጥ አባቶቻችን ሲጠቀሙባቸው የነበሩትን ልዩ ልዩ ዞዲያኮችንም ሆነ የጠልሰም እውቀት፤ በሀገር ደረጃ ወጥቶ እንዳያገለግል ብዙ ጉዳዮች የተጋረጡበት መሆኑ ነው። ከዘመናት በኋላ እኚያ ሁሉ ጥበብ እኚያ ሁሉ እውቀት፤ አስማትና የመናፍስት ሥራ ናቸው ተብለው አወቅን በሚሉ አላዋቂዎች ተወገዙ። ሳይንስ የራሱን ኪስ ለማደለብ ሲል የእኛን ጥበብ ጨምድዶ ወደ ገደል ጣለው። በውስጡ ምስጢራትን ያዘለ በመሆኑ እውቀቱ በጥቂት ማኅበረሰብ ውስጥ ባሉ ጥቂት ቤተሰቦች ሲተላለፍ ኖሯል። ጠልሰምን ጨምሮ ሀገራችንን ሊለውጡ የሚችሉ ብዙ ቁልፎችን የያዙ ምስጢራዊ ቤተሰቦች ዛሬም ድረስ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች አሉ።

የጠልሰም ጥበብ ዛሬ ላይ በመጥፋት ጎዳና ላይ እያዘገመ ይገኛል። ታምቆ ከነበረበት በባለቤትነት ወደ አደባባይ የሚያወጣው ባለማግኘቱ ወደ መክሰምና መኮሰስ ገብቷል። ብዙ ሊህቃንና የስዕል ጠቢባን በጠልሰም ዙሪያ ምርምር በማድረግ የእውቀቱን ጅራት ለመያዝ ቢታገሉም፤ በዋዛ እጅ የማይሰጥ እረቂቅና ድብቅ ሆኖባቸዋል። አሁን አሁን ሰዓሊያኑ በጥቂቱም ቢሆን በሥራዎቻቸው መሃል እንደ ማጣፈጫ ጠብ ሲያደርጉት እንመለከታለን። ከሀገራችን እውቅ ሰዓሊያን መካከል እስክንድር በጎሲያን፣ ወርቁ ጎሹ እና ዘሪሁን የትምጌታ ጠልሰምን ከዘመናዊው ስዕል ጋር አዋህዶ በመጠቀም ግንባር ቀደሞቹ ናቸው። ጠልሰም ከወደቀበት እንዲነሳ አድርገን በተቋም ደረጃ ሀገርና ሕዝብን የምንለውጥበት ቁልፍ ቢሆንም፤ አሁን ግን የመኖርና የመሞት ዕጣ ፈንታው ከሰዓሊያኑ እጅ ላይ ነው። የዚህን ጥበብ ግዙፍ ጠቀሜታ በመረዳት ከማንም ፈጥኖ ለመድረሱ ከእነርሱ የሚቀርብ አይኖርም። ይህን የተረዱም ዛሬን ስለጠልሰም በመሯሯጥ ላይ ናቸው።

የእኛ አባቶች የዓለምን ምስጢራዊ የእውቀት ቁልፍ የያዙ እውነተኛ የምድር ጌቶች ነበሩ። ከእነርሱ የተሰወረች ምስጢር፤ በልባቸው ያላደረች ጥበብና በአዕምሮዎቻቸው ያልፈሰሰ እውቀት ያለ አይመስልም። ለዚህም ነው ዛሬ ዓለም ሁሉ የረገጡበትን የእግር ኮቴ፤ የእጆቻቸው ዐሻራ ያረፈባቸውን የብራና መጽሐፍቶቻችንን እያነፈነፈ የሚያድነው። የእኛ የሆነውን ነገር ለማግኘት እንዲያ ሲያስሱ፤ የጥበብና እውቀቱ ባለቤት የሆንነው እኛ ግን ‘አይሞቀኝ አይበርደኝ…’ ብለን፤ ፍዝዝ ድንዝዝ ማለታችን ምኑን ቢያስነኩን ይሆን? የእኛ ጥበብ…የእኛ እውቀት አይነጥላ እየሆነብን ምትሀት…አስማት…የሰይጣን… እያልን አሽቀንጥረን የጣልናቸው የጥበብ አቁማዳዎች ቁጥር ስፍር የላቸውም። መርዶም ሳንቀመጥ ገድለን የቀበርናቸው የአባቶቻችን ጥበቦች፤ የሙት መንፈስ ቢኖራቸው ኖሮ በህልም፤ በቁም ቅዠት እየመጡ መውጫ መግቢያ ባሳጡን ነበር። ከእነዚህም መካከል አንደኛው ‘ርስተ ጌታ’ የተባለውና ከጠልሰም በፊት የነበረው ግዙፍ ጥበብ አንደኛው ነው። ምን ቀረሽ የማትባል የጥበብ ጸጋ በ’ርስተ ጌታ’ ተገልጣ ነበር። ጥበብ አካለ እውቀትን ለብሳ፤ ባልተበረዘውና ጸአዳ በሆነው የአባቶቻችን የልብ ዙፋን ላይ ተቀምጣም ነበር። ዛሬ ታዲያ ይሄ ሁሉ የት አለን? ከእኛ አባቶች የወረስነው የመጠሪያ ስምና የዘር ግንድ ብቻ ነውን?

እንደ ‘ርስተ ጌታ’ ሁሉ የቀረችውንም የጠልሰምን ጥበብ ጥለን እፎይ!… ተገላገልን እንበል? ወይንስ ሳንቀደም ቀድመን፤ ጠልሰምን ከጻዕረ ሞት አድነን እኛም እንዳንበት? በጥቂት ብራናዎች ላይ በጠልሰም ጥበብ ዛሬም ድረስ ሰፍረው የሚገኙትን ምስጢራት መፍታት ከቻልን፤ አሁንም አረፈደም…ሀገርና ሕዝባችንን እንቀይርበታለን። ጠልሰም ዘ ጥበብ

ነህ

በ19 መቶ በዜሮ ዜሮ ጥቅምት 15ት፤

የዓድዋ ባለ ድል ዳግማዊ ምኒልክ ያቋቋሙት፤

የኢትዮጵያ ክብር የአፍሪካ ኩራት፤

አደባባይ ወጣን መቶ አስራ ስድስተኛውን ልናከብርለት።

መከላከያችን የድንበር አጥራችን፤

የሀገራችን ክብር ዘብ የህልውናችን፤

የአብራካችን ክፋይ የበኩር ልጃችን፤

የጀግኖቹ አንበሳ አንተ ከፊት እንጂ አትሁን ከኋላችን፤

የኢትዮጵያ ሠራዊት መከላከያችን ከዚህም በላይነህ እናከብርሃለን።

ቀን በደህና ውሎ ሰላም ውሎ መግባት፤

እፎይ ብሎ ተኝቶ መነሳት፤

ከፈጣሪ በታች አንተ ስላለኸን የልባችን ኩራት።

ሰላም ሰላም ብዬ ሰላም ልበልህ፤

ቢያንስብህ ነው አንጂ ለአንተ አይበዛብህ፤

መከላከያችን ኩራታችን እና መመኪያችን ነህ።

መዝገበ ከበደ ባይሞትኖሮ

ሐሙስ ጥቅምት 15 ቀን 2016ዓ.ም

ኮተቤ ካራ(አዲስ አበባ)

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You