የኅዳር ወር ንፋስ በርትቷል፡፡ ልክ እንደድሮ ጥቅምት፤ ውርጩ ፊት ይለበልባል፡፡ ቀኑን ሙሉ ቢሮ ውስጥ ተቀምጠው የሚውሉት ዘውዴ መታፈሪያ፣ ገብረየስ ገብረማርያም እና ተሰማ መንግስቴ የቀትር ፀሐይ ሳያሞቃቸው ውለዋል። እንደለመዱት አመሻሽ ላይ በቢራ ለመሟሟቅ ማምሻ ግሮሰሪ ተገናኙ፡፡ ሦስቱም በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ሰፍረው የሚጠጡትን አዘው ጨዋታ ጀመሩ። የዛሬው ትልቁ አጀንዳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡
ተሰማ ፊቱ ላይ የተለየ ደስታ ይነበባል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ያረካው ይመስላል። ገብረየስ እና ዘውዴ ግን ብዙም ለውጥ አይታይባቸውም። እንደለመደባቸው ዘወትር የሚታይባቸው የተለመደ ዓይነት ስሜት ነበር፡፡ አልሞቃቸውም፤ አልበረዳቸውም፡፡ አልከፋቸውም፤ አልተደሰቱም፡፡ ዕለቱ ከሌላው ቀን የተለየ አልሆነላቸውም፡፡
ተሰማ ውስጡ ያለው ደስታ እየተናነቀው፤ ‹‹ ዛሬ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በተለይ ‹እኛ እይታችን ሀገራዊ ነው› ብለው አስረግጠው መናገራቸው በጣም አስደስቶኛል። በትክክልም ‹ኢትዮጵያ ከሁሉም ጫፍ ያሉ ዜጎቿ፤ በእኩል በነፃነት የሚኖሩባት፤ ሁሉ እምነት የሚከበርባት፤ ሁሉም ቋንቋ ሁሉ ባህል የሚከበርባት፤ የጎላች ያማረች የበለፀገች ሀገር የምትፈጥርበትን መንገድ እንሻለን።› ማለታቸው ማንኛውም ጤነኛ አስተሳሰብ ያለው ሰው ይደግፈዋል፤ ይህም ያስደስተዋል ብዬ አምናለሁ፡፡›› አለ፡፡ ተሰማ ይህንን ሲናገር ገብረየስ እና ዘውዴ እንዴት እየተመለከቱት እንደነበር አላስተዋለም፡፡ ሁለቱም ዝም አሉ፡፡
ተሰማ ምላሽ ሳይሰጡት ቢቀሩም፤ ምንም አልመሰለውም፡፡ ያስደሰተውን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር እየመዘዘ ለማስረዳት መሞከሩን ቀጠለ፡፡ ‹‹ሁላችንም ወንድማማቾች መሆናችንን የገለፁበት መንገድ ‹ የኢትዮጵያ መሠረት እያንዳንዱ ዜጋ ነው። ያ ዜጋ በጊዜ ሂደት ውስጥ ቋንቋና ባህል ቢያዳብርም፤ የራሱ እምነት ቢኖረውም፤ ሲጀመር ግን ያው ሰው ነበር። ኦሮሞ የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ ሲዋለድ ኦሮሞን የሚያክል ብሔር ፈጠረ፡፡ አማራ የሚባል ወይም ከአማራ አካባቢ የተነሳ አንድ ሰው ነበር፤ ሲዋለድ አማራን ፈጠራ፤ እንጂ ሲጀመር ጀምሮ ኦሮሞ የሚባል ብሔር ወይም አማራ የሚባል ብሔር የለም፡፡
አንድ ሰው በጊዜ ብዛት አንድ ቤተሰብ መሠረተ፤ የቤተሰብ ብዜት ውጤት ወደ ብሔር አደገ። ይሄ የሚያሳየው መሠረታችን ሰው መሆኑን ነው።› የሚለው ገለፃቸው እጅግ አስደስቶኛል። ‹ስለዚህ ሁላችንም ሰው ነን፡፡ ያዳበርነው ቋንቋ ማንነትና በጊዜ ብዛት የገነባነው ቤተሰብ ቢኖረንም ሁላችንም መሠረታችን አንድ ነው፡፡› ማለታቸው እኔ እና እናንተ ምንም ሊያጋጨን የሚገባ ነገር የለም ማለት ነው፡፡›› አለ፡፡
ገብረየስ ቀበል አድርጎ ለተሰማ ‹‹ እምንባላውና የምንጋጨውማ ብልህ ያመቱን ሞኝ የዕለቱን የሚለውን ብሂል ረስተነው ነው፡፡ የምናየው የፊት የፊታችንን የዕለቱን ብቻ ነው፡፡ ሁላችንም እኩል ሰው መሆናችንን ዘንግተን፤ ሌሎች ሰዎች እንዳልሆኑ ለመነጠል፤ ለመለየት እና ለማጥፋት እንሞክራለን፡፡ በትክክል ማንም ላስተውል ብሎ ዓይኑን ገልፆ ልቡን ከፍቶ የተመለከተ ሰው በደንብ ካሰላሰለ የሚያጋጭና የሚያባላው ምንም ነገር የለም፡፡ በእርግጥም አንድ ሰው ቤተሰቡን የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ነገር ግን ያ ኃላፊነት ሰዎችን እስከ ማጥፋት የዘለቀ ሊሆን አይገባም፡፡ ይህን ማድረግ ማለት ዛሬ ቤተሰቤን እጠብቃለሁ ብሎ የሌላውን ቤተሰብ ያጠፋ ሰው ነገ የእርሱም ቤተሰብ የሚጠፋ መሆኑን መገንዘብ አለበት። የዕለት የዕለቱን እያሰበ ሲንገበገብ ዛሬውን እያበላሸ፤ ነገውን ያደበዝዛል›› አለ፡፡
ዘውዴ ምንም አልተነፈሰም፤ ሁለቱም ተራ በተራ ሲናገሩ ያዳምጣል፡፡ በዛው በደስታ ስሜት ውስጥ እየዋኘ ያለው ተሰማ ገብረየስን በመደገፍ ቀጠል አድርጎ ‹‹ትክክል ብለሃል፤ ሁሉም አንድ ቤተሰብ ነው፡፡ አንዱ በሌላው ላይ ተነስቶ፤ ሌላውን ለመግደልም ሆነ በማንኛውም መልኩ ለማጥፋት ቢሞክር ድሉ ጊዜያዊ ነው፡፡ ድሉ ዘላቂ መሆን አይችልም፡፡ ዘላቂ ውጤት የሚገኘው በጦርነት ሳይሆን በሰላም ነው። በእርግጥም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ሁሉ፤ ‹ ለእኛ የቸገረን ነገር ሰላም ነው።› ሰላም ጠምቶናል። ሰላም ሆነን ብንሠራ በእዚህ ጊዜ ከእዚህ የተሻለ ደረጃ ላይ እንደርስ ነበር፡፡›› አለ፡፡
ዘውዴ እንደተቀመጠ ትንሽ ተነቃንቆ ጉሮሮውን ከጠራረገ በኋላ በጎርናና ድምፅ፤ ‹‹በደመና ጊዜ ስለመብረቅ አይወራም፡፡ ለሚወራውም ቀን ያስፈልገዋል፡፡ ያለበለዚያ መአት መጥራት ነው፡፡ የጠሩት መዓት ቢዘገይም አይቀርም፡፡ ከአፍ የወጣ ከጥርስ የነጣ እንደሚባለው ሁሉ፤ ሰላም ከፈለግን ሰላማዊ መንገድን እንደዋነኛ አማራጭ መውሰድ አለብን። በእርግጥ የሁሉም ሕዝብ ምኞት ሰላም ነው። ሕዝቡ ሰላም እና ልማት ይፈልጋል፤ ድህነት እንዲቀንስ ይፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ ከችግር እንድትገላገል ይፈልጋል፡፡ ዴሞክራሲ እንዲገነባ ይፈልጋል፡፡ ተቋማት እንዲገነቡ ይፈልጋል፡፡ ጦርነት የሚፈልገው ማን ነው? ይህንን በደንብ አጥርቶ መለየት ይገባል፡፡ በእርግጥም በፍፁም ሕዝብ ጦርነት አይፈልግም፡፡ ›› አለ፡፡
ተሰማ እንደተለመደው ዘውዴን መቃወም ጀመረ፤ ‹‹ትክክል ነህ! ሕዝብ ተጠቅሎ መሰደብ የለበትም፡፡ ሕዝብ ጦርነት ይፈልጋል ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን ጥያቄ አለኝ፡፡ በእርግጥ ሕዝብ ጦርነት አይፈልግም? ነገር ግን መካድ የማይቻል አንድ ነገር አለ፡፡ ኢትዮጵያውያን በጄ ብለው መንግሥት ነው ብለው ተቀብለው አብረው የኖሩለት ደግፈው ያበረቱት መንግሥት አለ ብሎ ለመከራከር ብዙ ምርምርን ይጠይቃል፡፡ ሁሌም ግጭት የሚመስል ነገር አለ፡፡ መጠኑ ምን ያህል ነበር? የሚለው ላይ መነጋገር ይቻላል፡፡ ነገር ግን ይብዛም ይነስም፤ ከመንግሥት ጋር መታገልን እኛ ኢትዮጵያውያን በተደጋጋሚ የምንፈፅመው ጉዳይ ነው፡፡ አባት ያቆየው ለልጅ ይበጀው። የሚባለው በጎ ነገር ሲቀመጥ ነው፡፡ እኛ ጋር ደግሞ መጥፎ ልማድ በመቀመጡ አባት ያቆየው ለልጅ አይበጀው በሚል አባባሉ በተቃራኒው እየተተገበረብን ነው።›› አለ፡፡
ገብረየስ እዚህ ላይ ተቃውሞ አለኝ በሚል ስሜት እልህ እየተናነቀው መናገር ጀመረ። ‹‹መጀመሪያ ሕዝብ ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውን በደንብ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ‹ሕዝብ የለመደው መደገፍ ሳይሆን መቃወም ነው።› የሚለውን ሃሳብ አልስማማበትም፡፡ የተወሰኑ ሰዎች የሕዝብ መገለጫ እንደሆኑ ተደርጎ መጠቀስ የለበትም፡፡ በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ‹ከመገዳደል እና ከመገዳደር፤ ሁልጊዜም እየተገፋፉ ኃይል ከማባከን ይልቅ ንግግርን እና ሰላምን ማስቀደም ይበጃል፡፡
በጦርነት ገንዘብ፣ ጊዜ እና ጉልበት ብቻ ሳይሆን ትውልድን ከመጨረስ እና ከማስጨረስ ይልቅ በትጋት ለሁሉም እንሥራ፡፡ ሥራን እናስቀድምና የድህንነት ታሪካችንን እጥፋት እናበጅለት፡፡›› ሲል እርሱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተላለፏቸው ሃሳቦችን እንደሚደግፍ ተናገረ፡፡
ተሰማ በበኩሉ፤ ‹‹ለነገሩ የእዚህች ሀገር ዋነኛ ችግር ብለን ልንጠቅሳቸው የምንችላቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ ዋናው ነገር አስቸጋሪዎች ነን። አስቸጋሪ እንግዳ ትራሱን ዘቅዝቆ ይተኛል። እንደሚባለው ማስቸገር ልማዳችን ነው፡፡ እናንተ የፈለጋችሁትን ብትሉም እኔ በበኩሌ እንደማንመች አምናለሁ፡፡›› አለ፡፡
ገብረየስ በበኩሉ ተሰማን እየተቃወመ መሆኑን ለመግለፅ ፈለገ፡፡ ‹‹ዋናው ችግር የሕዝብ አለመመቸት ጉዳይ ሳይሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ‹የሃሳብ አለመኖር ነው፡፡ ሰዎች ሃሳብ ቢኖራቸው ከግለሰብ ጋር ሳይሆን ከሃሳብ ጋር ይጨቃጨቁ ነበር፡፡ አሁን ብዙ ሰው የተሻለ አመራጭ ሲያመጣ አይታይም፡፡ የመጣን አማራጭ በግራና በቀኝ በስሜትና በተሳሳተ ስሌት መተንተን ልማድ ሆኗል፡፡ ይሄ ደግሞ ኢትዮጵያን ወደ ፊት አይወስዳትም።› ብለዋል፡፡ የእኔም እምነት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተመሳሳይ ነው። ኢትዮጵያን እየበደላት ያለው የሃሳብ ድርቀት ነው፡፡ በሃሳብ ድርቀት ሳቢያ ከመገዳደር ይልቅ መገዳደልን እንደሞያ ተያይዘነዋል፡፡
አንዳንዶች ደግሞ ሃሳብ ያስባሉ፤ ምኞት ይመኛሉ፤ ልክ ፈጣሪውን ባዶ እጁን ባርክልኝ እያለ እንደሚለምነው ሰው፡፡ ፈጣሪው ሊባርክለት ሲል ባዶ እጁን እንደተገኘው እና እንዳልተባረከለት ሰው ይሆናሉ፡፡ በእርግጥም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ ‹ ሃሳብ ብቻውን በቂ አይደለም፤ ሃሳብ መተግበር አለበት፤ ለመተግበር ትጋት ይፈልጋል። ቀን ከሌሊት መልፋት ያስፈለጋል፡፡ ካልተሠራ እና ካልተለፋ በስተቀር ለውጥ አይመጣም። ለዚያውም ልፋቱም ቀጣይነት ያለው መሆን አለበት፤ የአንድ ሰሞን ሥራ ብቻ ሳይሆን ሁሌ የሚደረግ ጥረት መኖር አለበት፡፡
ሃሳብ መንጭቶ ተግባር ሲታከልበት ግጭት ይቆማል፡፡ አሁን ግን እንኳን ተግባር አዲስ ሃሳብ የለም፡፡ ሰዎች አዲስ ሃሳብ ቢኖራቸው ይህና ባደርግ፤ ያንን ብተው፤ ይህን ብጨምር እያሉ አዕምሯቸውን በራሳቸው አዲስ ሃሳብ እና ሃሳባቸውን ተግባራዊ በማድረግ ዙሪያ ስለሚወጠሩ ለመገዳደል አይነሱም ነበር፡፡ የተሻለ ሃሳብ ሲኖራቸው በሃሳብ ለመገዳደር ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን አለመታደል ሆነና ዘመናችንን በመገዳደል ፈጀነው፡፡›› ብሎ ገብረየስ በረዥሙ ተነፈሰ፡፡
ተሰማ በገብረየስ ገለፃ ተደሰተ፡፡ ገብረየስን እየደገፈ፤ ‹‹አዲስ ሃሳብ አመንጪ በዝቶ፤ የሚተጋ ተበራክቶ ሁሉም በየራሱ የሕይወት ለውጥ ላይ ቢረባረብ ብዙዎቻችን እንደምንመኘው ሰላም ብቻ ሳይሆን የኢኮኖሚ እድገት እና ዴሞክራሲም ብርቅ አይሆንብንም ነበር፡፡ የፓርቲ አመራሮችም ሆነ እያንዳንዳቸው ፓርቲዎች በበቂ መጠን ሀገር የሚጠቅም ሃሳብ ቢኖራቸው ኖሮ፤ በእነሱም ላይ የወደፊት ተስፋችን ይለመልም ነበር፡፡ ትልቁ ጉዳይ ግለሰብም ሆነ ቡድን እንዲሁም ድርጅት ብቃት ያለው የነጠረ ሃሳብ ሊኖረው ይገባል፡፡
እኛ ግን ‹ነገር ወዳጅ ሰው ከመንገድ ዳር ቅበሩኝ› ይላል፡፡ እንደሚባለው ነገረኞች ነን፡፡ ለመጣላት፣ ለመጋጨት እና ጦር ለመማዘዝ ነገር እንፈለፍላለን። የሌለ ታሪክ ፈጥረን ካልተጋደልን ብለን ለያዥ ለገናዥ እናስቸግራለን፡፡ የእኛ ነገር ይኸው ነው። በሃሳብ ከመገዳደር ይልቅ ምርጫችን ምንጊዜም መገዳደል ነው፡፡›› ብሎ ሃሳቡን ደመደመ፡፡
ዘውዱ ለተሰማ ምንም ምላሽ አልሰጠም። ለዛሬ ዝምታን መርጧል፡፡ ገብረየስ ግን ‹‹ማለዳ የምትለቅም ዶሮ ጭልፊት አትጠልፋትም፤ እንደሚባለው ማንም ቢሆን ባገኘው ዕድል ሌሊቱ ሲነጋለት ማልዶ መሥራት አለበት። አለመሥራቱም ያው ነው፡፡ ዕድሉን አግኝቶ ካልሠራ ‹ገበያ ሂዳ ማንቀላፋት ሁለተኛ ጥፋት፤› እንደሚባለው ይሆናል። መሸጧን ትታ ስታንቀላፋ እንደተዘረፈችዋ ነጋዴ ከማይወጡበት ችግር ውስጥ መግባት ያጋጥማል። በሕይወታችን እያንዳንዳችን የምናደርገው እንቅስቃሴ በጥንቃቄ ካልታጀበ፤ አልሞትም ብሎ ሔዶ የማይቀበርበት ሀገር ደረሰ፡፡ እንደተባለው ሰውዬ የምንገባበት ችግር የማንወጣው ዓይነት ከባድ ይሆናል፡፡ ማንም ገድሎ ማትረፍ አይችልም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት አማራና ኦሮሞ ቢፈልጉም ባይፈልጉም በሰላም ለመኖር ያላቸው ምርጫ የአንድ ሀገር ዜጎች ወንድማማች መሆናቸውን አውቀው፤ ተከባብረው አብረው መኖር ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው አማራጭ ምንም አይጠቅምም። ወደ መልካም ውጤትም አይወስድም። ሌሎቹም ብሔሮችም ቢሆኑ፤ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በሰላም በፍቅር በትብብር ከመኖር ውጪ ምንም አዋጭ አማራጭ የላቸውም። የሚበጀው ሰላም፣ ፍቅር እና አብሮነት ብቻ ነው። ያለበለዚያ ግን ሞኝን ሁለት ጊዜ እባብ ነደፈው እንደሚባለው፤ ሁለት እና ሦስተኛ መገዳደል እና እልቂት ሀገርን ቁልቁል ወደ ኋላ ከመጎተት ውጪ ምንም ትርፍ የለውም፡፡
ፈተና ቢመጣ ፈተናውን በፅናት ለማለፍ አዲስ ሃሳብ ማመንጨት ተገቢ ነው፡፡ አዲስ ሃሳብ አመንጭቶ ተግቶ መሥራት ያስፈልጋል። መገዳደል በዝቶ ወንዙ በውሃ ተሞልቶ ክረምት ላይ ለመሻገር ቢያዳግትም፤ አዲስ ሃሳብ መንጭቶ፤ አዲስ ሃሳብ በትጋት እውን ሆኖ በጋ ሲመጣ ውሃው ደርቆ መሻገር ተራ የሚሆንበት ዕድል ስለሚፈጠር አዲስ ሃሳብ ማመንጨት ላይ እናተኩር፡፡ ከመገዳደል ይልቅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት በሃሳብ እንገዳደር፡፡›› ብሎ እርሱም ሃሳቡን ቋጭቶ ወደ ቤቱ ለመሔድ ብድግ አለ፡፡
የፌኔት እናት
አዲስ ዘመን ኅዳር 6 ቀን 2016 ዓ.ም