ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ኃይል እጦት በኋላ ቀር ኑሮ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችዋን ለመታደግ የተያያዘችውን የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሥራ አጠናቅቃ ከዳር እንዳታደርስ በርካታ እንቅፋቶች ገጥመዋታል። ሆኖም ግን እንቅፋቶች ሳይበግሯት በሰራቻቸው ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራዎች እሾህና አሜካላዎችን እያለፈች ግድቡን ወደ ማጠናቀቅ ደርሳለች፡፡
በውሃ ዲፕሎማሲ ላይ ስለተሰሩት ሥራዎችና የተገኙ ውጤቶች እንዲሁም በባሕር በር ዙሪያም ያነጋገርናቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና የዓባይ ጉዳይ ተመራማሪ ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ እንደሚከተለው ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እውን መደረግን ተከትሎ ከተለያየ አቅጣጫ የነበረውን ጫና ለመመከት በኢትዮጵያ በኩል የተሰሩ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ቢያብራሩልን?
ዶክተር ያዕቆብ፡- የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ወዲህ ከፍተኛ የሆነ የዲፕሎማሲ ጫና ተፈጥሮብን ነበር፡፡ የመጀመሪያው ጫና በግብጽና ሱዳን የተፈጠረ ሲሆን፤ ሀገራቱ በዚያን ጊዜ በአንድ ላይ ነበር የሚያስቡት፡፡ እኛን ሳታስፈቅዱ፣ ሳታማክሩ ግድቡን ልትሰሩ አትችሉም ይሉ ነበር፡፡
ለምርምር ሥራና ለጉባኤ ወደ ግብጽና ሱዳን ሀገራት ስንሄድ በፍጹም ሊታመኑ የማይችሉ አሉታዊ ሃሳቦችን ያንጸባርቁ ነበር፡፡ እኛን የሚጨርስ፣ ሕዝባችንን ለችግር የሚዳርግ፣ እርሻችንን የሚያደርቅ ሕዝባችንን ወደ ረሃብ የሚከት ግድብ ኢትዮጵያ ልትሰራ አትችልም፤ ከጀመረችም ማቆም አለባት የሚል ዘመቻ ነበር የሚያካሂዱት የጦርነት ዛቻም አለበት፡፡
የምዕራቡ ዓለም ደግሞ ብዙን ጊዜ ግብጽን ነው የሚሰማው፡፡ ግብጽ በጂኦ ፖለቲካ ረገድ በአውሮፓ፣ በእስያና በአፍሪካ መካከል ስላለች እና ለረጅም ዘመናት አውሮፓና አሜሪካ የሚሉትን ተቀብላ ስለምታራምድ በአፍሪካም በመካከለኛው ምሥራቅም፤ እንዲሁም ግብጽ በአረቦችና በእስራኤል መካከል ያለውን ግጭትና አለመግባባት እኔ ነኝ ድልድይ ሆኜ ግጭቱ እንዳይሰፋ፤ ጥረት እያደረኩና እየሰራሁ ያለሁት ስለምትል አውሮፓም፣ አሜሪካንም ምዕራቡ ዓለም በጠቅላላ ማለት ይቻላል እርስዋ የምትለውን ሁሉ የሚደግፍ ነው፡፡
በዚሁ ምክንያትም ኢትዮጵያ ላይ በርካታ ጫናዎች ይደርሱ ነበር፡፡ ግብጽ በናይል ውሃ ላይ ነው ሕይወቷ የተመሠረተው ኢትዮጵያ እንዴት ግብጽን ለመጉዳት ትነሳለች? በማለት በየሚሳተፉበት ጉባኤ ላይ ሁሉ ኢትዮጵያን ሲወቅሱ ይሰሙ ነበር፡፡
በኢትዮጵያ በኩል ይሄ ትክክለኛ ትርክት ስላልሆነ ግድቡን ለመሥራት ለረጅም ጊዜ ያቀደችበትና ለሕዝቧም የሚጠቅም እንደሆነ፤ በ1950ዎቹ ጊዜ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን፤ በአባይ ሸለቆ 33 ፕሮጀክቶች አዘጋጅታ ከነዚህ መካከልም በ1970ዎቹ ፊንጫ ፕሮጀክትን፣ ጣና በለስም እንዲሁ በ1990ዎቹ እውን አድርጋለች፡፡ አቅም ማጣትና ምቹ ሁኔታዎች ባለመፈጠራቸው ምክንያት ወደ ሥራ ሳይገባ የዘገየ እንጂ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክትም ከነዚህ መካከል አንዱ ፕሮጀክት ነበር፡፡ ቦርደር ዳም (Border Dam) ተብሎ የሚታወቅ፡፡ የጥናት ሥራ ስንሰራም ሆነ ስናቅድ እናንተን አስፈቅደን ሳይሆን ልማታችንን መሠረት አድርገን ነው የሚል ማብራሪያ ለሚቃወሙን ሁሉ በኢትዮጵያ በኩል ማብራሪያ ቢሰጣቸውም ሊቀበሉ አልቻለም፡፡
ኢትዮጵያ ይሄን ግድብ ለመሥራት ስታቅድ ሕዝቦቿን ከጨለማ ለማውጣት እንጂ ግብጽንም ሆነ ሱዳንን ለመጉዳት አይደለም፡፡ ይህ ግድብ ከጥቅም በስተቀር በማንም ላይ ጉዳት አያመጣም፡፡ ይህ ሁሉ እየታወቀ የኢትዮጵያን ማደግ የማይቀበሉ ሀገራት ስለግድቡ መስማትም ሆነ መግባባት ላይ መድረስ አልዋጥ ሲላቸው ይታያል፡፡
በሶስታችን መካከል የበለጠ መግባባትም ለመፍጠር ዓለም አቀፍ አጥኚ ቡድን ተቋቁሞ የግድቡን አጠቃላይ ሁኔታ እንዲያጠና ተደርጓል፡፡
በዚሁ መሰረት በማሕበራዊ ተጠቃሚነት ላይ በዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለሞያ የሆኑ አጥኚ ቡድኖችን አወዳድረን በጋራ ቀጥረን በማስገምገም ደግሞ እነርሱ የሚሉንን እንስማ ተብሎ በኢትዮጵያ በኩል ሀሳብ ቀርቦ ባለሙያዎች ተቀጥረው ከአንድ ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ ሰርተው ጥናታቸውን አጠናቀቁ፡፡ በዚህ ቡድን ውስጥ በሞያው የታወቁ የሶስቱም ሀገሮች ባለሞያዎች ተሳትፈውበታል፡፡
መጨረሻ ላይ ግብጽና ሱዳን ግድቡ አይረባም ብለው ሲያጣጥሉት የነበረው ሀሳብ ውድቅ ሆና ሥራውም ጥብቅና ዓለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን፣ የዓለምአቀፍ መሥፈርቶች ሁሉ ተጠቅሰው ግዱቡ በዚህ ረገድ ጥያቄ ሊነሳበት እንደማይችል ሪፖርት ጻፉ፡፡ ሪፖርቱ ለግብጽም፣ ለሱዳንም፣ ለኢትዮጵያም ግልጽ እንዲሆን ነው የተደረገው። ለሶስተኛ ወገን ሁሉ እንዲታወቅ የተደረገ ሪፖርት ነበር፡፡
ለወደፊት ግድቡ በግብጽና ሱዳን ላይ ተጽዕኖ ያስከትላል የሚል ነገር ካለ እየቆየ፤ሶስታችሁም ተመካክራችሁ ባለሞያ በመቅጠር ምክረሃሳብ መውሰድ ትችላላችሁ፤ነገር ግን የግድቡ ሥራ እንዲቆም የሚያስገድድ ችግር የሚያስከትልና በአደጋ ደረጃ የሚገለጽና የሚታይ ነገር የለም ብለው ነው የዳኙት፡፡ ሪፖርቱ፤ ለዓለም የቀረበ ነው፡፡ የዓለም አቀፉ ጫና በዚህ ተነፈሰ ማለት ይቻላል፡፡
ግድቡ ይጎዳናል የሚለውን ሀሳብ ደጋግመው ስለሚያነሱ፤ ምን እናድርግ ተብሎ ምክክር ሲጀመር የሶስቱ ሀገራት የውሃ ሚኒስትሮች የተሳተፉበት ሶስትዮሽ የተባለ የጋራ ኮሚቴ ተቋቋመ፡፡ ኮሚቴውም ከአንድ ዓመት በላይ ነበር ሥራውን የሰራው፡፡ አሁንም ለግብጽ ስሞታ ምላሽ ለመስጠት ሲባል በአካባቢና ማሕበራዊ ረገድ የግድቡን ተጽዕኖ ለማጣራት ሲባል አንድ ገለልተኛ የሆነ በውሃ ጥናትና ምርምር የተካነ ድርጅት ምክር ይስጠን ተብሎ ዋናውን ሥራ የሚሰራ አንድ የፈረንሳይ ድርጅት እና አንድ የደች ድርጅት ደግሞ ረዳት ሆኖ እንዲሰሩ፣ የ70/30 የሥራ ድርሻ እንዲኖራቸው ተደርጎ በውድድር እንዲቀጠሩ ተደረገ፡፡ ይሁን እንጂ ግብጾች ከአሁን በፊት እኛ የነበረንን የውሃ ድርሻ አክብራችሁ አርሱ ላይ ተመሥርታችሁ ነው የምትሰሩት የሚል የማሰናከያ ሃሳብ አቀረቡ፡፡
በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ ቀድሞ የነበረው የውሃ ክፍፍል ጊዜ ያለፈበትና የማያሰራ ነው፡፡ የቆየ ትርክት ነው። እኛ ደግሞ የምንፈልገው፤ ከመሠረቱ ጀምሮ የግድብ ሥራ ግብጽን፣ ሱዳንን፣ እንዴት ይጎዳል፣ እንዴትስ ተጠቃሚ ያደርጋል የሚለውን ሚዛን ነው እንጂ እናንተ የምትሉትን አንቀበልም የሚል ሃሳብ ተነሳ፡፡ በዚሁ ምክንያት ጥናቱ ኢንሴፕሽን የሚባል ደረጃ ደርሶ በግብጾች ጫናና ማስተጓጎል ቆመ፡፡
በኢትዮጵያ በኩል ለአካሄድ እንዲረዳ፤ ናሽናል ፓናል ኦፍ ኤክስፐርትስ ወይንም ብሄራዊ የኤክስፐርቶች ፓናል ቀደም ሲል ተቋቁሞ የማማከር ተግባሩን ቀጥሏል፡፡ በዚህ ውስጥም በውሃ ሀብት፣ በአካባቢ ጥበቃ፤ በጂኦፖለቲክስ፣ በሕግ፤ በዲፕሎማሲ፣ በግድብ ግንባታ ሞያ፣ ወዘተ የምርምር እውቀትና ልምድ ያላቸው ወደ 29 የሚሆኑ ባለሞያዎች እንሰዲሳተፉ ተደርጓል፡፡
ይህ የባለሙያዎች ቡድን በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አማካኝነት ነው የተቋቋመው፡፡ የባለሙያዎች ቡድኑ ኢትዮጵያ ሥራዋን እንዴት ብታካሂድ፣ ከግብጽና ከሱዳን የሚመጣባትን ጥያቄ በምን መልኩ ምላሽ ብትሰጥ ይሻላል፣ በነርሱ ጀርባም ሆኖ ጥያቄ ለሚያቀርብ፣ እንዲሁ በተመሳሳይ ጥያቄ ላላቸው ለተለያዩ አካላት ምላሽ መስጠት የሚችል ኤክስፐርቶችን አካቶ የተቋቋመው ነው፡፡ ፓናሉ ጠንካራና የሞያ ስብጥር ያለው ነው፡፡ አሁንም ዝግጁ ሆኖ በሥራ ላይ ያለ ፓናል ነው፡፡
እንደሚታወሰው እኤአ በጃንዋሪ 2020 በዋሽግተን ዲሲ ድርድር መሳይ ውይይት ተካሂዶ ነበር፡፡ እነዚህ በውሃ ሀብት፣ በሕግ፣ በጆኦፖለቲካ፣ በዲፕሎማሲና በተዛማጅ ሞያዎች እውቀቱና ልምድ ያላቸው በድርድሩ ጠረጴዛ ላይ ተቀምጠው እውቀታቸውን መሠረት በማድረግ ኢትዮጵያን ወክለው ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር መሳተፋቸው ይታወሳል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል በዚህ መልኩ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ የዋሽግተን ዲሲ ውይይት ወይንም ድርድር ለኢትዮጵያ ረብ ያለው ነገር ያላመጣ መሆኑን በመገንዘብ የኢትዮጵያ ወገን አቋርጦ ተመልሷል፡፡
ይሄ የኢትዮጵያ አካሄድ የዲፕሎማሲ ጫናን መቀነስ ብቻ ሳይሆን፣ ዲፕሎማሲው በሙሉ እውቀት ላይ ተመሥርቶ፤ ግድቡ ለኢትዮጵያ የሚጠቅመውን ያህል ሌሎች ሀገሮችን በከፋ ደረጃ የማይጎዳ መሆኑን በማሳየት ሥራ ተሰርቷል፡፡ ጉዳዩን በአብዛኛው የውሃና ኢኒርጂ ሚኒስቴር የሚመራው ቢሆንም፣ ጫን ያለ ነገር ሲኖር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ አልፎ አልፎ ደግሞ ጉዳዩ በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ የሚከናወንበት ሁኔታ ነው የነበረው፡፡
እንግዲህ በኢትዮጵያ ደረጃ የግብጽን፣ የሱዳንን፣ የነርሱን ወዳጆችና ደጋፊዎች ከግራም ከቀኝም ለመከላከልና ለመመከት ዲፕሎማሲያችን አንደኛ በኤክስፐርት ደረጃ የተዋቀረ፣ ሁለተኛም ተጠሪው መሥሪያቤት የውሃ ሚኒስቴር ስለሆነ በዚህ ደረጃም የተዋቀረ፤ ነገሩ ከፍ ሲል በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ አመራር ሲፈለግም ጠቅላይ ሚኒስቴር ድረስ የሚሄድ መዋቅር ያለው፤ የዲፕሎማሲ አካሄድ ነው፡፡ ይሄ በጣም ወሳኝና ውጤታማ አካሄድ ነበር፡፡
በተጨማሪ ሥራውን ለመደገፍ መላ ሕብረተሰብን በማስተባበር፤ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ፤ ዩኒቨርሲቲዎችን፣ የንግዱን ማሕበረሰብ፣ አርቲስቶችን፣ ታዋቂ ግለሰቦች ወዘተ የተካተቱበት ወደ 90 የሚሆኑ አባላትን የያዘ በብሔራዊ ደረጃ የተቋቋመ ካውንስል አለ፡ ፡ ካውንስሉ ለግድቡ ግንባታ የሚያግዝና ለግንባታ የሚውል ገቢ በማሰባሰብና በተለያየ መንገድ ለመከታተልም የተቋቋመ ሲሆን፣በተጓዳኝም የሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ተቋቁሞ የተጠናከረ ሥራ እየተሰራ ይገኛል፡፡
ዲፕሎማሲውን ከፍ ለማድረግ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ የሚመራው በተለያየ የሙያ ዘርፍ ውስጥ የሚገኙ አካላት የተሳተፉበት ፐብሊክ ዲፕሎማሲ እንዲሁ ተዋቅሯል፡፡ ይህም ግድቡ ለኢትዮጵያም ሆነ ለግብጽ፣ ለሱዳንና ለሌሎች ሀገሮች፣ በአጠቃላይ ለሁሉም የሚጠቅም መሆኑን ለማሳየት እንዲቻል፤ ይህንኑ ለግብጽ፣ ለሱዳንና ለሌሎች የጎረቤት ሀገራት ፖለቲከኞችና ባለሞያዎች ለማብራራት የተቋቋመ ነው፡፡
የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ወደ ግብጽ፣ ሱዳን፣ ጅቡቲና ዩጋንዳ ሄዷል፡፡ ከሱዳንና ከብጽም እንዲሁ ተመሳሳይ ቡድኖች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ተስተናግደዋል። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም አንዱ የጉብኝት መዳረሻ ሆኖ ነበር። ፐብሊክ ዲፕሎማሲ በአባልነት ብቻ ሳይሆን በሚሄዱበት ሥፍራ ምን ያጋጥማቸዋል፣ ምንስ ይጠቀማሉ፣በምን አይነት እራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው፤ በአጠቃላይ ውይይቶች ላይ ለመሳተፍ ምን አይነት ዝግጅት ያስፈልጋል በሚሉ ጉዳዮች ዙርያ ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ተከናውኗል፡፡
ዲፕሎማሲ ሁለት አይነት ነው፡፡ አንዱ በቀጥታ መንግሥት የሾማቸውና ያደራጃቸው፤ የመንግሥት ተጠሪ መሥሪያ ቤቶች የሚመሩትና የሚሳተፉበት ነው፡፡ ሌላው ዲፕሎማሲ መንግሥታዊ ያልሆነው ነው፡፡ በዜግነት፣ በእውቀትና በሥራ አጋጣሚዎች የሚካሄድ ዲፕሎማሲ ነው። ኢትዮጵያን የሚጠቅም ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም የማይጎዳ መሆኑን በማስረዳት የሚያግዝ ሲሆን፤ በዚህ መንግሥታዊ ባልሆነ ዲፕሎማሲ በውሃና በተያያዥ ዘርፎች የዲፕሎማሲ ተግባራት ተከናውነዋል ለማለት ይቻላል፡፡
በምርምር ዘርፉም ቢሆን፤ ውሃና ማሕበረሰብ በሚል ምሁራዊ የሆነ የጥናትና ምርምር ሥራዎችና የምክክር መድረኮች እንዲሁም ኢትዮጵያ የታላቁ የሕዳሴ ግድብን
ጨምሮ በውሃ ዘርፍ የምትሰራቸውን ለሀገር ጠቃሚ ሥራዎችን በተመለከተ መንግሥታዊ ባልሆነው የዲፕሎማሲ በርካታ ሥራ ተሰርቷል፡፡ በዚህ ሁሉ መንገድ ሥራዎችን በመሥራት ነው የውጭውን ጫና ለመቋቋም ጥረት የተደረገው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እነዚህ ሁሉ ስራዎች ሲሰሩ ያጋጠሙ ችግሮች ነበሩ?
ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ፡– ሥራዎች ሲሰሩ የተለያዩ ፈተናዎች አጋጥመዋል፡፡ በቃላት ሁሉ የሚገለጹ ጫናዎችና ፈተናዎችን በማሳለፍ ጭምር ነው ዲፕሎማሲው ሲካሄድ የቆየው፡፡ ግብጾች እጃቸው ረዘም እንደሚል ይታወቃል። ኢትዮጵያ የምታከናውነው የግድብ ሥራ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትልብናል በማለት ጩኸቷን ለአሜሪካና ለአውሮፓ በማሰማት ያለማቋረጥ ጥረት አድርጋለች፡፡
እኤአ በጃንዋሪ 2020 የዋሽግተን ዲሲ የአሜሪካው ፕሬዚደንት ትራንፕ ለግብጽ ወገናዊነታቸውን ማሳየታቸው ግልጽ ነበር፡፡ የውይይቱ ሂደት የኢትዮጵያን የግድብ ግንባታ ሥራ የሚያደናቅፍ ነበር፡፡ አሜሪካ ሶስቱን ወገኖች ጠርታ ለማወያየት ያደረገችው ጥረት ውጤቱ በፕሬዚደንቱ እይታ ጥሩ ሆኖ አልተገኘም፡፡ በአሜሪካን በኩል ለሁላችሁም ይበጃል ተብሎ ሰነድ ተዘጋጀ፤ ሰነዱ ግን ለኢትዮጵያ እራስን የሚገል አይነት ነው የነበረው፡፡ የኢትዮጵያ ወገን ሰነዱ ላይ ሳይፈርም ተመለሰ፡፡
ቀደም ሲል ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከሁለት ሚኒስትሮችና በድርድር ውስጥ ከሚገኙ አማካሪዎች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ‹‹ልምዱ፣ እውቀቱና የሀገር ፍቅርም አላችሁ፤ ይሄ የተረጋገጠ ነገር ነው፤ በዲፕሎማሲውና በድርድሩ በሙሉ ልባችሁ ሥሩ፤ ለኢትዮጵያ በሚሆን መንገድ እንደምትሰሩም አልጠራጠርም፤ ከልካይ የላችሁም።
አስፈላጊ ሀብት አሰባስቤ ግድቡን መገንባት የኔ ሥራ ነው፡፡ ግድቡን እኔ ገነባለሁ ዲፕሎማሲውን እናንተ አካሂዱ›› ነበር ያሉን፡፡ እንግዲህ የዋሽግተን ዲሲው ድርድር የተካሄደው በልበ ሙሉነትና በአርበኝነት መንፈስ ነበር፡፡
የአሜሪካኑ ፕሬዚደንት ተበሳጭተው ግብጽ ግድቡን መምታት ነበረባት፣ እዚህ ደረጃም መድረስ አልነበረባትም ማለታቸው ይታወሳል፡፡ ይሄ ሁሉ የዲፕሎማሲው ጫና ምን ያህል እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ጫናውን ለመቋቋም የተሰሩት ሥራዎች፤ በተለይም በአመራርም፣ በቴክኒክም የተደራጀ ኮሚቴ በማዋቀር እንዲሁም ከተለያየ የሞያ ዘርፍ የተውጣጡ ዜጎችና ባለሞያዎች ተሳታፊዎች የተካተቱበት ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስቀድሙ በመሆናቸው ጭምር ነው ውጤታማ ሥራ መሥራት የተቻለው፡፡ የግድብ ግንባታ ሥራውም ቢሆን የተለያዩ ፈተናዎችን በመቋቋም ነው እስከ አራተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ሥራ ማከናወን የተቻለው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ግድቡ የአፍሪካ ጉዳይ በመሆኑ የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊ መፍትሄ እንዲፈታ ከማድረግ አንጻር የኢትዮጵያ ሚና እና የተገኙ ውጤቶች ምንድን ናቸው?
ዶክተር ያዕቆብ፡- ግብጾች ጉዳዩን በጣም ስላጦዙትና የአሜሪካንም ተጽዕኖ ስላልተሳካ ጉዳዩ በዓለም መንግሥታት ሴኪዩሪቲ ካውንስል እንዲደርስ ተደረገ፡፡ ግብጾች አደጋ ላይ ነን ካውንስሉ ይዳኘን ብለው ነበር ያቀረቡት፡፡
ግብጽ እንዲህ ያለውን ነገር እንደምታደርግ በኢትዮጵያ በኩል ቀድሞም ግምት ስለነበር ጥብቅ በሆነ ምክክርና ውይይት ዝግጅት ተደርጎ ስለነበር በኤክስፐርቶች በኩል ጎን ለጎን ሥራዎች ሲሰሩ ቆይቷል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ለተመድ ሴኩሪቲ ካውንስል በቀድሞ በውሃ ሚኒስትሩ ክቡር ዶክተር ስለሺ በቀለ የተሰጠው መግለጫ፤ ግድቡ የልማት ፕሮጀክ እንጂ ሌላውን የሚጎዳና የሚያጠፋ የንኩሌየር ማብለያ እንዳልሆነ፤ ለጎረቤት ሀገሮች ጭምር የሚጠቅም የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭ የውሃ ፕሮጀክት መሆኑን የሚገልጽ ነበር።
ሴኪዩሪቲ ካውንስሉ የደህንነት ጉዳይ እንጂ የውሃ ግንባታና የልማት ሥራ ላይ አይመለከተውም ተብሎ ስለተተቸ የግብጾች አቤቱታ ከሸፈባቸው፡፡ በወቅቱም የኢትዮጵያ ሀሳብ የአፍሪካ ጉዳይ በአፍሪካ እንዲታይ የሚል ስለነበር፤ ጉዳዩ ለአፍሪካ አመራር ተላከ፡፡ በወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ደቡብ አፍሪካ ነበረች፡፡ ደቡብ አፍሪካ ሀገሮች በማይጋጩበትና ለሁሉም በሚጠቅም ሁኔታ ሥራው መካሄዱን ለማረጋገጥና ለመምከር ለአንድ ዓመት ሰርታለች።
አፍሪካ ሕብረት አወያይ ወይንም አመቻች እንጂ፤ ወሳኝም ዳኛም አይደለም፡፡ ሀገሮች ብሔራዊ ጥቅሞቻቸውን ለማስከበር ሲወያዩና ሲደራደሩ፣ ሀሳቡ በደንብ
እንዲንሸራሸር የማመቻቸት ሥራ ያከናውናል፡፡ በዚህ መልኩ በአፍሪካ ሕብረት በኩል እኤአ በ2020 በዚህ ሁኔታ ነበር የተጠናቀቀው፡፡ ግን ውጤት አልተገኘበትም፡፡
እኤአ በ2021 አዲስ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ተመረጠ፡፡ በወቅቱም ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ነበር የተመረጠችው፡፡ ኮንጎም የሶስትዮሽ ውይይቱን ለማመቻቸት ሞክራ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ግብጾች የሚመቹ ሆነው ስላልተገኙ፤ አልገፋችበትም፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት መሪዎች ቢለዋወጡም ጉዳያችን እስከታየለን ድረስ በሚል በጥንቃቄና በትጋት ጉዳይዋን በማቅረብ ስትሳተፍ ቆይታለች፡፡ የኮንጎ የመሪነት ጊዜም አልፎ ሴኔጋል ተተካች፤ እርስዋም ብትሆን ምንም ሳትሰራ 2022 አለቀ፡፡
ኢትዮጵያ ግድቧን እየሰራች ያለችው ሌሎችን በማይጎዳ መልኩ ተጠንቅቃ በመሆኑ ይህን ሥራዋን የሚያበረታቱና ጥቅሟንም የሚያስጠብቁላት እንዲሁም ግብጽንም ሱዳንንም የሚያሸማግሏት ወዳጆች፣ ሀገሮችም ሆኑ ሌሎች ከጎኗ እስከ ሆኑ ድረስ የምትቀበል መሆኗን ግልጽ በማድረግ ነበር በዲፕሎማሲው እስካሁን ሥትሰራ የቆየችው፡፡ የኢትዮጵያ አካሄድ በሙሉ ዝግጅትና ዲፕሎማሲ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ተቀባይነትንም አግኝታለች ማለት ይቻላል፡፡
የኢትዮጵያን አካሄድ ትክክል ነው ብለው የተቀበሉ ብዙ የአፍሪካ ሀገሮች አሉ፡፡ በነዚህ ሀገራት ተቀባይነት ያገኘችውም ጉዳይዋን በጥንቃቄ ይዛ በመራመዷና ማስረዳትም ስለቻለች ነው፡፡ ሲካሄዱ ለነበሩ ውይይቶችና ድርድሮች በኢትዮጵያ በኩል 153 ሰነዶች ቀርበዋል፡፡ ኢትዮጵያ በእንዲህ ያለው መልኩ በመንቀሳቀሷ የሚያሳፍራትና የጎደላትም ነገር አልነበረም፡፡ ለግድቡ ግንባታ በገንዘብ በኢትዮጵያውያን በኩል ይደረግ የነበረው ተሳትፎም ለዲፕሎማሲው ትልቅ አቅም የፈጠረ ነው፡፡ ዲፕሎማሲው ከሌሎች የሚመጣውን ጫናን ለመቋቋም ብቻ ሳይሆን፤ ስለግድቡ ሌሎች እንዲረዱት ለማድረግ በሰነድ የታገዘ፣ በተግባር የተደገፈ ሥራ በመሥራት ጭምር ነው፡፡ በዚህም በእስካሁኑ ሂደት ውጤታማ ስራ ተሰርቷል ማለት ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የቀጣይ ዘመን የውሃ ዲፕሎማሲ ምን ገጽታ ይኖረዋል ተብሎ ይታሰባል?
ዶክተር ያዕቆብ፡- እስካሁን የመጣንበት መንገድ በራሱ አመላካች ነው፡፡ ኢትዮጵያ የበርካታ ወንዞች ባለቤት ናት፡፡ ተከዜ አንድ ግድብ ብቻ ነው የተሰራለት፤ ባሮ አኮቦ ላይ ተጨማሪ ግድቦች ሊሰሩ ይገባል፡፡ ገናሌ ላይም ትልቅ ግድብ አለ፤ ዋቢሸበሌ ላይም ኃይል የሚያመነጭ መልካዋከና አለ፤ በኦሞ ጊቤ ላይም እንዲሁም አንደኛ ሁለተኛ ሶስተኛ ጊቤ እየተባለ የሚሰሩ ስራዎች አሉ፡፡ አሁን ደግሞ የኮይሻ ፕሮጀክት በግንባታ ላይ ነው፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በውሃ ሃብት የታደለች በመሆኗ በርካታ የልማት ሥራዎችን እየሰራች ነው፤ ወደፊትም ትሰራለች፡፡
ያለንን የውሃ ሀብት ከመሬት ጋር በሚገባ ብናስተገብራቸው ተጠቃሚነታችን ያድጋል፡፡ ተተኪው ትውልድ በተሻለ እውቀት ለአካባቢው የሚጠቅም ሥራ መሥራት ይኖርበታል፡፡ የኢትዮጵያ ልማትና የዕድገት ተስፋ በውሃ ሀብቶቿን በማልማት ላይ የሚመሠረት ነው ማለት ይቻላል፡፡
ዲፕሎማሲ ማለት፤ ትክክለኛውን ሥራ ሌሎች እንዲቀበሉ ማድረግ፤ እንዲሁም ሌሎች የሚሰሩትን ትክክለኛ ሥራ ለመቀበል ዝግጁ መሆን ነው፡፡ እዚህም እዛም ያልተስተካከለ ነገር ካለ እንዲስተካከል ማድረግ ነው፡፡ ቅቡልነቱና የጋራ ጥቅምም ከፍ እንዲል ማድረግ ነው፡፡
ስለዚህ በኢትዮጵያ በኩል ያለው የውሃ ሀብት ልማት ጉዳይ ዲፕሎማሲያችን ለአካባቢያችንም ለዓለምም ጠቃሚ መድረክና የእውቀት መስክ ስለሆነ ለወደፊት ጥሩ መሠረት ይጥላል ብዬ ነው የማስበው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይ የግጭት መንስኤ ሆኖ ዘመናት ተቆጥሯል፡፡ መንስኤው ምንድነው?
ዶክተር ያዕቆብ፡- በታሪክ ብዙ የተጎዳንባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ጣሊያን በኃይል ወርሮ ኢትዮጵያ ውስጥ በቆየባቸው ጊዚያቶች የባሕር በሩን ይዞ ቆይቶ ነበር፡፡ ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል ሆና በፌዴሬሽን ከተቀላቀለች በኋላ ደግሞ፤ የባሕር በሩ የኢትዮጵያ አካል ሆነ፤ ፌዴሬሽኑ ፈርሶ ኤርትራ አንድ ጠቅላይ ግዛት ስትሆን የባሕር በሩ የኢትዮጵያ ሙሉ አካል ሆነ፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላት ሀገር ነች፡፡
የኤርትራ አማጽያን፤ ጣሊያን የኤርትራን ግዛት በቅኝ በገዛበት አኳያ ነፃ ሀገር እንፈልጋለን አሉ፡፡ በዚህም የተነሳ ለ30 ዓመታት በአማጽያኑና በኢትዮጵያ መካከል ጦርነት ተካሄደ፡፡ አማጽያኑ አሸንፈው ኤርትራ ነጻ ስትሆን በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ አገዛዝ ወይንም ኢትዮጵያን ያስተዳድራት የነበረው ሕዘባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ድርድር ሳያደርግ፣ ለኢትዮጵያ ጥቅም መቆም ሲገባው ይህን ባለማድረጉ ኢትዮጵያ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የባሕር በር ሳይኖራት ቀርቷል፡፡
ችግሩ እስካሁን ቀጥሏል፡፡ እንዴት ነው የባሕር በር የምናገኘው የሚለው ጉዳይ ብዙ ሥራ ይጠይቃል፡፡ የጥናት ሥራም ይፈልጋል፡፡ ብዙ አዋቂዎች፣ የፖሊሲ ሰዎች ተሳትፎ ያስፈልጋል፡፡ ይህም ከኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከዚያኛውም ወገን ተሳትፎ መኖር አለበት፡፡ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ሥራ ይጠይቃል፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሰጥቶ መቀበል ብለዋል፡፡ ሰጥቶ መቀበል ተቀባይነት እንዲኖረውና ሂደቱም ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በደንብ መግባባትን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ እንደዋዛ የሚታይ ጉዳይ ነው ብዬ በግሌ አላምንም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይን አጥብቃ ይዛለች፡፡ በዚህ ላይም ሀሳብ ቢሰጡን፤
ዶክተር ያዕቆብ፡- ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ወደ ባሕር በር ነው ግንባሯ ያለው፡፡ ባሕር በር በነበራት ጊዜ ከልካይ አልነበራትም፡፡ በአሰብም በምጽዋም እቃዋንም፣ድርጅቷንም ሚስጥሯንም፣ ወደ ውጭ ለመላክም ሆነ ከውጭ ለመቀበል መንገዱም ሉዓላዊነቱም ነበራት፡፡ ነገር ግን በመካከል ላይ በተነሳ የአማጺ ነፃነት ንቅናቄ ለረጅም ጊዜ ጦርነት ተካሂዶ ኤርትራ ነፃ ወጣች ሲባል ድርድር ሳይደረግ እንደማናቸውም ተራ ነገር ኤርትራ የባሕር በሩን ይዛ እንድትሄድ መንገድ ተከፈተላት፡፡
አሁን አንግዲህ አቀበቱን እያረፍንም፣ እየተነፈስንም ቢሆን መወጣት ያለብን ይመስለኛል፡፡ እኔ እንደ አንድ ሙህርና መምህር አሁንም ደግሜ የምለው ከፍተኛ የሆነ የዲፕሎማሲ ሥራ ይጠይቃል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሥራ ሲጀምር ለባላንጦቻችንም ሆነ ለሶስተኛ ወገኖች ለማስረዳት ብዙ ዝግጅት ተደርጓል፡፡ ብዙ ሀሳብና እውቀት አንድ ላይ በማድረግ የተለያዩ ሂደቶችን በማለፍ ነው አሁን ግድቡ የደረሰበት ደረጃ ላይ ማድረስ የተቻለው፡፡ ይሄ ጥሩ ተሞክሮ መሆኑ እየታየና ምስክርነትም እያስገኘ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የባሕር በሯን እንድታጣ ተደርጓል፡፡ ይህም ትልቅ ስህተት ነው፡፡ አንድ ሀገርን የሚያስተዳድር መንግሥት ትልቁ የመጀመሪያ ሥራው መሆን ያለበት ለሀገር የሚጠቅም ነገር በዲፕሎማሲም ሆነ በሌላ ዘዴ ተጠቅሞ የሀገርን ጥቅም ማስጠበቅ ነበር፡፡ ነገር ግን በስንፍናም፣ በእውቀት ማነስም፣ በሸፍጥም ይሁን በሌላ ጥፋት ተሰርቷል፡፡ ሳንወድ የዚያ እዳ ተሸካሚ ሆነናል፤ ይሄንን መቀበል ያስቸግር ይሆናል። የተበላሸውን ነገር ለማስተካከል ትዕግሥትና ጥበብ ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ እንዳሉት ኢትዮጵያ የባሕር በሯን ለማስመለስ ጥንቃቄ፣ትዕግሥት የተሞላበት በሳል የዲፕሎማሲ ሥራ ያስፍልጋታል፡፡ በዚህ ረገድ ከማን ምን ይጠበቃል?
ዶክተር ያዕቆብ፡- መንግሥት ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ምክንያቱም ሀገርን ተጠቃሚ በሚያደርግ መንገድ ነገሩ በደንብ እንዲሳለጥ መንግሥት ዕውቀትን ገንዘብንና ሕዝብን በማደራጀቱና በማስተባበሩ በኩል ጠንክሮ መሥራት ይኖርበታል፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከባሕር በር ጋር የተገናኘ ሥራ የሚሰሩ መንግሥታዊ ተቋማት አሉ።ለዚህ እውቀትም ዝግጅትም አለኝ የሚሉ አካላት በጉዳዩ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ማድረግ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በአባይ እና በቀይ ባሕር መካከል መገኘቷ እንደጥቅምና እንደተግዳሮት የሚነሳ ነገር ካለ ቢያብራሩልን?
ዶክተር ያዕቆብ፡- አባይና የአባይ ገባሮች 86 በመቶ የሚሆነው ውሃ ጥቅም ላይ የሚውለው ለሱዳንና ለግብጽ ነው፡፡ በዚህም እነርሱ ውሃችንን አትንኩ ይላሉ፡፡ እኛ ደግሞ የጋራ ነው እንላለን፡፡ ሆኖም ለልማት ከማዋል ወደኋላ አንልም፣ ሉዓላዊ ግዛታችን ውስጥ የሚገኝ ውሃ ከመጠቀም የሚከለክል አንዳች ኃይል የለብንም ስንል ኖረናል፡፡
ይሄ በዲፕሎማሲ ትልቅ ተግዳሮት ሆኖ ቆይቷል። አሁን እውቀታች፣ አቅማችን፣ፍላጎታችንና ለልማት ያለን ቁርጠኝነትም ከፍ እያለ ሲሄድ ከ60 ዓመት በፊት የተጀመረውን እቅዳችችን ለመተግበር ትንሽ በትንሽ በመንቀሳቀስ ላይ እንገኛለን፡፡
ከነበሩት 33 ፕሮጀክቶች መካከል 10ሩ እንኳን ገና ሥራ ላይ አልዋሉም፡፡ ግን ሰርተን በማሳየት ተግዳሮቶችን እየተቋቋምናቸው እንገኛለን፡፡ እንደአያያዛችን ብዙ እንሰራለን ብዬ አስባለሁ፡፡ አቅማችንና አሰራራችን እያደገ ሲሄድ የታቀዱትን ብቻ ሳይሆን አዳዲስ እቅዶችንም ጨምረን እንሰራለን ብዬ አምናለሁ፡፡ ተግዳሮቶችን እየቀነስን ጥቅማችንን እያሳደግን ከሄድን ኢትዮጵያ በቀይ ባሕርና በአባይ ተፋሰስ መሃል መገኘቷ የራሱ የሆነ ጥቅም ያለው ነው፡፡ የእድገትም ምንጭ ነው፡፡
የባሕር በር ጉዳይን በተመለከተ የታሪክ ተመራማሪዎች ብዙ ነገር ሊነግሩን ይችላሉ፡፡ በቅርቡም ያየነው የቅኝ ግዛት ሥርዓት በመላ አፍሪካ ላይ የተጫነ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ቅኝ ተገዥ ባትሆንም የቅኝ ግዛት ጠባሳው አላረፈባትም ማለት አይቻልም፡፡ የኤርትራ ጉዳይም የሚያያዘውም ከዚሁ ጋር ነው፡፡ ከብዙ ድካም በኋላ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን እንድትተዳደር ተደረገ፡፡
በፌዴሬሽን መሆኑ ለኢትዮጵያም የሚጠቅም ነበር። ለኤርትራም ወገኖች የሚጠቅም ነበር፡፡ በኋላ ደግሞ የጂኦፖለቲካ ተጽዕኖን በመሥጋት የኢትዮጵያ መንግሥት ኤርትራን ከፌዴሬሽን የበለጠ የተዋሀደች ሀገር ትሁን በማለት ተንቀሳቀሰ፡፡ እናት ሀገር ወይንም ሞት የሚሉ ኤርትራውያን ከዚህ ጋር አብረው ከኢትዮጵያ መንግሥትና ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ተባብረው ኤርትራ 14ኛ ጠቅላይ ግዛት ልትሆን ቻለች፡፡ ያንን በመቃወም ደግሞ አማጽያን ተነስተው ለ30 ዓመታት ጦርነት ተካሄደ፡፡ ከዚያ በኋላ ኢትዮጵያ በተዳከመች ጊዜ ኤርትራ ነፃ ሀገር መሆኗን አወጀች፡፡ በዚህ ሁኔታ ነው እንግዲህ እንደዋዛ ኢትዮጵያ የባሕርበር ያጣችው፡፡ ይሄ በታሪክ እንደ ስህተት ይወሰዳል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ አመሰግናሉ።
ዶክተር ያዕቆብ፡ እኔም አመሰግናሉ፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ኅዳር 6 ቀን 2016 ዓ.ም