ጊዜው የሚሻው ለሰላም መሥራትንና አብሮ መቆምን ነው!

 የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም ወዳድ ሕዝብ ነው፡፡ ለዘመናት አብሮ ተከባብሮ በመኖርና የሰላም ተምሳሌት በመሆን በአርአያነት ሲጠቀስ የኖረ ነው፡፡ ከኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ አኩሪ መገለጫዎች መካከል የብሔር፣ የእምነት፣ የቋንቋ፣ የባሕልና ሌሎች ልዩነቶችን ዕውቅና በመስጠት ተሳስቦና ተከባብሮ የመኖር ትልቅ እሴት ነው፡፡

ሆኖም የዚህን ኩሩና ሰላም ወዳድ ሕዝብ አኩሪ ዕሴቶች ለማምከን የተለያዩ ሴራዎች በውስጥና በውጭ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ሕዝቡ የመከባበርና የመቻቻል እሴቱን እንዲያጣ በብሄርና በሃይማኖት በመከፋፈልና በማናቆር ግጭት እንዲነግስና በሂደትም የተዳከመች ኢትዮጵያ እንድትፈጠር በርካታ አካላት ያለመታከት ሰርተዋል፡፡ በዚህም የኢትዮጵያን የሰላም ዕሴት ደብዝዞ ነፍጥ ማንሳት እንደፋሽን ሲቆጠር ታይቷል፡፡

ይህንን አስተሳሰብ ከመሰረቱ ለመንቀልና ኢትዮጵያን ወደ ቀድሞው ዕሴቶቻቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ባለፉት አምስት ዓመታት በፍቅር እንደመር፤ በይቅርታ እንሻገር የሚል መርህን በማንገብ በመላ ሀገሪቱ ሰላምን የማስፈን እንቅስቃሴ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ በእስር ላይ የነበሩ የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት፤ በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ታግደው የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ፤ የታጠቁ አካላት ነፍጣቸውን እንዲያስቀምጡና በሀገራቸው ልማት ላይ በነጻነት እንዲሳተፉ ጥሪ በማድረግ ሰላሟ የተረጋገጠ ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡

ሆኖም መንግስት ባደረገው የሰላም ጥሪ እና ለሰላም ባለው ምኞት ልክ የተለያዩ አካላት ተገቢ ምላሽ ሲሰጡ አልታዩም፡፡ ይልቁንም አንዳንዶች መንግስት ለሰላም ያለውን ቀናኢነት በማጣጣልና እንደ ደካማነትም በመቁጠር በየጫካው ጦር ሲመዙ ታይተዋል፡፡ ሰላምንም ወደ ጎን በመተው ግጭትና ሁከትን አንግሰዋል፤ ጦርነትም በማወጅ ለበርካታ ዜጎች ዕልቂት ምክንያት ሆነዋል፡፡

በየጫካና በየዱሩም ነፍጥ በሚያነሱ ቡድኖች ምክንያትም አርሶ አደሩ ተረጋግቶ የእርሻ ሥራውን እንዳያከናውን፤ ገበሬው ነግዶ እንዳያተርፍ፤ ተማሪው በዕውቀት ገበታ ላይ እንዳይገኝ፤ ሰዎች ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ተንቀሳቅሰው እንዳይሰሩ ተደርገዋል፡፡ አልፎ ተርፎም ነፍጥ ባነሱ ቡድኖች አማካኝነት በርካታ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ ተሰደዋል፤ አካል ጉዳተኛ ሆነዋል፤ ሕይወታቸውንም አጥተዋል፡፡

ይህ ፍላጎትን በጠመንጃ ብቻ የማሳካት ምኞት አንድ ቦታ ሊገታ ይገባዋል፡፡ ለውጥ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ከጊዜና ከሁኔታ ጋር ነገሮች መለወጣቸው አንዱ የተፈጥሮ ግዴታ ነው፡፡ አንድ ቦታ የሚቆም ነገር የለም፡፡ ትላንት ትክክል ይመስል የነበረው ነገር ዛሬ ዋጋ ቢስ ይሆናል፡፡ ትላንት ለአሸናፊነት ያበቃው የትግል ስልትም ለዛሬው የሽንፈት ምንጭም ሊሆን ይችላል፡፡

ትላንት ስልጣን መቆናጠጥ የሚቻለው በብረት ነበር፡፡ በሕቡዕ መደራጀት፤ ማድባትና ማሴር ብሎም መግደልና መጠፋፋት የ1960ዎቹ የስልጣን መወጣጫ ብቸኛ መንገድ ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜም ተማሪዎችን አሳምጾ፤ ወጣቶችን አሸፍቶ፤ ዋሽቶና ለፍፎ ወደ ስልጣን ለመቃረብ የሚደረጉ በርካታ ሙከራዎች ነበሩ፡፡ ይሁንና አሁን ላይ ሁኔታዎች ተቀይረዋል፡፡

በኋላ ቀሩ የፖለቲካ ባሕል ውስጥ የሃሳብ ልዩነት ክብር የለውም፣ ዕውቅናም አይሰጠውም። በሐሳብ የተለየን እንደ ደመኛ ጠላት ማሳደድ፣ ማሰር፣ መግደል ወይም ማሰናከል የተለመደ ድርጊት ነበር፡፡ ነፍጥ አንስቶ ጫካ ገብቶ መንግስት መሆንም የሚያዋጣና በቀላሉም ተግባራዊ ማድረግ የሚቻል ነበር፡፡

ዛሬ ስልጣን ለመያዝ ብረት ማንሳት አያስፈልግም፡፡ ብረት አንስቶ ጫካ ቢገባም ትርፉ ሕይወትን መገበር፤ ወጣቶችን ማስጨረስና ሀገርን ማዳከም እንጂ ስልጣን በጠመንጃ የሚያዝበት ምንም አይነት መንገድ የለም፡፡ እሱ ከዘመኑ ጋር አብሮ አልፏል፡፡

ዛሬ ስልጣን ለመጨበጥ የሚስፈልገው የተሻለ ሃሳብ አምጥቶ ዕውቀትን ለገበያ ማቅረብ ብቻ ነው፡፡ በጠረጴዛ ዙርያ ቁጭ ብሎ በመመካከርና በሃሳብ የበላይነት በማሸነፍ ያለሙትን ማሳካት ይቻላል፡፡ በጠመንጃ ከማሸነፍ በሃሳብ የበላይነት ማሸነፍ ዛሬ ግዝፍ ነስቷል፡፡

ኋላቀር አስተሳሰብ ያለውንና አሁንም ስልጣንን በጠመንጃ ብቻ አሳካላሁ የሚለውን ወገን የሚቀበል እና ጦረኛ አስተሳሰብን የሚሸከም ጫንቃ፣ ሕዝብና ሀገር የለም፡፡ ፍላጎትን በሰላም ብቻ ለማሳካት ከመሞከር ውጪ አዋጭ ነገር እንደሌለ ሁሉም ተረድቶ ለሰላም በጋራ መቆም ጊዜው የሚሻው ሃሳብ መሆኑን መረዳት ይገባል!

አዲስ ዘመን   ኅዳር 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You