የችግሮቻችን የመፍትሄ አካል መሆን ይጠበቅብናል!

 የአንድ ሀገር እጣ ፈንታ የሚወሰነው በሀገሪቱ ውስጥ ባለው ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ነው። ይህ ደግሞ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የዚያን ሀገር ሕዝብ በዋነኛነት የሚመለከት መሰረታዊ ጉዳይ ነው። የእኛም ሀገር እውነታ ከዚህ የተለየ አይደለም፤ ሊሆን የሚችልበትም አማራጭ አለ ብሎ ለመቀበል መሞከር ጥፋቱ የከፋ እንደሚሆን ለመገመት አይከብድም።

የሰለጠነው ዓለም አሁን ላለበት የስልጣኔ ደረጃ/እድገት የደረሰው፤ ዛሬ ላይ ሆኖ ለመገኘት እንደ ሕዝብ የነበረው መሻት፣ መሻቱ የፈጠረው ቁርጠኝነት፣ ቁርጠኝነቱ፤ በተጨባጭ የፈጠረው ሀገራዊ አቅም እንደሆነ በትናንት ታሪካቸው ደምቆ የሚነበብ ነው። ይህም ከሁሉም በላይ ዛሬያቸውን መላው ሕዝባቸው እንደ ሕዝብ ከፍ ባለ ኃላፊነት ተነጋግሮና፣ ተደማም ጦ፣ ተናብቦ የፈጠረው መሆኑን ነው።

በርግጥ የፖለቲካ አመራሩ የለውጥ አስተሳሰቦችን ከማፍለቅ ጀምሮ፣ ለአስተሳሰቦቹ ተፈጻሚነት ስትራቴጂክ አመራር በመስጠት ሂደት ውስጥ የሚኖረው አበርክቶ ከፍያለ ነው፤ ይህ በሕዝብ ተሳትፎ በአግባቡ ካልታገዘ ግን በራሱ የአንድን ሀገር እጣ ፈንታ ይለውጣል ተብሎ አይታመንም። በዚህ ሁኔታ ስኬታማ የሆነ ሀገርም የለም።

ይህ እውነታ በእኛም ሀገር የተለየ ገጽታ የለውም፤ እንደ ሀገር ካለንበት፤ ለዘመናት ብዙ ዋጋ ካስከፈለን ኋላ ቀርነትና ከዚህ ከመነጨው ድህነት ለመውጣት ከፍ ያለ መሻት አለን፤ ይህንን ሀገራዊ መሻታችንን ተጨባጭ ለማድረግ በተለያዩ ወቅቶች፤ በተለያዩ ትውልዶች፤ የተለያዩ የለውጥ እሳቤዎች ተግባራዊ ሆነዋል። ለተግባራዊነታቸውም እንደ ሀገር ብዙ ዋጋ ተከፍሏል።

ይህም ሆኖ ግን ዛሬ ድረስ የመለወጥ መሻታችን ተጨባጭ ሆኖ ወደ ፈለግነው የዕድገት ደረጃ መድረስ አልቻልንም፤ ከዚህ የተነሳ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ አዲስ የለውጥ አስተሳሰብ ይዘን የመለወጥ መሻታችንን እውን ለማድረግ እየተንቀሳቀስን ነው። እስካሁን ባለው ተጨባጭ እውነታም ተስፋ ሰጭ ጅማሮዎች እንዳሉ ምስክርነት ለመስጠት የሚከብድ አይደለም።

ይህ በፖለቲካ አመራሩ ቁርጠኝነት እና በሕዝብ ተሳትፎ እየተመዘገበ ያለው ስኬት ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ለጀመርነው ትግል የመሰረተ ድንጋይ ሆኖ የሚያገለግል እንጂ በራሱ አልፋና ኦሜጋ አይደለም፤ በልማት የመለወጥና የማደጋችን መሻት ፍጻሜ ሳይሆን ጅማሬ ስለመሆኑ በብዙ መልኩ ለመረዳት የሚከብድ አይደለም።

በተለይም በየዘመኑ እየጀመርናቸው የሚመክኑ የለውጥ እሳቤዎች፤ ሕዝባዊ መሰረት ኖሯቸው፤ ሀገር እንደ ሀገር በጸና ዘመንን በሚዋጅ በመነጋገር፤ በመደማመጥና በመስማማት ላይ የተመሰረተ አዲስ የፖለቲካ ስርዓት ለመጪው ትውልድ ለማውረስ በሚያስችል የታሪክ ገጽ ላይ ነን። በዚህ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ፈተናዎችን ቀልለው የሚታዩ አይደሉም።

ፈተናዎቹ በባህሪያቸው በአስተሳሰብ ደረጃ ቀድሞ መቀየርን የሚጠይቁ፤ በተዛቡ ትርክቶች የተገነቡ ማንነቶችን መግራት፤ ትናንቶችን እስከ በጎ እና መጥፎ ትርክቶቻቸው ደፍሮ መቀበልና፤ ከነሱ በአግባቡ ተምሮ ነገዎችን የተሻሉ ማድረግ የሚያስችል ሁለንተናዊ ዝግጁነት እና ቁርጠኝነት, የሚጠይቁ ናቸው።

አሁናዊ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ እውነታዎችን ነጻ በሆነ ሕሊና/አዕምሮ አይቶ መገምገምን፤ ከግለሰባዊ እና ቡድናዊ ፍላጎቶች ወጥቶ ሀገራዊ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና የኢኮኖሚ መስተጋብሮችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መመልከት፤ ለሱ የሚሆን ግለሰባዊና ቡድናዊ ስብዕና መፍጠር፤ እራስን ለሀገርና ለሕዝብ መሻት ማስገዛት ይጠይቃል።

ከዚህ ውጪ እነዚህን የለውጥ ጊዜ ፈተናዎች አንዱ እጁን አጣምሮ ጠያቂና አቃቂር አውጪ፤ ከዚህም ባለፈ የፈተናዎች ምንጭና አቅም እየሆነ ባለበት ሁኔታ በቀላሉ ልንሻገራቸው የምንችላቸው አይደሉም። ሕዝባችንንም እንደ ሕዝብ በየዘመኑ ብዙ ዋጋ እየከፈለ የመጣበትን የለውጥ ፍሬ ባለቤት ልናደርገው አንችልም።

ከዚህ ይልቅ የሀገር ጉዳይ፤ የሕዝብ የመለወጥ መሻት በሆነ ቡድን ወይም በመንግስት ብቻ እውን የሚሆን አለመሆኑን ተረድተን፤ ለሕዝብ ፍላጎት ራሳችንን ተገዥ በማድረግ፤ ከጠያቂነት እየወጣን የችግሮቻችን የመፍትሄ አካል መሆን ይጠበቅብናል። ይህን ለማድረግ የሚያስችል ማንነት/ስብዕና ከሌለን ደግሞ የሕዝባችንን የማደግና የመለወጥ ሕልም ከሚያሳንሱ እኩይ ተግባራት ልንታቀብ ይገባል። በዚህም የታሪክ ተጠያቂ ከመሆን ራስን ማትረፍ ይቻላል!

አዲስ ዘመን   ኅዳር 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You