እመርታ በበጋ መስኖ ስንዴ ምርት

ግብርና ለአንድ ሀገር የሕልውና ምንጭ መሆኑ የሚያጠያይቅ ባይሆንም እንደ እኛ ላሉ ሀገራት ደግሞ ትርጉሙ ከዚህም በላይ የዘለለ ነው:: ከሀገራችን አጠቃላይ ሕዝብ ከሰማኒያ ከመቶ በላይ የሚሆነው በግብርና ስራ የሚተዳደር ነው። ከምንከተለው ባሕላዊ አስተራረስ ግን የአሀዛችንን ያክል አራሳችንን እንኳን መመገብ አልቻልንም:: በግብርናው ላይ ያለን አረዳድም መዘመን ባለመቻሉ ከነበርንበት ፈቀቅ ሳንለ፤ ዘመና ተቆጥረዋል::

የሀሳቤ መነሻ ያለፈን እያስታወሱ መውቀስ ሳይሆን ባለፉት አንድና ሁለት ዓመታት ውስጥ እየታዩ ስላሉ አዲስና ለውጥ ተኮር የሆኑ የግብርና አረዳድና የምርጥ መሻሻል ላወጋችሁ እንዲሁም ይሁንታን ልሰጥ ነው:: እኛ ኢትዮጵያውን ግብርና የሀገር የጀርባ አጥንት ነው እየተባን ያደግን ነን:: እንደ እውነቱ ሆኖ ሀገራችንን ከድህነት፣ ሕዝባችንንም ከርሀብ አልታደገውም:: ይባስ ብሎ ብዙ በለሙ መሬቶችና በበቁ ባለሙያዎች ተከበን እርዳታ ጠያቂዎች ሆነን ለዘመናት ሰንብተናል::

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ስለታዩትና እየታዩ ስላሉ ወደፊትም የሀገራችንን የተረጂነት ስም ይፍቃሉ፣ ትውልድንም ከርሀብ ይታደጋሉ ከተባሉና ከሀገር ባለፈ ዓለም አቀፍ የምርት ልውውጥ ይካሄድባቸዋል ስለተባሉ የግብርና ዘርፎች የተወሰኑትን ላንሳ:: የመጀመሪያው የበጋ መስኖ የስንዴ ምርት ነው:: ያለፈው አንድ ዓመታት በኢትዮጵያ የግብርና ታሪክ ውስጥ በተለይም በስንዴ ምርት ያለአንዳች መጠራጠር እምርታ ያሳየንበት ጊዜ ነበር ማለት ይቻላል::

ራስን በምግብ ከመቻል፣ ምርትን ከማሳደግና የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አኳያ በግብርናው ዘርፍ እየተወሰዱ ካሉ አበረታች ስራዎች መካከል የመስኖ ስራ አንዱ ነው:: የዓላማው መነሻ ራስን በምግብ ከመቻልና ከተረጂነት መላቀቅ ብሎም አዲስና የተሻሻለ የግብርና ስትራቴጂዎችን ማስተዋወቅ ነው። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮች ከመጥቀምና የፍላጎት መጣጣምን ከማስተካከል አኳያ መቃኘት የሚችልም ነው:: እንዲህ አይነቱ የእቅድ አተገባበር ካለን የሰው ኃይልና የመሬት ስፋት አንጻር በውጤቱና በቀጣይነቱ ከሀገር አልፎ ለአፍሪካ የንቃት ደወል መሆን የሚችል ነው::

ሀገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለትና ከዚያ በላይ ለሆኑ ዓመታት በመስኖ ልማት ስራ ራስን ለመቻል የምታደርገው ጥረት በተወሰነ መልኩ ተስፋ ሰጪ አቅጣጫን ያሳየ ነው። ሳይንሳዊ በሆኑ ምሬቶች፣ በልምድና በተሞክሮ ዳብራ ባለፉት አስርት ዓመታት ደግሞ ይበልጥ ተሻሽሎ ጭላንጭል ተስፋችንን ያሰፋ የመስኖ ልማት መመልከት ችለናል:: ይሄን እውነታ ወደተጨባጭ የቀየረው ደግሞ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የታዩ መስኖ ተኮር የግብርና ስራዎች ናቸው:: ይሄን በመሰለው የአቅጣጫ ለውጥ ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ በግብርናው ረገድ መሻሻልን ያሳየንበት ሁኔታ መፈጠሩን መረጃዎች ያመለክታሉ::

ያለፉት ሁለት ዓመታት እንደሀገር በግብርናው ዘርፍ አዲስ አብዮትን ያስነሳንበት ነው:: ሀገር የለውጥ አብዮት ያስፈልጋታል:: ልክ እንደግብርናው የለውጥ አብዮት በተለያዩ መስኮች ለሀገር በሚበጁ አሰራሮችና ትግበራዎች የሚቀጣጠል ነው:: የግብርና አብዮት የምግብ ዋስትና ላይ ብቻ የሚቀር ሳይሆን በሁሉም ዘርፎች ላይ ተጽዕኖው የጎላ ነው:: የትኛውም ፕሮፌሽን በቅቶና ነቅቶ ለመቆም ሀገር ከተረጂነት ማሕበረሰብ ደግሞ ከልመና መላቀቅ አለበት::

ትውልድ እየለመነ የሚበላባት፣ ሀገር በእርዳታ የምትተዳደርበት ታሪካችን ማብቃት አለበት:: ያ ልማድ ሲያበቃ ነው እንደሀገር ሕልሞቻችንን መንዝረን ሳንገዳገድ የምንቆመው:: እርዳታ ከድጋፍ ባለፈ የፖለቲካ ሴራ ነው:: የሚሰጡን ሀገራት በሰጡን ልክ የሚወስዱብን አለ::

 እስከዛሬ በተቀበልነው እርዳታ ልክ ብዙ ነገሮቻችንን አጥተናል::

የግብርና ዘርፉ መዘመን እንደሀገር፣ እንደማሕበረሰብ፣ እንደትውልድ ሰፊ ትርጉም ያለው ነው:: ከፖለቲካ አንጻር ስንቃኘው እንኳን የሉአላዊነት እና የደህንነት አንዱ ማሳያ ሆኖ የሚወሰድ ጉዳይ ነው:: በነገራችን ላይ አእምሮአዊና አካላዊ ስልጣኔዎች ያ ማለት ከማሰብና ከማድረግ ጋር ከመወሰንና ከመምራት ጋር የተያያዙ የንቃት ብቃቶች ከምንመገበው ምግብ ጋር በቀጥታ እንደሚገናኝ ስንቶቻችሁ ታውቃላችሁ? በምግብ ራስን መቻል ማለት ጠግቦ ከማደር በራቀ ዘርፉ ብዙ ትርጉም ያለው ነው:: ግብርና የጀርባ አጥንት የተባለው በዚህ ምክንያት ነው:: በዚህና በመሰለው ምክንያት የጀመርነው የምርት ንቅናቄ ይበል የሚያሰኝ መሆኑ አጠያያቂ አይሆንም::

መንግስት ለበጋ መስኖ ስንዴ በሰጠው ትልቅ ትኩረት አሁን ላይ ከውጪ የሚገባውን የስንዴ ምርት በሀገር ውስጥ በመተካት አዲስ የለውጥ አቅጣጫን አሳይቶናል:: ይሄ ለውጥ በቀላልና ዝም ብሎ የተገኘ ሳይሆን በእቅድና በስትራቴጂክ በታገዘ የአቅጣጫ ለውጥ የመጣ ነው:: በባለፈው ጊዜ ያልተቻለ ለውጥ ነው:: ከውጪ የሚገባን ምርት በሀገር ውስጥ ምርት መተካት የሚለው ጽንሰ ሀሳብ በቀላል የሚታይ ሳይሆን ብዙ ተያያዥ ለውጦችን ይዞ የሚመጣ ነው::

ይሄን በማስመልከትና በበጋ መስኖ ስለለማው የስንዴ ምርትና እየመጣ ስላለው ለውጥ የግብርና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኮሚኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ከበደ ላቀው ‹ባለፈው ጊዜ በተሰራ ስራ እንደ ሀገር የሚታይና ተጨባጭ ለውጥ አምጥተናል:: ከዝግጅትና ከተሞክሮ አንጻር በዘንድሮው የበጀት ዓመትም በቀጣይ ሶስት ሚሊዮን ሄክታር በበጋ መስኖ ለማረስ የታቀደ ሲሆን ከዚህ ውስጥም 117 ሚሊዮን ኩንታል የሚሆን ምርት ይጠበቃል› ሲሉ ተናግረዋል::

ከዚህ ጎን ለጎን በመደበኛው የመስኖ ስራ እንደሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ድንች፣ ጎመን፣ አቦካዶና የመሳሰሉ ምርቶች ጊዜአቸውን ጠብቀው እየለሙ ሲሆን በበጀት ዓመቱ በበጋ መስኖ ከሚለማው የስንዴ ምርት እቅድ ጋር ያልተያያዙ አቅጣጫ ተቀምጦላቸው ራሳቸውን ችለው የሚንቀሳቀሱ እንደሆኑ ጥቁምታ ሰጥተዋል:: በሌማት ትሩፋትም ቢሆን ብዙ ስራዎችን ሰርተን ብዙ እቅዶችን በማቀድ ለመጪው ጊዜ ዋስትና የሚሆኑ ስራዎችን እየሰራን እንገናኛለን ሲሉ አብስረዋል::

የዘንድሮው የበጀት ዓመት ከባለፈው የ 1.3 ሚሊዮን ሄክተር ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ ማደግ እንደቻለ ነው የተጠቀሰው:: በአንድ ዓመት ልዩነት ውስጥ የበጋ መስኖ ልማትን በእጥፍ ማሳደግ ከለውጥና የተሻለ ተስፋን ከመስጠት አኳያ ብዙ ትርጉም ሊሰጠው የሚችል ተግባሬ ነው:: በቀጣይም አድማሱን እያሰፋ በመሄድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከውጪ የሚገባን ምርት ከማስቀረት ጎን ለጎን የዋጋ ንረትን በማመጣጠን የኑሮ ውድነትን ያስተካክላል ተብሎ ይታመናል:: በተለይ በፍጆታ እቃዎች ላይ እየተስተዋለ ያለውን ንረት በመቆጣጠር ድርሻውን ይወጣል::

በመኸር ወቅት ያለውን የምርት ሽፋን ስናየው ከበጋ መስኖ ምርት ጋር ተቀራራቢ ነው:: አምና 2.8 ሚሊዮን ሄክተር መሬት በመኸር የስንዴ ምርት የተሸፈነ ሲሆን ዘንድሮ የአምናውን ቁጥር በማሳደግ 3.6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በስንዴ ልማት እንደሚለማ ገልጸዋል:: ከዓመት ዓመት ምርትና የሄክታሩ ቁጥር እየጨመረ የሚፈለገውን የማደግና የመለወጥ ግብ እንደሚመታ ካለፈው ማየት ይቻላል::

በጋና መኸር ክረምትና መስኖን ለብሰው ሕልውና የሚዘሩ ናቸው:: አብዛኛው የግብርና ስራችን ክረምት ላይ የተመሰረተ መሆኑ የማይካድ ሀቅ ቢሆንም እየተለማመድን የመጣነው የበጋ መስኖ ምርት የሰው ኃይልና ለም መሬት ይዘን ላልዘመነው ግብርናችን እና ራሱን በምግብ ላልቻለ ሕዝባችን ሁነኛ መልስ የሚሰጥ ነው:: ሀገርን ባልታዩና ባልተሞከሩ ለውጥ ለበስ አቅጣጫዎች ካልመራናት በአንድ አይነት አቅጣጫ ለውጥ ማምጣት አዳጋች ነው:: በመኸርና በበጋ መስኖ የሚመረቱ ስንዴና ሌሎች ምርቶች ከሀገር አልፈው ለውጪ ገበያ በመቅረብ ስምና ክብራችንን የሚያድሱበት ጊዜ ቅርብ ነው::

የታቀደውን እቅድ ለማሳካት ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ አስፈላጊ የሆኑ ሁሉንም አይነት አቅጣጫዎች እየተተለሙ እንደሆነ በመናገር ከዚህ ጎን ለጎን ከታች ከአርሶ አደሩ ጀምሮ በየደረጃው ለሚገኙ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በበቂና በስፋት የግንዛቤ ስራ እየተሰራ ነው። በዚህም ካለፈው ዓመት የተሻለ ምርትን እንድንጠብቅ ሆነናል ብለዋል:: እስከ ጥቅምት አጋማሽ ድረስ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና በአፋር ክልል ለበጋ መስኖ ስንዴ የቅድመ እርሻ ስራ ተሰርቷል:: በቀጣይም በሌሎችም አካባቢዎች መሰል ቅድመ ዝግጅቶች ተጠናክረው በዘንድሮው የበጀት ዓመት ከአምናው የተሻለ እምርታን እንጠብቃለን ብለዋል::

ያሉንን የሰው ኃይሎች ካሉን የተፈጥሮ ሀብቶች ጋር አቀናጅተን ግብርና መር በሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲና ስትራቴጂ የአምስት ዓመት የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅዳችንን ለመተግበር ችለናል:: በቀጣይ ለሚተገበረው የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድም እንደግብዐት በመሆን የተሻለ ለውጥን ለማምጣት ከወዲሁ እየተሰራ መሆኑ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሚሰሙ ድምጾች ያመላክታሉ:: በሁለት ዓመት ውስጥ በግብርናው ዘርፍ መሻሻልን ካሳየን የሚጠበቅብን የአቅጣጫ ለውጥ ማድረግ ነው::

እንደሀገር ከስንፍናና ከስልቹነት በስተቀር ሁሉ ያለን ሕዝቦች ነን:: ለውጥና እድገት ደግሞ ያለን ነገር በመጠቀም የሚመጡ መሆናቸው በረከቶቻችን ብቻቸውን ምንም እንዳይደሉ የሚጠቁም ነው:: በረከቶቻችንን ከማየት አልፈን ለሌላ ትልቅ ነገር መጠቀም ብንችል ዛሬ ላይ ራሳችንን ከመቻል አልፈን ለሌሎች የምንተርፍ መሆን በቻልን ነበር:: ለለውጥና ለስኬት ከተጋን አሁንም ብዙ እድሎች አሉን:: ብዙዎች በጥቂትና ምንም ሊባል በሚችል ተፈጥሮ ላይ ነው ራሳቸውን ችለው ለሌሎች መትረፍ የቻሉት:: እኛ ግን በበዛና በሰፋ ተፈጥሮ መሀል የድሀ ድሀ ሆነን እየኖርን ነው:: ይሄ እውነታ ከሁሉም በላይ ሊያስቆጨን የሚገባ ነገር ነው::

በውሀ ተከበን መራባችን ለሰሚው ግራ ነው:: በግብርናው ዘርፍ እንደዋና ግብዐት ከሚወሰዱ ነገሮች ውስጥ የመጀመሪያው የውሀ ሀብት ነው:: በአባይና ጣና፣ በአዋሽና ተከዜ፣ በጫሞና ኦሞ፣ በገናሌና ባሮ በሌሎችም ወንዞች ተከበን፣ የአፍሪካ የውሀ ገንቦ የሚል የቁልምጫ ስም ተሰቶን መራብና መጠማታችን ዛሬም ለብዙዎች ጥያቄ የሚሆን ነው::

በዚህ አያበቃም ለምና ድንግል በሆኑ፣ የሰጡትን በሚያበቅልና በሚያፈራ መሬት ላይ ቆመን፣ ተፈጥሮ ከሌላው አብዝታ ለእኛ መትረፍረፍን አድላን ተረጂ ስንሆን ይሄም ሌላው ወይ ጉድ የሚያስብል ጉዳይ ነው:: ሌላም አለ ሰባ ከመቶ ወጣት በሆነባት፣ ብርቱና ጉምቱ የስራ እጆችን ይዘን፣ የተማረ፣ የሚያስብ፣ የሚመራ ምሩቅ ባለሙያ ይዘን በጠባቂነት መታወቃችን ግራ አጋቢ ነው::

ስልጣኔ እንደ እኛ ቅርቡ የሆነ ማሕበረሰብ የለም:: እድገትና ብልጽግና እንደ እኛ አፍንጫው ስር የሚያውደለድልለት ትውልድ የለም:: ችግሩ ባሉን ነገሮች አለመጠቀማችን ነው:: ወርቆቻችንን እንደመዳብ ቆጥረን ሁሉን በሚያጠግብ መሬት ላይ በርሀብ እናዛጋለን::

ለዚህ ሀሳብ ምቹ ማስረጃ የሚሆነን የሁለት ዓመቱ በስንዴ ምርት ላይ ያሳየነው እምርታ ነው:: አልነቃንም እንጂ ከነቃን ከራሳችን አልፈን ለአፍሪካ የሚተርፍ ኃይል አለን:: በአጭር ጊዜ ውስጥ ስንዴን በበቂና በጥራት አምርተን እርዳታን ከማስቀረት ጎን ለጎን ለውጪው ማሕበረሰብ የማቅረብ ደረጃ ላይ ደርሰናል::

ድህነት አስተሳሰብ ነው:: ማንም በልጽጎ አልተፈጠረም:: ማንም በልጽጎ ሀገርና ሕዝብ አልሆነም:: በሰው ልጆች መካከል የተፈጠረው የኑሮ ልዩነት አስተሳሰብን ታኮ፣ ተነሳሽነትን ተደግፎ ነፍስ የዘራ ነው:: ለመለወጥ ከተጋን ሊለውጡን የሚችሉ በርካታ ተፈጥሮዎች አሉን:: ከድህነትና ከተረጂነት ለመላቀቅ ይሄን ለማድረግ ከማንም የተሻለ እድል አለን:: እንስራ…እንተባበር:: በአዲስ አቅጣጫ አዲስ ነገር እንፍጠር::

 በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን   ኅዳር 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You