ለሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚነት

ብዙ ጊዜ ስለ ሰላም ጥቅምና አስፈላጊነት የሀይማኖት አባቶች ይሰብካሉ፣ ዘማሪዎች ይዘምራሉ፣ አርቲስቶች ያቀነቅናሉ፣ ገጣምያን ይገጥማሉ፤ ባለቅኔዎችም ይቀኛሉ። ስለ ጦርነትን አስከፊነትን፣ አውዳሚነት፣ የእድገት ፀርነት፣ ጎታችነት በሚመለከት በርካቶች ፅፈዋል። የጦርነት አውዳሚነት ጠቅሰው የሰላም ዋጋን አጉልተው ብዙዎች ተናግረዋል፤ ጽፈዋል።

ዕውቁ ግሪካዊ ጸሐፊም እና የታሪክ ሰው ሔሮዶቱስ (490 – 425 ዓ.ዓ.) የጦርነትን አስከፊነት እና ሰላም የውሃና የአየር ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንዲህ ሲል ገልጾታል። “ In peace, sons bury their fathers. In war, fathers bury their sons! ” በሰላም ጊዜ ልጆች አባቶቻቸውን ይቀብራሉ፤ በጦርነት ጊዜ አባቶች ልጆቻቸውን ይቀብራሉ፤ ከዚህ የተነሳም ሁላችንም በሰላም እንኖር ዘንድ ሁላችንም ሰላምን መፍጠር አለብን ይላል።

ይህ የግሪካዊ የታሪክ አዋቂ አባባል የጦርነት እጅግ አስከፊ ገጽን ብቻ ሳይሆን የሰላምን ጥቅም አድማሳዊነት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የሰላም ዋጋ ይኼ ነው ተብሎ የሚተመን ባይሆንም፤ ሰላም የሁሉም ነገር፣ የነገ ዋስትና እንደሆነ የምንረዳው ሲደፈርስ፤ በጦርነትና አለመረጋጋት ውስጥ ስንሆን ነው።

በእርግጥ የጦርነትን አስከፊነት፣ የሰላምን አቻ የለሽነት ከኢትዮጵያውያን በላይ የሚያውቀው አለ ብሎ መናገር ይከብዳል። ” ማን ይናገር የነበረ፣ ማን ያርዳ የቀበረ ” እንደሚባለው፣ እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ላለፉት ግማሽ ምዕተ ዓመታት እርስ በእርስ ተዋግተን አይተነዋል። የጦርነት መራርነትን ቀምሰነዋል።

ብዙም ሳንርቅ ባለፉት ሁለት ዓመታት በቆየንበት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ከፍተኛ ዕልቂትና ውድመት ከማድረሱም በላይ፣ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ያስከተለው ጉዳት እንደ ዋዛ የሚረሳ አይደለም:: በዚህ የቅርብ ክስተት በተጨባጭ የጦርነትን አስከፊነት አይተነዋል። እንደ አገር ዋጋ ያስከፈለንን ጦርነት በመደራደር በሰላማዊ መንገድ መቋጨቱ መቻላችን ትልቅ ድል ነው።

የዓለም ታሪክ የሚያስረዳንም ጦርነት ለሰላም በተዘረጉ እጆች እንጂ በመሣሪያ እጦት እንደማይቆም ነው። እንዲሁም በሰላማዊ ድርድር እንጂ በአሸናፊና በተሸናፊ መንፈስ የተቋጩ ጦርነቶች ዘላቂ ሰላምን አያሰፍኑም። እዚህ ጋር መንግስትን ወደ ጦርነት እንዳይገባ የሄደባቸውን ርቀቶች ማስታወስና ማድነቅ ያስፈልጋል።

መንግስት ከጦርነቱ በፊት ሆነ ወደ ጦርነት ከተገባም በኋላ ሰላምን በተመለከተ ይዞት የነበረው አቋም፣ በብዙ መልኩ የሰላምን ሁለንተናዊ ጠቀሜታ ያገናዘበ እንደነበር ለመገመት የሚከብድ አልነበረም፣ የሀገር ሽማግሌዎችን እናቶችን ያካተተ ቡድን የሰላም መንገድ ጠራጊ አድርጎ ተንቀሳቅሷል።

ወደ ጦርነት ከተገባም በኋላ ቢሆን የኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብም ለመሰል የውጭ ተፅእኖዎች ሳይንበረከክ፣ የሰላም ንግግር ሐሳብን በዋናነት ሲደግፉና እንዲጀመርም ከፍተኛ ግፊት ሲያደርጉ ቆይቷል። በጦርነቱ የኃይል ሚዛኑ በእጁ ቢሆንም ጦርነቱ በሰላም ስምምነት ቢቋጭ ሀገርን አትራፊ የሚያደርግ መሆኑ አምኖ የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት እንዲፈረም ጥልቁን ድርሻ ተጫውቷል::

ይህ ስምምነት መፈረሙ በአካባቢው ደም አፋሳሹን ጦርነት በመግታት ረገድ ያበረከተውን አስተዋጽኦ ጎልቶ ይጠቀሳል:: በብዙ መስዋዕትነት የተገኘውን ሰላም ማጽናት ይጠይቃል። ዛሬ የተገኘውን ሰላም በፅኑ መሰረት ላይ ለመገንባት የጋራ ስምምነቶችን ማክበር እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። ሰላምን በፅኑ መሰረት ላይ ለማቆምና ለማጽናት በፕሪቶሪያ የተፈረመውን የጋራ ስምምነትን ሁሉም ወገኖች ማክበር አለባቸው።

የፌዴራል መንግስት የተገኘን ሰላም በማጽናት ረገድ የሄደበት እና እየሄደበት ያለው ርቀት የሚያስመሰግን ነው። የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነትን አንደኛ ዓመት በተመለከተ ከኢፌዴሪ መንግሥት በሰጠው መግለጫ፤ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ መንግሥት በሆደ ሰፊነትና ቁስሉ እንዲሽር ካለው ፍላጎት ረጅም ርቀት መጓዙን አረጋግጧል::

ከስምምነቱ መፈረም በኋላ የጥላቻውን ጉም ገፍፎ ወደ ትግራይ በግንባር ቀደምነት የተጓዘው በአፈ ጉባኤው የተመራው የፌዴራል መንግሥቱ ልኡክ ነበር:: ይህ ልኡክ ከተጓዘ በኋላ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የባንክና የአውሮፕላን አገልግሎቶች በፍጥነት እንዲጀምሩ መደረጉን አስታውቋል::

እነዚህን ሌሎች ተግባራት በማከናወን የፌዴራል መንግሥት የፕሪቶርያውን ስምምነት በተመለከተ ከሚጠበቅበት በላይ መጓዙን ጠቅሶ፤ በዚህም ለሰላም ያለውን ጽኑ አቋም ደጋግሞ ማሳየቱን አመልክቷል:: መንግስት የፕሪቶርያውን ስምምነት በተመለከተ ከሚጠበቅበት በላይ እየተጓዘ መሆኑን በማሳየት፤ ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ እንዲተገበር በማድረግ ረገድ መንግሥት ቁርጠኛ አቋም እንዳለው አረጋግጧል።

ሰላም መንግስት ስለ ፈለገ ብቻ እንደማይመጣ ይታወቃል። ይህ የመንግስት ጥረት ፍሬያማነት የሁሉም አካላት ተመሳሳይ ቁርጠኝነት በማሳየት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣትን ይጠይቃል:: በዚህ ረገድ ክፍተቶች መኖራቸውን ነው መግለጫው ለመገንዘብ የተቻለው።

መንግስት ብዙ ርቀት በመጓዝ ለሰላም ያለውን ጽኑ አቋም ቢያረጋግጥም፤ ከሌላኛው አካል እግር የመጎተት አዝማማሚያዎች እንዳሉ፣ይህም አይነቱ አካሄድ ጦርነቱ ካስከተለው ጥፋት፣ የሰላም ስምምነቱ ካስገኘው እፎይታ አንጻር በየትኛውም መልኩ ተቀባይነት የሚኖረው አይሆንም::

ይህ አይነቱ አካሄድ ዘላቂ ሰላምን፣ የሕዝቦችን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የሚያረጋግጥ እንዳልሆነ መረዳት ይገባል:: እንወክለዋለን ለሚባለው ሕዝብ ከገጠመው ፈተና የሚያላቅቅ አካሄድም አይሆንም። ይህ ብቻም ሳይሆን እንደ ሀገር የሰፈነውን የሰላም አየር የሚበርዝና ዳግም ወደ ጥፋት የሚወስድ ነው::

ለሀገር ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት መሰረት የሆነውና የዜጎች ሰቆቃ እንዲበቃ ያደረገው የፕሪቶሪያው ስምምነት ቅድመ ሁኔታ የለውም፤ ስለሆነም በስምምነቱ መሠረት መፈጸም ከሁሉም ወገን የሚጠበቅ ግዴታ ነው:: ያለውም ብቸኛው አማራጭ ይህንን ስምምነት ማስፈፀም ነውና በሁሉም ወገን ተመጣጣኝ አካሄድ በመጓዝ ሁሉን አሸናፊ የሚያደርገውን ሰላም አጽንቶ ማስቀጠል ነው።

ዳንኤል ዘነበ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You