በቡና እና ሻይ ልማት ሀገራችን ያላትን አቅም በሚገባ እንጠቀም!

 ኢትዮጵያ ቀደምትና ባለ ብዙ ፀጋ ሀገር ናት፡፡ ላለፉት ሺህ ዓመታት ኢትዮጵያ በታሪክም፣ በጥበብም፣ በነጻነትም፣… ቀዳሚ ሀገር ሆና የተገለጠችባቸው በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ እነዚህ የቀዳሚነቷ መገለጫ ሁነቶችና ክስተቶች ታዲያ በችሮታ የተበረከቱላት አልነበሩም፡፡ ይልቁንም ቀድመው ኖረው ቀድመው ሰርተው ያስቀደሟት የቀደምት ኢትዮጵያውያን የአዕምሮም፣ የተግባርም ፍሬዎች ናቸው፡፡

ይሄን የቀዳሚነት ልዕልናዋን እንደቀደመ ማስቀጠል ደግሞ የተተኪው ትውልድ ተግባር ነው፡፡ ሆኖም ትውልድ በመዘናጋቱ፣ ተተኪው ባለመትጋቱ ይሄን ቀዳሚነቷን ለሌላ ቀዳሚ እንድትለቅ፤ በነበር ቀድማ፤ አሁን ከኋላ ሆና እንድትገለጥ አደረጋት፡፡ ይሄን ለመቀየርም ነው ዛሬ ምድረ ቀደምትነቷን በማጉላት ወደ ቀደመ ልዕልናዋ ለመመለስ እየተሠራ ያለው፡፡

ከዚህ ከቀዳሚነቷ በተጓዳኝ የሚታየው ባለፀጋነቷም ቢሆን፣ ከፈጣሪ በተቸረችው በረከትም፤ ትውልዶች በሰሩት የላብ ውጤትም የተገኘ ነው፡፡ ታዲያ ይሄን ሃብት ተጠቅሞ ማደግም፤ ይሄን ሃብት ተሸክሞ መደህየትም የሃብቱ ባለቤት ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ እንደ ሀገር እምቅ ሃብት ይዘን፤ በድህነት፣ በረሃብና በተመጽዋችነት ታሪክ የመጠቀሳችን ጉዳይ ነጋሪ የሚሻ አይደለም፡፡

ይሄን የድህነት ታሪክ ከመቀየር አኳያ እንደ ሀገር ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው፡፡ ሃብቱን የሚያውቅ፤ ሃብቱን የማልማት ጥበብ የተቸረው፤ ሃብቱን አልምቶ የመልማት ሕልምን የሰነቀ መሪና ትውልድ ሲገናኝ ደግሞ ጉዞው የተሳለጠ፤ ውጤቱም የፈጠነና ያማረ ይሆናል፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያን ከድህነትና ከተረጂነት መዝገብ ለማውጣት የተደረገው የስንዴ ልማት ሥራ አበረታችና ተስፋ ፈንጣቂ ውጤት የተመዘገበበት ሆኗል፡፡

ይሄን ውጤት ተከትሎ በሩዝ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በቡና እና ሻይ ላይ እየተሰራ ያለው ሥራ እጅጉን አበረታች ውጤት እየታየበት ነው፡፡ ለምሳሌ፣ ሩዝን ከውጪ ማስገባት ማቆም የሚቻልበት ብቻ ሳይሆን፤ በቀጣይ ወደ ውጪ መላክ የሚቻልበት አቅምም እየተፈጠረ ስለመሆኑ መመልከት ተችሏል፡፡

ከዚህ ባሻገር ግን ቀድሞውንም የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ ከፊት ሆኖ የሚመራው የቡና ምርት ጉዳይ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው፡፡ ምክንያቱም ይሄ ሃብት የኢትዮጵያን ቀደምትነትም፣ ባለፀጋነትም አጣምሮ የያዘ፤ የኢትዮጵያ መልክ ሆኖም በዜጎቿ ማሕበራዊ መስተጋብር የሚገለጽ ነው፡፡

ቡና ለረዥም ዓመታት የኢትዮጵያን የወጪ ምርትም፣ የውጪ ምንዛሬ ግኝትም ሆኖ ከፊት ሲመራ፤ የሀገር ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ሆኖ የዘለቀ ምርት ነው፡፡ አሁንም እንደ ሀገር የወጪ ምርትን በዓይነትም፣ በጥራትም፣ በመጠንም ለማሳደግ በተያዘው አቅጣጫ መሰረት ትኩረት ከተሰጣቸው መካከል አንዱ ቡና ሲሆን፤ የሻይ ምርትም ከቡና ጋር ሌላ አቅም ሆኖ ኢኮኖሚውን እንዲያግዝ የማድረግ ከፍ ያለ ተግባር ውስጥ ተገብቷል፡፡

በተለይ በቡናው ዘርፍ ያለው እምቅ አቅም፤ በሻይ ዘርፉ ካለው ሰፊ የመልማት አቅም ጋር ተዳምሮ ቢሰራበት የሀገርን ተጠቃሚነት በእጅጉ የሚያሳድግ ነው፡፡ ይሄን የማድረግ ሥራው ደግሞ የግብርናውም፣ የንግዱም ዘርፍ ቢሆንም፤ ለሥራው ከተሰጠው ትኩረት አኳያ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ተቋቁሞ በልዩ ትኩረት እንዲመራ ተደርጓል፡፡

በዚህም ባለፉት ዓመታት በምርትም፣ በውጪ ምንዛሬ ግኝትም አበረታች ውጤት ተገኝቷል፡፡ የባለስልጣኑ መረጃ እንደሚያመለክተውም፤ ቀደም ሲል ወደ ውጪ ተልኮ ይገኝ የነበረው ዶላር በሚሊዮኖች ነበር፤ አሁን ግን በተሰራው ስራ በቢሊዮኖች ማግኘት ተችሏል፡፡ ይሄ የሆነውም ምርትን በማሳደግ ጭምር ሲሆን፤ ለምሳሌ፣ ቀድሞ 500ሺ ቶን የነበረውን የቡና አጠቃላይ ዓመታዊ ምርት ወደ 800ሺ ቶን ማሳደግ ተችሏል፡፡

ተደራሽነቱን ከማሳደግ አኳያም፣ ቀደም ሲል የኢትዮጵያን ቡና ሲገዙት ከነበሩት አሜሪካን፣ ጃፓን፣ ሳውዲአረቢያ፣ ቤልጅየምና ጀርመን በተጨማሪ፣ መዳረሻዎቹን ወደ 33 ሀገራት ከፍ ማድረግ ተችሏል፡፡ ይህ በእንዲህ አንዳለ 99 በመቶ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ጥሬ ቡና እንደመሆኑ ይሄንን መቀየር እና እሴት ጨምሮ መላክ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

እንደ ቡናው ሁሉ በሻይ ልማትና ግብይት ላይ የተሰራው ሥራና እየተገኘ ያለው ውጤት የሚያበረታታ ነው፡ ፡ ይሄ የሆነው ደግሞ በሻይ ቅጠልና ቅመማ ቅመም የግብይት ሥርዓት ተዘርግቶላቸው እንዲለሙ በመደረጉ ሲሆን፤ ለምሳሌ፣ ሻይ ቅጠል ወደ አራት ሺ ሔክታር ማሣ ላይ እየለማ፣ በዓመት እስከ ሦስት ሚሊየን ዶላር ገቢ እያስገኘም ነው፡፡

በዚህ መልኩ በሻይና ቡና ዘርፍ ያለውን ልማት ከማሳደግም ሆነ ለሃገር ሁለንተናዊ ብልጽግና ያላቸውን አበርክቶ ከማሳካት አኳያ የ15 ዓመት ስትራቴጂ እቅድ ተነድፎ እየተሰራ ሲሆን፤ በዚህ ሂደት የተገኘውም ጅምር ስኬት በላቀ ውጤት ታጅቦ ሊጓዝ የሚገባው ነው!

አዲስ ዘመን   ኅዳር 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You