ሰላም የሰው ልጅ ዋነኝ ግለሰባዊ ሆነ ማሕበረሰባዊ እሴት ነው። ከዚህ የተነሳም የትኛውም ማኅበረሰብም ይህን እሴት እንደ ግለሰብ ሆነ እንደ ማሕበረሰብ መጠበቅና ማስቀጠል የሚያስችሉ ሀይማኖታዊ፣ ባሕላዊና ማሕበራዊ አስተምሮዎች አሉት።
በተለይም ባለንበት ዘመን ሰላም ለአንድ ማሕበረሰብ ፤ ከዚያም ባለፈ ለዓለም የፖለቲካ፣ የማሕበራዊና የኢኮኖሚያዊ ስርዓት መረጋጋት ካለው የማይተካ አስተዋጽኦ አንጻር የሰላም ጉዳይ ዓለም አቀፍ የመነጋገሪ ርዕሰ ጉዳይ ከሆነ ውሎ አድሯል። በቀጣይም አጀንዳ ሆኖ ስለመቀጠሉ ብዙ አነጋጋሪ አይሆንም።
ከዚህ የተነሳም ባለንበት ዘመን ስለ ሰላም ድምጻቸውን ከፍ አድርገው የሚያሰሙ/ የሚጮሁ ግለሰቦች ሆኑ ተቋማት በስፋት እየተስተዋሉ ነው፤ ይህም ሆኖ ግን አሁንም በተለያዩ የዓለም አካባቢዎች ከሚስተዋለው የሰላም እጦት አኳያ የሰላም ጉዳይ ዋነኛ የዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ አጀንዳ እንደሆነ ቀጥሏል።
ይህ ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው የሰላም ጉዳይ በእኛም ሀገር ትልቁ አጀንዳ ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል። ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የተዛቡ ትርክቶች በፈጠሯቸውና እየፈጠሯቸው ባሉ ችግሮች በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የሰላም እጦቶች ሀገርና ሕዝብን ብዙ ዋጋ ማስከፈላቸው የሚታወስ ነው።
በተለይም በመከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በሕወሓትና በፌደራል መንግስት መካከል የተፈጠረውን ጦርነት፤ በሰላማዊ መንገድ መቋጨት ባለመቻሉ በተካሄደው ጦርነት የሀገርን ሕልውና አደጋ ውስጥ የከተተ አጋጣሚ ተፈጥሯል። በዚህም ዜጎች ለሞትና ለአካል ጉዳት፤ የሀገር ሀብትም ለውድመት ተዳርጓል።
ይህንን አደገኛ ታሪካዊ ክስተት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ በተካሄደ ድርድር በሰላም ስምምነት መቋጨት ተችሏል። ይህንን ተከትሎም በስምምነቱ መሰረት አካባቢው ከጥይት ድምጽ ነጻ ሆኗል። በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ተሰይሞም ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ በክልሉ የሲቪል አስተዳደር መዋቅሮችን ከመዘርጋት ጀምሮ ፤ ላለፉት ሶስት ዓመታት ጦሙን ያደረው የክልሉ መሬት ታርሶ አዝመራ መሰብሰብ የሚቻልበትን አስቻይ ሁኔታ ፈጥሯል። የክልሉ ሕዝብም ከጠባቂነት የሚታደገውን የሰብል ምርት መሰብሰብ የሚችልበት ደረጃ ደርሷል።
ከዚህም ባለፈ ከጦርነት በፊት የነበሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች / የመቀሌ የንጹህ መጠጥ ውሀ ፕሮጀክትን ጨምሮ ሌሎች ፕሮጀክቶች የሚጀመሩበትን ሁኔታ በማመቻቸት የክልሉ ሕዝብ ጦርነቱ ፈጥሮት ከነበረው የልብ ስብራት ወጥቶ ወደ ልማት ፊቱን እንዲያዞር የተሻለ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል፡፡
ይህ በክልሉ የሚስተዋለው ሰላምን የማጽናትና ልማትን የማስቀጠል እንቅስቃሴ በእጅጉ የሚበረታታ እና የመላውን ሕዝባችንን፤ በተለይም የባለሀብቱን እና የዲያስፖራውን ድጋፍና አጋርነት አብዝቶ የሚሻ ነው።
የክልሉ ተወላጅ የሆኑ ዲያስፖራዎች አሉባልታ እና ከጥላቻ ትርክቶች ወጥተው፤ ክልሉን መልሶ ለመገንባት፤ በክልሉ ያለውን ሰላም ጠብቆ ለማስቀጠል የሚደረገውን ጥረት በሁለንተናዊ መልኩ በማገዝ ለክልሉ ሕዝብ ያላቸውን አጋርነት በተጨባጭ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።
የትግራይ ክልል ሕዝብም አለመግባባቶችን በኃይል ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች የቱን ያህል አስከፊ ውጤት ይዘው እንደሚመጡ ባለፉት ሶስት ዓመታት ካሳለፋቸው አስቸጋሪ ቀናት በተጨባጭ ያስተዋለው በመሆኑ፤ አሁን ላይ በእጁ ያለውን ሰላም በመጠበቅ ሂደት ከፍያለ ኃላፊነት አለበት።
ይህንን ኃላፊነቱን ለመወጣት አለመግባባቶች በውይይት የሚፈቱበት መንገድ እንዲለመድ ጫና መፍጠር፤ ባሕል ሆኖ እንዲያድግ ማበረታታት ይጠበቅበታል። በተለይም ወጣቱ ትውልድ ከስሜታዊነት ወጥቶ በሰከነ መንፈስ ስለራሱ፣ ስለ ክልሉ እና ሀገሩ የሚያስብበትን የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠር ይኖርበታል!
አዲስ ዘመን ህዳር 3/2016