በሁሉም የግብርናው ቤተሰቦች የተጠናከረው የአዝመራ ስብሰባ -በኦሮሚያ ክልል

ወቅቱ አርሶ አደሩ የልፋቱን ፍሬ ማየትና አዝመራውን ሰብስቦ ጎተራ ማስገባት የሚጀምርበት ነው፡፡ አርሶ አደሩ በመኸር እርሻው ለዘር ያዘጋጀውን ማሳውን በዘር ሸፍኖ፣ ከአረምና ከተባይ ጠብቆ ቆይቷል፤ አሁን ደግሞ ሰብል መሰብሰብ ትልቁ ስራው ነው፡፡ አዝመራው በወቅቱና በአግባቡ ካልተሰበሰበ አርሶ አደሩ ለበርካታ ወራት በደከመበት የግብርና ስራ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል፡፡ እንደ ሀገር በግብርናው ዘርፍ ላይ ሲከናወን የቆየው ርብርብ የበለጠ ውጤታማ እንዳይሆን ያደርጋል፡፡

ይህ ወቅት አዝመራ ለመሰብሰቡ ስራ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጥበት ነው፡፡ ይህ ደግሞ አዝመራ የመሰብሰቢያ ወቅት ስለሆነ ብቻ አይደለም፤ አዝመራው ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ ሳቢያ እንዳይበላሽ ለማድረግም ጭምር ነው፡፡

የግብርና ሚኒስቴርና የብሔራዊ ሚትዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በአሁኑ ወቅት የደረሱ ሰብሎችን ሊያበላሽ የሚችል ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየታየ ነው፡፡ አርሶ አደሩ ምርቱን ከብክነት ለመጠበቅ የደረሱ ሰብሎችን ለመሰብሰቡ ስራ ትኩረት እንዲሰጥ የግብርና ሚኒስቴር አሳስቧል፡፡ ይህን ተከትሎም በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች የደረሱ ሰብሎችን የመሰብሰብ ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመላክተው፤ በአሁኑ ወቅት ከሰብል ጥበቃ በተለይም ከደረሰ ሰብል አሰባሰብ ጋር ተያይዞ የክትትል ሥራ እየተሰራ ነው፡፡ በተለይም ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እየታየ በመሆኑ በየአካባቢው ያለውን የደረሰ የሰብል ምርት የመሰብሰብ ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የደረሱ ሰብሎችን የማበላሸት ዕድሉ ሰፊ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት በየክልሉ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም አዝመራው በፍጥነት እንዲሰበሰብ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎችም የደረሱ ሰብሎችን የመሰብሰቡ ሥራ በባህላዊ እንዲሁም ዘመናዊ በሆነ መንገድ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

በኦሮሚያ ክልልም ይሄው እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ክልሉ በቅርቡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በተገኙበት የመኸር አዝመራ ስብሰባና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ማሳን በዘር የመሸፈን ስራ በይፋ ስነስርዓት መጀመሩ ይታወሳል፡፡

የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ በሪሶ ፈይሳ እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት በክልሉ አምስት በሚደርሱ ዞኖች ውስጥ በተያዘው ዕቅድ መሰረት የደረሰ ሰብል አዝመራ የመሰብሰቡ ሥራ ተጀምሯል፡፡ የአዝመራ ስብሰባውም በባሕላዊና በዘመናዊ መንገድ በተጠናከረ መልኩ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ምርት የመሰብሰቡ ስራም በአርሲና በምዕራብ አርሲ፣ ምስራቅ ሸዋ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ ሸዋና ምዕራብ ሸዋ አልፎም በምዕራቡ በኩል በሚገኙ ሰባት በሚደርሱ የክልሉ ዞኖች እየተከናወነ ነው፡፡ የምርት አሰባሰብ ሂደቱም ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እየታየ በመሆኑ የምርት አሰባሰብ ሂደቱን እያስተጓጎለ ነው፡፡

በሁለቱ አርሲና በሁለቱ ሐረርጌ ዞኖችም እንዲሁ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ወቅቱን ያልጠበቀ ከፍተኛ ዝናብ መጣሉን የጠቀሱት አቶ በሪሶ፤ ዝናቡ የምርት አሰባሰብ ሂደቱን እስከማስተጓጎል ደርሶም እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ወቅቱን ያልጠበቀው ዝናብ ጋብ እያለ መሆኑን ጠቅሰው፣ አዝመራው በጥሩ ሁኔታ እየተሰበሰበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለምርት አሰባሰብ ሂደቱ ሁለት አይነት ዘዴዎች ጥቅም ላይ መዋላቸውንም ምክትል የቢሮ ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ አንደኛው የተለመደው የሰው ኃይል መጠቀም እንደሆነ ገልጸው፤ እሱም በሰው ኃይል በእጅ እየታጨደና እየተከመረ፣ የሚወቃበት መንገድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህም ኮምባይነሮችና ሌሎች ዘመናዊ መሳሪያዎች በማይገቡባቸው አካባቢዎች ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሁለተኛው መንገድ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማለትም በኮምባይነሮች የሚሰበሰብበት መንገድ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ ሁለቱ ዞኖች አካባቢ እንዲሁም በሸዋ፣ ምዕራብ አርሲ፣ አርሲና በሁለቱ ሐረርጌ ዞኖች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ኮምባይነሮችን በመጠቀም ምርት እየተሰበሰበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ በተለይም የብርእ ሰብሎች በስፋት በኮምባይነር እየተሰበሰቡ ሲሆን፤ በተያያዘም በእጅ የሚሰበሰበው አዝመራም ምርቱ በትሬሸሮች እየተወቃ በአግባቡ እየተሰበሰበ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡

ዝናቡ አሁን ቆም ማለቱን ጠቅሰው፣ ሊመጣ የሚችል ስለመሆኑም የአየር ትንበያ መረጃ እንደሚያመለክት ተናግረዋል፡፡ ይህን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በሰፊው ንቅናቄ ተፈጥሮ ምርቱ እየተሰበሰበ ያለበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡ በቀጣይም አሁን በተጀመረው አግባብ እንዲሁም በላቀ ፍጥነት የደረሱ ሰብሎችን መሰብሰብ እንዳለባቸው አስታውቀው፣ ለዚህም ከወዲሁ ዝግጅት ተደርጎ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ምክትል የቢሮ ኃላፊው እንዳሉት፤ በክልሉ በዋናነት ደርሰው እየተሰበሰቡ ካሉት የምርት አይነቶች መካከልም ስንዴ፣ ጤፍ፣ ሩዝ፣ ባቄላ፣ አተርና አኩሪ አተር እንዲሁም ማሾ ይገኙበታል፤ እነዚህ የደረሱ ሰብሎች በሰው ኃይልና ቴክኖሎጂን በመጠቀም እየተሰበሰቡ ናቸው፡፡

ከሰብል አሰባሰብ ጋር ተያይዞ ብክነት ስለመኖሩ ያነሱት አቶ በሪሶ፤ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በራሱ ምርቱ በወቅቱ እንዳይሰባሰብ በማድረግ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡ ዝናቡ አርሶ አደሩ ምርቱን በጊዜ እንዳይሰበስብ ማስተጓጎሉ አንዱ ችግር መሆኑን ጠቅሰው፤ የመበስበስና ሌሎች ችግሮችን በማስከትልም ለምርት ብክነት አይነተኛ ምክንያቶች እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ይህ እንዳይፈጠር እዚህ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ሌላው ለምርት ብክነት ምክንያት የሚሆነው ምርቱ ታጭዶ በሰው ኃይል ተጓጉዞ ወደ አውድማ በሚወሰድበት ወቅት የሚፈጠረው ችግር ነው፤ በዚህ ወቅትም ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት በማመን ከፍተኛ ጥንቃቄ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ለዚህም ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መጠቀም ይገባል፡፡

ኮምባይነርና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ምርት ሲሰበሰብ ብዙ ብክነት አይፈጠርም ያሉት ምክትል የቢሮ ሃላፊው፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን መጠቀም ለተሻለ የምርት አሰባሰብ ሂደት ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በተቻለ አቅም በሰው ኃይል የመሰብሰቡን ሥራ ለማስቀረት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ነው ያመላከቱት፡፡

ይሁንና ከመሬት አቀማመጥ ጋር በተያያዘ ኮምባይነር ለመጠቀም አመቺ ባልሆነባቸው አካባቢዎች አሁንም ድረስ በሰው ኃይል እየተሰበሰበ ይገኛል፡፡ ምቹ በሆኑ አካባቢዎችም እንደ ኮምባይነር ያሉ ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ሙሉ ለሙሉ ተሟልተው ያልተዳረሱበት ሁኔታ መኖሩን የገለጹት አቶ በሪሶ፤ በተለይም ምቹ ባልሆኑ አካባቢዎች መንገዶችንና ድልድዮች እየተሰሩ ወደ ማሳዎቹ በመግባት አዝመራ ለመሰብሰብ ከፍተኛ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ልምዱንም ለአርሶ አደሩ ለማስተላለፉ ተጽዕኖ ሲፈጥር መቆየቱን አስታውቀዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ የምርት ብክነትን ለመከላከል ብሎም የተሳለጠ ሥራ ለመሥራት ቴክኖሎጂ ወሳኝ እንደመሆኑ ቴክኖሎጂውን ለማስፋት ክልሉ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ የተለያዩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ ሰፊ ሥራ እየተሠራ ነው፤ ተጽዕኖውን ለመቅረፍም ሰፊ ስትራቴጂ ተነድፎለት እየተሰራ ነው፡፡

አሁን ያለው የምርት አሰባሰብ ብዙ ክፍተት የለውም ባይባልም፣ የምርት አሰባሰቡ በጥሩ ሂደት ላይ ይገኛል ያሉት አቶ በሪሶ፣ እስካሁን ባለው የምርት አሰባሰብ ሂደትም 26 ሚሊዮን ኩንታል አካባቢ የሚደርስ የተለያዩ የሰብል ምርት መሰብሰቡን አስታውቀዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ በተያዘው በጀት ዓመት ከኦሮሚያ ክልል 265 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ይህን እቅድ ሊያሳካ የሚችል የቅድመ ዝግጅት ሥራ በመሥራት በምርት አሰባሰብ ወቅት ብክነት እንዳይከሰት እየተሰራ ነው፡፡ አሁን ያለው ሂደትም ዕቅዱን ሊያሳካ የሚችል ነው፡፡

በክልሉ በቀጣይ የምርት አሰባሰብ ሂደቱ የተሻለ እንዲሆን ባለሙያዎችና የክልሉ አመራሮች ወደ ታች ወርደው እየሰሩ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ በሪሶ፤ ከሚሰሩ ሥራዎች መካከልም የክትትልና ድጋፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች የሚጠቀሱ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ይህም የምርት ብክነትን ለመቀነስና ወቅቱን አዝመራ ወቅቱን ያልተጠበቀ ዝናብ እንዳያበላሸው መሰብሰብ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ያልደረሱ ሰብሎችም እንዲሁ ዝናብ መጣ ተብሎ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ገልጸው፣ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ አጠቃላይ በምርት አሰባሰብ ሂደት ውስጥ በክልሉ ጥሩ እንቅስቃሴ እንዳለ ነው የተናገሩት፡፡

ምክትል የቢሮ ኃላፊው እንዳብራሩት፤ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የአየር ትንበያው የሚያመላክተው ዝናብ እንዳለ ነው፤ በተለይም በምዕራብ አካባቢ ዝናብ አለ፤ በመሀል አገር አካባቢ ደግሞ አሁን ያለው የአየር ሁኔታ ምቹና ንፋስና ጸሐይ ያለበት በመሆኑ ወቅቱ ምርቱን ለመሰብሰብ ምቹ ጊዜ ነው፡፡

በደቡብ ኦሮሚያ ጉጂ አካባቢና ባሌም ጭምር በተመሳሳይ መልኩ የዝናብ ስርጭት ስለመኖሩ የጠቀሱት አቶ በሪሶ፤ በእነዚህ አካባቢዎች ምርት የደረሰ ባለመሆኑ ብዙ ጉዳት አያደርስም ብለዋል። ምርት በደረሰባቸው የኦሮሚያ አካባቢዎች አሁን ያለው የአየር ሁኔታ ጥሩ ነው የሚባል ግምገማ እንዳላቸውና አዝመራውም በጥሩ ሁኔታ እየተሰበሰበ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

አቶ በሪሶ እንዳስታወቁት፤ በምርት አሰባሰብ ሂደት ውስጥ ካጋጠሙ ችግሮች መካከል የመጀመሪያው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሲሆን፤ እሱም የተፈጥሮ ጉዳይ ነው፤ ከተፈጥሮ ጋር ተላምዶ የዝናቡን መቆም ተከትሎ ሰብሉ እንዳይበላሽ በተለያየ መንገድ ምርቱን መሰብሰብና ከብክነት መከላከል ዋናውና በስትራቴጂ የተያዘ ሥራ ነው፡፡

ለምርት ስብሰባው ኮምባይነሮችን በስፋት መጠቀም አንዱ መፍትሄ መሆኑን ጠቅሰው፣ በሰው ኃይል የታጨዱ ሰብሎችንም ትሬሸር መውቂያ ማሽኖችን በሰፊው በመጠቀም መውቃት አንድ የመፍትሔ አቅጣጫ ተደርጎ እየተሰራበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ሌላው የአየር ትንበያዎችን በመከታተል በሰው ኃይልና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ የደረሱ ሰብሎችን ለመሰብሰብ ከብሔራዊ ሜትሪዎሊጂ ተቋም ጋር በጋራ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ምክትል የቢሮ ኃላፊው እንዳስታወቁት፤ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የደረሱ ሰብሎችን እንዳያበላሽ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ግብርና ሚኒስቴር የሚችለውን ሁሉ በማድረግ ከክልሎች ጋር በጋራ እየሰራ ይገኛል፡፡ ከግብርና ሚኒስቴር በተጨማሪም ሥራውን በባለቤትነት በመያዝ የክልሉ ግብርና ቢሮም ከክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ በመጠየቅ እየሠራ ነው፡፡ በተያያዘም ሁሉም የግብርና ቤተሰቦች በዚሁ ሥራ ላይ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ምርቱ እንዲሰብሰብ እና ከብክነት እንዲድንም ጭምር ለመከላከል ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

በኦሮሚያ ክልል ባለው ተጨባጭ ሁኔታ አሁን ያለው የምርት አሰባሰብ በጣም ጥሩ የሚባል መሆኑን ጠቅሰው፣ በተለይም አርሶ አደሩ በከፍተኛ መነቃቃት ቤተሰቡን፣ ጎረቤቱንና አካባቢውን በማሳተፍ የተለያየ የምርት አሰባሰብ ዘዴዎችንን በመጠቀም በትኩረት እየሰራ መሆኑንና ይህም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው አመላክተዋል፡፡

በመጨረሻም አርሶ አደሩን ጨምሮ በየደረጃው ያለው አመራርና ባለሙያ አሁን ያለውን የአየር ሁኔታ በመከታተል ለምርት አሰባሰብ ሥራ ትኩረት መስጠትና ጊዜውን በአግባቡ በመጠቀም የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸው፤ ምርቱ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ ለመሰብሰብና ከብክነት ለመታደግ ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ህዳር 3/2016

Recommended For You