ለምን ተነጋግረንና ተግባብተን ችግሮቻችንን መፍታት ተሳነን?

ሀገር ማለት ምን ማለት ነው? ይሄ በጥበብ ለጸናን ለእኛ ቀላል ጥያቄ ነው፡፡ ከዓለም በፊት ሀገር ለሰራን፣ ከስልጣኔ በፊት ዘመነኝነትን ላበጀን ለእኛ ምንም ነው፡፡ ከራስ አልፎ ሌሎችን ባለሀገርና ባለታሪክ ማድረግ፣ ከራስ አልፎ ሌሎችን የሰላምና የነጻነት ባለቤት ማድረግ፣ ከራስ አልፎ ለሌሎች መትረፍ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን አዲስ ነገራችን አይደለም፡፡ አሁን አሁን ግን አይደለም ለሌላው ለራሳችን መሆን እያቃተን መጥቷል፡፡ ሰላም ናፋቂዎች ሆነናል፡፡ ተነጋግሮ መግባባት አቅቶን ብዙ ዋጋዎችን ከፍለናል፡፡ ለምን? በዚህ የነጻ አምድ ስር ይሄን ጥያቄ በመመለስ ለጋራ ሰላማችን የጋራ መፍትሄዎችን እናዋጣለን፡፡

ሰው ሁሉ በአንድ የጸና እውነት ስር የቆመ ነው..ሀገር በሚሉት እውነት ስር፡፡ ማናችንም ስለሀገር የገባንን ያክል ምንም ነገር ገብቶን አያውቅም፡፡ በገባን ልክ ግን እየኖርን አይደለም፡፡ በገባን ልክ ግን ሀገራችንን እያገለገልን አይደለም፡፡ ከገባን ይልቅ ባልገባን እየኖርን ትውልዱን ያለሀጢዐቱ ኩነኔኛ እያደረግነው ነው፡፡ የእውቀት አፍ ስለሌላው ይማልዳል እንጂ ማንንም ባለዕዳ አያደርግም። እኛ ግን በገባን እና በተረዳነው ሌሎችን ዋጋ እያስከፈልን ነው፡፡

እውቀት መረዳት ሳይሆን የተረዳነውን መኖር ነው፡፡ እንደ ሀገር፣ እንደ ፖለቲከኛ፣ እንደዜጋ የጠፋን ሀገር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ሳይሆን የገባንን መኖር ነው፡፡ የገባን እውነት ካላኖረንና ካልቀየረን ማወቃችን ብቻውን ትርጉም አይኖረውም፡፡ ወደማንም የምንቀስረው ጣት የለንም፡፡ ታሪኮቻችንን ያወየብነውና አንድነታችንን ያላላነው ራሳችን ነን፡፡ ከመፍትሄ ይልቅ ራስን ነጻ በማውጣት ትግል ውስጥ ተጠምደን ከድጡ ወደማጡ እየተንደረደርን እንገኛለን፡፡

ዛሬም ጣት ጠቋሚዎች ነን፡፡ ጣት መጠቋ ቆምና መወቃቀስ እንደማይበጀን እያወቅን እንኳን የምክክር ወንበር ላይ አልተቀመጥንም። ወንበሮቻችን ባዷቸውን ናቸው፡፡ አዳራሾቻችን ኦናቸውን ናቸው፡፡ በቃላት ሰልጥነን እዛና እዚህ ቃላት እየተወራወርን ለነገ ቁርሾ ሌላ የማይረባ ታሪክ እያስቀመጥን ነው፡፡ ትውልዱ እንዳይጠይቅና የተነገረውን ብቻ እንዲሰማ ተፈርዶበት ለክፉዎች መጠቀሚያ ሆኖ ይገኛል፡፡ በንቃት እንጂ በሙቀት የምትገነባ ሀገር የለችም፡፡ በምክክር ወንበር ፊት እውቀትና ምክንያታዊነት ነጻ ካላወጡን በስተቀር እዛና እዚህ ሆነን የምንለዋወጣቸው ቃላቶች ከዝቅታ አይታደጉንም፡፡

ቃላት መራቂና አስታራቂ ካልሆኑ ሞትን ሰባኪዎች ናቸው፡፡ አንደበቶቻችን ካልተገሩና ጨዋነትን ካልተላበሱ ከሰይፍ የሰሉ መከራዎቻችን የሚሆኑበት ጊዜ ይመጣል፡፡ ታላቁ መጽሀፍ ቅዱስ በምሳሌ መልዕክቱ ላይ ስለቃላት ሲናገር ‹ሰው ከአፉ ፍሬ መልካምን ይበላል› ይለናል፡፡ በዛው በምሳሌ መልዕክቱ ላይ ‹ሞትና ሕይወት በምላስ እጅ ውስጥ ናቸው› ሲል ይነግረናል፡፡ ቃላት ላልተጠቀመባቸው የሰላም መንገዶች ናቸው፡፡ ላልተጠቀመባቸው ደግሞ የጥላቻና የመለያየት ፍኖት መሆን ይችላሉ፡፡

እንደ ሀገር የዛሬ መከራዎቻችን የትላንት አንደበቶች የወለዷቸው ስለመሆናቸው ለሁላችንም ግልጽ ነው፡፡ ዛሬ ላይ መፍትሄ ያጣንላቸው ትላንት ላይ ሲነገሩ በይሁንታ የሰማናቸውና ጆሮ የሰጠናቸው የጥላቻ ንግግሮች እንደሆኑ እናውቃለን፡፡ በዓለም ታሪክ በሰው ልጆች መካከል የተፈጠሩ ጦርነቶችና የእርስ በርስ ግጭቶች መነሻቸው ቃላት ነው፡፡ በናዚው ሂትለር ከሚመራው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት እስከ ሩዋንዳ የእርስ በርስ ግጭት ድረስ የጥላቻ ንግግሮች የከፋ ሚና ተጫውተዋል፡፡

በእኛው ሀገር አብዛኞቹ ማሕበራዊ ነውጦች በጥላቻ ንግግሮች የጀመሩ ናቸው፡፡ ታሪክ አስታውሰንና አዛብተን የሰማነውና የተናገርነው ትርክት እንዳለ ሆኖ መለያየትን ከመፍጠር እንዲሁም ደግሞ ዋጋ በማስከፈል አኳያ የጥላቻ ንግግሮች የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ መች ገብቶን መች መልካም ነገር እንደምናወራ ባይገባኝም አሁንም ድረስ ከአንድነት ይልቅ ለጥላቻ የሰላ አንደበት ያለን ነን፡፡ ማሕበራዊ ሚዲያዎቻችን ሳይቀሩ የጥላቻ ንግግሮችን በመለጠፍ የሚስተካከላቸው የለም፡፡ በዚህ እርቅና ምክክር፣ ፍቅርና አንድነት በሚያስፈልገን ክፉ ጊዜ ላይ ለፍቅር የሚሆን ጊዜና እውቀት አለማግኘታችን መጪውን ጊዜ እንድንፈራው የሚያደርግ ነው፡፡

ጊዜው የፍጥነት ነው፡፡ የተናገርነው በጎም ይሁን መጥፎ በደቂቃ ውስጥ ለብዙ ሰው የመድረስ እድሉ የሰፋ ነው፡፡ ማሕበራዊ ገጾቻችንን ለበጎ ነገር ብንጠቀማቸው አሁን ላለው ሀገራዊ ምክክር እንደጉልበት በመሆን እገዛ ማድረግ እንችላለን። የሚከተሉን ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ስለፍቅርና ስለአብሮነት ብንጽፍና ብንመካከር በአንድ ጊዜ ሀምሳና ስልሳ ሺ ለሆኑ ማሕበራዊ ሚዲያ ተከታዮቻችን በጎ ነገርን ማስተማር አንችላለን። ሀገር ከእኛ የምትጀምር ናት፡፡ ሀገር ማለት ምን ማለት ነው ብዬ ስጠይቅ መልሱ ያለው በእኔና በእናንተ ሀሳብ፣ ምኞት፣ ድርጊትና ተሳትፎ ውስጥ ነው፡፡

ሀገራችንን እኛው አምጠን ካልወለድናት በስተቀር በማንም ዘንድ የለችም፡፡ እድሎቻችን እጃችን ውስጥ ናቸው፡፡ አንደበቶቻችንን ገርተን፣ ልቦቻችንን አስታርቀን የጥንቱን ክብራችንን እስካልመለስን ድረስ ከዝቅታ የሚታደገን ኃይል አይኖርም፡፡ ምዕራባውያን ስንሞት ከመቁጠር እና ስንራብ ስንዴ ከመስጠት ያለፈ በጎነት የላቸውም፡፡ ጎረቤቶቻችን በእኛ ድካምና ዝለት ውስጥ ገብተው ሌላ ጉስቁልናን ነው የሚፈጥሩብን፡፡ ብቻችንን እንድንጠነክር በአንድነት መቆም አማራጭ የሌለው ግዴታችን ይሆናል፡፡

እስኪ ለአፍታ ኢትዮጵያውያን እንቃኛት፣ እስኪ ለአፍታ ኢትዮጵያዊነትን እናስበው በብዙሀነት ውስጥ የጸና የብዙሀነት ውበት ነው አይደል? እኔ የአንተ የሌለው የጋራ ስምና ታሪክ ነው አይደል? በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ቅርሶች የታደለ የውበትና የማማር ምድር ነው አይደል? ስርዓትና ጨዋነት ያበቀለው የግብረገብነት ደሴት ነው አይደል? ታዲያ ለምን እንደተፈጥሮአችን መኖር አቃተን? ታዲያ ለምን ተነጋግረንና ተግባብተን ችግሮቻችንን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት ተሳነን?

የነዚህ ሁሉ ጥያቄ መልስ አንድ ነው እርሱም ራስ ወዳድነት ነው፡፡ ራስ ወዳድነት ለራስ ብቻ መኖር ነው፡፡ በጊዜአዊ ጥቅም የነገውን ትውልድ ዋጋ የሚያስከፍል፣ በሀገርና ሕዝብ ላይ መጨከን ነው፡፡ አዎ ተነጋሮ መግባባት፣ ተግባብቶ አንድ ሆኖ መቆም ያቃተን ለዚህ ነው፡፡ በትንሽ ልዩነቶች ብዙ ዋጋ እየከፈልን ያለነው፣ በጥቃቅን ነውሮች የከፋ ችግር እየደፈረሰብን ያለው ከእኛነት ማእድ ርቀን የእኔነትን ፖለቲካ ማራመድ ስለጀመርን ነው፡፡

ከእኛ በስተቀር ሁሉም ነገር እንደነበረ ነው። ታሪኮቻችን፣ ባሕሎቻችን ወግና ስርዓቶቻችን እንኳን አባቶቻችን እንዳስቀመጧቸው በክብር ስፍራቸው ላይ ናቸው፡፡ የተቀየርነው እኛ ነን፡፡ በእኛ መቀየር ውስጥ ግን ብዙ መልካም እሴቶቻችን ተቀይረዋል። አሁን ላይ እየከፈልነው ያለው የመለያየትና የመከፋፋል ዋጋ በማንም ሳይሆን በፖለቲከኞቻችን ራስወዳድነት የመጣ ነው፡፡ በየትኛውም የገዢና የተገዢ መደብ ውስጥ ፖለቲካ ሁለት አይነት መልክ አለው፡፡ የመጀመሪያው ‹ፖለቲካ ሕዝብን ሲመስል› ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ‹ሕዝብ ፖለቲካን ሲመስል ነው፡፡ በእኚህ ሁለት የፖለቲካ አስተሳሰቦች ስር ሁለት የተለያየ ሀገርና ሕዝብ አለ፡፡

ፖለቲካ ሕዝብን ሲመስል እንደራስ ወዳድነትና አክራሪ ሀገር አጥፊ የጥቂት ቡድኖች አስተሳሰቦች ቦታ አይኖራቸውም፡፡ ጥላቻና ጎጠኝነት ባይተዋር ሆነው ወደዳር ይገፋሉ፡፡ ፖለቲካውም ሆነ ፖለቲከኞቹ በሕዝብ ባሕልና እሴት፣ ወግና ስርዓት የተገሩ ስለሚሆኑ አመራራቸው ሕዝብ ተኮር ይሆናል፡፡ ማንንም እንዲበድሉ፣ በማንም ላይ ክፉ እንዲሆኑ የሚያስችል የሞራል ልዕልና አይኖራቸውም፡፡ ሕዝባቸውን እያሰቡ ወደስልጣን ወጥተው ሕዝባቸውን እያሰቡ ከስልጣን ይወርዳሉ። እንዲህ አይነቱ የመሪና ተመሪ የፖለቲካ ምሕዳር መነሻውን ሀገር አድርጎ ወደትውልድ የሚዘልቅ የማሕበረሰብ መልክ ነው፡፡ ችግሮች ቢፈጠሩ እንኳን በመነጋገር ይፈታሉ እንጂ አድገውና መንድገው የነገውን ትውልድ ዋጋ እንዲያስከፍሉ አይተውም፡፡ ጦርነት ጠል የሆነው ይህ መልከ ሕዝብ ፖለቲካ ወሳኝ ስርዓቶቹን በምክክር የገነባ ፖለቲካ ነው፡፡ ቅድሚያ ለራስ በሚል የፖለቲካ ንቃት ሀገር ሕዝብና ትውልድ የሚቀድሙበት የአገልጋይነት ጽንሰ ሀሳብ ነው፡፡ በእንዲህ አይነቱ የፖለቲካ ጥላ ስር አንድነትና ፍቅር፣ አብሮነትና ሕብረት ካልሆኑ ማንም የሚጎዳበት፣ ማንም የሚበደልበት የበላይና የበታች ስርዓት የማይታሰብ ነው፡፡

ሕዝብ ፖለቲካን ሲመስል ግን ከላይ የዘረዘርናቸው መልካም መንፈሶች አይኖሩም፡፡ በዚህ ፖለቲካዊ አረዳድ ውስጥ ፍቅርና አብሮነት ቦታ የላቸውም፡፡ በኃይል እና በእልኸኝነት በተደራጁ የፖለቲካ ጽንፈኞች በይዋጣልን ሀገርና ሕዝብን ለጉስቁልና የምንዳርግ እንሆናለን፡፡ እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ትልቁ ጉዳይ ፍቅር የቀደመበት አንድነት የለጠቀበት የአብሮነት ፖለቲካ መፍጠሩ ላይ ነው፡፡ ሕዝብ ፖለቲካውን እንዲመስል ሳይሆን ፖለቲካው ሕዝብን መስሎ በስርዓትና በጨዋነት አገልጋይነትን ባስቀደመ መልኩ ሁለገብ እንዲሆን መታረቁ ላይ ነው፡፡

በአእምሯችን ውስጥ ኢትዮጵያ ትቅደም። በልባችን ውስጥ፣ በሀሳባችን ውስጥ ሕዝብ ይቅደም፡፡ በፖለቲካችን ውስጥ፣ በስርዐታችን ላይ ትውልድ ይቅደም፡፡ በየትኛውም የስርዓት አውድ ውስጥ መነሻችን ሕዝብ ከሆነ ሕዝብ የሚጎዱ ድርጊቶችን አናደርግም፡፡ በደልን የሚጸየፍ፣ ጥላቻን የሚነቅፍ፣ ዘረኝነትንና አድሎአዊነትን የሚሞግት ነው የምንሆነው፡፡ ስለሀገር ስንል ራስወዳድነት የዋጀውን ጊዜአዊ ጥቅማችንን ትተን ስለብዙሀኑ ብንለፋ በሀገራዊ ምክክሩም ሆነ በሌሎች የአንድነት መድረኮች ፊት መድመቅ እንችል ነበር፡፡

መሰረቶቻችን ብዙሀነትን ከሕብረብሄራዊነት ጋር ያነጹ የመተሳሰብ ሀውልቶች ነበሩ። መነሻዎቻችን ከብዙ ሀሳብ፣ በብዙ ልቦች ለብዙ ነፍሶች ነበር። ፍቅር ያልገባበት ምንም አልነበረንም። ዛሬ ፍቅር የገባበት ምንም የለንም። መነሻዎቻችን ካለምልክት ብቻቸውን ቆመዋል። መሰረቶቻችን በጥላቻና በዘረኝነት ተቀይረው በእኔነት ወይበዋል፡፡ እንዴት? ለምን? ከስርዓት ወጣን፡፡ ከኢትዮጵያዊነት ሸሸን። በራስወዳድነት ጎለመስን፡፡ በማንአለብኝነት በረታን። መፍትሄው ምንድነው? መመካከር፡፡ ተማካክሮ መግባባት፡፡ ተግባብቶ አብሮ መቆም ነው፡፡

ስኬት በብልሀት በኩል የሚገኝ ነው። ብልሀት ደግሞ አብሮ መኖርንና መተቃቀፍን መርህ ያደረገ ስርዓት ነው፡፡ ከአንድ ብርቱ ሁለት መዳኒቱ እንደሚባለው ለችግሮቻችን አብሮ መቆም ነው መፍትሄው፡፡ ተከፋፍለንና ተለያይተን የምንጨምረው ችግር ከሌለ በስተቀር የምንቀርፈው የለም፡፡ ችግሮቻችን የቱንም ያክል ይግዘፉ ለመነጋገር መቀመጥ ከቻልን ዋጋ አያስከፍሉንም። መልካም እሴቶቻችን አብሮነትን ከመመለስ አኳያ የማይናቅ ሚና አላቸው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የደመቀባቸው እሴቶቻችን በሀገራዊ ምክክሩ ላይ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ መንገድ ልንከፍትላቸው ይገባል፡፡

እስኪ ዙሪያችንን እንቃኘው..ምን ይታየናል? ሰው፣ ጋራ ሸንተረር፣ አፈርና አራዊት፣ አእዋፍትና ተፈጥሮ ሀገር ማለት ያ ነው፡፡ የምናየው፣ የምንሰማው፣ የምንረዳው እርሱ ነው ሀገር፡፡ ከእኔ ወደሌላው፣ ከሌላው ወደእኔ የሚተላለፈው የባሕል፣ የስርዓት፣ የእምነትና የሀሳብ ልውውጥ ያ ነው ሀገር፡፡ እናም በተዋጣ ሀሳብ አገራችንን ለማቅናት እንንሳ፡፡

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ህዳር 3/2016

Recommended For You