ሙስናን በቃላት ከመጠየፍ ባለፈ

አንዳንድ ከባድ ጉዳዮች ትኩረት እና ዋጋ እንዲሰጣቸው ሲባል የአንድ ሰሞን አጀንዳ ይሆናሉ፡፡ ከዚህም ባለፈ ታስበው በሚውሉበት ወይም ግንዛቤ ለማስጨበጥ በሚከበሩበት ቀናትም በተመሳሳይ መልኩ ቀናቱን አስመልክቶ ኅብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲያገኝ የሚያስችሉ ሥራዎች ይከናወናሉ፡፡

ከነዚህም ባለፈ ለዘለቄታው የሕብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳዳግ ተብለው የሚሰሩ፤ አጀንዳ ሆነው የሚቆዩ ጉዳዮችም አሉ። ከነዚህም ውስጥ የሙስና ጉዳይ አንዱና ዋንኛው ነው። በተለይም ችግሩ በብዙ መልኩ እየተፈታተናቸው ለሚገኙ ሀገራት ሙስና አጀንዳ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም አጀንዳ ሆኖ የመቆየቱ ጉዳይ ብዙም ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፡፡

በ2002 ዓ.ም የተጀመረው የመንግስት ባለስልጠናት ሀብት እና ንብረት ምዝገባ ሙስናን ለመታገል እንደ አንድ አማራጭ መታየቱ ይታወሳል፡፡ የሀብት ማሳወቂያ እና ማስመዝገቢያ አዋጅ 2013 በድጋሚ እንዲሻሻል ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ እንዲህ እና መሰል እርምጃዎች ይወሰኑ እንጂ ሙስና ዛሬም የሀገር ስጋት መሆኑን ቀጥሏል፡፡

ትራንስፓይረሲ ኢንተርናሽናል አሁንም ሙስና የዓለማችን ዋነኝ ስጋት መሆኑን አሳውቋል፤ ችግሩን ለመፍታት የሀገር መሪዎች ከሕዝቡ ጋር በመሆን በቁርጠኝነት ካልተዋጉት ወደፊትም ስጋት ሆኖ እንደሚቀጥል አመልክቷል፡፡

ይህ ችግር እንደ ሀገር እኛንም በብዙ መልኩ እየተፈታተነን ስለመሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ሀገሪቱ ከድህነት አረንቋ ለመውጣት የተደረገውን ጥረት እየተፈታተኑ ካሉ ሰው ሰራሽ ችግሮች በዋነኛነት የሚጠቀስ ነው፡፡ የሀገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችንም የበለጠ እንዲወሳሰቡ አቅምም እየሆነ ነው።

በተለያዩ መንፈሳዊና ማሕበራዊ አስተምሮዎች ሰው ያልዘራውን እንዲያጭድ አልተፈቀደለትም፡፡ ሀብት ማፍራት የሚችለው በድካሙ፣ በላቡ እና በልፋቱ ነው። ከዚህ ውጪ በየትኛውም መልኩ በአቋራጭ ሀብት ለማፍራት የሚደረጉ ጥረቶች የሚወገዙ ናቸው፡፡

ከዚህ ቀደም ‹‹የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ›› መቋቋሙን አስመልክተው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር ‹‹ሙስና ሀገርን የሚበላ ነቀዝ ነው፡፡ ዋልጌ ባለሥልጣናት፣ በፍቅረ ነዋይ የታወሩ ደላሎች እና ባለሃብቶች አንድ ላይ ሲገጥሙ፤ ከነዚህ የሌብነት ፊታውራሪዎች ጀርባ ብዛት ያላቸው ዜጎች መሰለፍ ሲጀምሩ ሙስና የተባለው ነቀዝ ሀገርን እንደ ወረርሽኝ ያጠቃታል፡፡›› ነበር ያሉት፡፡

በርግጥ ሙሰኞቹ የሌላ ሠው ሕይወት ጉዳያቸው አይደለም፡፡ በእነርሱ ወንጀል ሕብረተሰቡ በጤና እና በማሕበራዊ ጉዳይ ስለሚገጥመው ችግር ምንም አያስጨን ቃቸውም፡፡ እነርሱ በገንዘብ፣ በሀብት እና በቁሳቁስ እንዲካብቱ የብዙዎችን ሕይወት አደጋ ላይ ይጥላሉ፡፡

‹‹እጅ መንሻ››፣ ‹‹ለምን በእጅ አትሄድበትም? ‹‹የደንቡን እኮ ፈልጎ (ጋ) ነው››፣ ‹‹ለሻይ ብትሰጠው››፤ ‹‹ብር ካለ፤ በሰማይ መንገድ አለ›› ተብለው እንደ ቀላል የሚነገሩት ንግግሮች ነገ ላይ ትልቅ ኪሳራ እንደሚያመጡ ወይም ዋጋ እንደሚያስከፍሉ አያጠራጥርም።

ብዙ ሀቀኛ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የግል ድርጅቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት መኖራቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ቀጣዩ ትውልድ እንዲህ አይነቱን አሠራር ከመከተል እንዲቆጠብ ትምህርት ቤቶች፣ ቤተሰብ እና የሃይማኖት ተቋማት ማስተማር ይኖርባቸዋል። እንዲሁም የመንግስት ተሿሚዎች ከድርጊቱ ነጻ መሆናቸውን በተጨባጭ በማሳየት ለብዙዎች አርአያ መሆን ይገባቸዋል፡፡

አሁን ላይ በመንግስት በኩል ኮሚቴ በማቋቋም፣ ሕብረተሰቡ ጥቆማ የሚሰጥበትን መንገድ በማስፋት፣ ከዚህ ሻገር ብሎም በሙስና እና ብልሹ አሰራር የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ማሳወቅ መጀመሩ ይቀጥል የሚያሰኝ ሥራ ነው፡፡ በቀጣይ ለብዙዎች ትምህርት ሊሆን እንደሚችል በመገንዘብ መሰል መረጃዎችን መስጠት ሕብረተሰቡን ለማስተማር ከፍተኛ አቅም ይፈጥራል፡፡

በተጨማሪም በተቋማት ከሙስና እና ከብልሹ አሰራር ጋር በተያያዘ በነጻነት ጥቆማ መስጠት የሚቻልባቸው ራሳቸውን የቻሉ ክፍሎች (ገለልተኛ የሆኑ) እና ሌሎች አማራጮችን በመፍጠር ችግሮችን ለመቀነስ መንቀሳቀስ ይገባል፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ ዘመኑን ሊዋጁ በሚችሉ አቅላይ እና ቴክኖሎጂ ላይ መሠረት ያደረጉ ሥርዓቶችን በመዘርጋት መሥራት ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን ወደ ጥቂት ግለሰቦች ኪስ የሚገባ ገንዘብ እና ያለ አግባብ የሚባክን የሀገር ሀብትን መታደግ ይቻላል፡፡

አሁን ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንዲሉ አበው፤ የጸጥታ ችግር ላለባት ሀገር፤ ከኑሮ ውድነቱ ጋር ግብግብ ለፈጠረው ዜጋ፤ አገልግሎት ለማግኘት ወደ ተቋማት ሲያመራ ‹የደንቡን› ካላደረስክ ምንም እታገኝም ብሎ ማመላስ በመንግስት ላይ ያለውን አመኔታ የሚያስቀር መሆኑን አጽንኦት ሰጥቶ ማየቱ ተገቢነት አለው፡፡

እንዲህ ያለውን ሠራተኛ (ሙሰኛ) ለመቀጣጫነት (ለማስተማሪያነት) አደባባይ በማውጣት ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ በማድረግ ሂደት ውስጥ የፍትህ አካላት ከፍ ባለ የኃላፊነት መንፈስ መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ሙስናን እና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል የአንድ ሰሞን ሥራ ብቻ ወይም ዘመቻ አይደለም፡፡ ከዚህ አንጻር የተቋቋመው ኮሚቴ እየሠራ ስላለው ሥራ ወቅታዊ ሪፖርቶችን ለሕብረተሰቡ ሊያቀርብ ይገባል። በቀጣይም ተከታታይ ጥናቶችን በማድረግ ሙስና ተንሰራፍቶባቸዋል ተብለው የተለዩ ዘርፎች ላይ እና ዋና ዋና ተዋናዮችን በሕግ ጥላ ሥር እንዲውሉ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

ከዚህም ባለፈ ሙስናን ለመከላከል የሚወጡ ሕጎች እና ፖሊሲዎችን በመፈተሽ ለሙስና በር ከፋች የሆኑትን መለየት እና ማሻሻል ያስፈልጋል፡፡ መላው ሕዝብም በሙስና ሳቢያ የሚደርሰው ችግር ሁሉንም የሚነካ መሆኑን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት፤ ጥቆማ በመስጠት ችግሩን አምርሮ መዋጋት እና መታገል ይኖርበታል፡፡

መንግስትም ከዚህ በፊት እንስዳታወቀው፣ የቅርብ ሰዎቹ በሙስና እና ብልሹ አሰራር እንዳይዘፈቁ መከላከል ብሎም መጠበቅ ይገባል፡፡ በሙስና ላይ የተሰማሩ ካሉ፤ እነርሱን በማጋለጥ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል። የመንግስት ባለስልጣናት ሙስናን በቃላት ከመጠየፍ ባለፈ በተግባር ተፈትኖ ያለፈውን አርአያነታቸውን ለሌሎች እንዲጋባ ማስተማር እንዲሁም መንገዱን ማሳየት ይኖርባቸዋል፡፡

በምስጋና ፍቅሩ

አዲስ ዘመን ህዳር 3/2016

Recommended For You