ለብሔራዊ ምክክሩ ስኬታማነት

የብዙ ባሕላዊና መንፈሳዊ እሴት ባለቤት የሆኑ ኢትዮጵያውያን ለገጠማቸው ችግር መላ መዘየድ ያውቁበታል፡፡ መከራ የቱንም ያህል ቢፈትናቸው ‹‹ይህም ያልፋል›› ‹‹ይሁን ተመስገን›› እያሉ መታገስን ብሎም መታዘብን ይመርጣሉ እንጂ ተስፋ አይቆርጡም። በርግጥ ሰው ያለ ተስፋ አንድ ቀን ማደር የማይቻለው ደካማ ፍጡር ነውና ተስፋ ማድረግን የግድ ይለዋል፡፡ ይህም ሆኖ ግን በሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ተስፋን የሚያጨልሙና ነገን በጭላንጭል ለማየት የሚፈትኑ ችግሮች መግጠማቸው አይቀሬ ነው፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያንም ብዙ ተስፋ አስቆራጭና እልህ አስጨራሽ የሆኑ በርካታ ችግሮች ገጥመውን ‹‹ይሁን ተመስገን›› በማለት አልፈናቸዋል፡፡ ዛሬም ቢሆን እንደ ሀገር ያልተሻገርናቸው በርካታ ችግሮች አለ፡፡ እነዚህ ችግሮች እርስ በእርስ እንዳንተማመንና እንድንፈራራ በማድረግ አንዳችን ሌላችንን በጥርጣሬ እንድናይ እያስገደዱን ነው፡፡ በአዳዲስ የተዛቡ ትርክቶችም እንዲሁ የእኛ የሆነውን ዛሬን ጨምሮ የልጆቻችንን ነገ የሚያበላሹ ክስተቶችን እያስተዋልን ነው፡፡

ያለንበትም ወቅት ከሁሉም በላይ በመሐከላችን ለተፈጠሩ ችግሮች መፍትሔ በማፈላለግ በውስጣችን ያለውን ቁርሾ ማስወገድ ይጠበቅብናል፡፡ ለዚህም ኢትዮጵያዊ በሆነ ወግና ባሕል ሰከን ብሎ መነጋገርና መመካከር ቀዳሚውና አማራጭ የሌለው ዘላቂ መፍትሔ ነው፡፡

‹‹ተማክረው ምን ያሉት ምን አይልም›› እንዲሉ አበው፤ ሀገሪቷ አሁን ከገባችበት ምስቅልቅሎሽ መውጣት የምትችለው ሕዝቡ በአንድነት ሆኖ መምከርና መመካከር፤ መወያየትና መደማመጥ፤ ሲችል እንደሆነ ይታመናል፡፡ ብሔራዊ ምክክር ወቅታዊ አጀንዳችን የሆነውም ለዚሁ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ካሳለፈችውና ካለችበት ፖለቲካዊ ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ብሔራዊ ምክክሩ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን አንገብጋቢ እንደሆነ በብዙዎች የሚታመን ጉዳይ ነው፡፡ በሀገራችን ለረጅም ጊዜ የቁርሾ ምንጭ ሆነው የቆዩ እንደ ሀገር ልንስማማባቸው የሚገቡ፤ በልዩነት የቆምንባቸው፤ ጫፍና ጫፍ ሆነን የምንቆስልባቸው ብዙ ጠርዞች አሉ፡፡

ችግሮቻችን የቱንም ያህል ቢሰፉ መፍትሔው መነጋገር፣ መመካከርና ኢትዮጵያዊ በሆነው ባሕልና ወግ ‹‹አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ›› መባባልና መረዳዳት ነው፡፡ ለዚህም በብዙዎች ዘንድ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ብሔራዊ ምክክሩ ዋንኛ አጋዥ አቅም ሊሆነን የሚችል ነው፡፡ ተስፋን ያነገበው ብሔራዊ ምክክሩ ቋጠሮዎችን ፈትቶ ቁርሾን ማሻር እንዲችል ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ ብዙ የቤት ሥራ አለ፡፡

እንደ ሀገር የተጋረጠብንን ሁለንተናዊ አደጋ ለመሻገር ብቸኛው አማራጫችን ሀገራዊ ምክክርና ንግግር ይሁን ካልን ደግሞ ትናንትን ለትዝታ ትተን ነገን ተስፋ ማድረግ የግድ ይለናል፡፡ ከዚህም በላይ ኢትዮጵያዊ በሆነ ጨዋነት መነጋገር፣ መመካከርና መደማመጥን ልምድ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡

በተለይም ለዘላቂ ሀገራዊ ሰላማችን መክፈል የሚገባንን የመጨረሻውን የሕይወት መስዋዕትነት ከመክፈል ይልቅ ወደ ቀደመው ማንነታችን ተመልሰን እንደ ባሕልና ወጋችን ችግሮቻችንን መፍታት ቅድሚያ የምንሰጠውና አማራጭ አልባ ምርጫ ሊሆን እንደሚገባ በአግባቡ መረዳትና ለተግባራዊነቱ ራስን ማዘጋጀት ተገቢ ነው፡፡

ለዚህም ብዙ ዋጋ የማይጠይቀን፣ ነገር ግን በብዙ እጥፍ የምናተርፍበት ኢትዮጵያዊ ባህልና ወግ አለን። የመልካም እሴቶች ባለቤትነታችን ለብሔራዊ ምክክሩ ስኬት ትልቅ አቅም ሊሆን የሚገባ ብሔራዊ ሀብታችን ነው፡፡ የቀደመው ኢትዮጵያዊ ማንነታችን፣ ወግና ሥርዓታችን፣ ባሕልና ዕምነታችን ለአሁነኛ ችግሮቻችን መፍቻ ትልልቆቹ ጉልበቶቻችን ናቸው ፡፡

ዛሬ እነዚህ ሁሉ ሀገራዊ ፀጋዎቻችን የት ገቡ፤ ምን ዋጣቸው፤ ብለን ልንጠይቅና ልንመረምር ይገባል። ለመጠየቅም ሆነ ለመመርመር ታዲያ ኢትዮጵያዊ በሆነ ጨዋነት ሰከን ብሎ እንደ አንድ ሕዝብ በጋራ መነጋገር ይገባል፡፡ ንግግርና ምክክራችንም ስለ ትናንቱ ሳይሆን ስለ ነገ ተስፋችን ቢሆን እርምጃችን ወደፊት ይሆናል፡፡

ፍጹም ኢትዮጵያዊ ባልሆኑ ማንነቶች መገፋፋታችን በዝቶ ጦርነት መለያችን በሆነበት፤ የፈጠርነው የተሳሳተ ትርክት ከባሕል ዕምነታችን አስወጥቶ አገር ሊያሳጣን እያንዣበበ ባለበት በዚህ ጊዜ አሽቀንጥረን የጣልነውን ኢትዮጵያዊ ማንነት መመለስ የውዴታ ግዴታችን ነው።

መለያችን እየሆነ ለመጣው የእርስ በእርስ ጦርነት፣ ረሃብ፣ መፈናቀልና ስደት ተጠያቂዎቹ እኛው፣ መፍትሔዎቹም እኛው ነንና ተስፋ ባለመቁረጥ ነገን ዛሬ እንሥራ፡፡ እርግጥ ነው አሁን የያዝነው መንገድ ብዙ ድካምና መሰላቸት፤ አባጣ ጎርባጣ የበዛበት፤ መንገድ ነው፡፡ ያም ሆን ግን አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በሀገሩ ጉዳይ ተስፋ አይቆርጥምና ስለ ኢትዮጵያ የሰላ ጆሮ የነጠረ ዓይን ይኑረን፡፡

ሕዝቡ የኑሮ ሸክሙ የቱንም ያህል ከብዶ ቢጫነው የኑሮ ብልሃቱ አይጠፋውምና ቆሎ ቆርጥሞ ውሃ ከጠጣ ‹‹ይሁን ተመስገን አገር ሰላም ይሁን›› በማለት በተስፋ የሚጠግብ ሕዝብ ነው፡፡ ለዚህም ነው ዕለት ዕለት የሚፈራረቅበትን መከራ፣ ችግር፣ ረሃብ፣ ጦርነት፣ ስደትና ጉስቁልናውን ተቋቁሞ ሀገራዊ አንድነትን ከሀገራዊ ምክክሩ በተስፋ እየጠበቀ ያለው።

ሀገር ሰላም ውላ ሰላም እንድታድር እንዲሁም ሕዝቦች በአንድነት፣ በመተባበርና በመግባባት እንዲኖሩ ብዙ ተስፋ የተጣለበት ብሔራዊ ምክክሩ ከሕዝቡ ተሳትፎ ውጭ ብቻውን ምንም አይደለም። ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የውይይት ሂደቶችን ከማመቻቸት ውጭ የማደራደር ሥልጣን የሌለው መሆኑ ለስኬታማነቱ የበርካቶችን የነቃ ሕዝባዊ ተሳትፎ ይፈልጋል፡፡

በተለይም ሀገሪቷ ያለፈችበትን ውጣ ውረድ በቅርበት የሚያውቁ የማኅበረሰብ ክፍሎች አባቶች፣ እናቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሚዲያ ባለሙያዎችና ሌሎችም ለምክክሩ ስኬት የጎላ ፋይዳ ይኖራቸዋል። እነዚህ አካላትም ፍጹም በሆነው ኢትዮጵያዊ ጨዋነት መክረውና ዘክረው ሀገራዊ አንድነትንና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በኃላፊነት መንፈስና በቁርጠኝነት ሊንቀሳቀሱ ይገባል፡፡

በሕዝብ ልብ ውስጥ የኖሩ ቁርሾዎች እንዲሽሩና የተለያዩ ቋጠሮዎች እንዲፈቱ ተስፋ የጣልንበት ሀገራዊ ምክክሩ ዕውን መሆን አለበት፡፡ ለዚህም በጎ የሆኑ እሴቶቻችንን ከጣልንበት ማንሳት ቀዳሚው ሥራችን ይሁን፡፡ ሆደ ሰፊነትን ከቤተሰብ ጀምረን በጎረቤት በአካባቢና በሀገር ላይ እናስተጋባ፡፡ ለብሔራዊ ምክክሩ ውጤታማነት የሰነቅነው ተስፋ ዕውን እንዲሆን ያለንን በማዋጣት ዘላቂ ሰላምን ለሀገራችን፤ አንድነትን፣ ስኬትና ብልጽግናን ለሕዝባችን እንመኝ ሰላም!

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን  ሕዳር  1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You