ግብርና ለኢኮኖሚ የጀርባ አጥንትና በኢትዮጵያውያን ሕይወት ውስጥ ሰፊ ድርሻ ያለው ነው፡፡ ግብርናው ሕዝብን ስለመገበና የሀገርን ምጣኔ ሀብት ስለደገፈ ብቻ ወሳኝ ዘርፍ የሆነው አይደለም። ከዚህም ባለፈ የግብርናው ዋና ባለድርሻ አርሶ አደሩ ክረምት ከበጋ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል እያመረተ ያለበት ሁኔታም አርሶ አደሩን የጥንካሬ ተምሳሌት አርጎታል፡፡ ግብርና ብዙ ሥራ ያለውና አድካሚ እንደመሆኑ አርሶ አደሩ ብቻ ሳይሆን በጠንካራው በአርሶ አደሩ ቤተሰብ ውስጥ ያደገ አብዛኛው ሰው ጠንካራና ብርቱ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
የዕለቱ እንግዳችንም የጠንካራ ገበሬ ልጅ ምሳሌ ውጤታማ መምህርና ነጋዴ ናቸው፡፡ ዶክተር መስፍን ሞላ ይባላሉ፡፡ ዶክተር መስፍን ገና በለጋ ዕድሜያቸው ከሰባት ዓመታቸው ጀምሮ ፍየል፣ ጥጃ እያሉ በርካታ ከብቶችን ጭምር አግደዋል፤ ገና የ12 ዓመት ታዳጊና የ6ኛ ክፍል ተማሪ እያሉም በሬ ጠምደው ማረስም ጀምረዋል፡፡ ከእርሻ ሥራው በተጓዳኝ በሬ ጠምዶ ከማረስ ጀምሮ በጉልጓሎው፣ በአረሙ፣ በአጨዳውና በውቂያ ሁሉ አልፈዋል፡፡
በዚህ ሁሉ ሥራና ድካም ውስጥ ከእዚህ ቤተሰብ ቤት አንድ ጉዳይ አይረሳም፡፡ እሱም ትምህርት ነው። በትምህርት ሰዓት ቀልድ የለም፡፡ የግብርና ሥራው በሙሉ የሚሰራው ከትምህርት ሰዓት ውጭ ነው፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ወላጅ አባታቸው ለትምህርት ትልቅ ቦታ የሚሰጡ በመሆናቸው ነው፡፡ ለእርሻ ሥራቸው የሚሰጡትን ያህል ትኩረት ለትምህርታቸውም እንዲሰጡ ያግዟቸዋል፡፡ ከትምህርት የተረፈ ጊዜያቸው ግን ሙሉ በሙሉ ለቤተሰቡ የግብርና ሥራ ይውላል፡፡ ይህም ጠንካራና ብርቱ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡
ከትምህርታቸው ጎን ለጎን በግብርና ሥራ ብርቱ ገበሬ እንደነበሩ ያስታወሱን ዶክተር መስፍን ለማ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የትምህርትና ስነ-ባህሪ ተቋም ዲን ናቸው። ጎበዝ ተማሪና ብርቱ ገበሬ የነበሩት ዶክተር መስፍን፣ የማያልቀው የገበሬ ቤት ሥራ ከትምህርታቸው አላስተጓጎላቸውም፤ ይልቁንም ጎበዝ ተማሪ እንዲሆኑ አገዛቸው፡፡ የግብርና ሥራው የቱንም ያህል ቢበዛ አንድም ቀን ከትምህርት ገበታቸው ተስተጓጉለው አያውቁም፡፡
ተወልደው ያደጉት በቀድሞ አጠራሩ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል በአዲሱ አጠራሩ ደግሞ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ ነው፡፡ በአዲሱ የክልል አደረጃጀት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መቀመጫ በሆነችው ሆሳዕና ተወልደው ያደጉትና የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም የተከታተሉት ዶክተር መስፍን፤ ገና ከልጅነት ዕድሜያቸው ጀምረው ከማለዳው 11 ሰዓት መነሳት የዕለት ተዕለት ተግባራቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
እሳቸው ተማሪ የነበሩበት ወቅት እንዲህ እንደ ዛሬው ተማሪ ብዙ የትምህርት ድጋፍ የሚያገኝበት ባለመሆኑ በብዙ ልፋትና ድካም ውስጥ እያለፉ ነው ትምህርታቸውን መከታተል የቻሉት፡፡ የልፋታቸው ውጤትም አስደሳችና አመርቂ ሆነላቸው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጥሩ ውጤት ማጠናቀቅ ቻሉ፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተውም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በትምህርት አስተዳደር ያዙ፡፡
የመጀመሪያውን የሥራ ዓለም ሕይወታቸውን አሀዱ ያሉት ከትውልድ አካባቢያቸው ሆሳዕና ከተማ 32 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው በሀዲያ ዞን ሶሮ ወረዳ ጊንቢቾ ከተማ ላይ በሚገኝ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በምክትል ርዕሰ መምህርነት ነበር፡፡ በጠንካራ የሥራ ባህል ያደጉት ዶክተር መስፍን፣ በወቅቱ የተማሩትን ትምህርት በሥራ ላይ ለማዋል ከፍተኛ ጉጉት የነበራቸው ስለመሆናቸውም እንደተመሰከረላቸው ይገልጻሉ፡፡
በወጣትነት ሙቅ ልባቸው የግብርና ሥራውን ያቀላጥፉ የነበሩት ዶክተር መስፍን፤ ይህን ብርታታቸውን በትምህርት ሕይወታቸው ደግመው ብቻ አላበቁም፤ ለሶስት ዓመታት በምክትል ርዕሰ መምህርነት ባገለገሉበት ወቅትም ደግመውታል፤ ይህን ትጋታቸውን የተመለከተው የሚሰሩበት ወረዳ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት የመማር ዕድል እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸውና ይህን ትምህርታቸውንም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መከታተላቸውን ገልጸዋል፡፡
ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ይዘው ወደ ዲላ ዩኒቨርሲቲ በማቅናት ሁለት ወር እንዳገለገሉ የዩኒቨርሲቲው ሀዋሳ ቅርንጫፍ የትምህርት ክፍል አስተባባሪ ሆነው ተሾሙ። በዩኒቨርሲቲው የዘጠኝ ወር የአገልግሎት ጊዜያቸውም የዲላ ዩኒቨርሲቲ የተከታታይ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል፡፡ ዶክተር መስፍን፤ በዩኒቨርሲቲው በርካታ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ ከአራት ዓመታት ቆይታ በኋላም የፒኤችዲ ትምህርታቸውን የመከታተል ዕድል ከዩኒቨርሲቲው አግኝተዋል፡፡
የፒኤችዲ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ በሚከታተሉበት ወቅት ደግሞ ዶክተር መስፍን ከቢዝነሱ መንደር ጎራ የማለት አጋጣሚ ተፈጠረላቸው፤ ይህም ትርፍ ጊዜውን በአግባቡ እንዲጠቀሙበት እድል ፈጠረላቸው፡፡ አጋጣሚውን ተጠቀሙበት፤ የፒኤችዲ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የንግድ ሥራን አብረው ይከውኑ ጀመር፡፡
‹‹ሰው ከጣረ ትልቅ ደረጃ ላይ ይደርሳል፤ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም የቻለና ለሥራ የሚተጋ ሰው ምንም አያቅተውም የሚል አመለካከት ያላቸው ዶክተር መስፍን፤ በወቅቱ የተለያዩ የመንግሥት ጨረታዎችን በመከታተል የስቴሽነሪ ዕቃዎችን ለተለያዩ ተቋማት ለማቅረብ ነበር ወደ ንግድ ሥራው የገቡት፡፡
በወቅቱ ጨረታ አሸንፎ የሚፈለገውን ዕቃ ገዝቶ ለማቅረብ እጅግ ፈታኝ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ያም ቢሆን ይህ ስራ ገና በጅምሩ በስም እንጂ ቆጥረው ከማያውቁት ገንዘብ ጋር አስተዋወቃቸው፡፡ ዶክተር መስፍን እንደሚሉት፤ ወደ ንግዱ ሲገቡ የስቴሽነሪ እቃዎች ምን ምን እንደሆኑ በቅጡ አያውቁም ነበር፤ መርካቶ ግን ሁሉንም አስተማራቸው፡፡ ‹‹ማንም ከእናቱ ማሕጸን አላገኘውም›› በሚል በ15 ቀናት ቆይታ የስቴሽነሪ ዕቃዎችን በመለየት ወደ ጨረታ እንደገቡ ይገልጻሉ፡፡
የንግድ ስራው ግን እየቆየ ሲሄድ እንደ አጀማመሩ አልጋ በአልጋ ሊሆንላቸው አልቻለም፡፡ ከተማ ውስጥ ያለው ውድድር በእጅጉ ፈተናቸው፡፡ በዚህ ምክንያትም ለንግድ ስራው ምቹ ባሏቸው ክልሎችና ወረዳዎች ላይም ሰርተዋል፡፡
ዶክተር መስፍን የፒኤችዲ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ቅጥር የመመለስ ፍላጎት አልነበራቸውም፡፡ ምክንያቱም ሳያስቡት የገቡበት የንግድ ሥራ አስተምረው ከሚያገኙት የወር ደመወዝ በብዙ እጥፍ ያደገና ባጭር ጊዜ ውስጥ ሃብት ማፍራት ያስቻላቸው ሥራ ሆኗል፡፡ የንግድ ሥራቸውን ብቻ ይዘው ቢቀጥሉ ብዙ ርቀት ሊጓዙ እንደሚችሉ ቢያውቁም፣ ከንግድ ስራው የሚያገኙት ገንዘብ ሥራውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚገፋፋ ቢሆንም፣ እሳቸው ግን አልቀጠሉበትም፡፡
የንግድ ሥራው የቱንም ያህል ቢጣፍጣቸው በማስተማር ሥራ ውስጥ የሚያገኙት እርካታ ትልቅ እንደሆነ ዶክተር መስፍን ይናገራሉ፡፡ ‹‹በነጻ ያስተማረችኝ አገሬ ናት፤ የአገሬ ውለታ አለብኝ›› በማለት ወደ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ተመልሰው የማስተማር ሥራቸውን ለመቀጠልና የንግድ ሥራውንም ጎን ለጎን ለማስኬድ ወሰኑ፡፡
ከፒኤችዲ ትምህርታቸው በኋላ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የትምህርትና ስነ-ባህሪ ተቋም ዲን መሆን የቻሉት ዶክተር መስፍን፤ በወቅቱ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሰላምን ከማስፈን ጀምሮ የተለያዩ ፕሮግራሞችን በመቅረጽ የትምህርት ተደራሽነትን በተለይም የማስተርስ ትምህርትን ማስፋትና የፒኤችዲ መርሃ ግብር እንዲጀመር ብርቱ ጥረት አድርገዋል፡፡
በኢትዮጵያ የመምህራን የትምህርት ታሪክ ውስጥ መምህራንን በማሰልጠን ተጠቃሽ ከሚባሉት መካከል ዲላ ዩኒቨርሲቲ አንዱ ነው የሚሉት ዶክተር መስፍን፤ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ባላቸው የ18 ዓመታት ቆይታ ሙሉ አቅማቸውን አሟጠው መጠቀማቸውን ጠቅሰው፣ በዩኒቨርሲቲው ለመጡ ለውጦች አሻራቸው እንዳለበትም አጫውተውናል፡፡
‹‹ያስተማረኝ ሕዝብ ነው፡፡ ስለዚህ ያስተማረኝን ሕዝብ በሙያዬ ሳገለግለው ነው ሕሊናዬ የሚረካው›› በማለት የንግድ ሥራውን በአብዛኛው በባለቤታቸው በኩል እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በንግዱ ማሕበረሰብ ዘንድ በጣም ጭካኔና ርህራሄ የሌለው ድርጊት እንደሚታይም ጠቅሰው፣ ግብር ከሚከፍለው ይልቅ የማይከፍለው የሚበልጥበት ሁኔታ እንዳለም ነው የተናገሩት፡፡ አጠቃላይ የንግድ ስርዓቱ የተበላሸ እንደሆነም መታዘብ መቻላቸውን ይገልጻሉ፡፡
በአሁኑ ወቅትም አዲስ አበባ ላይ ባሏቸው ወኪሎች አማካኝነት የስቴሽነሪ እቃዎቹን ለገጠር ከተሞችና ወረዳዎች እንደሚቀርቡ ጠቅሰው፣ ወረዳዎች ላይ በመስራታቸው የንግዱ ስራ ውጤታማ መሆን መቻሉንና ወደ ገጠር መሸሻቸው እንዳዋጣቸው አመልክተዋል፡፡ ‹‹የጨረታ ሥራ የተወሰነ ወቅት የሚያጣድፍና እጅግ በጣም አድካሚ ነው›› የሚሉት ዶክተር መስፍን፤ አሁን የንግድ ሥራ ዘርፋቸውን የመቀየር ሀሳብ እንዳላቸውም ይገልጻሉ፡፡
በንግዱ ስራ በኩል ከተማ ውስጥ ውድድር ሳይሆን መጠላለፍ ነው ያለው የሚሉት ዶክተር መስፍን፣ እንዲያም ሆኖ ከተማ መኖር ብዙ ጥቅሞች አሉት ብለዋል፡፡ ሙሉ ቤተሰቦቻቸውን አዲስ አበባ ማስገባታቸውንም ገልጸዋል፡፡ ዶክተር መስፍን በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውም ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ ይታወቃሉ። በእነዚህም የምርምር ሥራዎቻቸው አማካይነትም ባለፈው መስከረም ወር የረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግን ማግኘታቸውንም ገልጸዋል፡፡ ይህ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ያገኙት ዕውቅና በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ እጅጉን የተደሰቱበትና የኮሩበት የልፋታቸው ፍሬ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡ ከትምህርት አስተዳደር ጋር በተያያዘ ከሰሯቸው 11 የጥናትና ምርምር ሥራዎች ስድስቱ ለዚህ ማዕረግ ያበቋቸው መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
‹‹የሰው ልጅ ለምን ወደቅኩ እንጂ፤ ወደቅኩ ማለት የለበትም›› የሚሉት ዶክተር መስፍን፤ ማንኛውም ሰው ከደከመና ከጣረ ካሰበበት ይደርሳል፤ ሁሉም ሰው የወደቀበትን ምክንያት ለይቶ ለመነሳት ጥረት ማድረግ አለበት ይላሉ፡፡ በተለይም ወጣቶች ጊዜ፣ ዕውቀትና ጉልበታቸውን በአግባቡ መጠቀም ከቻሉ ውጤታማ የሚሆኑባቸው በርካታ ዕድሎች እንዳሉ ነው ያመለከቱት፡፡ ወጣቶች በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ሁሉ በርትተው እንዲሰሩና ተማሪዎችም ትምህርታቸውን ዋና ሥራቸው አድርገው ጠንክረው እንዲማሩ መክረዋል፡፡
በንግድ ሥራቸው ብዙ ሃብትና ንብረት ማፍራት የቻሉት ዶክተር መስፍን፤ በስቴሽነሪ እቃዎች አቅራቢነት ሥራቸውም የመንግሥትን ግብር በአግባቡ እንደሚከፍሉ ይናገራሉ፡፡ ቫት ብቻ በዓመት ከሁለት መቶ ሺ ብር በላይ እንዲሁም ከ170 እስከ 200 ሺ ብር ግብር እንደሚከፍሉ ገልጸዋል፡፡ ማሕበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር ሰው እንዲማር እንዲያድግና እንዲነግድ እመክራለሁ፤ አስተምራለሁ የሚሉት ዶክተር መስፍን፤ በዚህም አንዱ መንገድ ቢዘጋ ሌላ መንገድ እንዳለ አሳያለሁ ይላሉ፡፡
በርካታ ተማሪዎችን በትምህርት እንደሚያግዙ የሚናገሩት ዶክተር መስፍን፣ የተማሩትንም በተግባር ማሳየት እንደሚችሉ በማመላከት የሚያውቁትንና የሰሙትን ማንኛውንም ጠቃሚና ሰው የሚያድግበትን እንዲሁም የሚለወጥበትን መንገድ እንደሚያሳዩ ይገልጻሉ፡፡
ዶክተር መስፍን በኢትዮጵያ ትምህርት ዙሪያ ያልተደፈሩና ያልተጀመሩ ሥራዎችን መሥራት ያስደስታቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ትምህርት ብዙ ማነቆዎች እንዳሉበትም ይጠቁማሉ፡፡ የጥራት፣ የፍትሃዊነትና የተደራሽነት ችግሮቹን ነቅሶ ለማውጣት የተለያዩ ጥረቶች እያደረጉ እንደሆነ ነው የሚናገሩት፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ ትምህርት ሁለት ጥቅሞች አሉት፤ አንደኛው በግለሰብ ደረጃ ጥሩ ኑሮ መኖር ያስችላል፡፡ ሁለተኛው ማሕበረሰብን ማገዝ፣ መጥቀምና ለውጥ ማምጣት ነው፡፡ ጥናቶቹም ይህንኑ የሚመላክቱ ናቸው፡፡
በቀጣይ አራት ዓመት ጊዜ ውስጥም ለሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ የሚያበቃቸውን ተጨባጭ ለውጥ የማምጣት ዕቅድ እንዳላቸው የገለጹት ዶክተር መስፍን፤ ያን ጊዜ ትልቁን ስኬታቸውን እንደሚያዩ ነው የተናገሩት፡፡
የኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት አድጎና ተሻሽሎ ማየት ትልቅ ምኞታቸው እንደሆነም ጠቅሰው፣ በተለይም የትምህርት ጥራት፣ ተገቢነት፣ ፍትሃዊነትና ተደራሽነት ተስተካክሎ የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንደ ሌሎች አገራት ተማሪዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ እኩል መወዳደር የሚችሉበት ጊዜ እንዲመጣ ምኞታቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ለዚህም በብርቱ መሥራት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ህዳር 1/2016