ድህነትን በርግጥም ታሪክ ለማድረግ!

 ኢትዮጵያ ለግብርና ክፍለ-ኢኮኖሚ ምቹ የሆነ የአየር ንብረት፣ መሬት እና ሰፊ የውሀ ሀብት እንዳላት ብዙ ተብሏል ፤ ዘርፉን በማዘመን የተሻሻለ እና ጥራቱን የጠበቀ ምርት በማምረት የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ አቅም ማሳደግ እንደሚቻልም በስፋት ተነግሯል፣ ከፍተኛ የሥራ ዕድል የሚፈጥር፣ ከኢትዮጵያውያን የዕለት ተለት የሕይወት እንቅስቃሴ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ የኢኮኖሚ ምንጭ እንደሆነም በተለያዩ አጋጣሚዎች ተገልጿል፡፡

ይህም ሆኖ ግን ከተነገረለት ይልቅ ያልተነገረለት እየሆነ፣ በዘርፉ የተሰማራውን 80 ከመቶ የሀገሪቱን የሰው ኃይል /አርሶ አደሩን እንኳን መመገብ ሳይችል ቀርቶ ሀገሪቱ በተለያዩ ወቅቶች በተከሰቱ የድርቅ አደጋዎች፣ ዜጎች ለከፋ ረሀብ ተጋልጠዋል ፣ በዚህም ብዙዎች ለሞት፤ ለመፈናቀልና ለስደት ተዳርገዋል።

ከዚህም ባለፈ ዘርፉ በደህናውም ወቅት ምንም ትርፍ ምርት የማይፈጠርበት በመሆኑ ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች እንዲያቆጠቁጡና እንዲያድጉ የሚያግዝ ሀገራዊ የካፒታል ክምችት መፍጠር እንዳይቻል አድርጓል። የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ምንጭም ይሄው የግብርና ዘርፍ መሆኑ የሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት እንዲቀጭጭ ምክንያትም ሆኗል።

በትክክለኛ የፖሊሲ አቅጣጫና በሀገራዊ ራዕይ የተቃኘ ቁርጠኛ አመራር ያለመኖር፣ ለግብርና ልማት ምቹ የሆኑ አካባቢዎችን ለይቶ አለማወቅ፣ የግብርና ቴክኖሎጂ ልምምድ አለመኖር፣ የግብርና ባለሙያዎች ተደራሽነት ዝቅተኛ መሆን ዘርፉ የአቅሙን ያህል እንደ ሀገር የሚጠበቅበትን እንዳያበረክት ዋነኛ ተግዳሮት ሆኖበታል፡፡

የለውጥ ኃይሉ ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ አንስቶ፤ እነዚህን ክፍተቶች በመዝጋት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ በስፋት ተንቀሳቅሷል። በተለይም በዘርፉ ያለውን አመራርና ባለሙያ በአዲስ ዕይታ አስተሳሰቡ ብቻ ሳይሆን አሠራሩን እንዲቃኝ በማድረግ ረጅም ርቀት ተጉዟል። በዚህም እየተመዘገበ ያለው ውጤት ተስፋ ሰጭ ስለመሆኑ ዕለት ተዕለት የምናያቸው ተጨባጭ ተሞክሮዎች ማሳያ ናቸው።

የአርሶ አደሩ የተሻለ የምርት ግብዓትና ማዳበሪያ የመጠቀም ልምድ ማሻሻል፣ ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ጉልህ ድርሻ ካለው የመስመር እርሻ ስልት ጋር መለማመድ እንዲሁም ብጥስጣሽ እርሻ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ለማስቀረት በርካታ ኩታ ገጠም ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች በተያያዘ ሰፊ ማሳ ላይ ማምረት መጀመራቸው በባሕላዊ የምርት ስብሰባ ወቅት የሚባክነውን እስከ 30 በመቶ የሚደርስ ምርት ለመቀነስ አነስተኛና ከፍተኛ የምርት ስብሰባ ሜካናይዜሽን የመጠቀም ልምድ እየተሻሻለ መምጣቱ የዚህ እውነት አካል ናቸው።

ይህም የአርሶ አደሩን ምርታማነት በእጅጉ መሻሻል አስችሏል። በስንዴ ምርታማነት ላይ ያለውን ለማየት ብንሞክር እንኳን ፤ ከዚህ ቀደም በአንድ ሄክታር መሬት ከስድስት እስከ ስምንት ኩንታል ስንዴ ያመረት የነበር ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ግን በግብርና ሜካናይዜሽን በመታገዝ በሄክታር በአማካይ 64 ኩንታል ለማምረት ተችሏል። ይህ በሀገሪቱ በስንዴ ሊለማ ከሚችለው መሬት አንጻር ሲታይ የቱን ያህል በስንዴ ልማት እንደ ሀገር ያለንን አሁነኛ አቅም አመላካች ነው።

ይህ በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገበ ያለው ተስፋ ሰጭ ውጤት ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች በተያዘላቸው ዕድገት አቅጣጫ እንዲጓዙ የሚያግዝ ሀገራዊ የካፒታል ክምችት መፍጠር የሚያስችል ነው። ከዛም ባለፈ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪን ግኝትን በማሳደግ የሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት እመርታ እንዲያሳይ ትልቅ መነቃቃት ሊያመጣ ይችላል። በተለይም ለኢንዱስትሪና ለአገልግሎት ዘርፎቹ ዕድገት ሊኖረው የሚችለው አስተዋጽኦ የጎላ ነው ።

ይህም ሆኖ ግን አሁንም በዘርፉ ከሚስተዋለው ችግር አንጻር እየታየ ያለው ስኬት በተሞክሮ መልኩ የሚወሰድ፤ ገና ብዙ ማሰብ፣ ማቀድ እና መሥራት የሚጠይቅ ነው ። በተለይም ዘርፉን በሁለንተናዊ መልኩ በማዘመን፤ አርሶ አደሩ የተሻለ ተጠቃሚ የሚሆንበትን፤ ሀገርም እንደ ሀገር በዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም ተጨባጭ ተስፋ በማድረግ ተጠቃሚ የምትሆንበትን የአስተሳሰብ እና የአሠራር ሥርዓት ማበጀት እና በጠንካራ ዲሲፕሊን መምራት ያስፈልጋል። ይህንን ማድረግ ስንችልም ነው ድህነትን ታሪክ ልናደርግ የምንችለው!።

አዲስ ዘመን  ሕዳር  1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You