የአፍሪካን ቀንድ ቀጣናዊ የጋራ ልማትና እድገት ፍላጎቶች ለማሳካት የፌደራሊዝም እሳቤዎች አስፈላጊነት

በአፍሪካ ቀንድ በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ሕዝቦች የዘላቂ ሰላም፤ የልማት እና እድገት ተስፋቸው በጥብቅ የተሳሰረ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ምክንያቱም በቀጣናው በሚገኙ ሀገራት የሚኖሩ ሕዝቦች አሰፋፈር እና ትስስር፤ በጋራ እያሳለፏቸው ያሉ ሰው ሠራሽም ሆነ የተፈጥሮ አደጋዎች፤ በጋራ ጥቅም ላይ ቢውሉ ቀጣናውን ይበልጥ ሊያስተሳስሩ እና ለቀጣናው ሰላም እና እድገት ሊውሉ የሚችሉ ሃብቶች መኖር ተስፋቸው የተሳሰረ መሆኑን አመላካቶች ናቸው፡፡

የትስስሩ አስፈላጊነት በዚህ ብቻ አያበቃም፤ ለረጅም ጊዜ ቀጣናው ከሚታወቅበት ተከታታይነት ካላቸው ግጭቶች፤ ስር የሰደደ ድህነት፤ ስደት፣ መሠረታዊ የሆኑ ፍላጎቶችን እንኳ ለማሟላት ከለጋሽ ሀገራት እና ድርጅቶች ላይ ያለ እና የተጣባ ጥገኝነት ለመላቀቅ ሀገራቱ በጋራ የሚያስተሳስራቸው ጠንካራ ሥርዓት ማበጀት አሁን በምንገኝበት ክፍለ ዘመን የግድ ይላቸዋል፡፡

ሀገራቱ በየራሳቸው የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንደተጠበቀ ሆኖ በተመረጡ እና ለቀጣናው መሠረታዊ ለውጥ በሚያመጡ ጉዳዩች ዙሪያ የጋራ ፍላጎትን መሠረት ባደረገ መልኩ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ የሚመሩበት በፌደራላዊ እሳቤ የሚመራ አደረጃጀት ፈጥረው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል።

ይህን ማድረግ ካልቻሉ፤ ለቀጣናው ማኅበረሰብ እንደ ጥቅልም ሆነ በየሀገራቱ የሚኖሩ ዜጎችን ዘላቂ ሰላም፤ የኢኮኖሚ፤ ማኅበራዊ ዕድገት እና የኑሮ መሻሻል ምላሽ እየሰጡ ከሌሎች የዓለም ክፍሎች ጋር እኩል የሚራመዱበት ሁኔታ ሊኖር አይችልም። ለዚህም ቀጣናው ከአሳለፋቸው እና እያሳለፋቸው የሚገኙ ነባራዊ ሁኔታዎች ግልጽ ምስክሮች ናቸው፡፡

ሉዓላዊ በሆኑ ሀገራት መካከልም የሚኖር ዘላቂ እና በጋራ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ፤ በጋራ በተሻለ መልኩ ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮችን የሚፈታ፤ በጋራ ቢለሙ እና የጋራ ተጠቃሚነት ቢያረጋግጡ የተሻለ ውጤት ሊያመጡ የሚችሉ እንዲሁም የግጭት ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን በጋራ ስምምነት ግልጽ በሆነ አግባብ እና አደረጃጀት የሚመራበት ሥርዓት ፈጥሮ ለመንቀሳቀስ ፌደራላዊ እሳቤዎችን መከተል ያስፈልጋል፡፡

ፌደራሊዝም በባሕሪው በአብሮነት የግል እና የጋራ ፍላጎቶችን ዴሞክራሲዊ እና ሚዛናዊ በሆነ አግባብ አቀናጅቶ ለሰው ልጆች ነፃነት፤ እኩልነትን፤ ሰላም፤ እድገት እያረጋገጡ የሚሄዱ አደረጃጀቶች በየደረጃው ተደራጅተው ወደ ሥራ መግባትን የሚደግፍ እና የተለያዩ ቅርጽ ያላቸው ፌደራላዊ የፖለቲካ ሥርዓቶችን አቅፎ የሚይዝ ፍልስፍና ነው። የሁሉንም መብት እና ፍላጎት በውይይት፤ በንግግር እና በመተማመን ማስከበር የሚያስችል የጋራ የሆነ ሥርዓት የሚፈጠርበት እሳቤ ነው፡፡

ፌደራሊዝም ሀገራት እንደ ሀገር፤ በቀጣና ደረጃ፤ በአህጉር እንዲሁም በዓለም ደረጃ በግል እና በጋራ ቢከናወኑ የተሻለ ውጤት ሊያመጡ እና የሰው ልጅን እና የሚኖርበትን ምሕዳር አሰናስለው የበለጠ ተጠቃሚ ሊደርጉ የሚችሉ ጉዳዮች በየደረጃው ተለይተው እና ተሳስረው የሚፈጸሙበትን አሠራር፤ ሥርዓት እና አደረጃጀት የሚደግፍ ነው፡፡

በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሀገራዊ ጉዳዮቻቸውን ከጋራ ጉዳዮቻቸው ጋር አስተሳስረው በቅንጅት እና በትብብር ካልሠሩ ሀገራት ችግሮቻቸውን ቀርፈው በጋራ የማደግ ተስፋቸው የተመናመነ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም። በተለይም በከፋ ችግር እና ድህነት ውስጥ ባለው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ችግሮችን በዚህ መልኩ መፍታት ካልተቻለ፤ ችግሩ ይበልጥ እየተባባሰ በከፋ መልኩ ለቀጣዩ ትውልድ ከመተላለፍ ባለፈ ሌላ መውጫ በር ይኖራል ተብሎ አይታሰብም።

በዓለም ላይ ካሉ የፌደራሊዝምን እሳቤ ከሚጋሩ አደረጃጀቶች የአውሮፓ ኅብረትን የአጀማመር ሁኔታ በአጭሩ መመልከት ተገቢ ነው። የአንድን ችግር ምንጭ በጋራ በማስተዳደር ለጋራ ጥቅም ለማዋል የሚያስችለውን አሳቤ በመያዝ፤ የራስ አስተዳደር እና የጋራ አስተዳደር አስተሳስሮ እና አናቦ የተጀመረው የአውሮፓ ኅብረት አሁን ላይ የደረሰበትን እና እየሄደበት ያለውን እርቀት ሲታይ አስተማሪነቱ ከፍ ያለ ነው፡፡

እንደሚታወቀው የአውሮፓ ኅብረት ጥንስስ በ1951 እ.አ.አ በስድስት አውሮፓ ሀገሮች የተመሠረተው የአውሮፓ የዴንጋ ከሰል እና ብረት ማኅበረሰብ (European Coal and Steel Community) መሆኑ ይታወቃል፡፡መነሻ ሃሳቡ አውሮፓውያኑ በተከታታይ ግጭቶች እና በሁለት የዓለም ጦርነቶች ያሳለፋቸውን ችግሮች ላለመድገም ሀገራቱ ያላቸውን የድንጋይ ከሰል እና ብረት አስተዳደር ወደ ጋራ አስተዳደር ለማምጣት ነው፡፡

ይህ በሀገራት መካከል ሊኖር የሚችል የግጭት ፍላጎት በመቀነስ በጦር መሣሪያ የታገዘ ኃይል የተቀላቀለበት ግጭትን ለማካሄድ የሚያስችል ማቴሪያል ማግኘት የማይታሰብ እንዲሆን ለማድረግ የተከናወነ ነው። በተለይም በፈረንሳይ እና በጀርመን መካከል የነበረውን ግንኙነት በትብብር ላይ የተመሠረተ በማድረግ የጋራ የሆኑ ጉዳዩችን በጋራ ማከናወን ታሳቢ ያደረገ ነበር፡፡

ለዚህ ለአውሮፓ ኅብረት መጀመር መነሻ የሆነ እንቅስቃሴ በፈረንሳይ የወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የነበሩት ሮበርት ሹማን ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱ እና በስማቸው የሚጠራው የሃሳብ መግለጫ ሰነድ (shuman declaration) ለማኅበረሰቡ መመሥረት መነሻ ተደርጎ ይወሰዳል። ጀን ሞኔት ደግሞ የማኅበረሰቡ አደረጃጀት ነዳፊ ተደርገው የሚወሰዱ ሲሆን የመጀመሪያው ፕሬዚዳንቱም ነበሩ።

የነዚህ ቁልፍ ሰዎች ተግባር የሚያመላክተን ለቀጣናቸው ሰላም እና እድገት አርቀው የሚያስቡ እና የፌደራሊዝም እሳቤ የተላበሱ መሪዎች የአውሮፓን ዘላቂ ሰላም እና የጋራ እድገት አሻገረው በማየት የመነሻ ጥንስሱን የጠነሰሱ የፖለቲካ መሪዎች መሆናቸውን ነው። ከነዚህ መሪዎች የአፍሪካን ቀንድ ሰላም እና ደህንነት፤ ልማት እና እድገት የሚመኙ እና የወደፊቱን የቀጣናውን ብሩህ ተስፋ አሻግረው የሚያዩ የፖለቲካ መሪዎች ብዙ ሊማሩ ይገባል።

የቀጣናው ሀገራት መሪዎች የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የፌደራሊዝም እሳቤን መሠረት ያደረገ እንቅስቃሴ ሊያደርጉ እንደሚገባ ያመላክታል፤ በተለይም በሀገራችን ለሚነሱ ቀጣናዊ የጋራ ልማት እና የጋራ ተጠቃሚነት እሳቤዎች መሠረት የሚሆን ተሞክሮ ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባ ነው፡፡

በሀገራችን ወቅታዊ የሆነው ሁሉም የቀጣናው ሀገራት ተጠቃሚ የሚሆኑበት እና በጋራ ፍላጎት መመለስ የሚችለው የወደብ ጥያቄ እና ሌሎች ቀጣናውን ለማስተሳሰር የሚችሉ እንደ የኤሌክትሪክ ኃይል፤ የመንገድ፤ የባቡር፤ የአየር እና የባሕር ትራንስፖርት፤ የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች፤ የመጠጥ ሆነ ለግብርና ሥራ የሚውል ውሃ፤ የአካባቢ ጥበቃ፤ የጋራ ገበያ ወዘተ. የመሳሰሉ በጋራ ቢመሩ የበለጠ አዋጭ እና ለሁሉም የመጠቀም እድል ይፈጥራሉ።

ይህንን የጋራ ተጠቃሚነት መሠረት ያደረገ እሳቤ ተግባራዊ ለማድረግ፤ ጉዳዮችን በጋራ ማስተዳደር የሚችል አካል የፌደራሊዝምን እሳቤ መሠረት በማድረግ በማቋቋም ጥንስሱን መጀመር ወይም ለጥንስሱ ኢጋድ አለ ከተባለም ኢጋድን ሙሉ በሙሉ አደረጃጀቱን እና አሠራሩን በመለወጥ ወደ ሥራ ማስገባት ይቻላል።

ይህም ለቀጣናው መጭ ዘመናት ተስፋ ያለው እና ቀጣናውን ከሚታወቅበት እና መገለጫው እየሆነ ከመጣው ግጭት፤ ስር የሰደደ ድህነት፤ ስደት ለማላቀቅ ተስፋ የሚሰንቅ ተግባርን ማከናወን ያስችላል፤ ለዚህም በቀጣናው በሁሉም ዘርፍ የሚገኙ ልሂቃን እና ኅብረተሰብ ክፍሎች ደግመው ደጋግመው ሊያስቡበት የሚገባ እውነታ ነው።

የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትም የጋራ ችግሮቹን ለመፍታት እና የቀጣናውን ሰፊ የጋራ መልማት ዕድሎች በመጠቀም በቀጣናው ተዓምራዊ ለውጥ ለመምጣት እና ለቀጣይ ትውልድ የተሻለ በጋራ ችግሮችን መፍታት እና በጋራ ማደግ የሚያስችሉ ቀጣይነት የሚኖራው መሠረቶችን ጥሎ ማለፍ የዚህ ዘመን ትውልድ ግዴታ ሁኖ ይታያል፡፡

እስከ አሁን በቀጣናው ሴራውም፤ መጠላለፉም፤ መጋጨቱም ተሞክሮ አዋጭ ሆኖ አልተገኘም፤ በግል እንደ ሀገር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ከሀገር ሀገር የሚለያዩ አፈጻጸሞች ያሏቸው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የጋራ የሆኑ ቀጣናዊ ችግሮችን ለመፍታት እና የጋራ እድገት እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተቻለበት ሁኔታ አለ ብሎ ለማለት አያስደፍርም፡፡

በመሆኑም አሁን በምንገኝበት ክፍለ ዘመን እና ነባራዊ ሁኔታዎች የፓራዳይም ለውጥ ማድረግ እና የፌደራሊዝምን እሳቤ መሠረት ያደረጉ ተግባራትን በመፈቃቀድ፤ በመተባበር እና በመከባበር ላይ ተመሥርቶ ለመሥራት የሚያስችል ሁኔታዎችን መፍጠር ግድ ይላል። ከዚያ ውጭ ያሉ አማራጮች በሙሉ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ተሞክረው የፈቱትም ችግር ሆነ ያመጡት የጋራ ልማት ከዚህ ግባ የሚባል አይደለም፤ ለዚህ ደግሞ ምስክሩ የቀጣናው ነባራዊ ሁኔታ ነው፡፡

ኃይለየሱስ ታዩ ( ዶ/ር)

በፌደራሊዝም ጥናት ረዳት ፕሮፌሰር

አዲስ ዘመን ህዳር 1/2016

Recommended For You