ከዓመታት በፊት፣ በዚህ ሳምንት (ከግንቦት 12 እስከ 18) በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከተከናወኑ/ከተከሰቱ ድርጊቶችና ክስተቶች መካከል ጥቂቶቹን ለማስታወስ ያህል፡- ግንቦት 12 ቀን 1929 ዓ.ም – የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር በደብረ ሊባኖስ ገዳም መነኮሳት፣ ካህናት፣ ዲያቆናትና የአካባቢው ምዕመናን ላይ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ፈጸመ። ጣልያኖች የኢትዮጵያውያንን የጀግን ነት መንፈስ ለመስበር ከመጀመሪያው ተዘጋጅተው ነበር የመጡት። ለዚህ ደግሞ እንደ አንድ ዕርምጃ የወሰዱት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያንን ማንበርከክ ነው። ምንም እንኳን ጥቂት ጳጳሳት ከእነርሱ ጋር ለመሥራት ባያንገራግሩም እንደ አቡነ ጴጥሮስ ያሉ ቆራጥ አባት መፈጠራቸው፣ ብዙዎች ገዳማትና አድባራት አርበኞችን መርዳታቸውና ካህናቱም ‹‹ወግጅልኝ ድጓ ወግጅልኝ ቅኔ፣ወንዶች ከዋሉበት እውላለሁ እኔ›› እያሉ ሀገራቸውን ለመከላከል በረሀ መውረዳቸው ጣልያኖችን ዕረፍት ነሥቷቸው ነበር።
በተለይም ደግሞ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በማርሻል ግራዝያኒ ላይ በተቃጣው የግድያ ሙከራ ዋነኞቹ ተሳታፊዎች አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ከደብረ ሊባኖስ ገዳም ጋር ግንኙነት አላቸው መባሉ፣ አርበኛው ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስ የአካባቢው ተወላጅ በመሆናቸው ከደብረ ሊባኖስ ገዳም ጋር ግንኙነት አላቸው ተብሎ መታሰቡ፣ እንዲሁም ታዋቂው አርበኛ ደጃዝማች ኃይለ ማርያም ማሞ ከገዳሙ መነኮሳት ጋር ይገናኛል መባሉ ጣልያኖች በደብረ ሊባኖስ ላይ የዘንዶ ዓይናቸውን እንዲጥሉ አደረጋቸው። ደብረ ሊባኖስ ገዳም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ያለው ቦታ የጣልያኖችን የጥፋት ትኩረትን ሳበ።
ቤተ-ክርስቲያኒቱን እንዲሁም በእርሷም በኩል የጀግንነቱን መንፈስ አከርካሪውን ለመስበር ያሰቡት ፋሽስቶች የታላቁ ጻድቅ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ምዕራፍ፣ የእጨጌውን መቀመጫና ለአያሌ ገዳማት መመሥረት ምክንያት የሆነውን ገዳም ሌላውን ሊያስደነግጥ በሚችል መልኩ በአሰቃቂ ሁኔታ ለማጥፋት ወሰኑ። በዚህም መሠረት ማርሻል ሩዶልፎ ግራዝያኒ ያቀናበረውና ጄኔራል ማሌቲ የመራው ጦር ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ወረደ። የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ፍልሰተ ዐጽም የተከናወነበትን በዓል ለማክበር የተሰበሰቡትን ምእመናንና መነኮሳትን መጨፍጨፍም ጀመረ።
በጫጋል፣ በውሻ ገደል፣ በሥጋ ወደሙ ሸለቆና በደብረ ብርሃን አጠገብ በእንግጫ በተከናወነው ጭፍጨፋ ገና ነፍስ ያላወቁ ሕፃናት የቆሎ ተማሪዎችን ጨምሮ ከ1801 እስከ 2201 የሚደርሱ ምዕመናንና መነኮሳት በግፍ ተረሸኑ። በገዳሙ የነበሩ መጻሕፍት፣ የከበሩ ዕቃዎች፣ ንዋያተ ቅድሳት፣ ገንዘብና ሌሎች ንረቶች ተዘረፉ። ገዳሙም ነፃነት እስኪመለስ ድረስ በመከራ ውስጥ ኖረ። * * * ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም – የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢ.ሕ.ዲ.ሪ) ፕሬዚዳን ትና የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢ.ሰ.ፓ) ሊቀመንበር፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የነበሩት ሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማ ርያም ወደ ዚምባብዌ ኮበለሉ።
የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎችና የፖ ሊስ ሠራዊት አባላትን ይወክላሉ የተባሉና ከተራ ወታደር እስከ ሻለቃ ድረስ ማዕረግ ያላቸው 120 የጦሩ አባላት ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም በአራተኛ ክፍለ ጦር ግቢ ውስጥ ተሰብስበው ያቋቋሙት ‹‹የጦር ኃይሎች፣ የክብር ዘበኛ፣ የፖሊስ ሠራዊትና የብሔራዊ ጦር አስተባባሪ ኮሚቴ›› መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ከዙፋናቸው አውረደ። ስያሜውንም ‹‹ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ›› ብሎ በመለወጥ ስልጣን ይዞ ኅብ ረተሰባዊነት (Socialism)ን የፖለ ቲካ – ኢኮኖሚ መርሁ አድርጎ አገር መግዛት ጀመረ።
የመሰረተ ልማት አውታሮችን በተለይ ደግሞ ትምህርትን ለማስፋፋት ከተደረገው ጥረት ባሻገር የእርስ በእርስ ጦርነት፣ እስራትና ስርዓት አልበኝነት የአገዛዙ መለያዎች ሆኑ። በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተለይ ደግሞ ኤርትራ ውስጥ ያለው ጦር ሲሸነፍ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃ/ማርያም የሚወስዱት ዕርምጃ፣ የሊቀመንበሩ ግትርነት እንዲሁም ሌሎች ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች ተደምረው የጦሩ መሪዎች በሊቀመንበሩ ላይ ጥርሳቸውን ነከሱባቸው። መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግም ሞክረው ሳይሳካ ቀረ።
የአገሪቱ ችግርም ከድጡ ወደ ማጡ ሆነ። ከዚህ ሁሉ ችግር ለማምለጥ ከአገር መውጣትን ምርጫቸው ያደረጉት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም ሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም በኬንያ በኩል አድርገው ዚምባብዌ ገቡ። ግንቦት 16 ቀን 1983 ዓ.ም – እሥራኤል ቤተ-እሥራኤላውያንን ከኢትዮጵያ ወደ እሥራኤል ለመው ሰድ ‹‹ዘመቻ ሰለሞን (Operation Solomon)›› የተባለውን ዘመቻ ማካሄድ ጀመረች። በዘመቻ ሰለሞን በአንድ ቀን ከግማሽ (በ36 ሰዓታት) 14 ሺ 325 ቤተ-እሥራኤላውያን በ35 አውሮፕላኖች ከኢትዮጵያ ወደ እሥራኤል ተወስደዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2011
አንተነህ ቸሬ