ድሮ ድሮ “ውድ” ለወዳጅ የሚጻፍ የደብ ዳቤ መክፈቻ ቃል ነበር:: ዛሬ ደግሞ ለነፍስ ለቀረበ ወዳጅ የሚሰጥ የቁልምጫ ስም ነው:: ፍቅረኛንና የትዳር አጋርን ውዴ ማለት ግድ ነው:: ጆሮ አስፍስፎ ይጠብቃላ! የቃሉ ፍቺ አንድም ተወዳጅ አንድም በቀላሉ የማይገኝ (ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል) ማለት ነው:: ጨዋታችን በቃሉ ሁለተኛ ብያኔ ዙሪያ ነው:: ብዙ ገንዘብ የሚያስወጡ (ውድ) ነገሮችን ስለሚወዱ ሰዎች እናወጋለን::
ውድ ነገሮችን ትወዳላችሁ ? ወይም ውድ ነገሮችን የሚወዱ ሰዎች ገጥመዋችሁ ያውቃሉ? ውድ ነገርን መውደድ ጤናማ ሰዋዊ ባህሪ ነው ልትሉ ትችላላችሁ። ነገር ግን መጠን አለው። ምንም ነገር ቢሆን ልኩን ሲያልፍ ችግር መሆን ይጀምራል። በያዝነው ሳምንት አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ በተላለፈ ወንጀል ነክ ፕሮግራም መጠን ባለፈ የግዢ ሱስ ምክንያት የትዳር አጋሯ ሳያውቅ ከፍተኛ ብድር ውስጥ ተዘፍቃ ቤታቸው በሐራጅ ተሸጦ ባለቤቷንና መንታ ልጆቿን ጥላ ለእስር የተዳረገች እንስት ታሪክ ቀርቦ ነበር። ባለታሪኳ ለዚህ የበቃችው ማንም ሰው እንደ አቅሙ በየቀኑ የሚፈጽመው ግዢ እርሷ ግን አቅሟ የማይፈቅደውን ነገር ሁሉ ሱስ ሆኖባት እየተበደረች በመግዛቷ ነው።
ውድ ነገርን መውደድም ቅጥ ሲያጣ ሱስ ይሆናል። ውድ ወዳዶችን መተዋወቅ ትፈልጋላችሁ ? እነሱን በአካል ማግኘት በጣም ቀላል ነው። ሰንደይ ማርኬት ላይ ሦስት መቶ ብር የሚሸጥ ሱሪን የከተማው ታዋቂ ሞል ገብተው ያለክርክር በአንድ ሺህ ብር ሲገዙ ታገኟቸዋላችሁ። በሚንቀሳቀሱበት ቦታ ሁሉ ዓይኖቻቸው ለየት ያለ ጫማ፣ ልብስ፣ መነጽርና የእጅ ስልክ ላይ ያርፋሉ። ደግሞ አይተው ዝም አይሉም። ጠጋ ብለው በጣም ያምራል ! ከየት ገዛኸው ? ከውጭ ተልኮልህ ነው ? ይመቻል ? እያሉ ጥያቄ ይደረድራሉ። ባስ ሲልም ትሸጠዋለህ ? ብለው በዋጋ ለመደራደር አያመነቱም። ለዓመታት የተለዩትን ሰው ድንገት ሲያገኙት እንዴት ነህ ? በማለት ፈንታ ጫማና ልብስህ ያምራል ማለት ይቀናቸዋል።
የራሳቸው ያልሆኑ ቢላ ቤቶችና ዘመናዊ መኪናዎች ፊት ተደንቅረው ወይም ባጋጣሚ ባገኟቸው ዝነኞች ጉያ ተሸጉጠው ፎቶ መነሳት ሆቢያቸው ነው። የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ ይሁኑ ለአምልኮት የሚሄዱት እጅግ የተዋበ ሕንፃ ወዳለው ማምለኪያ ስፍራ ነው። አንድ ነገር ውድ ከሆነ ታዋቂ ብራንድ ነው ብለው ያስባሉ። ዝነኞች ከፍተኛ ክፍያ ተከፍሏቸው የሚያስተዋውቋቸውን የንግድ ምል ክቶች እነርሱ ያለምንም ክፍያ በኩራት ገላቸው ላይ በቋሚነት ይነቀሷቸዋል።
የማይታ ወቅ የንግድ ምልክት ያለው አዲስ ልብስ መግዛት አይፈልጉም። ልምዱ ያላቸውን ቡቲኮች አስቸ ግረው ታዋቂ የሆኑ ብራንዶችን በውድ ዋጋ ከሰል ባጅ ተራ ያስመጣሉ። የብራንድ ነገር ውስጣቸው ነው። ደብዳቤው ብራንድ በሆነ ወረቀት ይጻፍ እንጂ ከሥራ መሰናበ ታቸው አያስጨንቃቸውም። ሁለት ሦስት ቅያሬ ልብስ ከሚኖራቸው ይልቅ ዳጎስ ያለ ዋጋ ያለው አንድ ብራንድ የሆነ ልብስ ቢኖራቸው ይመርጣሉ። ጉልት ገበያ ብትወስዷቸው እንኳን ብራንድ ቲማቲምና ድንች ከመፈለግ ወደኋላ አይሉም።
የቀብር ስነስርዓት ላይ እንኳን ከአጉል ልማ ዳቸው አይቆጠቡም፤ ኀዘኑን ረስተው ሳጥኑ ላይ በማፍጠጥ ብራንድ መሆኑንና አለመሆኑን ያጣራሉ። በአንድ ወቅት አንድ ናይጄሪያዊ አባቱን እጅግ ውድና ቅንጡ በሆነ የቤት መኪና መቅበሩ ዓለምን አስገርሞ ነበር። ያለጥርጥር ይህ ናይጄሪያዊ ከውድ ወዳዶች አንዱ ነው። ውድ ነገር ትኩረታቸውን ይስበዋል። እነዚህን ሰዎች የማድመጥ ዕድል ከገጠማችሁ በአሜሪካን አገር ባለ 18 ካራት የወርቅ መጸዳጃ ቤት ስለመሠራቱና ለጎብኚዎች ክፍት ተደርጎ ረዥም ጊዜ ሳይወስዱ እንዲጠቀሙ በት ሊደረግ እንደሆነ ይነግሯችኋል።
ወይም ደግሞ በዓለም ላይ ለአንድ ቀን አዳር በሚያስከፍለው ዋጋ ውድ የሆነው ሆቴል ጄኔቫ ውስጥ የሚገኘው ፕሬዚዳንት ዊልሰን ሆቴል መሆኑንና በዚህ ውድ ሆቴል የሚገኙት አስር ክፍሎች ለአንድ አዳር 65 ሺህ ዶላር እንደሚከፈልባቸው እየተደነቁ ይነግሯችኋል። ቀንቷቸው አንዳች ነገር ከገዙ ስልክ በመደወል የሚያውቁትን ሰው ሁሉ ካላገኘንህ ይላሉ። ለምን አላችሁኝ ? ሾው ለማሳየትና ስለዋጋው ሌክቸር ለማድረግ ነዋ ! ኪሳቸው በድርቅ ሲመታ ደግሞ ሳይነጋ ቅባቱ ሻይ ቤት ሄደው ዳቦ በሻይ እየነከሩ ይበሉና ቀትር ላይ ካልዲስ ካፌ በረንዳ ላይ ተኮፍሰው ይታያሉ። ሲያገኙም ሲያጡም ያውቁበታል አይደል ! አይ … ሱስ !
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2011
የትናየት ፈሩ