የጠንካራተቋማትግንባታ ምስክር

በዓለም አቀፍ ደረጃ በብልፅግና የሚታወቁ አገራት ለከፍታቸው መንስኤ የሆኑ አበይት ምክንያቶችን እንደሚጠቅሱ ሁሉ፣ ከድህነት መላቀቅ የተሳናቸውም ለዝቅታቸው በርካታ ሰበቦችን ይደረድራሉ:: መልከአ ምድራዊ አቀማመጣቸው ምቹ አለመሆኑና በተፈጥሮ ሃብት አለመታደላቸው ደግሞ ከሰበቦቻቸው መካከል ጎልቶ ይሰማል::

እንደ ምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ምልከታ ግን እነዚህ አገራት በዕድገት ወደ ኋላ ለመቅረታቸውና ለድህነታቸው በመንስኤነት የሚያቀርቧቸው ምክንያቶች ሚዛን የሚደፉ ሆነው አይገኙም:: በእርግጥ ለግብርና ምቹ በሆነና በበቂ ሁኔታ የተፈጥሮ ሃብት ባለበት አካባቢ የሚኖር ሕዝብ ከሌላው የተሻለ የኢኮኖሚ ዕድገት ይኖረዋል:: ይህ ማለት ግን የተፈጥሮ ሀብት ክምችት ብቻውን ኢኮኖሚን ያሳድጋል ማለት አይደለም::

‹‹በተፈጥሮ ሀብት መበልፀግ ብቻውን የእድገት ምንጭ ቢሆን ኖሮ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን የመሳሰሉ አገራት ድሃ ሆነው፣ ምንም ዓይነት የተፈጥሮ ሀብት የሌላቸው እንደ እስራኤል ዓይነት ሀገሮች ደግሞ በኢኮኖሚ የላቁ አይሆኑም ነበር›› የሚሉት ምሁራኑ፣ ከሁሉ በላይ ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት የተለያዩ ተቋማት የሚፈጥሩት ሁለንተናዊ አቅም ወሳኝ መሆኑን ያሰምሩበታል::

በዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ስመጥር የምጣኔ ሃብት ባለሙያ የሆኑት ማርጋሬታ ጂኒክ ሃኑዝ፣‹‹የአንድን አገር ብልፅግና ለመገመት ተቋማቱን ብቻ መመልከት በቂ ነው፣ ‹‹If you want to predict the prosperity of a coun­try, just look at its institutions.››ማለታቸው ለዚሁ ነው::

እንደ እርሳቸው ሁሉ ሌሎች ምሁራንም ‹‹በአሁን ወቅት በሁለንተናዊ እድገት የሚታወቁ አገራት የከፍታቸው አበይት ምክንያቶች ዘመናዊ፣ ውጤታማና ተጠያቂነት የሰፈነበት ተቋም በመገንባታቸው ነው፣ በተለይ ለማደግ የሚታትሩ አገራት ይህን በአግባቡ በመገንዘብ ለተቋማት ፈጠራ ብሎም አቅም መጎልበት ትኩረት መስጠት ቢችሉ በቀላሉ ትሩፋቱን መቋደስ አይቸገሩም››ይላሉ::

የኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት ፕሮፌሰር ቢሩ ፓካሽ ፖል፣‹‹Why Institutions Are so Im­portant for Growth›› በሚል ፅሁፋቸው፣ ለአንድ አገር ሁለንተናዊ እድገት በተለይ የተቋማት አቅም ወሳኝ መሆኑን ያሰምሩበታል:: ለዚህ እሳቤአቸውም እኤአ እስከ 1970 ዎቹ ማብቂያ ተመሳሳይ የኢኮኖሚ አቅም ላይ የነበሩት አይቮሪኮስትና ሜክሲኮ በዋቢነት ያቀርባሉ::

ፀሃፊው ሁለቱ አገራት የትላንትና ገጽታቸው ታሪክ ሆኖ በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ የዕድገት ደረጃና ገፅታ ላይ የመገኘታቸው ዋነኛው ምክንያት አፍሪካዊቷ አገር የተቋማት አቅምና ሚና በአግባቡ መረዳት ባለመቻሏ መሆኑን ያመላክታሉ::

ለአንድ አገር ሁለንተናዊ እድገት የተቋማት ሚና ወሳኝ መሆኑን ከመስማማት ባሻገር ከተቋማት መካከልም ይበልጥ ወሳኝ የሆኑትን መለየት የተመረጡት ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ፋይዳው በቀላሉ የሚገለፅ እንዳልሆነ የሚያስገነዝቡ ምሁራን ቁጥርም ቀላል አይደለም::

የእሳቤው አራማጆች በአንድ ሃገር ውስጥ ሁለንተናዊ እድገትና ብልፅግናን ለማስተዋወቅ በተለይ የፋይናንስ፣ የትምህርት፣ የፍትህ ብሎም የሕዝብ አስተዳደር ተቋማት ከሌሎች በተሻለ የላቀ ሚና እንዳላቸው ይጠቁማሉ:: ለእነዚህ ተቋማት ሰላማዊ መሳለጥ ወሳኝ የሆነው የፀጥታና የደህንነት ተቋማት ግንባታም እጅጉን ወሳኝ መሆኑን ያሰምሩበታል::

በሊዝበን ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ኢኮኖሚስት የሆኑት ሊያም ብራንትን የመሳሰሉ ምሁራን በአንፃሩ ‹‹፣Which institutions matter for economic growth? በሚል ጥናታቸው፣ ይሕን እሳቤ ውድቅ ያደርጉታል::

የልዩነት አቋማቸው ደግሞ ‹የፖለቲካዊ፣ የኢኮኖሚያዊም ሆነ የማህበራዊ ተቋማት ሁለንተናዊ አቅም የአንድን አገር እድገት ቢወስንም ከሁሉ ገዝፎ አቅም መፍጠር የሚችለውና ዋነኛው አስፈላጊ ተቋም የትኛው ነው የሚለውን በቀላሉ መግለፅ ይቸግራል›› የሚል ነው::

አገራቱ ኢኮኖሚያቸውን በላቀ መልኩ ለማሻሻል አፈፃፀማቸውን ለማጎልበት ይረዳል የሚሉትን ተቋማት በፈለጉት መልኩ የማዋቀር ነፃ ፈቃድ ያላቸው መሆኑን የሚነግሩን ምሁሩ:: ፋይዳቸው የላቁ ተቋማትን መለየትና ትኩረት ለመስጠት ከተቸገሩም ብቸኛ አማራጫቸው የሌሎችን በተለይ በኢኮኖሚ እድገት ማማ ላይ የተሰቀሉ አገራትን የተቋማት ልየታና አወቃቀር መቃኘት እንደሚችሉም ያመላክታሉ:: ምልከታቸቀው ይለያይ እንጂ ሁሉም ምሁራን የተቋማት አቅም የአንድ አገር እድገት መሰረት ስለመሆኑ ያሰምሩበታል::

ወደ አገራችን ስንመለከት ኢትዮጵያ የተቋማት የእድገት ቁልፍነት የመረዳት ድክመት እንዳለ በርካቶች የሚያስማማ ሃቅ ነው:: በሙከራ ደረጃም ቢሆን የተመለከትነው የተቋማት ስሪት በድርጊትና ባላቸው ውቅር በርካታ ችግሮች ሲታይበትም ቆይቷል::

የተቋማት አቅም ግንባታ በዘመቻ መልክ ያዝ ለቀቅ በሚል መልኩ ካልሆነ በስተቀር መድረሻውን በመወሰን በተጠና እና ወጥ በሆነ መልኩ ሲካሄድም አላስተዋልንም:: ጠንካራ ተቋማት ባለመኖራቸው ምክንያት ኢትዮጵያ ከዓመት ዓመት ግዙፍ የሚባሉ ኪሳራዎችን ስታስተናግድ ቆይታለች::

ይሁንና መሰል ችግርን ፈጥኖ ማስተካከል ካልቻለ አገር በምትፈልገው ፍጥነት መራመድ አትችልም:: ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ ከተፈለገ ተቋማት በመገንባት ሂደት ውጤታማ የሚሆኑበትን መንገድ መፈለግ አቅምና አደረጃጀታቸው ምን ያህል አዋጭ ብሎም አመቺ ነው? የሚለው በየጊዜው መከታተል የግድ ነው::

ወሳኝ የሚባሉ ተቋማት በአግባቡ ማደራጀትና ተደራራቢ ተግባር የሚፈፅሙትን መለየት ብሎም ወደ አንድ ማጠፍ ከተቻለም አለአግባብ ይባክን የነበረ ከፍተኛ መጠን ያለው የሕዝብና የአገር ሃብትን ከኪሳራ መታደግ ያስፈልጋል::

ከለውጡ ወዲህ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አመራር ኢትዮጵያ የፈለገችው ለማሳካት እና ያሰበችበት ቦታ ለመድረስ ተቋማዊ ግንባታ ላይ ይበልጥ መትጋት እንዳለባት ጠንቅቆ የገባው ይመስላል::

አመራሩ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ኢትዮጵያን ለማበልፀግ በሚያግዝ መልኩ ተቋማዊ አቅምን ለማጎልበት የተለያዩ ጥረቶችን አድርጋል:: እያደረገም ይገኛል:: በዚህም መሻሻሎች እየታዩ ለውጦችንም መመልከት እየተቻለ መጥቷል::

በተለይ ከዚህ ቀደም በሙስና ተተብትበው የነበሩ በአግባቡ ቢሰራባቸው የአገር ካስማ የሆኑ ተቋማትን ከተዝረከረከ አሰራር ማላቀቅ ብሎም ፈር ማስያዝ ተችላል:: ለዚህም በተለይ የገቢዎችና ጉምሩክ እንዲሁም በቀድሞ ስሙ “ሜቴክ” ተብሎ ይጠራ የነበረውና ከለውጡ ወዲህ ስሙን የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቀየረው ተቋም ጥሩ ማሳያ ሆነው ሊቀርቡ የሚሉ ናቸው::

ከለውጡ በፊት የሙስና ገነት የነበረውና ከለውጡ በሃላ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 398/2009 የተቋቋመው የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽንም እንዲሁም ልማት ባንክ በተቋማት ሪፎርም ተግባራ ተጨባጭ ውጤት ካስመለከቱት ተርታ የሚጠቀሱ ናቸው::

ከለውጡ ወዲህም ሰላምን በማስጠበቅ ረገድ የደህንነት ጥበቃ ተቋማትን እንደ አዲስ በሚባል መልኩ ማደራጀት ተችላል:: በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ እንዲሁም ለታላቅ ሀገር ታላቅ ተቋም በሚል የተደራጀው ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንም በዚህ ረገድ አብይ ማሳያ ሆነው ይጠቀሳሉ::

አንድ አገር ስኬትና ኪሳራን የምታወራርደው ባለመችው፣ እልምታም ባበቃችው ትውልድ ነው። ትምህርት ደግሞ ይህን ትውልድ እውን ለማድረግና ለአንድ አገር እድገት መሰረት፣ ዋልታና ማገር መሆኑ ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚገባ አይደለም:: ትምህርትን በአግባቡ የተጠቀሙ እና ውጤታማ የትምህርት ሥርዓት የተከተሉ የዓለም አገራት ቁሳዊና ሰብዓዊ እድገታቸው ጎልቶ የሚታይ ነው::

በአሁን ወቅት እንደ አገር የጠንካራ ተቋማት ግንባታን እውን ለማድረግ በሚደረግ ጥረት የአገር እድገት ምሶሶ መሆናቸው ተለይቶ ከሚሰራባቸው ተቋማት መካከል ትምህርት አንደኛው ነው:: ባለፉት ሁለት ዓመታትም የዘርፉን ተቋማዊ ተክለ ቁመና እና ደካማ አፈፃፀም ለማጠናከር ብሎም ለማስተካከል አዲስ መንገድ መራመድን ጨምሮ ስር ነቀል የሚባል ለውጥን እያስመለከተም ይገኛል::

ከለውጡ ወዲህ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ሁለንተናዊ አቅምን በማጎልበት ረገድ የተከናወኑ ተግባራት ከሁሉ በላይ የጠንካራ ተቋማት ግንባታ እውን እየሆነ ስለመምጣቱ ምስክር ሆኖ ሊቀርብ የሚችል ነው::

እንደሚታውቀው የኢፌዴሪ ሠራዊት ዋና ዓላማ ሕብረ ብሔራዊ አንድነቷ የፀና፣ የበለፀገች ኢትዮጵያን ሕገ መንግስታዊ ሥርዓት፣ የሀገረ መንግስቱ እና የሀገረ መንግስቱን ግዛታዊ ሉዐላዊነትና አንድነት እንዲሁም የሕዝብ ደህንነት ከማንኛውም ዓይነት የውስጥና የውጭ ጥቃት መከላከል ነው።

ይህ መከላከያ ሰራዊት ራሱን ከዘመኑ ጋር ከሚሄድ ቴክኖሎጂ እንዲያስተዋውቅ፣ በዓላማው ላይ ግልፅነት እንዲኖርና በውስን ሀብት ውጤታማ መሆን የሚችልበት ስልት በሚገባ መቀመርም ፋይዳው ከትርፍም በላይ ከህልውና ጋር የሚቆራኝ ነው::

በአሁን ወቅትም ከቀድሞ በተለየ መልኩ የሀገር መከላከያ በሁሉ ረገድ ጠንካራ ተቋም እንዲሆን በተለይም መከላከያ ሰራዊቱ ወቅቱ የሚጠይቀውን ዘመናዊ የውትድርና እውቀትና ተግባርና ምግባር እንዲያካብት መደረጉ በግልፅ እየተስተዋለ ነው::

ከቀናት በፊት በተካሄደው 116ኛው የሠራዊት ቀን ክበረ በአል ላይም ተቋሙም ሆነ ሰራዊቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅነት በሚመጥን፣ በቀጣናው ላለብን ከፍተኛ ኃላፊነት ብቁ በሆነ፣ የሕዝብ አሜነታን በተጎናፀፈ፣ በወታደራዊ ዕውቀትና ክህሎት እንዲሁም ዘመናዊነት በዳበረ፣ በአስተማማኝ ዝግጁነት ጦርነትን በሩቁ ማስቀረት በሚችል፣ በዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ተገቢውን ሚና የሚጫወት ኃይል የመፍጠር ራዕይ በሚያሳካ መልኩ መደራጀታቸው በአደባይይ መመልከት ተችላል::

በበአሉ ላይ የተገኙ ከፍተኛ አመራሮችም ኢትዮጵያ ከምንም ጋር ጦርነት ውስጥ የመግባት ፍላጎት ባይኖራትም የመከላከያዋን አቅም በእጅጉ እንዳጎለበተችና ጀግንነትና ከዘመናዊነት ጋር እንዳቆራኘች ማረጋገጫን ሰጥተዋል::

በዚሁ በአል ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር ዐቢይ አሕመድም ሲገልፁ እንደሰማንንና እንደተመለከትነውም፣ በሰራዊቱ ውስጥ በተሰራው ሪፎርም በወታደራዊ ቴክኒክ የበለፀገ የውጊያ ልምድ ያለው በተግባር የተፈተነ የአፍሪካ ኩራት የሆነ የመከላከያ ሠራዊት ተገንብቷል:: መከላከያ አሰላለፉና ትጥቁ በምድር ብቻ ሳይሆን በባሕርም፣ በአየርም የተደራጀና የታጠቀ እንዲሆን ማድረግም ተችሏል::

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ‹‹ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ ከጀግኖች የተረከብናትን ኢትዮጵያ እንደተከበረች እና ማንነቷ እንደተጠበቀ ለማስቀጠል ወታደራዊ ዝግጁነታችንን አሳድገናል ቁመናችንን አዘምነናል›› ሲሉ ኢትዮጵያ ጠንካራ የመከላከያ ተቋም እየገነባችው ስለመሆኑ ማረጋገጫን ሰጥተዋል::

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፣ ‹‹የምድር ኃይል፣ የአየር ኃይል፣ የባሕር ኃይል እና የሳይበር ኃይሎቻችንንም ዘመኑን እና ኢትዮጵያን በሚመጥኑ መልኩ እየገነባን የተሻለ አስተማማኝ ደረጃ ላይ ማድረስ ችለናልም››ብለዋል።

መከላከያ ላይ የተሰራው የሪፎርም ስራ የጠንካራ ተቋማት ግንባታ ምስክር ከመሆን ባሻገር የአገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲራመድና ካሰበችው እንድትደርስ ትልቅ ዋስትናን የሚሠጥ ነው::

ይሁንን ስኬታማው የሪፎርም ስራ የሚደነቅ ቢሆንም በተለይ ቀጠናው አሁን ካለበት ውጥረትና ከውጭም ሆነ ከውስጥ አንዳንዶች አገርን ዋጋ ለማስከፈል የሚያደርጉት ጥረት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ይበልጥ መጎልበት እንዳለበት የሚያከራክር አይደለም::

መሰል ኢትዮጵያን በጽኑ መሠረት ላይ የሚያቆሙ ጠንካራ ተቋማት የመፍጠሩ ትግልም ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል:: ይህ በሚሆንበት ሂደት በተለይ የአንዳንድ ተቋማት ግንባታ ውጤት በአንድ ጀንበር የሚመጣና የሚመዘን እንዳልሆነ ጠንቅቆ መገንዘብ ያስፈልጋል::

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላከያ ሰራዊት ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች አብራክ የወጣ ለሕዝብ ደኅንነትና ለሀገር ሉዓላዊነት የአካልና የሕይወት መስዋዕትነት የሚከፍል ብሔራዊ ኃይል ነው:: ሰራዊቱ የአሸናፊነት ሥነ-ልቦና ከፍታና የድል ምንጩ ጠንካራውና ነጻነቱንና ብሔራዊ ክብሩን አሳልፎ የማይሰጠው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው::

የሕዝብ ልጅ የሆነው ሰራዊት ከሕዝቡ ጋር ያለውን ትስስርና አንድነት ለማጠናከርና የሕዝቡን የባለቤትነት ስሜት ይበልጥ እንዲጎለብት ለማድረግም የሰራዊት ቀን ትልቅ መድረክ ሆኖ ያገለግላል::

የቀኑ መከበርም የመከላከያ ተቋማት ተክለ ቁመና የሰራዊቱ በሁሉ ረገድ በላቀ ከፍታ ላይ መራመድ ለወዳጅም ለጠላትም ለማስመልከትና ማንኛውም የውጭም ሆነ ውስጥ ኃይል ኢትዮጵያን ከመተንኮስ አስቀድሞ ቆም ብሎ እንዲያስብ በማድረግ ረገድ ግዙፍ አቅም ይፈጥራል::

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/2016

Recommended For You