ለሀገራዊምክክሩስኬትመገናኛብዙኃንሙያዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል!

 ሀገራችን በተለያዩ ዘመናት/ወቅቶች ከውስጥም ከውጭም አስቸጋሪ ፈተናዎች አጋጥመዋታል። በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶችም ፈተናዎቹን በብዙ መስዋዕትነት አሸንፈው በመውጣት አሁን ያለችውን ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ለዚህ ትውልድ አስረክበዋል።

ይህም ትውልድ እንደ አንድ ሀገር ተረካቢ ትውልድ በብዙ መስዋዕትነት ዛሬ ላይ የደረሰችውን ሀገር በተሻለ መልኩ ለመጪው ትውልድ ማስረከብ ይኖርበታል። ለዚህ ደግሞ ከሁሉም በላይ ትናንት ላይ እንደ ሀገር ዋጋ ላስከፈሉንና ዛሬም እያስከፈሉን ላሉ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ማፈላለግ ይጠበቅበታል። በተለይም ሀገሪቱ የብዙ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች፤ የተለያዩ ሀይማኖቶችና አስተሳሰቦች መገኛ ከመሆኗ አንጻር እነዚህን ልዩነቶች በማክበር፤ ለሀገር ዕድገት፣ ሰላምና መረጋጋት አቅም የሚሆኑበትን አስቻይ ሁኔታ መፍጠር የትውልዱ ዋነኛ ኃላፊነት ነው።

ልዩነቶችን በኃይል ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች ለዘመናት ሀገርና ሕዝብን ብዙ ዋጋ እንዳስከፈሉ ሀገራዊ ትርክቶቻችን በስፋት የሚያነሱት እውነታ ነው። ችግሩ አሁን ላለንበት ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎች ዋነኛ ምክንያት እንደሆነም ይታመናል። ኃይል እና የኃይል አማራጭን የፖለቲካ አቅም አድርጎ የመመልከት ባህል፤ ከትናንት ባለፈ ዛሬ ላይ / በ21 ክፍለዘመን እንደ ሀገር የቱን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለን ባለፉት ሶስት ዓመታት የመጣንባቸው አስቸጋሪ /አስጨናቂ መንገዶች እና በዛ ውስጥ የነበሩና ያሉ ውጣ ውረዶች ተጨባጭ ማሳያ ናቸው።

በቀደሙት ረጅም የሀገረ መንግስት ታሪካችን ለንግግርና ለውይይት፤ ለይቅርታና ለሰላም የተዘረጉ እጆችን አክብሮ ለመንቀሳቀስ የሚያስችል የፖለቲካ ባህልና ማሕበረሰባዊ አስተሳብ መፍጠር ባለመቻላችን፤ በሕዝባዊ ለውጡ ዋዜማ ብሩህ ሆነው ያየናቸው ነገዎቻችን እንዲደበዝዙ ምክንያቶች ሆኗል።

አንድም በአግባቡ ተጽፈው ካላለቁ ትናንቶች የሚቀዱ፤ በሌላ በኩል በትናንት መንገድ ላይ ቆመው ያልተገባ አካሄድ የሚሹ ግለሰቦችና ቡድኖች በሚፈጥሩት የግጭት ትርክቶች ሀገር እንደሀገር ለመክፈል የተገደደችው ሆነ እየከፈለችው ያለው ዋጋ ይህ ትውልድ ሊሸከመው የሚችል አይደለም ። ትውልዱ እንደ ትውልድ በብዙ መስዋዕትነት የተቀበላትን ሀገር ለራሱም ሆነ ለመጪዎቹ ትውልዶች የማስተላለፍ ከፍያለ ኃላፊነት አለበት። ይህ ማኅበረሰባዊ ብቻ ሳይሆን ፍጥረታዊ ኃላፊነትም ጭምር ነው። ለዚህ የሚሆን ውስጣዊ መነቃቃት እና ዝግጁነትም እንደሚኖረው ለጥያቄ የሚቀርብ አይሆንም።

ይህንን መሻቱን እውን ለማድረግ ከሁሉም በላይ ከራሱ የሚነሳ ሀገርን እንደሀገር ሊወርስ የሚችል ሰላም ያስፈልገዋል። ይህንን ለማምጣት ደግሞ በእውቀት ላይ የተመሰረተ የመነጋገር እና ተነጋግሮ የመግባባት ባሕል መፍጠር ይኖርበታል። ዘመኑን ሊዋጅበት የሚችልበት የሰላም መንገድ ይሄው ብቻ መሆኑን መረዳት ይጠበቅበታል። ከሁሉም በላይ እንደሀገር ይዘናቸው በመጣናቸው ችግሮቻችን፣ ሆነ ዛሬ ላይ ለመግባባት ተግዳሮት በሆኑብን ልነቶቻችን ዙሪያ ኃላፊነት እንደሚሰማው ትውልድ ተነጋግሮ ለመግባባት፤ ተግባብቶም የተሻለች ሀገር ለመስራት በሚያስችል ሁለንተናዊ ቁመና ውስጥ መገኘት ይኖርበታል።

ለዚህ ደግሞ እንደሀገር ችግሮቻችንን ተነጋግረን ለዘለቄታው መፍታት እንችል ዘንድ የተቋቋመው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሁለንተናዊ በሆነ መንገድ ስኬታማ እንዲሆን፤ ከፍ ባለ የኃላፊነት መንፈስ መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል። ለዚህ የሚሆን ዝግጁነትና ቁርጠኝነት መፍጠር ይኖርብናል። በተለይም የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ለኮሚሽኑ ዓላማ ስኬት የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነው። የተዛቡ ትርክቶችን ከማስተካከል ጀምሮ በምክክር እንደ ሀገር ጠንካራ የጋራ ትርክቶች ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ሂደት ውስጥ የሚኖራቸውን ሙያዊ አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ ሊሆኑ ይገባል።

ልዩነቶችን ከማግዘፍና ከማስፋት ይልቅ ለሀገር ግንባታ አቅም የሚሆኑበትን አማራጭ መፍጠር፤ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የያዛቸው ሀሳቦች ወደ መሬት እንዲወርዱና ተግባራዊ እንዲደረጉ ጠያቂና ተሳታፊ ሆነው በጋራ መስራት ይጠበቅባቸዋል። በማሕበረሰብ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ሀሳቦች ወደ ሚዲያው እንዲመጡ፤ በሀሳቦቹ ዙሪያ መግባባቶች እንዲፈጠሩም ስትራቲጂክ በሆነ መንገድ መንቀሳስ ይኖርባቸዋል!

አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/2016

Recommended For You