‹‹አህሊ››-ቤተሰባዊዝምድናንየሚያሳየውየሀረሪብሔረሰብመገለጫ

ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች መገኛ ነች። ይህ ደግሞ እጅግ ብዙ ባሕል፣ ማንነት፣ ወግና ማራኪ እሴቶች እንዲኖራት ምክንያት ሆኗል። ከምስራቅ ተነስተን እስከ ምዕራብ፤ ከደቡብ ጀምረን እስከ ሰሜን ብንጓዝ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በሚያስደንቅ ሁኔታ የተለያዩ እጅግ ማራኪ እሴቶችን እናገኛለን። የአመጋገብ፣ የአለባበስ፣ የአጨፋፈር፣ የሀዘን፣ የመረዳዳትና አብሮ የመኖር እሴቶች እንደየብሔረሰቡ ባሕል የራሱ ልዩ እሴት እንዳለው መረዳት እንችላለን።

በዛሬው “ሀገርኛ” አምዳችንም ተነስቶ ከማይጠገበው፤ ተዝቆ ከማያልቀው የኢትዮጵያ ሕዝቦች እሴት ውስጥ አንዱን መዝዘን ልናስተዋውቃችሁ ፈልገናል። አቅጣጫችንንም ወደ ምስራቁ ክፍል አድርገን ሀረር ላይ ከትመናል። ሀረር በአብሮ መኖር፣ በቋንቋ፣ በአመጋገብ፣ በሃይማኖት፣ በንግድ፣ በታሪክ፣ ቅርስ ባሕልና በብዙ እሴቶች የታደለች መሆኗ ይታወቃል። በዚህ ዳሰሳችንም ሁሉንም ጉዳይ አንስተን ባንችልም አንድ ነገር ላይ ግን ትኩረት ማድረግ ፈልገናል። እርሱም የሀረሪን ቤተሰባዊ ዝምድና የሚያሳይ “አህሊ” ተብሎ የሚታወቅ አደረጃጀት ነው። በመሆኑም ለዛሬው “አህሊ” ምን እንደሆነና በሀረሪ ብሔረሰብ ቤተሰባዊ አደረጃጀትና ትርጉሙ ምን መልክ እንደሚኖረው እንመለከታለን።

አቶ ተወለዳ አብደሸ የሀረሪ ክልል ባህል ቅርስ ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ናቸው። እርሳቸው የሚመሩት ክፍል “የሀረሪ ብሔረሰብ የማይዳሰሱ ቅርሶች ክንዋኔዎችና ሃይማኖታዊ፣ ባሕላዊና ማሕበራዊ ስነ ስርዓቶች”ን የሚያሳይ ጥናታዊ መጽሐፍ አዘጋጅቷል። በዚህ ውስጥ ደግሞ “አህሊ” (የቤተሰብ ዝምድናና አጠቃላይ አደረጃጀት) በሚመለከት የማሕበረሰቡን ትክክለኛ እሴት ለማስቀመጥ መሞከራቸውን ይናገራሉ።

“የማንኛውም ማሕኅበረሰብ መሰረት የሚጣለው በቤተሰብ ላይ ነው” የሚሉት የቢሮ ኃላፊው፤ በመሆኑም ቤተሰብ ከመሰረታዊ የማሕበረሰብ መዋቅሮች በመጀመሪያ ደረጃ ላይ እንደሚጠቀስ ይናገራሉ:: የባሕል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮው ያዘጋጀውን ጥናታዊ መጽሐፍ መሰረት አድርገውም ስለ “አህሊ” አደረጃጀት አጠቃላይ ይዘት አብራርተውልናል።

ሀረሪ- የቤተሰብ አመሰራረት

የቤተሰብ መሰረቱ በትዳር የተሳሰሩ አባወራ እና እማወራ ሲሆኑ ልጆች እና እንደየማሕበረሰቡ ባሕል በአባልነት የሚካተቱ ቤተዘመዶች እና አጋሮች ተጨምረውበት ቤተሰብ ይመሰረታል:: በሀረሪዎች ባሕል መሰረት የቤተሰብ መነሻዎች አባትና እናት (አው እና አይ) ናቸው:: ሀረሪዎች አባት፣ እናት፣ የሚወልዷቸው ልጆች፣ የሚያሳድጓቸው የቤተ ዘመድ ልጆች እና በስራ ምክንያት አብረዋቸው የሚኖሩ ሰዎች ጭምር የቤተሰብ አባል ናቸው:: ይህ አሀዳዊ የቤተሰብ መዋቅርም “ጋራች” በመባል ይታወቃል::

የሀረሪ ቤተሰብ ራሱን “ጋር ሀዋዝ” ብሎ ይጠራል:: በሀረሪዎች ቤተሰባዊ ትስስር በጣም ጠንካራ ሲሆን የብሔረሰቡ አባላት ከኃይማኖትና ባሕል ጋር የተያያዘ የቤተሰብ አደረጃጀትና የኑሮ ዘይቤ አላቸው:: በዚህም መሰረት የቤተሰቡ ራስ አባወራው ነው:: ቤተሰቡን የመምራትና ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ገቢ የማስገባት ኃላፊነቶች በሱ ላይ ያረፉ ናቸው:: ቀደም ባሉት ጊዜያት በሀረሪ ሚስት ገቢ ማስገባት አይጠበቅባትም:: የገቢ ምንጭ ካላትም ለቤት አስተዳደር እንድትጠቀምበት አትገደድም ነበር:: ከስራ ክፍፍል አንጻርም ወንድ ቤተሰቡን የሚያስተዳድርበት ገቢ ማምጣት የእርሱ ኃላፊነት በመሆኑ የውጪውን ሥራ ማከናወን ይጠበቅበታል::

የእማወራ ኃላፊነት የቤት ውስጥ አስተዳደር ስራዎች፣ ምግብ ማዘጋጀትና ማቅረብ እንዲሁም ልጆችን መንከባከብ ናቸው:: ይህ ሁኔታ በተወሰነ ደረጃ በሂደት ለውጥ እያሳየ መጥቶ አሁን ላይ ከቤት ውጪ ባለ ስራ በተለይም በንግድ እና በቢሮ ስራ ላይ የተሰማሩ የሀረሪ ሴቶችን ማየት እየተለመደ መጥቷል።

‹‹አህሊ›› (የስጋ ዝምድና)

በሀረሪዎች ከቤተሰብ ቀጥሎ ዝምድና ትልቅ ዋጋ ይሰጠዋል:: በደም የተሳሰሩ ሀረሪዎች “ቃማ በሰር አህሊ” ተብለው ይጠራሉ። “አህሊ” ዘመድ (ቤተ ዘመድ) ማለት ነው:: በሀረሪዎች ሶስት የቤተዘመድ መነሻዎች አሉ:: እነዚህም ‹‹ደም አህሊ›› (የሥጋ ዝምድና)፣ ደድ ‹‹አህሊ›› (የጓደኝነት ዝምድና) እና ‹‹መትናሰብ አህሊ›› (የትዳር ዝምድና) ናቸው::

‹‹ደም አህሊ››

ደም አህሊ ማለት የደም፣ የስጋ ዝምድና መኖርን ያመለክታል:: የስጋ ዝምድናን አብዱላሂ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል:: ‹‹የስጋ ዝምድና (አህሊ) ግለሰቡን ከቤተሰብ ቤተሰብን ከሌላ ወይም ከሌሎች ቤተሰቦች ጋር የሚያስተሳስር የትውልድ ግንኙነት ነው:: የስጋ ዝምድና በሀረሪ ሕብረተሰብ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አለው:: በሕብረተሰቡ ማሕበራዊ ሕይወት ላይ በተለይ በጋብቻ፣ በሞትና በውርስ ጉዳይ ላይ ወሳኝ ሚና አለው:: ደም አህሊን ‹‹ጋራች›› የሚለው ቃል ሊገልጸው ይችላል:: ስፋቱ ዘመድ አዝማድን ያጠቃልላል::

‹‹ደም አህሊ›› በቤተሰባዊ ጉዳዮች ላይ ወሳኝ ሚና ያለው አካል ነው:: የራሱ የሆኑ መዋቅሮችም አሉት:: ከመዋቅሮቹ መካከል ጋር -ሃዋዝና አህሊጋራች የሚሉት ይጠቀሳሉ:: ጋር-ሃዋዝ የቅርብ ቤተሰቦች ሲሆኑ አህሊ-ጋራች ደግሞ ሰፊውን ቤተሰብ የሚያጠቃልል ነው::

‹‹ደድ አህሊ››

ደድ አህሊ ከጓደኝነት ጋር የተያያዘ ዝምድና ነው:: በሀረሪ ብሔረሰብ ጓደኝነት ትልቅ ስፍራ አለው:: መሪኝ እና ጌል፣ ሙጋድ፣ ጀመዓ የመሳሰሉ ማሕበራዊ አደረጃጀቶች ሁሉ ከጓደኝነት ጋር የተያያዙ ናቸው:: በዚህ የጓደኝነት ትስስር ውስጥ ደም አህሊ ሊኖርም ላይኖርም ይችላል:: ዋናው ቁም ነገር ደድ አህሊው የጠበቀ የጓደኝነት ትሥሥር መሆኑ ነው::

‹‹መትናሰብ አህሊ››

‹‹መትናሰብ አህሊ›› የትዳር ዝምድናን የሚያመለክት ነው:: ትዳር ብዙዎችን ያስተሳስራል:: በአጠቃላይ እነዚህ ቤተሰባዊ ትስስሮች ጋብቻ፣ ሞት እና ውርስ በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ወሳኝ ሚና ያላቸው በመሆኑ በሀረሪዎች ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች ላይ ተጽዕኗቸው የጎላ ነው:: የሀረሪ ብሔረሰብ በእነዚህና በመሳሰሉት ዝምድናዎች እርስ በርስ የተሳሰረ በመሆኑ በተለምዶ ‹‹ሶስት ሀረሪዎች ባሉበት ሌላውን ሀረሪ አትማ›› የሚባል አባባል አለ:: ይህም ያለምንም ጥርጥር የምታማው ሰው ከሶስት አንዳቸው ጋር ዝምድና ይኖረዋልና ነው::

የቤተዘመድ አባላት መጠሪያ ስያሜዎች

በሀረሪዎች የቤተዘመድ አባላት የሚጠሩባቸው ስያሜዎች አሏቸው:: ለምሳሌ ያህል “አው” አባት፣ “አይ” እናት፣ “ሊጂ” ወንድ ልጅ፣ “ቀሀት” ደግሞ ሴት ልጅ ይባላሉ:: ሌሎቹ የዝምድና ትስስሮች በአብዛኛው የዝምድናውን መስመር የሚያሳይ የተለየ መጠሪያ አላቸው:: ለምሳሌም ያህል “ኢህ” ወንድም፣ “አህት” እህት፣ “አባ” ታላቅ ወንድም፣ “አባይ” ታላቅ እህት፣ “ባብ” ወንድ አያት፣ “ኡማ” ሴት አያት፣ “ኢዜር” አጎት (የአባት ወገን)፣ “አና” አክስት (የአባት ወገን)፣ “ካካ” አጎት (የእናት ወገን)፣ “አክስት” አክስት (የእናት ወገን)፣ ይባላሉ።

ከዚህ በተጨማሪም በሀረሪዎች ዘንድ የቤተሰብ መጠሪያ ያላቸው ቤተሰቦች አሉ:: በሀረሪዎች የዘር ሀረግ ሰንሰለትን መሠረት ያደረገው ቤተዘመድ ‹‹ጋራች›› በሚል መጠሪያ ይታወቃል:: በዚህ የዝምድና መስመር ‹‹ጋራች›› ውስጥ በተለየ ሁኔታ የሚታወቅ ሰው የዚያ ቤተሰብ መጠሪያ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል:: ለምሳሌ ነጪህ አፈር ጋራች (የፈረንጅ ክልስ ያለባቸው ቤተሰቦች)፣ ሲኔ ጋራች (ከትግራይ አካባቢ የመጡ ቤተሰቦች) እንዲሁም በራሶ ጋራች ስራቸው ከማዕድን ጋር የተያያዘ ቤተሰቦች መጠሪያን ያመለክታል:: በዚህ መሰረትም አንድ ቤተሰብ በዘር ሐረጉ ውስጥ በመልካም ስብዕናው፣ ማሕበረሰቡን በማገልገል፣ በልግስናው የሚታወቅ ቀዳሚ የቤተሰብ አባል ስም ላይ ‹‹ጋራች›› በመጨመር ራሱን ይጠራል:: ይህም ‹‹የእገሌ ዘሮች›› ወይም ‹‹እንዲህ አይነት ሥራ የሰሩ ሰዎች ዘሮች›› እንደ ማለት ነው:: ይህ ስያሜ የመጠሪያው ባለቤት የነበሩ ቀደምቶች የሚታወቁባቸውን ምግባራት የሚገልጽ ነው::

የስም አወጣጥ

ስም የአንድ ነገር መጠሪያ በመሆኑ በታሪክ፣ በባሕል፣ በቋንቋ እና በማሕበረሰብ ጥናት ውስጥ ትልቅ ትኩረት ይሰጠዋል:: ነገሮችን፣ ክስተቶችን እና ኡደቶችን አንዱን ከአንዱ ለይቶ ለማወቅም ሆነ ለማጥናት በማሕበረሰቡ የተሰጣቸውን መለያ ስም ወይም ስያሜ ማወቅ የግድ ነው:: ስም በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ ያለው ፋይዳ በመጠሪያነት ብቻ የተገደበ አይደለም:: ይልቁንም ታሪክን፣ ክስተቶችን፣ ታላላቅ ሰዎችን፣ ማሕበራዊ ስኬቶችን እና አጋጣሚዎችን የመዘከር አገልግሎትም ይሰጣል:: ስለዚህም የሰው ልጆች የስም አወጣጥ እና አሰያየም ሥርዓትን ዘርግቷል::

ከስም አወጣጥ ስርዓቶች አንዱ ደግሞ ከሰው ልጅ ልደት ጋር ተያይዞ አዲስ ለተወለዱ ልጆች የሚሰጠው የመጠሪያ ስም ነው:: የተለያዩ ማሕበረሰቦች እንደ ወግና ባሕላቸው፣ ልማድ እና እምነታቸው የተለያዩ የስም ማውጣት ስርዓቶችና አሰያየሞች አሏቸው:: ሀረሪዎችም የራሳቸውን ባሕል እና እምነት ተከትለው አዲስ ተወልደው ማሕበረሰቡን ለሚቀላቀሉ ልጆቻቸው ስም ያወጣሉ:: በሀረሪዎች ባሕል አዲስ ለተወለደ/ች ልጅ ስም የሚወጣው ሕፃኑ/ኗ በተወለዱ በሳምንታቸው ነው:: ስም የማውጣት ሂደቱ የራሱ የሆነ ወግ እና ስርዓት ያለው ሲሆን ከሕፃኑ ወላጆች እና የቤተሰብ አባላት በተጨማሪ ቤተ ዘመድንም ያሳትፋል::

በዚህም መሠረት የሕጻኑ(ኗ) ወላጅ ቤተዘመዶች በሀረሪዎች ዘንድ “ሀሪስ” እየተባለ የሚጠራ ገንፎ እና “ስሪ” የሚባል ዳቦ አዘጋጅተው በአራስ ቤት ይገኛሉ:: ቤተዘመዱ በተዘጋጀው ምግብ ከተስተናገደ በኋላ ስም የማውጣት ሂደቱ ይጀመራል::

በሀረሪ ብሔረሰብ ዘንድ ለልጆች ስም ከሚወጣባቸው መንገዶች አንዱ የአባት ቤተ ዘመድ፣ የእናት ቤተ ዘመድ፣ አባት እና ሌሎች የአባት ወገን አባላት አምስት አምስት ስሞች እንዲያቀርቡ በማድረግ ከቀረቡት ስሞች መካከል እናት ለልጇ የሚሆነውን ስም እንድትመርጥ የሚደረግበት ነው:: በዚህም መሠረት ከቀረቡት ስሞች ውስጥ የወደደችውን ስም ትመርጥና ለልጇ ስም ሆኖ ይጸድቃል:: የዚህ አይነት ስም አወጣጥ ቆየት ባሉት ጊዜያት ሲተገበር የነበረ ነው:: ይህም በአገራችን በስፋት ከተለመደው ስም የማውጣትን መብት ለአባት ከመስጠት በተለየ መልኩ በሀረሪ ለእናቶች የውሳኔ እድል የተሰጠበት ምክንያት ልጅን አርግዛ ከመውለድ፣ አጥብታና ተንከባክባ ማሳደጓ በማሰብ እንደሆነ ይገለፃል::

ሀረሪዎች ስም በማውጣት ሂደት ሰፊ የቤተ ዘመድ አባላትን ማሳተፋቸው ማሕበራዊ ትስስርን ከመፍጠርም ባሻገር የልጃቸው ስም በአንድ ጊዜ በማሕበረሰቡ ውስጥ እንዲታወቅ ያደርጋል:: በዚህም የተነሳ ልጆች ሲያድጉና የእነሱን ስም በማውጣቱ ሂደት የተሳተፉ የቤተዘመድ አባላትን የማወቅ እድሉ ሲያጋጥማቸው በማሕበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ተፈላጊነት እና ቤተሰባዊ ትስስርን የሚያስረዳቸው በመሆኑ ስም የማውጣት ስርዓቱ ከፍ ያለ ማሕበራዊ ፋይዳም ያለው ነው::

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/2016

Recommended For You