ያለፈውን ለማማረር ሳይሆን መጪውን ለማስተካከል በጋራ እንምከር

ባለፉት ሶስት ዓመታት ሀገራችን የተለያዩ የሰላም መደፍረስ ችግሮች አጋጥመዋታል። በችግሩም ውድ ከሆነው የሰው ልጅ ሕይወት ጀምሮ ከፍተኛ ንብረት ውድሟል፤ የዜጎች መፈናቀል በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተከስተዋል። በውጤቱም ብዙዎቻችን ያሳዘነና አንገት ያስደፉ የታሪክ አጋጣሚዎችን ለማሳለፍ ተገደናል።

ችግሮቹን በመቆጣጠር የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የተለያዩ ስራዎች በመንግስት በኩል እየተከናወኑ ቢሆንም፤ ችግሩ ዘርፈ ብዙ፤ ከትናት የተሻገሩ የቤት ስራዎችን ጭምር ያካተተ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር አልተቻለም። ከዚህም የተነሳ ዛሬም የሰላም ጉዳይ ሀገራዊ ፈተና እንደሆነ ይገኛል።

ችግሩን ለዘለቄታው በመፍታት በመላው ሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚችለው በሕዝቦች ይሁንታ በመነጋጋር መተማመንና መስማመት ላይ ሲደረስ መሆኑ ይታመናል። ለዚህ ደግሞ እንደ የኃይማኖት ተቋማት፤ ሲቪክ ማሕበራትና ተመሳሳይ ተቋማት ትልቅ ድርሻ ያላቸው ቢሆንም የእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ግን የተለየ አካሄድን የሚጠይቅ ሆኗል። ይህንንም ከግምት በማስገባት አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ በስራ ለይ ይገኛል።

የምክክር ኮሚሽኑ ዋና ተግባርም ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ መሠረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር በማድረግና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር የመምራትና የማስተባበር ስራዎችን ማከናወን ነው። በዚህ ረግድ የምክክር ኮሚሽኑ መስራት ያለበትን ስራ አቅሙ በፈቀደ በየደረጃው እያከናወነ እንደሆነ እንገነዘባለን። ይህም ሆኖ ግን የምክከር ኮሚሽኑ አላማ ከግብ ሊደርስ የሚችለው ሁላችንም የድርሻችንን ለመወጣት የሚጠበቅብንን ስንሰራ ስለመሆኑ ብዙም ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም።

ከአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የሚጠበቀው፤ የተለያዩ አላማዎችን አንግበው በፖለቲካው መድረኩ ላይ ያሉ ኃይሎችና ልሂቃን እንዲሁም ሕዝቡ ውስጥ ያሉ ጥያቄዎችና ሀሳቦችን በማውጣት ውይይት እንዲደረግባቸው አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር። በዚህም ከማሕበራዊ አስከ ፖለቲካዊ እይታ ያሉ የሀሳብ ልዪነቶች አደባባይ ወጥተው ለአገራዊ አንድነት ገንቢ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ማድረግ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ እያንዳንዳችን እንደ ዜጋ የሚኖረን ድርሻ አለ። ዋናው ነገር በግለሰብ ደረጃ የኔ ተሳትፎ ምንም ለውጥ አያመጣም ከሚል አመለካከት ራሳችንን አላቀን ጉዳይ ከኛው ለእኛው እንደሆነ በመረዳት አጋጣሚውን ለመጠቀም ዝግጁ መሆኑ ላይ ነው።

በቀዳሚነት መገንዘብ ያለብን እኛን ኢትዮጵያውያንን የገጠመን አይነት የጸጥታ መደፍረስ ችግርም እና ሩዋንዳ ባሉና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑን መረዳት፤ የእያንዳንዳችን ተሳትፎ የሚያመጣው ለውጥ እንዳለ ያለ ጥርጥር ለመቀበል እራስን ማዘጋጀት ነው። ጉዳዩ የኛ ሀገሪቷም የእኛ ከመሆኗ አንጻር በምንም አይነት ሁኔታና ስሜት ውስጥ ብንሆን ጉዳዩ አያገባንም ልንል የምንችልበት ምንም አይነት ምርጫ የለንም።

የውይይት መድረኩ/ሜዳው ሀገርን እንደ ሀገር የመታደግ፤ ከግጭት አዙሪት በማውጣት ዘላቂ ሰላምና ልማት መፍጠር በዚህም ለዜጎች የምትመች ሀገር መፍጠር ነው። ለዚህ ደግሞ ያለን አቅም ሙሉ በሙሉ በመጠቀም ለኮሚሽኑ ዓላማ ስኬት የመቆም የዜግነት እና የሞራል ግዴታ አለብን። ለዚህም ይመስለኛል በርካታ ኢትዮጵያውያን የኮሚሽኑን እንቅስቃሴ በትኩረት እየተከታተሉ የሚገኙት።

በርግጥ የምክክር ኮሚሽኑን ዓላማ ያለፈውን ለማማረር ሳይሆን ዛሬንና መጪውን ጊዜ ለማስተካከል ነው። ከላይ እንደተጠቀሰው የምክክር ኮሚሽኑ ዓላማ ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ መሠረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር በማድረግ ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር ነው። ለዚህ ደግሞ ባለፈው ተከስተው የነበሩ ስህተቶች መነሳት አልያም መወሳት ያለባቸው መጪውን ለማስተካከልና በተሻለ መንገድ አቅጣጫ ለማስያዝ ብቻ መሆን አለበት።

የኮሚሽኑ ተግባር ትላንት የተፈጸሙት ስህተቶችና ጥፋቶች እንዳይደገሙ በሕዝቦች መካከል የጋራ መግባባትን መፍጠር እርስ በእርስ መተዋወቅና መረዳዳትን ማስቻል ነው። እንደ ሀገር የገጠሙን ችግሮች በዚሁ መቀጠል አይኖርባቸውም። ለማስቆም ደግሞ የእያንዳንዳችን ተሳትፎ ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ከመቼውም ግዜ በበለጠ ጉዳዩ ዛሬም የነቃ የሕዝብ ተሳትፎ የሚጠበቅበት ወቅት ነው።

በሀገራችን ለሚከሰተው ችግርም ሆነ ለምናገኘው ደስታ ተጋሪም ተካፋይም መሆናችን አይቀርም። ታዲያ እንደ ዜጋ መጪውን ዘመን ከግምት በማስገባት በአንድ ወገን ችግሩን ለመቀነስ ወይንም እንዳይፈጠር ለማድረግ፤ በሌላ በኩል የሰላሙን ዜና ለማብዛት ወስነን ልንቀሳቀስ ይገባል።

እዚህ ላይ ገና ከጅምሩ ከመፍትሄው ችግሩ ገዝፎባቸው ከመነታረክ ውጪ ምንም አዲስ ነገር አይኖርም የሚል እሳቤ ያላቸውና ተስፋ ያጡ ምክክር ክርክር አልያም ድርድር አለመሆኑ ሊገነዘቡና በዚህ በኩል ያለባቸውን ብዥታ ሊያስተካክሉ /ሊያርሙ ይገባል።

ጉዳዩን የበለጠ ግልጽ ለማድረግ በኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ከተቀመጠው ላይ ጥቂት ጀባ ልበላችሁ። ”ምክክር እንደ ድርድር ዜጎች ሊያሳኩ በሚያስቧቸው ውስን የሆኑ ፍላጎቶች ላይ ስምምነቶች እንዲፈጠሩ ከማድረግ ይልቅ ዜጎች ሰብዓዊ፣ ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮቻቸውን በዘላቂነት የሚፈቱበትን መደላድል ይፈጥራል።

”ድርድር የሚታዩ ወይም የማይታዩ ይዞታዎችን በማከፋፈል ወይም ለአንደኛው ወገን በመስጠት ግጭትን ለማብረድ የሚያገለግል ይሆናል። ምክክር ግን በሰዎች መካከል አዲስ የመከባባር፣ የመተማመን እና የመተባበርን ባህል በማዳባር የዜጎችን ግንኙነት ከፍ ለማድረግ ይረዳል።

” በክርክር ውስጥ የሚስተዋለው አንዱ የሌላውን ሀሳብ ውድቅ በማድረግ የበላይነትን ለማሳየት ሲሆን በምክክር ሂደት ውስጥ ግን ይህ ሁኔታ ፈጽሞ አይኖርም:: በምክክር ሂደት የሚሳተፉ ተሳታፊዎች አንዳቸው የሌላኛውን ሀሳብ በአግባቡ በማድመጥ የዚያን ሰው ሀሳብና ፍላጎት ለመረዳት ጥረት ያደርጋሉ፤ በሂደቱም የጋራ የሚሉትን እና የሚያግባቧቸውን መፍትሔዎች ያመነጫሉ::

”በዚህም መሰረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ አካታች አገራዊ ምክክሮችን ማካሄድ የተሻለ አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ፤ በሂደትም የመተማመንና ተቀራርቦ የመስራት ባሕልን ለማጎልበት ፤ እንዲሁም የተሸረሸሩ ማሕበራዊ እሴቶችን ለማደስ ጠቃሚ በመሆኑ ይህንን ከግብ ለማድረስ ምክክር ትልቅ አቅም ይሆናል።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/2016

Recommended For You