አካል ጉዳተኛነት በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ ችግሮች ሊመጣ እንደሚችል እሙን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን በየጊዜው በሚከሰተው የመኪና እና መሰል አደጋዎች፣ በግጭት እንዲሁም በሌሎች ሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት የአካል ጉዳተኛው ቁጥር ከፍ ሊል እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ አካል ጉዳተኞቹ ሰው ሠራሽ የአካል ድጋፍ በቀላሉ ማግኘት ስለማይችሉ ሊሠሯቸው ከሚፈልጓቸው ነገሮች እንዲቆጠቡ መገደዳቸው ደግሞ ችግሩን የከፋ ያደርገዋል፡፡
አሁን ላይ ግን እንዲህ ዓይነቱን ችግር ለማቅለል “የኢትዮጵያ የአካል ድጋፍ አገልግሎት ማዕከል” በይፋ ተመርቆ ለበርካቶች ለመድረስ ሥራውን ጀምሯል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ድረ-ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት “መሥራት፣ ማገልገልና መስጠት እየቻሉ በተለያዩ የአካል ጉዳቶች ሕክምና ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሚሆን እንደ አዲስ የተደራጀውን የኢትዮጵያ የአካል ድጋፍ አገልግሎት ማዕከልን ዛሬ ተመልክተናል፡፡ ለኢትዮጵያ ከዚህም በላይ ትልቅ ተቋም ያስፈልጋታል”፡፡
ማዕከሉ በተፈጥሮ እና በአደጋ ምክንያት የአካል ጉዳተኛ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች በሀገር ውስጥ አጋዥ ቁሶችን ለማምረት እና ለማቅረብ የተቋቋመ ማዕከል ነው፡፡ በተጨማሪም ማዕከሉ አጋዥ ቴክኖሎጂዎችን ለማምረት፣ ለማደስ እና ለማቅረብ የተቋቋመ ሲሆን፤ ተደራሽ፣ ጥራት ያለው እና ደንበኛ ተኮር የሰው ሠራሽ እንዲሁም የአካል ድጋፎች አገልግሎትን ለኅብረተሰቡ የሚሰጥ እንደሚሆን ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በተለያዩ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የተሻለ ሰው ሠራሽ የአካል ድጋፍ የሚያቀርብ ተቋም መገንባቱን የገለጹት ጠቅላይ ሚስትሩ፤ ብዙውን ጊዜ በቂ ትኩረት ስለማያገኙ ማገልገል እየቻሉ ተረጂና ተመጽዋች የሚሆኑ ዜጎች መኖራቸውን አስታውቀዋል፡፡ መንግሥት አካል ጉዳተኞችን የሚያስታውስ ሥራ እናከናውን ብሎ ሲነሳ ብቁ ባለሙያዎች ቢኖሩም፤ በዘርፉ በቂ ግብዓት የተሟላላቸው ተቋማት እንዳልነበሩ በማውሳት፤ አሁን ላይ ዘመናዊ መሣሪያዎች ያሉትና ይበልጥ የተማሩ ባለሙያዎች የታከሉበት፤ እንዲሁም፣ አካል ጉዳተኞችን በማገዝ ረገድ ሰፊ ሥራ የሚከናወንበት ማዕከል መገንባት እንደተቻለ አስረድተዋል፡፡
በጦርነትም ሆነ በተለያዩ አደጋዎች እጃቸውን አሊያም እግራቸውን ያጡ ዜጎች በማዕከሉ ገብተው አጋዥ አካል ወይም ሰው ሠራሽ አካል ተገጥሞላቸው የሚንቀሳቀሱበትና ማገልገል የሚችሉበት ዕድል እንደተፈጠረላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹ ሲሆን፤ ማዕከሉ በቀጣይ በተለያዩ አደጋዎች ምክንያት የጆሮ ማዳመጥ ችግር እና የማየት ችግር ያጋጠማቸውን ዜጎች ጭምር ማገዝ የሚችልበትን አቅም እንዲያገኝ፣ ተቋሙ በቴክኖሎጂ አማካኝነት ዓይነ ስውራንን የሚያግዙ መነጽሮችን ወደ መሥራት ማደግ እንዳለበት አሳስበዋል።
ታካሚዎች በተቋሙ ለሕክምና በሚንቀሳቀሱበት ወቅት አዕምሯቸውን የሚያድሱ አረንጓዴ መናፈሻዎች፣ የስፖርት ማዕከላትና ልምምድ የሚሠሩባቸው ንጹህ ስፍራዎች የተገነባ መሆኑን ሲያስረዱም ‹‹የሰው ልጅ ከአካል ስብራቱ ይልቅ ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስደው የአእምሮ ስብራቱ ነው፡፡ አእምሯችን ሲጎዳ ነፀብራቁ አካላችን ላይ ስለሚታይ መንፈስን የሚያድሱ መሠረተ ልማቶች ናቸው፡፡›› በማለት የማዕከሉን ውብነት ገልጸዋል፡፡
በማዕከሉ ግንባታቸው የተጠናቀቁ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረጊያ ስፍራዎች ማለትም የመዘናኛ ስፍራ፣ የአካል ድጋፍ ማምረቻ እና የፊዚዮቴራፒ መስጫዎች ተገንብተዋል። የማዕከሉን አገልግሎት ማሳደግ ከተቻለም ከኢትዮጵያ አልፎ እና ተርፎ ለአፍሪካም ጭምር በዘርፉ አጋዥ የሆነ ሥራ ለማከናወን መነሻ የሚሆን ማዕከል መሆን ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ አካል ድጋፍ አገልግሎት ማዕከል በቴክኖሎጂ በታገዘ መንገድ ጥራት ያለውና ደንበኛ ተኮር የሰው ሠራሽና የአካል ድጋፍ አገልግሎቶችን ለኅብረተሰቡ እየሰጠ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው ብሔራዊ የአካል ድጋፍና ተሃድሶ ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደ ሥራ የተገባ ሲሆን፤ በተለያዩ ምክንያቶች አገልግሎት መስጠት ያቆሙ የተሃድሶ ማዕከላት ዳግም ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ ተችሏል፡፡ ከዚህ አኳያም በጥቁር አንበሳ፣ ሀረር እና ጋምቤላ ሆስፒታሎች የነበሩ የተሃድሶ ማዕከላት ዳግም አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያ የአካል ድጋፍ አገልግሎት ማዕከል ሁሉን አቀፍ ጥራቱን የጠበቀ የተሃድሶ ሕክምና እና የአካል ድጋፍ አገልግሎት ለመስጠት እንዲያስችለው በማዕከሉ የሰው ኃይል በማቅረብ፣ መሳሪያዎችን በማሟላት እና ከተለያዩ አካላት ድጋፍ እንዲያገኝ በመደረጉ በአሁን ወቅት ለበርካቶች አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
በሀገራችን በተለያዩ አደጋዎችና ሁኔታዎች ምክንያት ለሚከሰት አካል ጉዳተኛነት የአካል ድጋፍ አገልግሎትን ለማሳደግና ችግሩን ለማቅለል ሲባል ከዚህ ቀደም ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ጀርባ ለበርካታ ዓመታት ቀደም ባለ ቴክኖሎጂ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረውን ተቋም በብዙ መልኩ በአዲስ መልክ በማዘመን የኢትዮጵያ አካል ድጋፍ አገልግሎት በሚኒስትሮች ምክር ቤት በ2014 ዓ.ም መቋቋሙን ዶ/ር ሊያ አስታውሰዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት፣ ማዕከሉ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሆነ እና ለሌሎች ፕሮጀክቶች ተምሳሌት የሚሆን ነው። ሌሎች ፕሮጀክቶችም አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ መሆን ያለባቸው ሲሆን፣ ይህንን ያላካተቱ ነባር ፕሮጀክቶች ደግሞ እንደገና የማሻሻል ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ማዕከሉ ከዚህ ቀደም ከውጭ የሚገቡ አካል ድጋፍ ቁሳቁሶችን በራሱ አቅም ማምረት መጀመሩ ትልቅ እምርታ እና ለአካታች የጤና አገልግሎት ተደራሽነት መሻሻል ሚናው የጎላ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
አካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታዎችን እና ድጋፍ ባለማግኘታቸው ምክንያት ከበርካታ ተሳትፎዎች እንዲወሰኑ ያደርጋቸዋል ያሉት ከንቲባዋ፣ በቀጣይም አካል ጉዳተኞችን ያማከል ሥራ በስፋት መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም