ዛሬም ነገም፣ ስለባሕር በር መነጋገር አስፈላጊም አስገዳጅም ነው!

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከጥቂት ሳምንታት በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ስለቀይ ባሕር ጉዳይ ሰፊ ገለፃ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ ገለፃውን ተከትሎ ጉዳዩ የበርካታ ወገኖችን ቀልብ ስቧል፡፡ የባሕር በር እና የወደብ ጥያቄ ከሦስት አስርተ ዓመታት በላይ ኢትዮጵያውያንን ሲያነጋግር የቆየ አጀንዳ በመሆኑ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃ ተገቢና ሕዝባዊ ውይይቶችን የሚጋብዝ እንደሆነ በበርካታ ወገኖች ታምኖበታል፡፡ በሌላ በኩል ጉዳዩ ተገቢና ወሳኝ አገራዊ አጀንዳ ቢሆንም፣ ወቅታዊ የሀገሪቱ ችግሮች ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ የሚገልፁ ወገኖችም አልጠፉም፡፡

በቅድሚያ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ፣ የሕዝብ ብዛት፣ ጂኦ-ፖለቲካዊ ሁኔታዎች እንዲሁም ዓለም አቀፍ የውሃ ሕግጋት ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ያላት ጥያቄ ተገቢና ሕጋዊ እንዲሆን ዋስትና ይሰጣሉ፡፡ ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ኃይል እንደነበረች ታሪክ የሚያውቀው ሐቅ ነው፤ ተፈጥሯዊ አቀማመጧ ለቀይ ባሕር ቅርብ ነው፤ ሀገሪቱ የምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ ጂኦ- ፖለቲካዊ ነባራዊ ሁኔታዎች (ፀጥታና ደህንነት፣ ንግድ፣ የኃያላን አገራት ፉክክር…) የኢትዮጵያን ንቁ ተሳትፎና ክትትል ይፈልጋሉ፤ ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት አገር የባሕር በር አልባ (Land­locked) የመሆኗ መራራ ሐቅ አስደንጋጭና አንገት የሚያስደፋ ነው፡፡

ታዲያ እነዚህ የሚያስቆጩና የሚያስደነግጡ ሐቆች ስለቀይ ባሕር ለማውራት ጊዜ የመምረጥ የቅንጦት እድል ይሰጣሉ? ለመሆኑ ስለቀይ ባሕር ለማውራት ትክክለኛው ጊዜ መቼ ነው? በቀይ ባሕር አካባቢ ያሉ ቀጣናዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ሰፊ የቆዳ ስፋት፣ ትልቅ የሕዝብ ቁጥር፣ ከባሕሩ ጋር ልዩ ታሪካዊና ቅርብ ትስስር ያላትን ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን፣ ‹ትንንሽ› እና ከባሕሩ በብዙ ርቀት ላይ የሚገኙ ሀገራትን ትኩረት በእጅጉ የሚስቡ ናቸው። ከቀይ ባሕር ርቀው የሚገኙ ሀገራት ሁልጊዜም ስለቀይ ባሕር እያሰቡና እያወሩ፣ በቀይ ባሕር ላይ ያለችው ኢትዮጵያ ‹‹ስለቀይ ባሕር ለማውራት አሁን ትክክኛለው ጊዜ አይደለም›› ማለት አይገባትም፡፡

በእርግጥ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በርካታ ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች እንዳሉ አይካድም፡፡ ‹‹ችግር ስላለ ስለሌላ ችግር መወራትና መታሰብ የለበትም›› ማለት ግን ተገቢ አይደለም፡፡ ምናልባትም የቀይ ባሕር ጉዳይ ለብዙዎቹ ምጣኔ ሀብታዊ ችግሮች መፍትሔ የሚሰጥ ዐቢይ ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገለፃቸው፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በዚህ ጉዳይ ላይ መክሮና ዘክሮ፣ ከስሜት ነፃ በሆነ መንገድ አስልቶ ለልጆቹ መልካም ነገር ማስቀመጥ እንዳለበትና አጀንዳው ከፓርቲ ጋር ግንኙነት የሌለው የሀገርና የሕዝብ ብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ እንደሆነ በአፅንዖት አስገንዝበዋል። ‹‹… ኢትዮጵያ በውሃ የተከበበች ደሴት፣ ነገር ግን ውሃ የሚጠማት ሀገር ናት፡፡ የእኛ ሀገር በሙሉ ዙሪያው ውሃ ነው፤ ግን ውሃ ጥማት አለብን … በቀይ ባሕር ጉዳይ የማንወያይ ከሆነ ስለስንዴም ሆነ ስለአረንጓዴ ልማት መነጋገር ማቆም አለብን… የቀይ ባሕር ጉዳይ በደንብ ንግግር ያስፈልገዋል፡፡ ቢሆንም ጉዳዩን አንናገረውም፣ አናነሳውም፣ ‹ለግጭት… ነው› ይባላል፤ ግን እንደዚያ አይደለም፤ እኛ ግጭት አንፈልግም…›› ብለዋል፡፡

አዎ፣ የቀይ ባሕር ጉዳይ ያልተቋረጠ ንግግርና ድርድር ይፈልጋል፡፡ እኛ ብንሸሸውም እሱ ይከተለናል፡፡ ‹‹አጀንዳው ግጭት ይቀሰቅሳል፣ ወዳጆቻችንንና ጎረቤቶቻችንን ያስቀይማል…›› ተብሎ የሚታለፍ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ያላት ጥያቄ የስግብግብነት አልያም ወዳጅን የሚያስከፋ ሳይሆን ፍትሐዊ ተጠቃሚነትንና ዘላቂ ወዳጅነትን የሚያፀና ነው፡፡ በፍትሐዊ ጥያቄ የሚያኮርፍና ለግጭት የሚጋበዝ ወዳጅና ጎረቤት ካለ፣ ወዳጅነቱና ጉርብትናው ከአንጀት ሳይሆን ከአንገት ነበር ማለት ነው፡፡

ይህ ዓይነቱ ወዳጅነት ደግሞ በቀይ ባሕር ብቻም ሳይሆን በሌላ ፍትሐዊ ጥያቄ በሌላ ጊዜም ቢሆን ጭምብሉን አውልቆ መታየቱ አይቀርም፡፡ ኢትዮጵያ የዓባይን ውሃ ሳትጠቀም ከዚህ በላይ መቆየት እንደማትችል በዓባይ ግድብ ግንባታ እንዳሳየች ሁሉ፣ ከቀይ ባሕርም ተገልላ መቀጠል አትችልም። በተለይ የመጪው ጊዜ ነባራዊ ሁኔታዎች ይህን የሚፈቅዱ አይደሉም፡፡

በቀይ ባሕር ላይ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ለኢትዮጵያ ያላቸውን አንድምታ ታሳቢ ያደረጉ ፖሊሲዎችና አሠራሮች ያስፈልጋሉ (እነዚህ አሠራሮች ከብሔራዊ ጥቅም ባሻገር፣ የሕዝቦችን ታሪካዊ ወንድማማችነትና አብሮነት ከግምት ውስጥ ያስገቡ ሊሆኑ ይገባል፤ ኢትዮጵያ ደግሞ ይህን በማድረግ የምትታማ አገር አይደለችም)፡፡ ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር የተነጠለች ሀገር እንድትሆን ያደረጉ አካሄዶች ከዚህ በላይ እንዲቀጥሉ መፍቀድ አይገባም፡፡ ሀገሪቱ ወደ ቀይ ባሕር እንዳትጠጋ የሚሸረቡ ሴራዎችን በጥንቃቄ መመልከትና መመከት ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያን ታሳቢ ያላደረጉ በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባሕር አካባቢ የሚፈጠሩ የፖለቲካና የኢኮኖሚ አደረጃጀቶች ውጤታማ እንደማይሆኑ ማስገንዘብና ኢትዮጵያም የእነዚህ አደረጃጀቶች አባል እንድትሆን ጠንክሮ መታገል ይገባል፡፡ ኢትዮጵያን ያላሳተፈ ‹‹የቀይ ባሕር ፎረም››፣ ‹‹በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ የሚዋሰኑ የዓረብ እና የአፍሪካ መንግሥታትን ትብብርና ቅንጅት የማሻሻል ዓላማ አለኝ›› ቢል፣ ትርፉ ትዝብት ብቻ ነው፡፡

ግብፅና ሱዳን አብዛኛው ውሃው ከኢትዮጵያ የሚመነጨውን ዓባይን ‹‹የሕልውናችን መሠረት ነው›› ካሉ፣ ከቀይ ባሕር ጋር ጥብቅ ታሪካዊና ጂኦ- ፖለቲካዊ ትስስር ያላት ኢትዮጵያም ‹‹ቀይ ባሕር ሕልውናዬ ነው›› የማለት ሙሉ መብት አላት፡፡ ከቀይ ባሕር ተጠቃሚ ለመሆን ከኢትዮጵያ የተሻለ ታሪካዊ፣ ጂኦ-ፖለቲካዊና ሕጋዊ ጥያቄ የማቅረብ ትክክለኛ መብት ያለው አገር ማን ነው?!

ትናንት ስለቀይ ባሕር እየተነጋገርን ከነበረ ትክክል ነበርን፤ ዛሬ ስለቀይ ባሕር እያወራን ከሆነ ትክክል ነን፤ ነገም ስለቀይ ባሕር የምናወራ ከሆነ ትክክል እንሆናለን፡፡ ትናንትም፣ ነገም፣ ዛሬም፣ ሁልጊዜም ስለቀይ ባሕር ለማውራት ትክክለኛ ጊዜዎች ናቸው። በአጭሩ፣ ‹‹ስለቀይ ባሕር ለማውራት ትክክለኛው ጊዜ መቼ ነው?›› ለሚለው ጥያቄ ትክክለኛውና ተገቢው መልስ ‹‹ሁልጊዜም!›› ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን የቀይ ባሕርን ጉዳይ በበላይነት መምራትና ለዓለም ሀገራት ምሳሌ መሆን ሲገባን፣ ቀይ ባሕር ከእጃችን አፈትልኮ የወጣበት አጋጣሚ ታሪካዊ ስህተትና ውርደት መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል። ስለቀይ ባሕር ማሰብና መወያየት ይህን ታሪካዊ ስህተት የማረም የረጅሙ ጉዞ መጀመሪያ እርምጃ እንደሆነ መረዳት ይገባል፡፡

ታዲያ በዚህ ረጅም ጉዞ ውስጥ ዋናውና አስፈላጊው ነጥብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ የተናገሩት ነው … ትልቅ የጦር ኃይል አለኝ ተብሎ በስሜት ተገፋፍቶ ጉዳዩን በኃይል አስፈፅመዋለሁ ማለት ተገቢ አይደለም፤ የኃይል አማራጭ ተገቢ አይደለም ተብሎ ደግሞ እውነታውን መደበቅና ስለጉዳዩ አለመነጋገር ትክክል አይደለም፡፡ መወያየት፣ መነጋገር፣ መደራደር፣ ሰጥቶ መቀበል፣ በጋራ መጠቀም፣ አብሮ ማደግ፣ ዘላቂ ሰላምና እድገትን እውን ማድረግ! የኢትዮጵያ ፍላጎትም ሆነ ተገቢው መንገድ ይህ ብቻ ነው! ዛሬም ነገም በሰከነ መንፈስ ስለቀይ ባሕር እናውራ፣ እንነጋገር!

ፒያንኪ ዘኢትዮጵያ

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You