«ለሁሉም ጊዜ አለው፤»

ትውልድ ቢሔድ ቢመጣ ዘመን የማይሽረው ወርቅ የጠቢቡ ይትበሀል አለ። «ለሁሉም ጊዜ አለው፤» የሚል። ዘመን ተሻጋሪ። ዛሬም ያልጨረተ። ሕያው። በታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ መክብብ 3:1-8 ላይ ደግሞ፤«ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው፤ ከሰማይ በታች ለሚከናወነው ለማንኛውም ነገር ወቅት አለው፤ ለመወለድ ጊዜ አለው፤ ለመሞትም ጊዜ አለው፤ ለመትከል ጊዜ አለው፤ ለመንቀልም ጊዜ አለው፤ ለመግደል ጊዜ አለው፤ ለማዳንም ጊዜ አለው፤ ለማፍረስ ጊዜ አለው፤ ለመገንባትም ጊዜ አለው፤ ለማልቀስ ጊዜ አለው፤ ለመሣቅም ጊዜ አለው፤ ለኀዘን ጊዜ አለው፤ ለጭፈራም ጊዜ አለው፤ ድንጋይ ለመጣል ጊዜ አለው፤ ድንጋይ ለመሰብሰብም ጊዜ አለው፤ ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው፤ ለመለያየትም ጊዜ አለው፤ ለመፈለግ ጊዜ አለው፤ ለመተው ጊዜ አለው፤ ለማስቀመጥ ጊዜ አለው፤ አውጥቶ ለመጣልም ጊዜ አለው፤ ለመቅደድ ጊዜ አለው፤ ለመስፋትም ጊዜ አለው፤ ለዝምታ ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው፤ ለመውደድ ጊዜ አለው፤ ለመጥላትም ጊዜ አለው፤ ለጦርነት ጊዜ አለው፤ ለሠላምም ጊዜ አለው።»ይለናል።

ይህ ታላቅ ቃል ተገቢውን ጊዜ መርጦ ማድረግ ወይም “ታይሚንግ/timing”ለሕዝበ አዳም ስጋም ሆነ ነፍስ አስፈላጊ መሆኑን ያመለክታል። በተለይ ለመሪነት ወይም ለአመራር ደግሞ እስትንፋስ ነው ማለት ይቻላል። የአንድን መሪ ስኬት ወይም ውድቀት የመበየን አቅም እንዳለው የዘርፉ ልሒቃን አጽንኦት ይሰጣሉ። ታይሚንግ ተገቢውንና ትክክለኛውን ጊዜ መርጦ የመወሰን ወይም ለድርጊት የመነሳት ችሎታ ነው። በእጅ የገባን መልካም አጋጣሚን ሳያባክኑ መጠቀምም ነው። ከዚህ በተጨማሪ ለውጥን ለመተግበር ፣ ትክክለኛውን መልዕክት በትክክለኛው ጊዜ ለማስተላለፍ ወይም ለተግባቦት ፣ ለቀውስ አመራር ፣ መሪው በስሩ ካሉ አመራሮች ጋር ሳይቀር ለመነጋገርና አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘውም ጣልቃ ለመግባት ታይሚንግ ወሳኝ ነው። በአጠቃላይ ታይሚንግ የተዋጣለት መሪ መለያ ነው።

ስለ ታይሚንግ ይህን መንደርደሪያ እንዳነሳ በተለይ ያስገደደኝ ሰሞነኛው የባሕር በር ጥያቄ ነው። 120 ሚሊዮን ሕዝብ ላለውና ከ1.1ሚሊዮን ስኩየር ኪሜ ስፋት ለሚያካልል እና በአመት ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለወደብና ለኪራይ ለሚያወጣ ፤ ለእልፍ አእላፍ አመታት ባለወደብ ለነበረ ሀገር የወደብ ጉዳይ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ቀዳሚ አጀንዳም ነው። ጥያቄው ይሄን አንገብጋቢ አጀንዳ ወደፊት የአመጣንበት ታይሚንግ ተገቢ ነው የሚለው ነው። እንደ ጓያ ነቃይ የፊት የፊቱን እንዲሉ ሌሎች የባሱ የፊት የፊት አጀንዳዎች የሉንም ወይ። ሠላምና ደህንነት፣ የኑሮ ውድነት፣ ሀገራዊ ምክክር፣ የሽግግር ፍትሕ፣ ወዘተረፈ ውዝፍ አጀንዳዎች ከፊት እያሉ በአናቱ የወደብን ጉዳይ የማምጣት ታይሚንግ ትክክል ነው ስል እጠይቃለሁ። እስኪ ሃሳብ እንሰናዘርበት።

በነገራችን ላይ የሀገራችን ባሕር በርና ወደብ አልባ መሆኗ እንደ እግር እሳት ከሚያንገበግባቸው ዜጎች አንዱ ነኝ። ደርግን ፣ ሕወሓትንና ሸዓብያን እንዲሁም ታሪካዊ ጠላቶቻችን ከዚህ ታላቅ ደባ ጀርባ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ስላሉበት ፖለቲካዊ ነፍስ ካወቅሁበት ጀምሮ እንዳወግዝኋቸው አለሁ። በተቀረው አጀንዳ ሆኖ የሚነሳበት ትክክለኛ ጊዜው መቼ ነው ከሚለው ውጪ የባሕር በር ወይም የወደብ ጉዳይ ሀገራዊ አንገብጋቢ አጀንዳ መሆኑን እገነዘባለሁ። ሆኖም ያለንበት ሁኔታ ጥያቄው የሚነሳበት ትክክለኛ ጊዜ ነው ወይ ስል እጠይቃለሁ። ነገርን ነገር ያነሳዋልና ከዚህ ሰሞነኛ ጉዳይ ጋር ተያይዞ በአማርኛው የሪፖርተር ጋዜጣ ላይ የተነሱ ሃሳቦችን ላካፍላችሁ።

ዮናስ አማረ ባለፈው እሁድ ለንባብ በበቃው የአማርኛ ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ባስነበቡን መጣጥፍ የቅርብ ታሪካዊ ዳራውን በማንሳት ይጀምራል። የኤርትራን ዕጣ ፈንታ የሚወስነው ሕዝበ ውሳኔ ሊካሄድ በዋዜማው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተቃውሞ ማስነሳታቸው ይታወሳል። እ.ኤ.አ. ጃኑዋሪ 4 ቀን 1993 በሺህ የሚቆጠሩ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች አደባባይ ወጥተው ታላቂቱን ሀገር ኢትዮጵያ የሚከፋፍልና ወደብ አልባ ሀገር የሚያደርግ ነው ያሉትን የኤርትራን መገንጠል በመቃወም መውጣታቸው አይዘነጋም። የጊዜው መንግሥት ለዚህ ተቃውሞ የሰጠው ምላሽ ጠንከር ያለ ነበር። በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት ዕርምጃ ቆሰሉ። ሁለት ተማሪዎች በሆስፒታል እንዳሉ መሞታቸውም ተረጋገጠ።

ኢትዮጵያ የባሕር በር አልባ ሀገር እንዳትሆን የሚለው የብዙ ዜጎች ጩኸት ሰሚ አጥቶ ቀረ። የኤርትራ መገንጠል ጉዳይ አፍጥጦ መጣ። ግንቦት 16 ቀን 1985 ዓ.ም. በተካሄደ ሪፈረንደም ኤርትራ ሉዓላዊት ሀገር ሆነች። ከኤርትራ ሕዝበ ውሳኔ ጎን ለጎን ይነሳ የነበረው የባሕር በር ወይም የወደብ ጥያቄም በጊዜው በነበረው መንግሥት ሆን ተብሎ ወደ ጎን መገፋት መጀመሩን ብዙዎች ያስታውሱታል። የታሪክ ምሁሩ ዳግማዊ ተስፋዬ (ዶ/ር) ከ1985 እስከ 1992 ዓ.ም. በነበሩት ዓመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ልሂቃን፣ እንዲሁም በአካዳሚክ ማኅበረሰቡ ዘንድ በባሕር በር ጉዳይ ከፍተኛ ውይይቶችና ክርክሮች ይደረጉ እንደነበር ያስታውሳሉ። ነገር ግን ይህንን ሁኔታ ያልወደደው የጊዜው አስተዳደር ሆን ብሎ በሚመስል መንገድ እነዚህን ውይይቶች እንዲዳፈኑ አድርጓል ይላሉ።

በጊዜው የነበረው ሥርዓት ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበሩት ሌተና ጄኔራል አበበ ተክለ ሃይማኖት እ.ኤ.አ. በ2007 ‹‹Ethiopian’s Sovereign Right of Access to the Sea Under International Law›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት መመረቂያ ጽሑፍ፣ የባሕር በር ጉዳይ ወደ ጎን የተገፋበትን መነሻ ምክንያት በሰፊው አብራርተዋል። ‹‹የገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እስከ 1994 ዓ.ም. ነበርኩ። የጦሩ ከፍተኛ አመራር እንደመሆኔ መጠን መንግሥት በባሕር በር ጉዳይ ላይ ያለውን አቋም በቅርበት ማወቅም ነበረብኝ። በጊዜው የባሕር በር ጥያቄን በተመለከተ የተለየ ምስጢራዊ አቋም አልነበረንም።

የእኛ ዋናው ትኩረት ኢትዮጵያ የባሕር በር ጉዳይን ረስታ፣ ተጨባጩን ሀቅ ተቀብላ ሠላም በመገንባትና ድህነትን በማጥፋት ላይ ብታተኩር ይሻላል የሚል ነበር። ‹‹በጊዜው እኔም ሆነ ብዙዎቹ በከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ያሉ ባለ ሥልጣናት የባሕር በር ጉዳይን ማንሳት፣ ከአዲሱ ሕገ መንግሥታችን ጋር የሚጋጭ ነው ብለን እናስብ ነበር። የባሕር በር ጥያቄ የሚያነሱት ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 39 የደነገገውን የብሔር ብሔረሰቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብት የሚቃወሙ ናቸው ብለን እናስብ ነበር።

«የኤርትራን ነፃነት የማይቀበሉ ያለፈው የፊውዳላዊና የወታደራዊ ሥርዓት ናፋቂዎች ናቸው። የባሕር በር ጥያቄ የሚያነሱት የሚል አመለካከት ነበረን። ኢትዮጵያ የባሕር በር ወይም ወደብ ሊኖራት ይገባል የሚሉ ወገኖችን ፍፁም ስቃወም ነበር የኖርኩት፤›› በማለት ሌተና ጄኔራል አበበ በዚህ ጥናታቸው አስፍረዋል። ልክ እንደዚህ ወደ ጎን ሲገፋ የቆየው የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ከኤርትራ መገንጠል ጋር ተያይዞ ጠንከር ብሎ ቢነሳም፣ መንግሥት ጉዳዩ አይነሳብኝ በማለቱ ከውይይት መድረኮች ርቆ መቆየቱ ይታወሳል። ከ40 ያላነሱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በ1985 ዓ.ም. ከሥራ መባረራቸው መንግሥት በአካዳሚክ ማኅበረሰቡ ዘንድ የባሕር በር ጉዳይ እንዳይነሳ በመፈለጉ እንደሆነ ይወሳል። በዚህ ጊዜ የኤርትራ ሕዝበ ውሳኔ እንደሚካሄድ፣ እንዲሁም የባሕር በር ጥያቄ ገፍቶ እንደ መምጣቱ የመንግሥት ዕርምጃ ይህንኑ ፀጥ ለማሰኘት ያለመ ነበር የሚል ግምት አስነስቶ አልፏል።

የኤርትራ መገንጠል ኢትዮጵያ የባሕር በር አልባ አድርጓታል ቢባልም፣ ኢትዮጵያ በኤርትራ ወደቦች በነፃነት መገልገል እንደቀጠለች ታሪክ ያወሳል። በተመድ ሪሊፍ ዌብ በተባለ ድረ ገጽ ላይ የሠፈረው፣ ‹‹Eritrea – Ethiopia: IRIN Focus on Assab‚ 5 June 2000›› በሚል ርዕስ የቀረበው ሀተታ ኢትዮጵያ በአሰብ ወደብ ከቀረጥና ከታሪፍ ነፃ በሆነ መንገድ መጠቀም መቀጠሏን ያወሳል። ስትገነጠል ለኢትዮጵያ አሰብ ወደብን በነፃነት እንድትገለገልበት ፈቅዳ የነበረችው ኤርትራ፣ በሒደት ግን ከጎረቤቷ ጋር አለመስማማት ውስጥ እንደገባች ተጠቅሷል። ለሁለቱ ተጎራባቾች አለመግባባት ምንጭ የነበሩት ደግሞ የወደብ አስተዳደር ጉዳይ፣ የኮሚሽን ክፍያና የመገበያያ ገንዘብ ጉዳይ አንደነበሩ ተመላክቷል። የሁለቱ ተጎራባቾች ውዝግብ በሒደት መካረሩንና ወደ ድንበር ጦርነት መሸጋገሩን ዘገባው ያትታል። ከድንበር ጦርነቱ በፊት ለኢትዮጵያም ሆነ ለራሷ ለኤርትራ ከፍተኛ የባሕር ንግድ መተላለፊያ በር የነበረው አሰብ ወደብ በሒደት ጥቅም አልባ ወደመሆን መሸጋገሩን ይህ ዘገባ ጨምሮ ያብራራል።

ኤርትራ ነፃ ሀገር ስትሆን የአሰብ ወደብ 70 በመቶ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን ነበሩ። ኢትዮጵያ ወደቡን ላለመጠቀም ወስና ወደ ጂቡቲ ወደብ ፊቷን ስታዞር ግን ይህ ሁኔታ መቀየሩ ይነገራል። ሁለቱ ሀገሮች ወደ ጦርነት ሲገቡ ደግሞ አንዱ የሌላውን ሀገር ዜጋ በማስወጣቱ ከአነስተኛ ንግድ እስከ የወደብ አገልግሎት ሥራዎች ተሰማርተው የቆዩ አሰብ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዕጣ ፈንታም መፈናቀል መሆኑ ተነግሯል። የኤርትራ ሰዎች ለወደብ አገልግሎቱ ይከፈለን የሚሉት ኮሚሽን እየጨመረ መምጣቱ እንደ ችግር ተነስቷል። የመገበያያ ገንዘባቸውን ወደ ናቅፋ በመቀየር የንግድ ሚዛንን ለማስቀየር መሞከራቸውም ሌላው እንቅፋት ተብሏል። በሌላ በኩል አንዲት ፍሬ ቡና ሳያመርቱ የኢትዮጵያን ቡና በርካሽ እየገዙ ከአፍሪካ ቀዳሚ የቡና ላኪ ሀገሮች ተርታ ለመሰለፍ መሞከራቸው ልዩነቱን የሚያሰፋ ብልጣ ብልጥ ዕርምጃ በሚል ይነገራል።

ዘገባው እንደሚለው ኮሚሽን የሚቀበሉበትን የወደብ መሠረተ ልማት ኢትዮጵያ በራሷ ወጪ ልታድስ ይገባል የሚል አቋም ኤርትራውያኑ ይዘው ነበር። በሌላ በኩል በሶቪየት ኅብረት ድጋፍ ተገንብቶ በነበረው የድፍድፍ ነዳጅ ማጣሪያ አጠቃቀም ላይ ጥያቄ መፈጠሩ ይነገራል። ለኤርትራም ሆነ ለኢትዮጵያ አገልግሎት ይሰጥ የነበረውንና የጋራ ሀብት ሆኖ የሚታየውን የነዳጅ ማጣሪያ ኢትዮጵያ በራሷ ወጪ ታድሰ መባሉ የሁለቱን ሀገሮች ግንኙነት ካሻከሩ ምክንያቶች እንደ አንዱ ይወሳል። በዚህ ሁሉና በሌሎችም ተደራራቢ ምክንያቶች ወደ ጦርነት የገቡት ኤርትራና ኢትዮጵያ ከጦርነቱ በኋላ መልሰው ጉርብትናቸውን ለማደስ በመቸገራቸው የኢትዮጵያ የወደብ አገልግሎት አማራጭ በጂቡቲ ላይ ብቻ የተገደበ ሆኖ እንደቆየ ይነገራል። የታሪክ ምሁሩ ዳግማዊ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ታኅሣሥ 3 ቀን 1993 ዓ.ም. አልጄርስ የተፈረመው የሠላም ስምምነት የኢትዮጵያን የወደብ ጥያቄ ጉዳይ የተከደነ አጀንዳ እንዳደረገው ይናገራሉ። ከሺህ ዓመታት በላይ ወደብ አጥታ የማታውቀዋ ኢትዮጵያ ‹‹የወደብ አልባነት ክስተት ገጠማት›› ሲሉ ያስረዳሉ።

አክሱም የአዱሊስ ወደብን በ702 ዓ.ም. በዓረቦች ወረራ በማጣቷ መዳከሟን ያነሱት ምሁሩ፣ ሆኖም በመካከለኛው ዘመን ሀገሪቱ እንደዘይላ ባሉ ወደቦች መገልገሏን ያወሳሉ። ይህ ሁሉ አልፎ ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በኋላ ሀገሪቱ መልሳ ወደብ አልባ መሆኗ በብዙ መንገድ ለጉዳት እንደዳረጋት ነው የሚናገሩት። የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ እ.ኤ.አ. ጁላይ 16 ቀን 2013 ላይ ለወደብ ኪራይ ሀገሪቱ በቀን ሁለት ሚሊዮን ዶላር ትከፍላለች ማለታቸውን ያስታውሳሉ። በዓመት እስከ ሁለት ቢሊዮን ዶላር አሁን ድረስ ታወጣለች መባሉንም ተጨማሪ የጉዳት ማሳያ አድርገው አስቀምጠውታል።

የዓለም አቀፍ ሠላም ጥናት መምህሩ አቶ ጋረደው አሰፋ በበኩላቸው፣ ‹ኢትዮጵያ እንደ አሰብ ባሉ ወደቦች ካልተጠቀመች ወደቡ የግመል መጠጫ ይሆናል› በሚል የተንሸዋረረ ዕይታ መሪዎቿ ታላቂቱን ሀገር ወደብ አልባ አድርገዋት መኖራቸውን ይናገራሉ። ኢትዮጵያ የባሕር በር አልባ ሀገር መሆኗ ሀገራዊ የሥነ ልቦና መቃወስን የፈጠረ ጉዳይ መሆኑንም ይገልጻሉ። ወደብ አልባ መሆን ከሥነ ልቦና አልፎ ዲፕሎማሲያዊ መሽመድመድንም በኢትዮጵያ ላይ ያስከተለ ስለመሆኑ አስረድተዋል።

በ1985 ዓ.ም. የተመድ ዋና ጸሐፊ ግብፃዊው ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ ኤርትራን ለማስገንጠል አዲስ አበባ ሲገቡ ለተቃውሞ አደባባይ ከወጡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል ሰባት ተማሪዎችን መግደሉና ብዙዎችን ማቁሰሉ የሚነገረው የያኔው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ በወደብ ጉዳይ አንዳችም ምክረ ሃሳብም ሆነ ተቃውሞ እንደማይሻ ቁርጥ አቋም የያዘ ይመስል ነበር ይባላል። ‘በጂቡቲ ላይ ብቻ ጥገኛ ሆነን እንዴት ልንዘልቀው ነው’ የሚሉ ድምፆች መስሚያ አልነበራቸውም ይባላል።

የጊዜው መንግሥት በወደብ ጉዳይ የሚነሱ ሃሳቦችንም ሆነ ሃሳብ ሰጪዎችን በቀናነት መመልከት የተወ እንደነበር ታሪክ ከትቦታል። ሌላው ቀርቶ ስለቀይ ባሕር የተሠሩ ፊልሞች ከመድረክ እንዲወርዱ መደረጉ ይነገራል። በአርቲስት ጥላሁን ጉግሳ የተሠራው ፊልም የገጠመው ዕጣ ይህ ነበር ይባላል። ድምፃዊ ቴድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) በ1997 ዓ.ም. በሠራው አልበም ውስጥ ያካተተው ‹ካብ ዳህላክ› ሙዚቃ ሕዝብ ቢወደውም የወቅቱን አገዛዝ ክፉኛ ያበሳጨ እንደነበር ይነገራል።

የኢሕአዴግ አስተዳደር የባሕር በር ጉዳይ አይነሳ ቢልም ጉዳዩ ጭርሱን ተዳፍኖ አለመቅረቱ ይነገራል። ታሪክን፣ ጂኦግራፊን፣ ኢኮኖሚንም ሆነ ጂኦ ፖለቲካዊ መነሻ ነጥቦችን ተመርኩዘው የባሕር በርና የወደብ አስፈላጊነትን በየጊዜው ለመተንተን የሞከሩ ወገኖች ግን ኢትዮጵያ በኪራይ ወደብ ያውም በጂቡቲ ላይ ብቻ ጥገኛ ሆና መዝለቁ እንደሚከብዳት ለረጅም ጊዜ ሲወተውቱ ቆይተዋል። ከጂቡቲ ጋር 349 ኪሎ ሜትር ድንበር የምትጋራው ኢትዮጵያ፣ ከኤርትራ ጋር 912፣ ከኬንያ 861፣ ከሶማሊያ 1‚600፣ ከሱዳን 744፣ እንዲሁም ከደቡብ ሱዳን ጋር 1‚114 ኪሎ ሜትር የድንበር መስመሮችን የምትጋራውና ምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ ለሚባለው ቀጣና እምብርት የሆነችው ኢትዮጵያ ያለ ወደብ መቅረቷ ብዙ ሀገር ወዳድ ዜጎችን ሲያሳስብ የቆየ ጉዳይ እንደነበር ይታወቃል።

ኢትዮጵያ በየቀኑ ከ3.3 ሚሊዮን በላይ በርሜል ነዳጅ ዘይት ለሚተላለፍበትና የዓለማችን ወሳኝ ንግድ መስመር ለሆነው ለቀይ ባሕር ቀጣና የቅርብ ሩቅ ሆና መኖሯ ቢዳፈንም፣ ውስጥ ውስጡን ሲብላላ የቆየ ጉዳይ ነበር ይባላል። በየቀኑ ከ160 በላይ ግዙፍ የንግድ መርከቦች የሚቀዝፉበት ቀይ ባሕር ከ700 ቢሊዮን ዶላር በላይ የዓለም ዓመታዊ ንግድ ልውውጥ የሚካሄድበት ነው። የስዊዝ ቦይና የሕንድ ውቅያኖስ መገናኛ የሆነው ቀይ ባሕር የእስያንና የአፍሪካ አኅጉራትን ከአውሮፓ አኅጉራት ጋር የሚያስተሳስር የዓለም ቁልፍ የንግድ መስመርም ነው።

ሻሎም ! አሜን።

 በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ጥቅምት 28/2016

Recommended For You