ጉዳዩ፤
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2009 ዓ.ም የጋራ መኖሪያ ቤት በኪራይ መልኩ የተቀበሉ መምህራን በ1997 ዓ.ም የጋራ መኖሪያ ቤት ተመዝግበው ሲቆጥቡ የቆዩ በ13 ኛው ዙር የዕጣ ዕድለኛ የሆኑት በዕጣ በወጣላቸው እና በኪራይ እየኖሩበት ያለው ቤት ተመሳሳይ ከሆነ በአንዱ ውል እንዲይዙ ምርጫ ተሰጣቸው፡፡መምህራኑም በምርጫቸው መሠረት በኪራይ መልኩ ይዘውት የነበረውን ቤት መረጡ፤ ውል ለመዋዋልም ተንቀሳቀሱ።
በወቅቱም መዋዋል የምትችሉት በ13ኛው ዕጣ ዋጋ ነው ተባሉ። ይህም ትልቅ ቅሬታና አለመግባባት ፈጠረ። በ2011 ዓ.ም የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በተመለከተ የወጣውን መመሪያ የሚጥስ እንደሆነም መምህራኑ አመለከቱ፡፡በመመሪያው መሠረት መስተናገድ አልቻልንም ሲሉ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የመልካም አስተዳደርና ምርመራ ቡድን ቅሬታቸው አቀረቡ፡፡
የመምህራን ቅሬታ፤
በ2009 ዓ.ም የቤት ኪራይ ከተላለፈላቸው 5000 መምህራን መካከል የተወሰኑት 1997 ዓ.ም የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተመዝጋቢ በመሆናቸው ቤት ደርሷቸዋል፡፡ይህንንም ተከትሎ በ2011 ዓ.ም ለመምህራን በኪራይ ስለሚቀርቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለማስተላለፍና ለማስተዳደር በወጣው መመሪያ ቁጥር 01/2011 መሠረት፤ በኪራይ መልኩ እየኖሩበት ያለውና በ13ኛው ዙር ዕጣ የደረሳቸው ቤት ተመሳሳይ ከሆነ በኪራይ በያዝነው ቤት ውል መዋዋል እንደምንችል የሚገልጽ ነው፡፡
ይህንን የቤቶቹን የወቅቱን ዋጋ ተገማች ያደረገ መመሪያ መሠረት በማድረግ፤ በዕጣ የደረሰን ቤትና በኪራይ መልኩ እየኖርንበት ያለው የጋራ መኖሪያ ቤት ተመሳሳይ ስለሆነ መቀየር እንፈልጋለን ብለን አመለከትን፡፡መመሪያውን ታሳቢ ባደረገ መልኩም መቀየር ትችላላችሁ የሚል ምላሽ ተሰጠን ይላሉ፡፡
መመሪያው በሚለው መሠረት ሂደቱን ተከትለን ለማስፈጸም መንቀሳቀስ ጀመርን፡፡ይህ ሲሆን የአዲስ አበባ ቤቶች ኤጀንሲ የአሁኑ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን እስካሁን ድረስ ስንከፍል የነበረው የቤት ኪራይ ሳይያዝ፤ ቤቱ በወቅቱ በነበረው ዋጋ ማስተላለፍ ሲገባቸው በ13ኛው ዙር ዕጣ በወጣበት በ2013 ዓ.ም በኮዬ ፈጬ ዋጋ እንዲተላለፍ አደረጉ፡፡
እኛም አሠራሩ ትክክል አይደለም፤ ልንስተናገድ የሚገባው /በ2009 ዓ.ም ባለው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዋጋ ነው በሚል ቅሬታችንን ይዘንን እንዲያስተናግዱን አቤት አልን። የቤቶች ልማት ምላሽ ግን እኛ ትክክል ነን፤ በመመሪያው መሠረት ነው የሠራነው የሚል ሆነ፡፡
በዚህ ሂደት ላይ የአዲስ አበባ ካቢኔ ጥያቄያችን በሚቀበልና ትክክለኛነቱን በሚያረጋግጥ መልኩ ውሳኔ አሳለፈ፡፡ይህን መሠረት በማድረግም ጥያቄያችንን ብናቀርብም በአግባቡ አዳምጦ ለማስተናገድ ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡በወቅቱ የሚሰጡን ምላሽም ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ዕዳ አለበት፤ እናንተን አናስተናግድም አሉ፡፡
የምናስተናግዳችሁ የከተማ አስተዳደሩ ከመወሰኑ በፊት ባለው ነው ጨርሳችኋል የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው በመጠቆም፤ለጉዳያችም ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆን አልቻሉም፤ ስለችግሩም የከተማው ትምህርት ቢሮ እና መምህራን ማኅበሩም ያውቃሉ፡፡
ካቢኔው የወሰነው ውሳኔ የእኛን ጥያቄ በሚደግፍ መልኩ በመሆኑ ልንስተናገድ የሚገባን ባቀረብነው ውሳኔ ነው የሚሉት መምህራኑ፤ የቤቱን ውል ልንዋዋል የሚገባን በ2009 ዓ.ም በነበረው ዋጋ እንጂ በ13ኛው ዙር ዕጣ በወጣበት ዋጋ አይደለም ባይ ናቸው፡፡በተጨማሪም እስካሁን በኪራይ መልክ ስንከፍለው የነበረው ገንዘብ እንደ ወጪ አልተያዘልንም የሚልም ቅሬታ አላቸው፡፡
ከመመሪያው ውጪ በ13ኛ ዙር ዕጣ ዋጋ እንድንስተናገድ የተፈለገው ለምንድን ነው? ፤ በ2009 /በ2013 ዓ.ም ባሉት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዋጋ መካከል በአንድ ቤት ከ50ሺ ብር በላይ የዋጋ ልዩነት አለው፡፡ይህን የዋጋ ልዩነት መክፈል ለእኛ ለመምህራን ከባድ ነው ሲሉም ቅሬታቸውን ያቀርባሉ፡፡
የኮርፖሬሽኑ ምላሽ፤
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የጋራ መኖሪያ ቤቶች ማስተላለፍ ዳይሬክተር ካሳሁን ዘውዴ በመምህራኑ ቅሬታ ዙሪያ ፤ በሰጡት ምላሽ፤ የጋራ መኖሪያ ቤቱ በ2009 ዓ.ም በኪራይ መልኩ ለመምህራን ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ከዚያም ሐምሌ 3/2013 ዓ.ም ላይ በኪራይ የነበሩ ቤቶች በሙሉ /በወቅቱ በተላለፈበት ወቅቱ ሲባል/ 2009 ዓ.ም በተላለፈበት ዋጋ ግምት ውስጥ ገብቶ ለመምህራን እንዲሰጥ በካቢኔ ተወስኗል፡፡
መመሪያው በወቅቱ ሲል መምህራኑ ቤቱን ባገኙበት ወቅት በነበረው ዋጋ ማለቱ ነው፡፡መመሪያ በተለያየ መልኩ የኪራይ ቤቱን የያዙ ሲልም ከኪራይ ውጪ በዕጣ የደረሳቸው መምህራ አሉ ማለት ነው ፡፡ መምህራኑ የተሰጣቸው አንድ ዕድል ነው፡፡ከሁለቱ አንዱን ዕድል መምረጥ ይገባቸዋል፡፡ይህም የያዙትን ቤት ይዘው መቀጠል ወይም ደግሞ ዕጣ የወጣላቸውን ቤት መያዝ ነው፡፡
ስለዚህ በኪራይ ቤት ይዘውት የነበረውን ቤት ለመውሰድ ሲወስኑ፤ በዕጣ የወጣላቸው ቤት ላይ ቤቱ ለራሳቸው ስለወጣ፤ የወጣላቸውን ቤት ተመላሽ በማድረግ በኪራይ መልክ እየኖሩበት ያለውን መዋዋል ይችላሉ፡፡ልዩነት የሚፈጥረው የሚዋዋሉበት ዋጋ ነው፡፡
ዕጣ የወጣላቸው በ13ኛ ዙር ከሆነ ዕጣ በወጣላቸው ዋጋ /በወቅቱ ሲስተም ውስጥ በተቀመጠው ዋጋ / ገንዘቡን ከፍለው ይዋዋላሉ፡፡ በኪራይ የነበሩበትን ቤት ይዘው መቀጠል የሚፈልጉ ደግሞ በሁለት መልኩ ይስተናገዳሉ፡፡ አንደኛው ልክ ዕጣውን በሚዋዋሉበት ጊዜ የዕጣውን ልመልስና በኪራይ የያዝኩት ላይ አሁን ባለው በወቅቱ ዋጋ ልስተናገድ ማለት ነው፡፡ይህንን ሲወስኑ በወቅቱ ሲስተሙ ውስጥ በገባው ዋጋ ይስተናገዳሉ፤ በዚህም አግባብ የተስተናገዱ አሉ።
የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ በጉዳዩ ላይ ሐምሌ 3 ቀን 2013 የደረሰበት ውሳኔ ፤ በኪራይ የነበሩ ቤቶች በወቅቱ በነበረው ዋጋ ማለትም በ2009 ዓ.ም በነበረው ዋጋ እንዲስተናገዱ የሚጠይቅ ነው፡፡ከሐምሌ 3 ቀን 2013 በኋላ የነበሩ ጥያቄዎችም በዚሁ አግባብ ተስተናግደዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ከሆነ፤ እስካሁን ያልከፈሉና ያልተስተናገዱ ካሉ ቢመጡ በ2009 በነበረው ዋጋ ይስተናገዳሉ፡፡ቀድመው የከፈሉትና ውል የያዙት ግን ብሩ ሊመለስላቸው አይችልም፡፡ምክንያቱም የገባው ወደ መንግሥት ካዝና ነው፡፡ውሳኔው ወደ ኋላ ጎትተንና መልሰን ሰዎችን ተጠቃሚ የምናደርግበት አግባብ የለም፡፡ ይህ ዕድል ነው፡፡
በዚህ መሠረት መስተናገድ የሚፈልጉ መምህራን ወደ ቤቶች ልማት መጥተው መስተናገድ ይችላሉ፤ እስካሁን ሲኖሩበት የነበረው የመንግሥት ቤት በእጃቸው መኖሩንና ኪራይ መክፈላቸውን የሚያሳይ መረጃና ከትምህርት ቢሮ የተጻፈ ደብዳቤ ይዘው መቅረብ አለባቸው፡፡ቤቱ የተሰጠው ለመምህራን እና ለትምህርት ቢሮ ከመሆኑ አንጻር ፤ ትምህርት ቢሮ የሚያስፈልገውን መረጃ ትክክለኝነት አረጋግጦ መላክ እንደሚኖርበትም ኃላፊው አመልክተዋል፡፡
ከሰነዶች የተገኙ መረጃዎች ለኮርፖሬሽኑ የተጻፈ ቅሬታ፤
መምህራን ቅሬታቸውን በቀን 02/07/2013 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ፤ በኪራይ በተሰጣቸው ቤቶች ውስጥ እየኖሩ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ እንዲሁም ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ሲቆጥቡና ሲጠባበቁ ቆይተው የ13ኛው ዙር የኮንዶሚኒየም ቤት ባለ ዕድል መሆናቸውን ይጠቅሳል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ግን ለመምህራን በኪራይ ስለሚቀርቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለማስተላለፍና ለማስተዳደር በወጣ መመሪያ ቁጥር 01/2011 መሠረት በክፍል አራት(4) በአከራይና ተከራይ መብትና ግዴታ በተዘረዘረው ቁጥር 20 ልዩ የተከራይ መብት ንዑስ ቁጥር 3 ላይ በተገለፀው መሠረት፤ መምህሩ የቤት ኪራይ ተጠቃሚ ሆኖ መንግሥት በዘረጋው የቤት ልማት ፕሮግራም በራሱ ወይም በትዳር አጋሩ ስም ቤት ዕጣ ከደረሰው ተመሳሳይ የቤት ዓይነት ከሆነና በኪራይ የያዙትን ቤት ከፈለጉ በወቅቱ በሚኖረው የቤት የማስተላለፊያ ዋጋ ግምት ተሰልቶ በረጅም ጊዜ ሽያጭ በስሙ እንዲተላለፍት ይደረጋል ይላል፡፡ይሁንና፤ በ13ኛው ዙር ቤት ደርሶን ቅያሬ በመጠየቅ በመመሪያው መሠረት መዋዋል ሲገባን ይህ አልሆነም፡፡
በመሆኑም በ13ኛው ዙር በቤት መተላለፊያ ዋጋ እንድንዋዋል መደረጉ መመሪያውን የጣሰ በመሆኑ፣ በተለያዩ ዙር የተላለፉ ቤቶችን በአንድ ዓይነት የመተላለፊያ ዋጋ እንድንከፍል መደረጋችን፤ ሙሉ ዕድሜውን በመምህርነት እስከ ጡረታ እያገለገለ ያለውን መምህር ተጠቃሚነት ያላገናዘበ እና በመመሪያ ተራ ቁጥር 20 ንዑስ ቁጥር 1 (አንድ) ከግምት ውስጥ ያላስገባ አሠራር እየተሠራ መሆኑ፤ ተመሳሳይ የቤት ዓይነት በተለዋጭ ተተክተው ለሌላ ለሚተላለፍለት ወገን የማስተላለፊያ ዋጋ እና እየኖርንበት ያለው የኮንዶሚኒየም የተላለፈበት ዋጋ ከግምት ውስጥ ያላስገባ በመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ ለመምህራን በኪራይ ስለሚቀርቡ መኖሪያ ቤቶች በወጣው መመሪያ መሠረት እንዲያዋውለን እና በወቅቱ በሚኖረው የቤት የማስተላለፊያ ዋጋ እንድንከፍል ወይንም እንዲተላለፍልን የሚል ማመልከቻ በፊርማቸው አስደግፈው ለከተማው ቤቶች ኤጀንሲ ያስገቡ ሲሆን በግልባጭም ለአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ እና ለአዲስ አበባ መምህራን ማህበር አሳውቀዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በደብዳቤ የሰጠው ምላሽ፤
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን መምህራን ላቀረቡት ቅሬታ መጋቢት 29 ቀን 2013 ዓ.ም በደብዳቤ ቁጥር ቤ/ል/ኮ/ቁ1/19/ 8938 ለቀረበው ቅሬታ ከመመሪያ አንጻር መልስ መስጠትን ይመለከታል በሚለው ደብዳቤው፤ መምህራኑ በቀን 02/07/13 ዓ.ም በተጻፉት ማመልከቻ ከአሁን በፊት ለመምህራን መንግሥት ባመቻቸው ፕሮግራም በኪራይ የጋራ መኖሪያ ቤት አግኝተው እየኖሩበት መሆኑን በመግለፅ በጋራ መኖሪያ ቤት ፈላጊዎች ምዝገባ ተመዝግበው ሲጠባበቁ በ13ኛው ዙር ዕጣ ባለ እድል መሆናቸውን በመግለጽ ለመምህራን በኪራይ ስለሚቀርቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለማስተላለፍ እና ለማስተዳደር በወጣው መመሪያ ቁጥር 1/2011 ክፍል 4 በአከራይና ተከራይ መብትና ግዴታ በተዘረዘረው ቁጥር 20 ልዩ የተከራይ መብት ንዑስ ቁጥር 3 ላይ በተገለጸው መሠረት፤ መምህሩ የቤት ኪራይ ተጠቃሚ ሆኖ መንግሥት በዘረጋው የቤት ልማት ፕሮግራም በራሱ ወይም በትዳር አጋሩ ሥም የቤት ዕጣ ከደረሰው ተመሳሳይ የቤት ዓይነት ከሆነና በኪራይ የያዙትን ቤት ከፈለጉ በወቅቱ በሚኖረው የጋራ መኖሪያ ቤት ማስተላለፊያ ዋጋ ግምት ተሰልቶ በረጅም ጊዜ ሽያጭ በስሙ እንዲተላለፍለት ይደረጋል ይላል፡፡
ነገር ግን በ13ኛው ዙር ቤት ደርሶን ቅያሬ በመጠየቅ በመመሪያው መሠረት መዋዋል ሲገባን፡- በ13ኛው ዙር የቤት ማስተላለፊያ ዋጋ እንድንዋዋል መደረጋችን መመሪያውን የጣለ በመሆኑ፤ በተለያዩ ዙሮች የተላለፉ ቤቶችን በአንድ ዓይነት የማስተላለፊያ ዋጋ እንድንከፍል መደረጋችን፤ ሙሉ ዕድሜውን በመምህርነት እስከጡረታ እያገለገለ ያለውን መምህር ተጠቃሚነት ያላገናዘበ እና መመሪያ ተራ ቁጥር 20 ንዑስ ቁጥር አንድን ከግምት ውስጥ ያላስገባ አሠራር እየተሠራ መሆኑ፤ ተመሳሳይ የቤት ዓይነት በተለዋጭ ተተክተው ለሌላ ለሚተላለፍለት ወገን የማስተላለፊያ ዋጋ እና እየኖርንበት ያለው ኮንዶሚኒየም የተላለፈበት ዋጋ ከግምት ውስጥ ያላስገባ በመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ ለመምህራን በኪራይ ስለሚቀርቡ መኖሪያ ቤቶች በወጣው መመረያ መሠረት እንዲያዋውለን እና በወቅቱ በሚኖረው የማስተላለፊያ ዋጋ እንድንከፍል ስንል በሙሉ ድምፅ በፊርማችን በማረጋገጥ እናመለክታለን በማለት በጠየቁት መሠረት የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ኮርፖሬሽኑ እንደሚለው፤ ጥያያቄዎቹ ሁሉም በአንድ ጉዳይ ላይ በወቅታዊ የጋራ መኖሪያ ቤት ማስተላለፊያ ዋጋ እንድንከፍል መደረጉ መመሪያ የጣሰ ሥራ ተፈጽሞብናል የሚል እና የመምህራንን ተጠቃሚነት ያላገናዘበ አሠራር እየተሠራ ነው የሚል ነው ሲል ያጠቃልለዋል፡፡ይሁንና ተቋሙ በመመሪያና አሠራር የሚመራ በመሆኑ በዚህም መሠረት በ13ኛው ዙር የጋራ መኖሪያ ቤት ዕጣ እድለኞች ሆነው በኪራይ ከያዙት ቤት ጋር ተመሳሳይ ለሆነ መምህራን በዕጣ የደረሰን ቤት ተመላሽ ተደርጎ በኪራይ የተሰጠን ቤት በመመሪያው መሠረት በሽያጭ ይተላለፍልን ብላችሁ ባቀረባችሁት ጥያቄ መሠረት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ለመምህራን በኪራይ ስለሚቅርቡ ቤቶች ለማስተላለፍና ለማስተዳደር በወጣው መመሪያ ቁጥር 1/2011 ክፍል አራት መሠረት፤
አንቀጽ 20 ንዑስ አንቀጽ 1‹‹ተከራይ ሙሉ ዕድሜውን በመምህርነት እስከ ጡረታ ካገለገለ እስከዚያ የከፈለው ኪራይ ታስቦ ባለው መደበኛ አሠራር የቀሪውን የቤቱን ዋጋ በወቅቱ በሚኖረው የቤት ማስተላለፊያ ዋጋ ግምት ተሰልቶ በረጅም ጊዜ በሽያጭ ቤቱ ይተላለፍለታል›› በሚለው መሠረት እየተሠራ መሆኑ፣ በዚሁ እንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 3 «መምህሩ በቤት ኪራይ ተጠቃሚ ሆኖ መንግሥት በዘረጋው የቤት ልማት ፕሮግራም በራሱ ወይም በትዳር አጋሩ ሥም የቤት ዕጣ ከደረሰው ተመሳሳይ የቤት ዓይነት ከሆነና በኪራይ የያዙትን ቤት ከፈለጉ በወቅቱ በሚኖረው የቤት ማስተላለፊያ ዋጋ ግምት ተሰልቶ በረጅም ጊዜ ሽያጭ በስሙ እንዲተላለፍለት ይደረጋል» በሚለው እና ባቀረባችሁት ጥያቄ መሠረት እንድትስተናገዱ የተደረገ ሲሆን በወቅቱ በሚኖረው የቤት ማስተላለፊያ ዋጋ ማለት አሁን ያለውን ማለት ሲሆን በዚህም መሠረት በ13ኛው ዙር የጋራ መኖሪያ ቤት በተወሰነው የካሬ ማስተላለፊያ ዋጋ መሠረት እንድትከፍሉ መደረጉ ትክክለኛ በመመሪያው እና ባለው አሠራር መሠረት የተሠራና እየተሠራ ያለ መሆኑን እናሳውቃለን ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡
‹‹ፍትሃዊነት የጎደለው ምላሽ››
ምንም እንኳን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን መምህራን ላቀረቡት ቅሬታ መጋቢት 29 ቀን 2013 ዓ.ም ለቀረበው ቅሬታ ከመመሪያ አንጻር መልስ መስጠትን ይመለከታል በሚለው ደብዳቤው፤ ለሰጠው ምላሽ መምህራኑ በቀን 12/08/2013 ዓ.ም በፃፉት ደብዳቤ ‹‹ፍትሃዊነት የጎደለው ምላሽ›› ሲሉ አጣጥለውታል፡፡
ደብዳቤው ላቀረብነው አቤቱታ ፍትሃዊ ያልሆነ ምላሽ እና መሪያውን ያላገናዘበ መልስን ይመለከታል ሲል፤ ኮርፖሬሽኑ የሰጠው ምላሽ የመምህሩን ተጠቃሚነት ያላገናዘበ ከማንኛውም የቤት ተጠቃሚ ዜጋ የበለጠ እንዲከፍል መደረጉ፤ በዕጣ የደረሰንን ወይም ተመላሽ ያደረግነውን ቤት ኮርፖሬሽኑ ለሌላ የሚያስተላልፍበት የቤት ዋጋ እና በመመሪያው መሠረት በቅያሬ ያገኘነውን ቤት አሁን ባለው የቤት ማስተላለፊያ ዋጋ ማዋዋሉ በሕግ አግባብ ትክክል አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡በተጨማሪም እስከአሁን ስንከፍለው የነበረው አለመያዙ በራሱ መምህሩን ተጠቃሚ ያላደረገ እና ዕጣው የወጣው ከመሪያው በኋላ መሆኑ በአጠቃላይ መምህሩን ተጠቃሚ ያላደረገ እንዲያውም ተጎጂ በማድረጉ መምህራን ማኅበሩም ሆነ ትምህርት ቢሮው ለተሰጠው መልስ በጥንቃቄ እንዲያየው አሳስበዋል፡፡
የካቢኔ ውሳኔ፤
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ15ኛው መደበኛ ስብሰባ ቀደም ሲል ለመምህራን በኪራይ የተላለፉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በሽያጭ እንዲተላለፍላቸው ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ተግባራዊ ለማድረግ ከትምህርት ቢሮ አመራርና ባለሙያዎች፤ ከመምህራን ማህበር ተወካዮችና ከቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን አመራርና ባለሙያዎች በቀን 11/01 2014 ዓ.ም የተደረገ ቃለ ጉባዔ እንደሚከተለው ሰፍሯል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ለመምህራን በኪራይ ተሰጥቶ የነበረ ቤት በሽያጭ እንዲተላለፍላቸው ከወሰነበት ቀን ጀምሮ የሽያጭ ውል እስከሚጠናቀቅበት ቀን ድረስ በጡረታ የሚገለሉ መምህራን ኪራይ የከፈሉት ገንዘብ ታስቦላቸው በ2009 ዓ.ም በነበረው የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤት ማስተላለፊያ ዋጋ መሠረት ይስተናገዳሉ፡፡በሹመት ከመምህርነት ሥራ የለቀቁ መምህራን ሹመት ላይ ስለመሆናቸው ከፓርቲ ጽሕፈት ቤትና ከትምህርት ቢሮ ማረጋገጫ ደብዳቤ ማቅረብ አለባቸው ይላል፡፡
የቤቶቹ የማስተላለፊያ ዋጋም በካቢኔው ውሳኔ መሠረት የ2009 ዓ.ም የ20/80 የጋራ መኖሪያ ቤት ማስተላለፊያ ዋጋ ሆኖ፤ ለስቱዲዮ 2483 በካሬ ሜትር፣ ለባለ አንድ 3438 በካሬ ሜትር እና ለባለ ሁለት መኝታ 4394 በካሬ ሜትር ይሆናል፡፡ይሁንና በአሠራር ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ከሁለቱ ተቋማት የተውጣጡ ኮሚቴዎች በማደራጀት ለትምህርት ቢሮና ለቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ኃላፊዎች አቅርቦ ውሳኔ እንዲሰጥበት ይደረጋል ሲል አስቀምጧል፡፡
መመሪያው ምን ይላል?
ለመምህራን በኪራይ ስለሚቀርቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለማስተላለፍና ለማስተዳደር የወጣ መመሪያ ቁጥር 01/2011 የአከራይና ተከራይ መብትና ግዴታ አንቀጽ 20 ልዩ የተከራይ መብት በሚለው ሥር የተቀመጡ ዝርዝር አስረጂዎች መካከል፤ ተከራይ ሙሉ ዕድሜውን በመምህርነት እስከ ጡረታ ካለ እስከዚያ የከፈለው ኪራይ ታስቦ ባለው መደበኛ አሠራር የቀሪውን የቤቱን ዋጋ በወቅቱ በሚኖረው የቤት ማስተላለፊያ ዋጋ ግምት ተሰልቶ በረጅም ጊዜ ሽያጭ ቤቱ ይተላለፍለታል ይላል፡፡
በሁለተኛው ተራ ቁጥር ደግሞ ተከራይ በመምህርነት እያገለገለ እያሉ በሞት ቢለዩ በዚህ አንቀጽ ንፁስ አንቀጽ አንድ በተገለፀው አግባብ የትዳር አጋር እና ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ልጆች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል ሲል ያስቀምጣል፡፡እንዲሁም መምህሩ የቤት ኪራይ ተጠቃሚ ሆኖ መንግሥት በዘረጋው የቤት ልማት ፕሮግራም በራሱ ወይም በትዳር አጋሩ ሥም የቤት ዕጣ ከደረሰው ተመሳሳይ የቤት ዓይነት ከሆነና በኪራይ የያዙትን ቤት ከፈለጉ በወቅቱ በሚኖረው የቤት የማስተላለፊያ ዋጋ ግምት ተሰልቶ በረጅም ጊዜ ሽያጭ በስሙ እንዲተላለፍለት ይደረጋል፡፡በተጨማሪም በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንጽ 3 ቀደም ሲል ተከራይ በኪራይ የያዘውን ቤት በረጅም ጊዜ ሽያጭ በሥሙ እንዲተላለፍለት ከተደረገ አከራይ ተመሳሳይ የቤት ዓይነት በተለዋጭ የሚተካ ይሆናል ሲል መመሪያው በግልፅ አስቀምጧል፡፡
ሞገስ ተስፋ እና ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ጥቅምት 28/2016