በርግጥም የሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን የሉአላዊነትና የክብር ጉዳይ ነው

ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ያለፈችባቸው የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች የበርካታ ችግሮቿ ጠባሳዎች ናቸው። ይህ እውነታ ለሰብአዊ እርዳታዎች እጆቿን ወደሌሎች ሀገራት እንድትዘረጋ ሲያስገዳዳት ቆይቷል።

ሀገራችን እስከዛሬ በውስጥና በውጭ ኃይሎች በተነሱባት ጦርነቶች የሕይወት ጥፋትና የንብረት ወድመት ሰለባ ሆናለች። ይህን ተከትሎ በሚፈጠሩ ስደትና መፈናቀሎችም በርካታ ሰብአዊ ጉዳቶች አጋጥመዋታል። የጦርነት ክፋት መልከ ብዙ ነው። በሰው ልጆች ላይ ከሚያደርሰው መቅሰፍት ባለፈ የሚያስከትላቸው ችግሮች ተዘርዝረው አያልቁም።

ጦርነት ባለበት ሀገር ገበሬው ከአርሻው አይውልም። ከአውድማው እህል ከቡቃያው ምርት አይታይም። ሰኔ ሐምሌ፣ እሸት፣ ልምላሜ ይሏቸው በረከቶች ሁሉ የ‹‹ነበር›› ታሪክ ይሆናሉ። ጦርነት ሀገር ይፈታል፣ ቤተሰብ ይበትናል። ከመንደር ቀዬ አፈናቅሎ ባሕር አሻግሮ ያሰድዳል። ጦርነት ያየው ሕዝብ ከመንደሩ ውሎ አያድርም። ነፍሱን ለማዳን ቤት ንረቱን ጥሎ ይፈናቀላል።

ለእንዲህ ዓይነት እውነታዎች አዲስ ያልሆነው የሀገራችን ሕዝብ በስደትና መፈናቀል መንገዶች ደጋግሞ ተመላልሷል። እንዲህ በሆነ ጊዜ ከውጭ ሀገራትና ከራስ ወገን ጓዳ ‹‹እነሆ›› የሚሉ እጆች መጣመራቸው ሰብአዊ ድጋፎች መበርከታቸው ዕሙን ነው ።

ከራሷ ዜጎች ባለፈ በጦርነት ሳቢያ የሚሰደዱ የውጭ ሀገራት ዜጎችን ተቀብላ ማስተናገዷም አዲስ አይደለም። አሁንም ድረስ ይህቺን ምድር በእንግድነት የሚረግጡ ስደተኞች የዓመታት ኑሮን እያሳለፉ ይገኛሉ። ይህ እውነታ እንዳለ ሆኖ በሀገራችን ሕዝቦች ላይ አሁንም ድረስ የሚደርሰው መፈናቀል የትኩረት ዓይኖች እንዲያርፉበት የሚያሻው ነው።

በጦርነትና ድርቅ ምክንያት ከመኖሪያ ቀያቸው የሚፈናቀሉ ወገኖች ምንጊዜም የሌሎች አካላት እገዛና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ይህ ዓይነቱ ችግር እየተደጋገመ ሲመጣ ደግሞ ሁሌም እጅን ለእርዳታ ከመዘርጋት የሚያሳጥር መላና መፍትሔ መቀየሱ አይቀሬ ይሆናል።

ከሰሞኑ ይፋ የሆነውና ይህን ሀቅ የሚያረጋግጠው የመንግሥት ሃሳብ በጉዳዩ ላይ ትኩረት እንዲሰጥበት አመላካች የመሆን ፋይዳ አለው። በኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በኩል የተሰጠው መግለጫ እንደሚያመላክተው፣ የሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን የሉአላዊነትና የክብር ጉዳይ ጭምር ነው።

የብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ምክር ቤት ሰብሳቢው አቶ ደመቀ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ለራሷ ምላሽ መስጠት መቻሏ ሰብአዊ ድጋፍ ለሚያሻቸው ወገኖች አቅምን ይፈጥራል። ይህ ተግባራዊ ይሆን ዘንድም የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ ይጠበቃል።

በዓመታዊው የብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ምክርቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ እንደተጠቆመው የልማት ሥራዎችን ማጠናከር የሰብአዊ ድጋፉን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማጎልበትና አቅምን ለመገንባት ያግዛል።

በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን የተለያዩ ስፍራዎች የተፈናቃይ ወገኖች ቁጥር በብዛት ተመዝግቧል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉትም በክልሎች ለሚገኙና አፋጣኝ ምላሽ ለሚያሻቸው ተፈናቃዮች ዝርዝር ዕቅድ ማዘጋጀት ተገቢነት ይኖረዋል።

አስካሁን በነበሩ ተሞክሮዎች በየጊዜው ለሚያጋጥሙ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች እርዳታ የመጠየቅ ልማድ አዲስ ሆኖ አያውቅም። አሁን ግን ችግሩን በዘላቂነት ለመቋቋም የሚያስችል ጠንካራ ራስን የመቻል ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።

ራስን ከተረጂነት አላቆ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ላይ ለመድረስም በጋራ የመሥራት አስፈላጊነትን አቶ ደመቀ አስምረውበታል። ለዚህም ክልሎች በአካባቢያቸው ችግሮች እንዳይከሰቱ ከማድረግ ባለፈ በራሳቸው አቅም ተገቢውን ምላሽ የመስጠት አቅምን ሊያዳብሩ ይገባል።

ኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ ዓመታት ባጋጠሟት ችግሮች ከተረጂነት ልማድ ሳትወጣ ቆይታለች። ይህ እውነታም ለራሷ ችግር ራሷ እንዳትደርስ ምክንያት ሆኖ ነበር። በስብሰባው ላይ እንደተጠቀሰውም ይህ ዓይነቱ ሀቅ ሀገራችን በሉአላዊነቷ ምሉዕ ሆና እንዳትዘልቅ አድርጓታል።

የብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም በበኩላቸው እንደገለጹት ፣ የሀገርን ክብር አስጠብቆ ከተረጂነት ለመላቀቅ የሰብአዊ ድጋፍ ፍላጎትን በራስ አቅም መሸፈን ሊለመድ ይገባል።

ተደጋግሞ እንደሚነገረው ከተፈናቃዮች እርዳታ ጋር ተያይዞ ሊፈጸሙ የሚችሉ የሙስና ተግባራት የአገልግሎቱ ስጋት ናቸው። የስብሰባው ሃሳብ እንደሚጠቁምው ግን ለእንደህ ዓይነቱ ችግር ትክክለኛውን የተረጂዎች ቁጥር አስቀድሞ መለየት አንዱ መፍትሔ ይሆናል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ እርዳታን ላልተገባ ጥቅም የሚያውሉ ራስ ወዳዶችን በሕግ ተጠያቂ ማድረግ የግድ ይላል። ጠንካራ የሚባል ተቋማዊ አደረጃጀትን በማስፋትም ከተረጂነት ስሜት መላቀቅ አስፈላጊ ነው።

በሀገራችን በተለይ በድርቅ ምክንያት የሚፈናቀሉ ወገኖች በሚያጋጥማቸው የከፋ ችግር ከቀያቸው ርቀው ይጓዛሉ። ለዚህ መሰሉ ችግር መፍትሔ ለመሻትም በኢትዮጵያ የተለያዩ ስፍራዎች የሚገኙ ቦታዎችን ማልማት ተገቢ ይሆናል።

በስብሰባው እንደተጠቀሰው ደግሞ፣ በሀገሪቱ የተሟላ የመስኖ ልማት ከተዘረጋለት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ እስካሁን መልማት የቻለው 65 በመቶው ብቻ ነው። በመሆኑም ቀሪውን ቦታ በመንግሥት ደረጃ በማልማት የታሰበውን ዓላማ ዕውን ማድረግ ይቻላል።

የታሰበውን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ክልሎች የሚያዝላቸውን በጀት በተገቢው መንገድ ሊጠቀሙበት ይገባል። የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ እንዳሉትም፣ ክልሎች በየጊዜው የሚመደብላቸውን የእርዳታ በጀት በአግባቡ ማስተዳደር ኃላፊነታቸው ሊሆን ይገባል።

ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የሚገኘውን በረከት ዕውን ለማድረግ ምርቱ በተገቢው መንገድ ለተጠቃሚው ሊደርስ ይገባል። ለዚህ ደግሞ የገበያው ሥርዓት በአግባቡ ተመርቶ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ መሆን አለበት። በገበያው ላይ የሚስተዋሉ ስብራቶችን ጠግኖ ክፍተቶችን ለመሙላትም የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፎ አስፈላጊ ነው። ለዚህ ተግባራዊነትም ከፌዴራል እስከ ወረዳ የሚዘረጉ መዋቅሮች በአግባቡ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል።

የሰው ሠራሽና ተፈጥሮ አደጋዎች ሲደርሱ ለሀገር ከፍ ያለ ድህነት ያቀብላሉ። ሕዝቦች በተገቢው መንገድ በዕድገት ጎዳና እንዳይራመዱም ጋሬጣና ዕንቅፋቶች ናቸው። በነዚህ ችግሮች መዘዝ ሀገር ኢኮኖሚዋ ይሳሳል። ጓዳዋ ይራቆታል። ህልውናዋ ከአደጋ ስለሚወድቅም በሌሎች ሀገራት ደጋፊነት እንድትቀጥል ትገደዳለች።

ለዜጎች መፈናቀል ምክንያት የሚሆኑ ችግሮችን ከማጥናትና አስቀድሞ መፍትሔ ከመስጠት ባለፈ ችግሩ ሲከሰት የራስን መላ ማፈላለግ ተገቢ እንደሚሆን ይታመናል። ለዚህም ከመንግሥት ለውጡ በኋላ ተግባራዊ መደረግ የጀመሩትን የሌማት ቱርፋት፣ የበጋ መስኖና መሰል እንቅስቃሴዎች ወደተግባር መለወጥ ያስፈልጋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዳሉትም! የሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን የሉአላዊነትና የክብር ጉዳይ ነው። የሀገርን ክብር በማስጠበቅ ከተረጂነት ለመላቀቅም የሰብአዊ ድጋፍ ፍላጎትን በራስ አቅም መወጣትን መላመድ ይገባል።

ሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም መወጣት ብሔራዊ አርበኝነትን የሚጠይቅ የቁርጠኝነት ስሜት ነው። ኢትዮጵያ በሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ለተጎዱ ወገኖቿ በራሷ አቅም ተግባራዊ ምላሽ እንድትሰጥም የሁሉም አካላት ሀብረት ክንደ ብርቱ ሊሆን ግድ ይለዋል።

እንዲህ ሲሆን ሰው የመሆን ትርጉሙ ይደምቃል። ሰብአዊነት ቃሉ ይገዝፋል። ኢትዮጵያዊነት ይሉት ስም ከቦታው ይገኛል። አንድነትና መተሳሰብ ዕውን ሆኖም ‹‹ከራስ ቆርሶ ለራስ ማጉረስ›› ብሂል በተግባር ይታያል።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 28/2016

Recommended For You