የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ለመተግበር መንግሥት የወሰደው ቁርጠኛ ርምጃ የሚበረታታ ነው!

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ያህል የዘለቀውና የብዙዎችን ሕይወት የቀጨው፤ ያፈናቀለውና ለስደት የዳረገው ጦርነት የተቋጨበት የፕሪቶሪያው ስምምነት ከተፈረመና ኢትዮጵያም ፊቷን ወደ ሰላም ካዞረች አንድ ዓመት ተቆጠረ፡፡

በዚህ አንድ ዓመት ሰላም ከመስፈኑ ባሻገር የትግራይ፤ የአማራና የአፋር አርሶ አደሮች ወደ ግብርና ሥራቸው ተመልሰዋል፤ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን እንደገና የማቋቋም ሥራዎች ተጀምረዋል፤ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ተመልሰዋል፤ የተፈናቀሉ ዜጎችም ወደ ቀያቸው ተመልሰው ሰፍረዋል፡፡ በአጠቃላይ ሕይወት ከጦርነቱ በፊት እንደነበረችው ለመመለስ በመንግሥትና በሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እንዲሁም በመላው ሕዝብ ተሳትፎ የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡

በተለይም መንግሥት በጦርነቱ በእጅጉ የተጎዳውን የትግራይ ሕዝብ መልሶ ለማቋቋምና ጦርነቱ ያሳረፈበትን ሥነልቦና ለማከም በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ከስምምነቱ መፈረም በኋላ የጥላቻውን ጉም በመግፈፍ ወደ ትግራይ በግንባር ቀደምነት የተጓዘው በአፈ ጉባዔው የተመራው የፌዴራል መንግሥቱ ልዑክ ነበር። ይህ ልዑክ ከተጓዘ በኋላ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የባንክና የአውሮፕላን አልግሎቶች በፍጥነት እንዲጀምሩ ተደርገዋል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በተመሠረተ ጊዜ መሳሳብና መጓተትን ለማስቀረት ሲባል የአመራሩን ድርሻ ክልሉ እንዲወስድ በማድረግ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ፋታ አግኝቶ ፊቱን ወደ ሰላምና ልማት እንዲያዞር ተደርጓል።

የግብርና ሥራውን ለማገዝ የሚመለከተው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በክልል ደረጃ ከሚጠበቅበት በላይ ሠርቷል። ዩኒቨርሲቲዎችንና ትምህርት ቤቶችን ወደ አገልግሎት ለመመለስ የትምህርት ሚኒስቴር በርካታ ተግባራትን አከናውኗል። በክልሉ ተቋርጦ የነበረውን ትምህርት እንዲጀመር ከማድረግ ባሻገር ከሁለት ዓመታት በኋላ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ተማሪዎች እንዲወስዱ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ተችሏል፡፡

የመከላከያ ሠራዊት የሕዝቡን ችግር ለመፍታት ከራሱ በጀት ቀንሶ አያሌ ተግባራት አከናውኗል። የሰላም ስምምነቱን እንደ ዕድል በመጠቀም ሕዝብን ከችግር በማዳን፣ መንግሥታዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በማስመጀር ኃላፊነቱን ተወጥቷል። ከፌዴራል መንግሥቱም አልፎ ክልሎች ከአነስተኛ በጀታቸውና ገቢያቸው በመቀነስ የትግራይ ክልልን ደግፈዋል።

ሆኖም በመንግሥት በኩል የተደረገውን ያህል የሚመጥን ምላሽ ከዚያኛው ወገን አልተገኘም፡፡ በሰበብ አስባቡ የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚጋፉ ድርጊቶችና አሉታዊ ሃሳቦች ጭምር በየጊዜው ሲደመጡና ሲታዩ አንድ ዓመቱ አልፏል፡፡ የፕሪቶሪያው ስምምነት የሰላም ስምምነቱን የፈረሙ አካላት ከአሉታዊ ድርጊቶችና ንግግሮች እንዲታቀቡ የሚያስገድዳቸው ቢሆንም ሌላኛው ወገን አካላት ስምምነቱን የሚጥሱ ድርጊቶችና ሃሳቦችን ሲያንጻባርቅ ታይቷል፡፡

ሆኖም የፕሪቶሪያው ስምምነት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የሚያጸናና የዜጎችን ሰቆቃ የሚቀርፍ ስምምነት በመሆኑ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሚተገበር ነው፡፡ ስምምነቱ የኢትዮጵያን መሠረት ከማጽናቱም ባሻገር በጦርነት ሰቆቃ ውስጥ የነበሩትን የትግራይ፤ የአማራና የአፋር ሕዝቦችን እፎይታ ያጎናጸፈ ነው ፡፡

ከፕሪቶሪያው ስምምነት ቀጥሎ የተካሄደው የናይሮቢ ስምምነት መተማመንን የፈጠረና ኢትዮጵያ የጀመረችውን የሰላም መንገድ የሚያጸና ነው፡፡ በተለይም በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጡ መሠረተ ልማቶችንና ሰብዓዊ ድጋፎችን በሚፈለገው መልኩ ለማድረስ መሠረት የጣለ ነው፡፡ በዚሁ መሠረትም በትግራይ፤ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ተቋርጠው የነበሩ የቴሌኮሙኒኬሽን፤ የኤሌክትሪክና የባንክ አገልግሎቶች መልሰው ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ለማድረግ አስችሏል፡፡

ስለዚህም ለሀገር ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን መሠረት ያደረገውና የዜጎች ሰቆቃ እንዲያበቃ ያደረገው የፕሪቶሪያው ስምምነት መፈጸም ከሁሉም ወገን የሚጠበቅ ግዴታ ነው፡፡ ያለውም ብቸኛ አማራጭ ይህንን ስምምነት መፈጸምና ማስፈፀም ብቻ ነው።

ነገር ግን ከመንግሥት ውጪ ያሉ አካላት እነዚህን ስምምነቶች በተደጋጋሚ ሲጥሱ ይታያሉ፡፡ ይህ ደግሞ እንደ ሀገር የሰፈነውን የሰላም አየር የሚበርዝና ዳግም ወደ ጥፋት የሚወስድ በመሆኑ ሊታረም ይገባል!

አዲስ ዘመን ጥቅምት 28/2016

Recommended For You