ሀገር እና ሊቀ ሃሳቦች

ሀገራችን ኢትዮጵያ በተግባቦት መንፈስ ሀገራዊ አንድነትን ለመፍጠር የምክክር ኮሚሽን አቋቁማ ከዛም ዘለግ ሲል የተለያዩ የምክረ ሃሳብ መድረኮችን አዘጋጅታ የአንድነት ጎዳናዎቿን በማሰናዳት ላይ ትገኛለች፡፡ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አንጻር ስንቃኘው ያለፉትን ሁለትና ሶስት ዓመታተት ሃሳብ በመቃረምና ምቹ የአንድነት ጎዳናዎችን በመጥረግ ሂደት ላይ እንደነበረ በመጨረሻም ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቆ ለእርቀ ሰላም በሚያበቃው የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ መረጃው አለን፡፡

እንደሀገር ከምንጊዜውም በላይ ራሳችንን ለተግባቦት የምናዘጋበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ባለመግባባትና ያለፈን በማስታወስ የከፈልናቸው ዋጋዎች ዛሬም ጥዝጣዜያቸው አልሻረም፡፡ ባለፈው ጊዜ ጦርነት፣ ባለፈው ጊዜ የብኩርና ሽሚያ ዛሬ ላይ ብዙ ዋጋዎችን እየከፈልን እንደሆነ እኔና እናንተ ምስክሮች ነን፡፡ በእርቅና በወዳጅነት ካተቀበልነው ሁሌም ቢሆን የሚመጣው ካለፈው የሚብስ ነው፡፡ ያለፉ የእውነትም ሆኑ የሀሰት ትርክቶችን ዘግተን በአዲስ መነቃቃት መጪውን ስንቀበል ነው የጥንቱ ኃያልነታችን የሚመለሰው፡፡

እኛን እና ታሪካችንን በተመለከተ ሁልጊዜም አንድ እውነት አለ፡፡ ፍቅርን የቋጠረ፣ አንድነትን የቀለመ አብሮነት፡፡ ይሄ መነሻችን እና መድረሳችን ነው፡፡ ዓለም ያወቀንና የተቀበለን በዚህ ማንነታችን በኩል ነው፡፡ የገባን ብዙ ነው እንደገባን አለመኖራችን ግን እየጎዳን ነው፡፡ በትላንት ጉያ ውስጥ ያሉ የጀግንነትና የሉዓላዊነት፣ የነጻነትና የዘመናዊነት ቀንዲሎቻችን የአብሮነት ውጤቶቻችን እንደሆኑ እያወቅን እንኳን ለዚህ ክብር ለዋጋ ስንከፍል አንታይም፡፡

ኢትዮጵያ ለፍቅር የእትብቱ ማዲያ ናት፡፡ እኛ ለሰላምና ለአብሮነት መነሻ ታሪኮች ነን፡፡ አሁን ላይ ብርቅ የሆኑብን ዘመናዊነትና ስልጣኔዎች፣ ፊተኝነትና ቀዳማዊነት ከእኛ ተነስተው ወደዓለም የተሰደዱ ናቸው፡፡ ከፍቅር ስለራቅን ነው የራቁን። ከአንድነትና ከአብሮነት ስለሸሸን ነው የሸሹን፡፡

ሰፊ ሜዳ ያስፈልገናል፡፡ ዘረኝነትና ብሔርተኝነት ደብዝዘው ኢትዮጵያዊነት ብቻ የሚያቀነቅንበት ፖለቲካ፣ ራስ ወዳድነትና ጥቅመኝነት ኮስሰው አብሮነት የሚጎመራበት መድረክ፡፡ አእምሯችንን አጽድተን ልዩነቶቻችንን እስካላጠበብን ድረስ ከመባስ ባለፈ የሚሻል ህመም አይኖረንም፡፡ ሳይቃጠል በቅጠል..የሚለው አባባል እዚህ ጋ መነሳቱ ግድ ነው፡፡ የባሰ ዋጋ ሳንከፍል፣ ከዝቅታ ወደመደፋት፣ ከድጡ ወደማጡ ሳንገባ አብሮነታችንን የምንመልስበትን እድል መፍጠር ይጠበቅብናል፡፡

ከየትኛውም በጎ ነገር በላይ እድሎቻችን በመነጋገር ውስጥ ነው ያሉት፡፡ የሰው ልጅ ወደዚች ምድር ሲመጣ በፍላጎት፣ በምኞት እንዲሁም በተለያየ ሃሳብ ተከሽኖ ነው፡፡ አይደለም ከሌላው ጋር ከራሳችን ጋር እንኳን የማይግባባበት ጊዜ አለ፡፡ አይደለም ከሌላው ጋር ቀርቶ እግር ከእግር ይጋጫል፡፡ እንደዚሁ ሁሉ ተነጋግረን እንድንግባባ፣ ተመካክረን አብረን እንድንኖር ልዕለ አእምሮ ተሰጥቶናል፡፡

አእምሮ ልዩነቶችን ለማስታረቅ ትልቁ አቅም ነው፡፡ የይቅርታና የፍቅር ዋጋ ለማሰላሰል ጥልቁ ጉልበት ነው፡፡ ጥላቻን በፍቅር መቀየር፡፡ በእርቅና በምክክር ወደአብሮነት መመለስ ነው። ለጥላቻ እየበረታ ለፍቅር የሚደክም አእምሮ አልተሰጠንም፡፡ እንዳውም ሚዛን ላይ እናውጣው ካልን የተሰጠን አእምሮና ልብ ከፍቅር ውጭ ጥላቻን የማያውቅ ነው፡፡ ታላቁ የነጻነት አባት ኒልሰን ማንዴላ ይሄን እውነት ሲገልጸው ‹ፍቅር ተፈጥሯዊ ጥላቻ ግን በትምህርት የምናገኘው ነው› ብሎ ነው፡፡

ከዚህ የነጻነት ታጋይ አስተምህሮም ሆነ ከሌላ ዓለማዊና መንፈሳዊ ንጻሬ አኳያ ስናየው በመካከላችን ያለው የብሔርም ሆነ የእኔ እበልጥ እኔ ሽኩቻ እንደ ፖለቲካ ባሉና ራስን ብቻ ከመጥቀም አባዜ ከሚመነጪ ርህራሄ አልባ እሳቤዎች የተፈጠሩ እንደሆኑ እንደርስበታለን፡፡ ያለፉትን በርካታ ዓመታት አእምሯችን ለአንድነት የሚሆን ዋጋ ሲከፍል አልታየም፡፡ በጥሎ ማለፍ ውስጥ የጎለመሰ ነው፡፡ የጥሎ ማለፍ እሳቤ ደግሞ ትውልዱን መሰል ኢሰብዓዊ ልምምዶችን እያስተማረ ሀገርን ባዶ የሚያስቀር ነው፡፡

ፖለቲካችን አሁን ላሉብን ማህበራዊ ነውጦች ጣት የሚቀሰርበት የመጀመሪያው ተጠያቂ ነው፡፡ ይሄ የብዙዎቻችን እምነት ቢሆንም ፖለቲካውን ለማጥራት ስንጥር ግን አንታይም፡፡ የሚመጣውም ሆነ የሚሄደው ፖለቲከኛ በአንድ ዓይነት ራስን በማወደስ ልክፍት ውስጥ የወደቀ ነው፡፡ ስልጣንን ለሕዝብ ሰጥቶ ሀገርን በማገልገል መንፈስ ውስጥ መጥቶ የሄደ ፖለቲከኛ የለም፡፡ ይሄን ዓይነቱ ራስን ማዕከል ያደረገ ልምምድ ትውልዱን ለራስ ወዳድነትና ለጥቅመኝነት ዳርጎታል፡፡

ሀገር የፖለቲካ መልክ ናት፡፡ እኔና እናንተ ሳንቀር እንኳን ፖለቲካ ጸንሶ የወለደን የፖለቲከኞቻችን የአስተሳሰብ ውጤቶች ነን፡፡ እዛ መንደር መነጋገርና መግባባት ቢኖር እኔና እናንተ መንደር ተነጋግሮ መግባባት አይቸግረንም። ፖለቲከኞቻችን ያሸረጡትን የራስወዳድነት ሽርጥ አውልቀው አንድነትን ይልበሱ፡፡ ያኔ ሕዝብ ማቁን አውልቆ ጸዐዳውን ይለብሳል፡፡ አላማችን በእርቅና በተግባቦት ኢትዮጵያን ማስቀጠል ከሆነ ለጥላቻ የበረታ አእምሯችን ለፍቅር እንዲንበረከክ እናለማምደው፡፡ ሕዝብ ተኮር በሆነ ብዙሃነት በፖለቲካችን አናት ላይ የፍቅር ጣይ ትውጣ፡፡

ይቺ ሀገር የእኔና የእናንተ አንድነት ካላጸናት የውጭ ርዳታና ድጎማ አያጸናትም፡፡ ሁሉም በክፍቶቻችን እየገቡ መፍትሔ አልባ መለያየትን የሚፈጥሩብን ናቸው፡፡ በነጠረና ብዙሃነትን በተላበሰ ምክረ ሃሳብ ቀዳዳዎቻችንን ደፍነን መጪውን ጊዜ እስካተቀበልን ከዝቅታ የሚታደገን አይኖርም፡፡ በጀመርነው የምክክር መድረክ ላይ ሃሳብ በመስጠትና በመቀበል ኢትዮጵያን ማሻገር ለነገ የማንለም ኃላፊነታችን ነው፡፡

ታላላቅ ስልጣኔዎች ከሃሳብ የሚጀምሩ ናቸው። ዘመን ተሻጋሪ በሆነ የብዙሃነት እውነት ምድርን ያቆነጁ ሃሳባውያን እንኳን መነሻቸው ሃሳብ ነበር፡፡ የነሶቅራጠስና የነአርስቶትል ተራማጅ አመለካከት ዛሬም ድረስ ሕይወታችን ሆኖ በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ የሚኖረው ምክንያታዊነትን ባዘለ መንገድ ነው፡፡ ሃሳቦቻችን ምክንያታዊነትን ያዘሉ ከሆኑ ወደከፍታ የማይሄድበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ሃሳቦቻችን ለአንድነት መንገድ በሚዘጋ ራስ ወዳድነት ውስጥ ከሆኑ ግን በምንም መፍትሔ አናገኝም፡፡

አጉል መሻት ከሸነቆረው የዘረኝነትም ይሁን የጥላቻ ቀዳዳ መውጫችን ምክረ ሃሳብ ነው። በሃሳብ ካልተሸናነፍን በምንም ብንሸናነፍ ልክ አንሆንም፡፡ ያለፉ ታሪኮቻችን የጦርነት እና የኃይል መድረኮች ነበሩ፡፡ ኮሽ ባለ ቁጥር ጦር እየተማዘዝን ስንገልና ስንሞት ነበር፡፡ በዚህም እልፍ ወያባ ታሪኮችን ከመጻፍ ጎን ለጎን ለዛሬ ጉስቁልና መነሻ የሚሆኑ ቁርሾዎችን ፈጥረናል፡፡ ከሃሳብ ጎሎ በኃይል ለበረታ አእምሮ ገሎ ከመሞት በቀር ጀግንነት የለውም፡፡ ተነጋግረን በመግባባት ተነጋግሮ የሚግባባ ትውልድ እንፍጠር፡፡ ላለውም ሆነ ለሚመጣው ትውልድ በኩረ መነሻዎቹ እኛ ነንና ተታርቀን እርቅን፣ ተፋቅረን ፍቅርን፣ አንድ ሆነን አንድነትን ልናስተምረው ይገባል፡፡

ሃሳብ የሌላት ሀገር ማር የሌለው ቀፎ ናት፡፡ ቀፎ ማር እንዲሰጥ አበቦች ባሉበት፣ ለምለምና ለንቦች ምቹ በሆነ ቦታ ይሰቀላል፡፡ ይሄ ካልሆነ ግን ንቦች ወደቀፎው አይገቡም፣ ቀፎውም ማር አይዝም… በተስፋ ብቻ ቀን እንቆጥራለን፡፡ ልክ እንደቀፎው ሀገር ሰላምና ብልጽግና፣ አንድነትና ፍቅር እንዲኖራት የሃሳብ ስልጣኔ፣ የእርቅና የምክክር ባህል ያስፈልጋታል፡፡ አሁናዊው የሀገራችን ሁኔታ ከአበባ እንደራቀው ማር አልባ ቀፎ ነው፡፡ ቀፎው ማር እንዲይዝ የቦታ ለውጥ ያስፈልገዋል፡፡ ሀገራችን ሰላም እንድትሆን የምክክር መድረክ ያስፈልጋታል፡፡

ትግላችን ከሌሎች ሀገርና ሕዝቦች ጋር ቢሆን ጥሩ ነበር፡፡ እኛ ግን የምንታገለው ከራሳችን ጋር ነው፡፡ እያወደምን ያለን የራሳችንን ታሪክ ነው። እያበላሸን ያለንው የራሳችንን ትውልድ ነው፡፡ በእኛው እኛው እየተጎዳን ብዙ ዘመናትን ተሻግረናል፡፡ ሰው ከራሱ ጋር እንዴት ይጣላል? የሰሉ የክፋት አንደበቶቻችን ፍቅርን እንዲዘምሩ፣ ለመለያየት የበረቱ ምላሶቻችን ስለአንድነታችን ደጅ እንዲጸኑ ከፊታችን ያለውን ሀገራዊ ምክክር እንጠቀምበት፡፡

ህልሞቻቸን መግባባትን ካለበሱ ከምኞት ባለፈ ፍሬ አይሰጡንም፡፡ በብሔር ደፈጣ የመጣንበት ረጅም ጎዳና ከድህነትም ሆነ ከኋላቀርነት አልታደገንም፡፡ የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል እንደሚባለው በጋራ ጉዳያችን ላይ ፉክክር ውስጥ የገባንበት ሁኔታ ነው የሚስተዋለው። የሚመጣው ካለው ካልተሻለ፣ ያለው ካለፈው ካልበረታ የተሻለ ነገር ማለማችን ፋይዳ አይኖረውም። በፉክክር ብቻ ካለውሃ ባዷቸውን የተቀመጡ ብዙ ማድጋዎች አሉን፡፡ ሊያጠግቡንና ሊያረኩን የሚችሉ ታሪክና እሴቶቻችን ወዳጅነትን አጥተው ደብዝዘን አደብዝዘናቸዋል፡፡

በሃሳብ ልውውጥ በሃሳብ የበረታ ትውልድ መሥራት ከየትኛውም አበይት ጉዳያችን ፊተኛው ነው፡፡ ለሁሉም ግፍ ያለፉትን ሃምሳ ዓመታት እናነሳለን፡፡ እኛም እኮ የዚህ ትውልድ አንድ አካል ሆነን እየኖርን ነው፡፡ አሁን ላለችው ኢትዮጵያና አሁን ላለው ትውልድ ምን እያደረግን ነው? ወቃሽ ከመሆን እና ያለፈውን ከመተቸት ውጭ ምን የሚያስመሰግን ሥራ ሠራን? የቆምንው እኮ በዛ ዘመን የፍቅርና የአብሮነት ክንድ ነው፡፡ የምንጠራው እኮ አባቶቻችን ባጸኑት የአንድነት ስም ነው፡፡ እንጂማ ምን ስም አለን? ከጥላቻና ከመገፋፋት ሌላ ምን ያተረፍነው ነገር አለ?

የሄደው እንዳለ ሁሉ የሚመጣም ትውልድ አለ፡፡ ለመመስገንም ሆነ ለመተቸት ጊዜው የእኛ ነው፡፡ ያለፈውን የፖለቲካ ሥርዓት እንደኮነንን ሁሉ መጪው ትውልድ እኛ ባነወርነው ሃምሳ ዓመታት ላይ የእኛን ትውልድ ጨምሮ እንዳያስነውረን ዛሬን በጎ እንሥራ፡፡ ትናንሽ ቀዳዳዎቻችን ሰፊ እስኪሆኑ ሳንጠብቅ በቶሎ መድፈንን እንልመድ፡፡ አንዳንድ ንትርኮች ትላንት ላይ ተቋጭተው ቢሆን ዛሬ ላይ በዚህ ልክ አይበድሉንም ነበር፡፡ የዛሬ ትናንሽ መመላለሶች ነገ ላይ የበረቱ ሆነው ዋጋ እንዳያስከፍሉን ማሰቡም ተገቢ ነው፡፡

ትውልዱ የፍቅር ውርስ ያስፈልገዋል፡፡ ወንድማማቾች በቀይ ምንጣፍ ላይ ተያይዘው ሲራመዱ እንዲያይና ለዛ ክብር ራሱን እንዲያዘጋጅ ምልክት እንስጠው፡፡ ከዛሬ አርቆ የተስፋ ነገን እንዲያይ የመነጋገር ውርስን እናውርሰው። በፖለቲካውም ሆነ በፖለቲከኞቻችን ሥጋት የወደቀበት ትውልድ እየተፈጠረ ነው፡፡ ተስፋ እንጂ ሥጋት ማንንም አጽንቶ አያውቅም። ክፍተቶቻችን በፍቅር ተሞልተው፣ በእርቅና በምክክር ታርቀው ጦርነትን እርም የሚል ትውልድ ዘርተን እናብቅል፡፡

ያለፈውን ትተን መጪውን የምንቃኝበት በፍቅር ጀምሮ በፍቅር የሚያበቃ አዲስ ታሪክ ያስፈልገናል፡፡ የቂም በቀል ሳይሆን የወንድማማችነት ውርስ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ሀገር ሰላምን ባነገቡ በላቁ ሃሳቦች ካልተማገረች የዘላቂነት ዋስትና አይኖራትም፡፡ ይሄ ጊዜ ከመቼውም በላይ ራሳችንን ከጦርነት ነጻ የምናወ ጣበት፣ የወንድማማቾች ግፊያ የሚያበቃበት ነው፡፡ ስለሀገራችን ሁሉንም በጎ መስዋዕት የምንከፍልበት ነው፡፡

የምንገፋፋው ባልገባንና ባልተረዳነው ያለፈ ታሪክ እንደሆነ ግን ታውቃላችሁ? በሀገራችን ጥቂቶች የሚነዱት እልፍ መንጋ አለ፡፡ መንጋው ከኋላ ሆነው ለሚነዱት መጠቀሚያ ነው፡፡ እናም አልገባንም የምንለው በምክንያት ነው፡፡ ሳይገቡን ከምንጣላባቸው ይልቅ ገብተውን የሚያዋድዱን እልፍ የጋራ በረከቶች አሉን፡፡ ወደገቡንና የጋራችን ወደሆኑት ጸጋዎቻችን እስካልተመለስን ድረስ ባልገቡን ነገሮች ዋጋ መክፈላችን ይቀጥላል፡፡

ትውልዱን በነገር መርዘን ጎራዴ የምንማዘዘው ምንም ባገባን መሆኑ የምንጊዜም አግራሞቴ ነው፡ ታሪክ ያዛነፋቸው እና እኛው ራሳችን ያዛነፍናቸው የመለያየት ቁርሾዎች ለማንም እንደማይጠቅሙ ከተረዳን ሰንበትበት ብለናል፡፡ እንዳረዳዳችን ግን ከማይጠቅመን የኩርፊያና የመለያየት መንፈስ ውስጥ ስንወጣ አንታይም፡፡ ዛሬም ድረስ በነዛ ባልገቡን ነገሮች ስር ቆመን ዋጋ ከፍለን ዋጋ የምናስከፍል ነን፡፡

በሀገራችን ሰማይ ላይ የተስፋ ፀሐይ እንድንወጣ ምስራቅ መሆን አለብን፡፡ ምስራቅ በሌለበት ፀሐይ አትኖርም፡፡ ምስራቅ ካለ ጀምበር አለች፡፡ ጀምበር ካለ ትንሳኤ አለ፡፡ በእርቅና በምክክር ለሀገራችን የፀሐይ መውጫ አድማስ ሆነን ትውልዱን የፍቅር ፀሐይ እናሙቀው የመጨረሻ መልዕክቴ ነው፡፡

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/2016

Recommended For You