አዲስ ዘመን ድሮ

የሰሜን ኬንያ ሶማሌዎች ያብጣሉ፡፡ ምን ይሆን የሚያሳብጣቸው? ምላሹን “አዲስ ዘመን” ድሮ ይነግረናል። ካቲካላ ያስከተለው ጠንቅ በህጻናቱ… በሌላ በኩል ደግሞ ጓደኛውን ገድሎ ለጅብ ስለሰጠው ግለሰብ የወጣ መረጃም አለ፡፡ “…እንዲያው ሴቶች በድፍረትና በይሉኝታ ማጣት ከወንዱ ብሰዋል” ይለናል ከወይዛዝርት ገጽ የተገኘው መልዕክት፡፡ “ከእርስዎ ለርስዎ” የተሰኘው አምድም አንዳንድ ነገሮችን ያስታውሰናል፡፡

ካቲካላ ያስከተለው ጠንቅ

ደብረ ዘይት ፤ዕድሜያቸው 4 እና 6 ዓመት የሆነ የአቶ ዓለሙ ምህረቱ ሁለት ልጆች ወላጆቻቸው በሌሉበት የካቲካላ አረቄ ከጠርሙስ አግኝተው ስለጠጡ፤ በዚሁ ጠንቅ ታላቅየው ወዲያውኑ ሲሞት የታናሽየው ልጅ ሕይወት ግን በሐኪሞች ብርታት ለመዳን ችሎአል፡፡

(አዲስ ዘመን ህዳር 17 ቀን 1979 ዓ.ም)

ጓደኛውን ገድሎ ለጅብ ሰጥቷል የተባለ እጁን ለፖሊስ ሰጠ

አዲስ አበባ ውስጥ በቦሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ቦሌ ኮተቤ እየተባለ በሚጠራው ገጠራማ አካባቢ ጓደኛውን ገድሎ ለጅብ ሰጥቷል የተባለ ተጠርጣሪ ግለሰብ በቅርቡ እጁን ለፖሊስ ሰጠ፡፡

የከተማው ፖሊስ ኮሚሽን አስተዳደር ከትናንት በስቲያ እንደገለጸው ግለሰቡ ደቡ ዳቢ የተባለውን ጓደኛውን በጩቤ ወግቶ የገደለው፤ አምጣልኝ ሳልለው ከሴት ጓደኛዬ 50 ብር ተቀብሎ ለግል ጥቅሙ አውሏል በሚል ነው፡፡

ግለሰቡ ድርጊቱን ከፈጸመ በኋላ ከለሊቱ ሰባት ሰዓት የካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ በመድረስ እጁን መስጠቱን ገልጿል፡፡

የቦሌ ክፍለ ከተማና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባሎች ወደ ሥፍራው ባመሩበት ወቅት የሟች አስክሬን በጅብ መንጋ እየተበላ እንዳለ ማግኘታቸውንና ጅቦቹን በማባረር ጥቂት የሟች የሰውነት ክፍሎች ለማግኘት መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

(አዲስ ዘመን ታህሳስ 20 ቀን 1997 ዓ.ም)

የሰሜን ኬንያ ሶማሌዎች ያብጣሉ

በሰሜን ኬንያ አውራጃ የምትገኘው በሲኦሎ ከተማ ውስጥ ባለፈው ዓርብ በተደረገው ግጭት ላይ አራት ሶማሌዎች ሲሞቱ ዘጠኝ የሚሆኑ ደግሞ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የከተማይቱን ጸጥታ ለማስከበር የእንግሊዝ ወታደሮች ወደ ሥፍራው ተልከዋል፡፡

……….

ግጭቱ የተቀሰቀሰው ፖሊሶች 1000 በሚሆኑ ሱማሌዎች ላይ ተኩስ በከፈቱ ጊዜ ነው፡፡ ሶማሌዎች ምርጫ የሚደረግባቸውን ሥፍራዎች ከበው መራጮችን ያስፈራሩ እንደነበር ታውቋል፡፡

…….

ምንም እንኳን በኢሲኦሎ የሚገኙት የምርጫ ሥፍራዎች እንደወትሮው ክፍት ቢሆኑም፤ ሶማሌዎቹ ባለፈው ሳምንት በተደረገው የኬንያ ምርጫ ላይ አድመው ተካፋይ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ እነሱም የሰሜን ኬንያ አውራጃ ከኬንያ ተገንጥሎ ለሶማሊያ እንዲሰጥ ፍላጎት አላቸው፡፡

(አዲስ ዘመን ሚያዚያ 23 ቀን 1955 ዓ.ም)

የአፍሪካ ዕድል መሠረቱ በአዲስ አበባ ተጣለ

– ካዛብላንካና ሞኖሮቪያ ተሰርዞ

አንድ ቻርተር ተፈረመ

የካዛብላንካና የሞኖሮቪያ የሌሎቹንም ብሎኮችና ቻርተሮችን ሠርዞ የአፍሪቃን አንድነት የሚመሠርተው “የአፍሪቃና የማላጋሲ አገሮች ድርጅት ቻርተር ግንቦት 17 ቀን ለግንቦት 18 ቀን አጥቢያ 1955 ዓ.ም ከለሊቱ ሰባት ሰዓት ከ35 ላይ በአፍሪቃ አዳራሽ ተፈርሟል፡፡

በአማርኛ፣ በዓረብኛ፣ በፈረንሣይኛና በእንግሊዝኛ የተጻፈውን ቻርተር የፈረሙት ሰሞኑን ጉባዔ ሲያደርጉ ከሰነበቱ ሃያ ስምንቱ የሀገራትና የመንግሥታት መሪዎች ሲሆኑ የሩዋንዳና የማዳጋስካር መሪዎች ደግሞ በእንደራሴዎቻቸው በኩል አስፈጽመዋል፡፡

( አዲስ ዘመን ግንቦት 19 ቀን 1955ዓ.ም )

ለወይዛዝርት ገጽ አዘጋጅ

አዘጋጅ ጳውሎስ ኞኞ

*አንዳንድ ሴቶች ጥፋታቸው ሳይታያቸው እየቀረ ሞራላችን የተበላሸው በወንዶች ነው ሲሉ እሰማለሁ። ተሳስተዋል፡፡ አንዳችን በአንዳችን ላይ ልናመሃኝ አንችልም፡፡ ሁላችንም ተበላሽተናል፡፡ የብልሽቱ መሠረት በሊቃውንት ተመርምሮ መታወቅ አለበት፡፡ ሴቱም ወንዱም ሰካራምና ዝሙተኛ ሆነ፡፡ የመጥፊያው ምንጭ አልታወቀም፡፡ እንዲያው ሴቶች በድፍረትና በይሉኝታ ማጣት ከወንዱ ብሰዋል፡፡ ባዓይን፣ ባፍንጫና በግንባር ልዩ የመነጋገሪያ ቋንቋ ከፈጠሩ ጊዜው አጭር አይደለም፡፡ በትምህርት ቤትም ቢሆን ቦታ ሲያጣብቡ የሚገኙት እስከ 6ኛ ክፍል ነው፡፡ ሕግ አውቀው ዳኝነት አይረዱም፡፡ አስተዳደር ተምረው ሀገር ገዢ አልሆኑም።

በወታደርነትም ሙያ ቢሆን በወህኒ ቤት ዘበኝነት የተቀጠሩትን ብቻ እናያለን፡፡ የባልትና ሙያ ኖሯቸው ያሳዩት ግልጋሎት የለም፡፡ በዴሞክራሲ ሕግ መሠረት ከእኛ ጋር እኩል ሁኑ ብለን መብት ብንሰጣቸው ለሥራ የኛን አርአያ በመከተል ፋንታ በየክርታሱ እየተወሸቁ ተበላሽተው እኛንም በከፊል አጠፉን፡፡ ለሀገር ልማትና ለወሰን ጥበቃ በየበረሃው ስንከራተት እነሱ ሊያበረታቱን ሲገባ ፍቅርህ ገሎኝ ሞቼ ተቀብሬያለሁና በቶሎ ድረስልኝ እያሉ በማባበል ያሸንፉናል፡፡ ከሴት ተለይቶ ለመኖር ተፈጥሮን መግታት አስቸጋሪ ሆነ፡፡ የሴቶቹ ጉድ ብዙ

 ቢሆንም፤ በጠቅላላው የማኅበሩ ጠላቶች እነርሱ ናቸው ለማለት ብደፍርም፤ እነርሱን ለዚህ ያበቃቸውና እኛንም ለውድቀቱ ያንበረከከን፤ መንፈሳችንን ያላላው የተዳፈነው ነገር ይታወቅ እላለሁ፡፡ በእኛም በነሱም አይፈረድም፡፡ አቶ ጳውሎስ ምን ይላሉ?

ሽመልስ አስፋው(ከገሙ ጎፋ)

-እኔስ የምለው በጥቂቱ ነው፤ሴቶቹ አይብዙ እንጂ በሁሉም ሥራ ቦታ አሉ፡፡ በእኛም በእነሱም ካልተፈረደ በማን ይፈረድ? በእግዜር ነው? ብቻ ብቻ በአዳምና ሐሄዋን ጊዜ የተጀመረ ሰበብ እስካሁንም አለ፤ ”ጌታዬ ሔዋን ናት” “የለም ጌታዬ! እባቢቱ ናት አኮ”፡፡

ከእርስዎ ለርስዎ

*እንደ እናት እህትና ወንድም የምመካባት ዘመዴ በማላውቀው ነገር ፊት ነስታኝ ተጨንቄያለሁ፡፡ ምን ይሻለኛል?

ሻሚል ሻወል(አሰበ ተፈሪ)

-ከድሮው ፈገግታሽ አትለወጪብኝን አዚምላት፡፡

*የመፈቀር ዕድል ሲያገኙ የሚጠቀሙበት ሰዎች በስተመጨረሻ ጊዜያቸው ምን የሚሉ ይመስልሃል?

(ብሩክ ጠንክር (ከዶሮ ማነቂያ)

-“ማሪኝ ብዬሻለሁ እሞትብሻለሁ!” የሚለውን የሚያቀ ነቅኑ፡፡

*ማደሪያ የለኝም ምን ይሻለኛል?

-ግንድ ይዘህ ብትዞር፡፡

(አዲስ ዘመን ታህሳስ 3 ቀን 1997 ዓ.ም)

*በጋዝ መወደድ ሕብረተሰቡ ምን ይማራል?

– ቆጥቦ መጥቀምን፡፡

*አንተ ለተቀጠርክበት መሥሪያ ቤት ትጉህ ሆነህ ጎንበስ ቀና እያልክ ስትሠራ በቀጥታ ሥራው የሚመለከተው “በርታ” እያለ ሲሄድ ምን ትለዋለህ?

ሳራ ተሾመ

-አጨብጭቦ አዳሪ፡፡

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/2016

Recommended For You