አዲስ ዘመን ድሮ

በጊዜ ርዝመት፣ በዝማኔ ርቀት ያልተጎረዱ የአዲስ ዘመን ትውስታዎች ትናንትን እንደዛሬ ይነግሩናል። “በቃል ያለ ይረሳል፤ በጽሁፍ ያለ ይወረሳል” ማለትስ እንዲህ አይደል? ከድሮዎቹ የአዲስ ዘመን የመረጃና የመዝናኛ ርዕሰ ጉዳዮች በ1986ዓ.ም የአሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ አቋሟን የመቀየር ጉዳይን ይመለከታል። የጤና ባለሙያዎችን እያነጋገረ ያለ አንድ ጉዳይም አለ። ዝንጀሮ ሰብል እንጂ ሰው በላ ቢባል መገረም አይቀርም። ከጳውሎስ ኞኞ “አንድ ጥያቄ አለኝ” አዝናኝ ደብዳቤዎችም ጥቂቱን እናንብ፡፡

የአሜሪካ መንግሥት ስለ ኢትዮጵያ የአቋም ለውጥ አለማድረጉን ገለጸ

የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ሰላምና እርቅ ስለተባለው ኮንፈረንስ ያለውን አቋም አዛብቶ ለማቅረብ የተለያዩ የግል መጽሔቶችና ጋዜጦች የተቀነባበረ ዘመቻ በማድረግ ላይ ናቸው።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሚስተር ማርክ ባስ ሰሞኑን የሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫ የዘገቡት በርካታ የግል ጋዜጦችና መፅሄቶች አሜሪካ በኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ላይ ያላትን የእምነትና የድጋፍ ፖሊሲ የቀየረች አስመስለው ቢያቀርቡም በአሜሪካ በኩል አንዳችም የአቋም ለውጥ አለመኖሩን በዚያው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አምባሳደሩ በተደጋጋሚ አረጋግጠዋል።

ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለ ሙዳይ የተባለው ሳምንታዊ የግል ጋዜጣ በታህሳስ 3 እትሙ ላይ እንደዘገበው የአሜሪካ መንግሥት የታህሳስ ዘጠኙን የሰላም እና የእርቅ ጉባዔ እንደ ታላቅ ቁምነገር በመመልከት የአቋም ለውጥ አሳይቷል ከሚል የሌለ ድምዳሜ ደርሷል።

(አዲስ ዘመን ታህሳስ 23 ቀን 1986ዓ.ም)

ጉዳዩ የጤና ባለሙያዎችን እያከራከረ ነው

ጫት አነቃቂ ከሆኑት ከሻይ፣ ከቡናና ከአልኮል እንጂ ከአደገኛ መድሃኒቶችና ዕጾች ጋራ አይመደብም ሲሉ በመስኩ ጥናት ያደረጉ ምሁር አስታወቁ። አንድ የጤና ጥበቃ ኤክስፐርት ደግሞ ጫት ከአደገኛ መድሃኒቶችና ዕጾች እንደሚመደብ ገለጹ።

ዶክተር መኮንን ሀጎስ፣ በመመኮ የተባለው የግል ድርጅት አማካሪ ሰሞኑን ለጋዜጣው ሪፖርተር በሰጡት መግለጫ ጫትን ጨምሮ በአንድ ሺ አምስት መቶ ዕጽዋት ላይ ጥናት ሲያደርጉ መቆየታቸውንና በጥናታቸውም ጫት ከአደገኛ መድሃኒቶችና ዕጾች ሊመደብ እንደማያስችል ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

ማንኛውም ነገር ከመጠን በላይ ከተወሰደ ጎጂነት እንዳለው የገለጹት ዶክተር መኮንን በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የአደገኛ መድሃኒቶችና ዕጾች መቆጣጠሪያ፣ መከላከያ ቡድን ከፍተኛ ኤክስፐርት የሆኑት አቶ አብርሃም ገብረ ጊዮርጊስ ጫትን ከካናቢስና ኮኬይን ጋር ይመደባል በማለት ለመገናኛ ብዙኃን በቅርቡ የሰጡት መግለጫ የተሳሳተ ነው ብለዋል። ጫትን ከአደንዛዥ ዕጾች መመደብም ፍጹም ኢ ሳይንሳዊ መሆኑንም አስምረውበታል፡፡

(አዲስ ዘመን ታህሳስ 29 ቀን 1990ዓ.ም)

ዝንጀሮ ሰው በላ

ጅማ፤ (ኢዜአ)፡- በከፋ ጠቅላይ ግዛት በሊሙ ኮሣ ወረዳ ግዛት በርቄ በተባለው ቀበሌ አንድ ዝንጀሮ የ2 ዓመት ዕድሜ ያለው ወንድ ልጅ መብላቱ ተነገረ።

ዝንጀሮው ሕፃኑን ልጅ ከበላ በኋላ በተጨማሪ አንዲት የ3 ዓመት ዕድሜ ያላት ልጅ ለመብላት ሲሞክር ሰው ደርሶ አድኗታል። ሆኖም ልጅቷን ለመብላት መሬት ጥሎ በመቦጫጨቅ የመቁሰል አደጋ ያደረሰባት መሆኑ ከቀበሌው መልከኛ ተገልጧል ሲል የወረዳው ግዛት ጸሐፊ አቶ ለማ አዱኛ ገለጡ።

ዝንጀሮው አንዱን ልጅ በልቶ ሌላዋን ልጅ ያቆሰለው ልጆቹ በቤታቸው አቅራቢያ ሲጫወቱ አግኝቷቸው መሆኑን ዋና ጸሐፊው በተጨማሪ አረጋግጠዋል።

ይኸው ዝንጀሮ ልጆቹን ከመብላቱ በፊት፤ ከ30 ያላነሱ በጐችና ፍየሎች በልቶ ወደ ጫካ እየተሸሸገ የኖረ መሆኑ ታውቋል።

(አዲስ ዘመን መስከረም 1 ቀን

1962 ዓ.ም)

አንድ ጥያቄ አለኝ

– ይድረስ ለጳውሎስ ኞኞ

* በሀገራችን አባባል ማርያም የሳመችው የሚባለው ልክ አፍንጫዬ መሐሉ ላይ አለ። ሰዎች እንደሚሉኝ አንዳንድ ጊዜ ሴቶቹ “ውይ ታድለህ ማርያም አፍንጫህን ስማሃለች” ይሉኛል። እኔ ግን በዚህ አባባል አላምንም። ይህ ነገር በእርግጥ ማርያም የሳመችን ነው?

አ-ለማ

-አይደለም። ከመወለድ የሚመጣ ነው። ይህ ነገርም እስከ እድሜ ልክዎ ድረስ አይለቅም። አንዳንዱ ሊሰፋ ወይም ሊጠብ ይችላል። ሐኪሞች ግን በኦፕሬሽን ያስለቅቁታል። ለምን እንደሚያስለቅቁት ልናገር? በእሱ ብዙ ጥንቆላ ስላለበት ነው። እንደየአቀማመጡ ወይም እንደየቦታው ሁኔታ የሰውን ጠባይ ወይም ዕድል ይነግረናል ስለሚሉ ነው። ለምሳሌ ያህል አፍንጫው ላይ ያለውን እንዲህ ይሉታል። “የተጉአዥነት ምልክት ነው። አፍንጫቸው ላይ ጥቁር ነገር ያለባቸው ሰዎች አንድ ቦታ አርፈው ከሚሠሩት ሥራ ይልቅ በመዞር ሲራራ ነጋዴ በመሆን የሚሠሩት ሥራ መልካም ውጤት አለው። በአንድ ቦታ ተቀምጦ የሚሠራ ሥራ አይሳካላቸውም” ይላሉ። የእርስዎ ሥራ ምንድነው?

የካቲት 27 ቀን በወጣው ዓምድህ አንዲት የ15 ዓመት ወጣት ነኝ ያለች “ከንፈሬ ትልቅ በመሆኑ እጮኛ እየተመለሰ ተቸገርኩ። ከንፈሬን ምን ላድርገው ?” ብላ ጠይቃ ነበር። አንተም ሐኪሞችን ጠይቂ ምናልባት ሳይችሉ አይቀሩም ብለሃታል። አሁን የምለው በየሆስፒታሉ ከምትንከራተት ቢጤው ከቢጤው ይስማማል እንደሚባለው ሁሉ እኔም ከንፈሬ ትልቅ ስለሆነ “ለንቦጫም አንተን የምንይዘው ከንፈርህን ለመሸከም ነው?” እያሉኝ እጅግ ተቸግሬ ነበር። አሁን ቢጤዬን በማግኘቴ በደብዳቤ ተገናኝተን እንድንጋባ ታደርግልኝ ዘንድ እለምንሃለሁ። ለእኔ ለመጻፍ ብትፈልግ አሰላ ለአቶ ባዩ በየነ ብለህ ብትልክ ይደርሰኛል። ግን እንድትገልጥላት የምፈልገው ቁመተ ረዥም፣ ቀጭን፣ ጠጉረ ሉጫ መሆኔን አስረዳልኝ። አድራሻዋን እንድትገልጥልኝ አሳስብልኝ። በስልክ ቁጥር 158 ልታገኘኝም ትችላለህ፡፡

ባዩ ዘነበ

አሩሲ አሰላ

– እቱ ትባያለሽና ምን ትያለሽ? ከተጋባችሁ የውል አባት ለመሆን ደስ ይለኛል፡፡

(አዲስ ዘመን ነሐሴ 10 ቀን 1964ዓ.ም)

በሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You