የኢትዮ -ስሎቬኒያ ምክክር የሁለቱን ሀገራት የንግድ ግንኙነት ለማሳደግ ያስችላል

አዲስ አበባ፦ የኢትዮጵያ – ስሎቬኒያ ምክክር የሁለቱን ሀገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማሳደግ እንደሚያስችል ተገለጸ።

በምክክሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሀደራ አበራ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን እና የስሎቫኒያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሚስተር ማርኮ ሰቱኪ የተመራ ልዑካን የተሳተፈ ሲሆን ይህም የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ዘርፎች ያለበትን ደረጃ የዳሰሰ መሆኑን ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሀደራ አበራ እንደገለጹት ፤ የኢትዮጵያና የስሎቬኒያ ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ ነው። ስሎቬኒያ በቅርቡ ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ መክፈቷ እያደገ ለመጣው ዲፕሎማሲ ግንኙነት ማሳያ ነው ብለዋል።

የአሁኑ የፖለቲካ ምክክር ሶስተኛው ሲሆን ይህ ምክክርም የንግድና ኢንቨስትመን ግንኙነት ለማሳደግ የሚያግዝ መሆኑ አመላክተው፤ ኢትዮጵያ እ.እ.አ በ2023 ቡናን ጨምሮ ሶስት ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ምርቶችን ወደ ስሎቬኒያ መላኳን ተናግረዋል።

በአንጻሩ ስሎቬኒያ ደግሞ አራት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ምርት ወደ ኢትዮጵያ የላካለች መሆኑን ተናግረው፤ ሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ትብብራቸውን ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የስሎቬኒያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሚስተር ማርኮ ሰቱኪን በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ መንግሥትም ኢኮኖሚውን ለማሳደግ እየወሰደ ያለው ርምጃ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው፤ የስሎቬኒያ ባለሀብቶችም በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግ የሚችሉበትን እድል እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል።

ስሎቬኒያ ባለፉት 20 ዓመታት ኢኮኖሚዋን በእጥፍ አሳድጋ ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት መቻሏን የገለጹት ሚስተር ማርኮ፤ ስሎቬኒያ ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ መስኮች ለመተባበር ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል። በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን ግንኙነት ላይ ውይይት መደረጉን ነው የገለጹት።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ማብራሪያም፤ ስሎቬኒያ የመጀመሪያ ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ መክፈቷን ገልጸው፤ ይህም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ያሳድጋል ብለዋል።

ሁለቱ ሀገራት ከሁለትዮሽ ግንኙነት በተጨማሪ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በአውሮፓ ህብረት በሚካሄዱ ጉዳዮች ዙሪያ ሁለቱ ሀገራት ተቀራርበው ለመሥራት እየተነጋገሩ መሆኑን ጠቁመው፤ በተለይ ስሎቬኒያ በንብ ርባታ እና በማር ምርት ያላትን የረጅም ጊዜ ልምድ ለኢትዮጵያ ታካፍላለች ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ ንብና የማር ምርት ያላት ሀገር ናት። ነገር ግን በብዛትም በጥራትም የተሻለ ማምረት እንድትችል ሰፊ ልምድ ካለው ሀገር ጋር ተቀራርቦ መሥራቱ ጠቀሜታው የጎላ ነው ያሉት አምባሳደር ነቢያት፤ ሁለቱ ሀገራት በቋሚነት ምክክር እንዲያደርጉና በጋራ እንዲሠሩ የሚያስችል ስምምነት እንደሚያደረጉም አመልክተዋል።

በሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You