
አዲስ አበባ፡-የምግብ ደህንነትን በማረጋገጥ ሂደት ከአምራች እስከ ሸማች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ጥሪ አቀረበ።
የባለሥልጣኑ የምግብ ምዝገባና ፍቃድ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መንግሥቱ አስፋው ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፣ ምግብ የተፈላጊነቱን ያህል በአግባቡ ተመርቶና ተዘጋጅቶ ለተጠቃሚው ካልደረሰ ጉዳቱ እጅጉን የከፋ ነው። ለአስከፊ ጤና እክል፣ ከፍ ሲልም ለሞት ይዳርጋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በዓመቱ ከ600 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የምግብ ወለድ በሽታዎች ሲጠቁ፣ 420 ሺህ የሚሆኑት እንደሚሞቱ መረጃዎች ያሳያሉ። ከዚህም ውስጥ ከ125ሺህ በላይ የሚሆኑት ሰለባዎች ህፃናት ናቸው ብለዋል።
ይህ አሃዝ ደህንነቱ ባልተጠበቀ ምግብ ምክንያት በኅብረተሰቡ ላይ ሊደርስ የሚችለውን የጤና ጉዳት መከላከልና መቆጣጠር የግድ ለመሆኑ ምስክር የሚሠጥ መሆኑን የጠቆሙት አቶ መንግሥቱ፣ በተለይ ምግብን በተገቢው መንገድ በማምረት፣ በመያዝ፣ በማከማቸት፣ በማጓጓዝ ወይም ለተጠቃሚ በማቅረብ ሂደት ደኅንነት የማረጋገጥ ወሳኝ ስለመሆኑን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የምግብ ምርቶችን ጥራት እና ደህንነት ለመቆጣጠር የተለያዩ ሥራዎችን ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር እየሠራ እንደሚገኝና የምግብና የመድኃኒት አዋጅ ቁጥር 1112/2011 የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ጠንካራ ድንጋጌዎችን መያዙን አስገንዝበዋል።
በአዋጁ ትግበራ ተቋሙ ኅብረተሰቡን በምግብ ደህንነት ከሚከሰቱ የምግብ ወለድና ሌሎች በብክለት ከሚከሰቱ ችግሮች ለመከላከል ከፌዴራል እስከ ክልል ባሉ አወቃቀሮች ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እየተካሄደ መሆኑን የገለፁት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ ለአብነትም በኢትዮጵያ የምግብ ወለድ በሽታዎችን ለመቀነስ የተደረጉ ጥረቶች እመርታ እያሳዩ መምጣታቸውን ጠቁመዋል።
‹‹ይሁንና ምግብ ደህንነት ጉዳይ ለአንድ ተቋም ወይም ለአንድ አምራች ብቻ የሚተው አይደለም፣ ውጤቶችን ለማስቀጠል ከአምራቾች እስከ ሸማቾች ሁሉም ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ይኖርበታልም›› ብለዋል።
እንደ ሀገር የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ የምርመራና ቁጥጥር ሥራዎችን ማጠናከር፣ የምግብ ምርቶችን ጥራትና ደህንነት የሚቆጣጠሩ ተቋማትን አቅም ማጎልበት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የምግብ ደህንነት ስጋቶችን ለመቋቋም የሚያስችሉ መረጃዎችና ምክሮችን ለህብረተሰቡ ማቅረብ፣ የምግብ ደህንነት ዓለም አቀፍ ጉዳይ በመሆኑ ሀገራት የምግብ ደህንነት ስጋቶችን ለመቋቋም በተለይም የመረጃ ልውውጥ፣ የጋራ ምርምርና የድንበር ተሻጋሪ የምግብ ደህንነት ስጋቶችን በጋራ መፍታት በጋራ መሥራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
‹‹በሀገሪቱ በዘርፉ የተሰማሩ የምርምር ተቋማት ሳይንስን መሠረት አድርገው የሚያከናውኗቸው ጥናቶች ምግብን ከእርሻ እስከ ተጠቃሚ ድረስ ባለው ሰንሰለት በአግባቡ በማዘጋጀትና በማቅረብ፣ ሊደረግ የሚገባውን ጥንቃቄ ሊያመላካቱ ይገባልም›› ብለዋል።
ሸማቹ ምርቶቹን ሲገዛ ከተለምዶው የተለዩ ባሕሪያትን የሚያሳይ ከሆነ፣ በተለይም ምግቦቹ የጣዕም፣ የይዘት፣ የመጠንና የሽታ ልዩነት ካላቸው፤ የምግብ ክለሳ ችግሮች ሲያጋጥሙ/ሲከልሱ ወይም እንደዚህ አይነት መሰል ጥርጣሬዎች ሲኖሩት ለኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ወይም ለክልል ተቆጣጣሪ አካላት ጥቆማ በማቅረብ የዜግነት ድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
የዓለም የምግብ ደህንነት ቀን በየዓመቱ ግንቦት 30 ቀን የሚከበር ሲሆን፣ ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ “Food Safety: Science in Action” የምግብ ደህንነት፡ ሳይንስ በተግባር” በሚል መሪ ቃል ለ6ኛ ጊዜ የፊታችን ቅዳሜ ይከበራል።
በታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም