የከሸፈው የወጣቶች አትሌቲክስ ቻምፒዮና

በማንኛውም ስፖርት በእድሜ ገደብ የሚካሄዱ ውድድሮች ዋነኛ ዓላማቸው ወጣትና ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት መሆኑ ልክ “አንድ ሲደመር አንድ” ያህል ቀላል አመክንዮ ነው። በአፍሪካ ግን ይህ አይሠራም። በኢትዮጵያ ደግሞ የባሰ ነው። በአፍሪካ ስፖርቶች ከእድሜ ተገቢነት ጋር የተያያዙ የተገቢነት ጥያቄዎች የሁልጊዜም ጥያቄና የአህጉሪቱ ስፖርት “ነቀርሳ” ቢሆኑም ብዙዎቹ ሀገራት ችግሩን ለመቅረፍ ጨከን ብለው በወሰዱት ውሳኔ በተጨባጭ የሚታይ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። ኢትዮጵያም የዚህ ችግር ገፈት ቀማሽ ከሆኑ ሀገራት አንዷ ብትሆንም የተጣመመውን ለማቅናትና ስፖርቱን ገዝግዞ እየጣለ የሚገኘውን ነቀርሳ ነቅሎ ለመጣል የረጅሙን መንገድ ጉዞ የጀመረች አይመስልም።

ለሰባት ቀናት በድሬዳዋ ሲካሄድ ቆይቶ ባለፈው እሁድ የተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ስያሜው ባጭሩ ሀገር አቀፍ የወጣቶች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ተብሎ ሊጠራ ይችላል። በተግባር ግን ፈፅሞ የወጣቶች ቻምፒዮና መሆን አልቻለም። እንደ አጠቃላይ ይህ ቻምፒዮና ከዓላማው አኳያ ከሽፏል ማለት ይቻላል። ይህንንም ከባለሙያዎች እስከ አሠልጣኞችና ራሳቸው አትሌቶች እንዲሁም የውድድሩ ባለቤት በሆነው አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የታመነበት ነው።

በዚህ ቻምፒዮና በጣት የሚቆጠሩ (በተይም በአጭር ርቀት ሴቶች) ወጣቶች ተወዳዳሪ ሆነው ከመቅረባቸው ባሻገር በአጠቃላይ በሁሉም የውድድር አይነቶች በተገቢው እድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶችን ማየት አልተቻልም። ገና ቻምፒዮናው ከመጀመሩ አስቀድሞ የፌዴሬሽኑ የህክምና ባለሙያ ሆነው ለረጅም ዓመታት ያገለገሉት ዶክተር አያሌው ጥላሁን “ይህ ቻምፒዮና ከሽፏል” በማለት ነበር የሚዲያ ባለሙያዎች ከእድሜ ተገቢነት ጋር በተያያዘ ስላለው ችግር ለመጠቆም የሞከሩት።

ከስምንት ኦሊምፒኮች በላይ በዚህ ሙያ ማገልገል የቻሉት ዶክተር አያሌው አልተሳሳቱም። በቻምፒዮናው የተጋነነ የእድሜ ተገቢነት ችግር ለሁሉም ሰው ግልፅ ሆኖ መታየት የጀመረው ገና ከጅምሩ ነው።

አንጋፋው ኦሊምፒያን ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ ከብሔራዊ በዱን ጀምሮ በተለያዩ በርካታ ክለቦች በማሠልጠንና ትልቅ ስም ያላቸው አትሌቶችን በማሠልጠን ይታወቃሉ። የሞስኮ ኦሊምፒክ የ10ሺህ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊው ሻምበል ቶሎሳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታላላቅ አትሌቶችን በማፍራት የሚታወቀው የመቻል ክለብ የአትሌቲክስ የቴክኒክ ኃላፊ ሆነው እየሠሩ ይገኛሉ። እሳቸው ይህን የወጣቶች ቻምፒዮና ሳይሆን “ሁለተኛው የኢትዮጵያ ቻምፒዮና ነው” ሲሉ ከእድሜ ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ገልፀውታል።

ይህ ቻምፒዮና ከሦስት ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ ከተካሄደው የአዋቂዎቹ የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ቻምፒዮና የሚለየው በድሬዳዋ መካሄዱ ካልሆነ በቀር ከእድሜ ጋር በተያያዘ ብዙ ልዩነት እንደሌለው የተናገሩት ሻምበል ቶሎሳ “ይህ የወጣቶችን ህልም የሚያጨልምና የኢትዮጵያን አትሌቲክስ የሚገድል ነው” ሲሉ ለአዲስ ዘመን ተናግረዋል።

“የዕድሜ ማጭበርበር ጉዳይ በኢትዮጵያና በኬንያ እንደአጠቃላይ የምስራቅ አፍሪካ ግዙፍ ችግር ነው” ያለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ጀግናው አትሌት ስለሺ ስህን፣ ከዚህ በፊት በተካሄዱ የአፍሪካና የዓለም ወጣቶች ቻምፒዮና ላይም በግልፅ የታየ ችግር መሆኑን አልሸሸገም።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለፃ፣ ችግሮቹ ዛሬ የመጡ አይደሉም። ይሄ የዕድሜ ችግር በዓለም አትሌቲክስም እንደ አበረታች ንጥረነገር (ዶፒንግ) እየታየ ነው። አሁንም ችግሮች ቢቀጥሉም ግን ፌዴሬሽኑ ትኩረት ሰጥቶ ለመሥራት ጥረት እያደረገ ነው። ለዚህም የአትሌቶችን ሰነድ ለማየት፣ በህክምና ባለሙያዎች ለማረጋገጥም እየተሞከረ ነው። ያም ሆኖ ችግሩን በፌዴሬሽኑ ብቻ መፍታት አይቻልም፤ ክለቦችና ክልሎች ችግሩን ተረድተው ራሳቸው የዕድሜ ማጭበርበርን ከአትሌቲክሱ ለማስወገድ መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ምክንያቱም ለአትሌቲክሱ ዕድገት አይጠቅምምና።

ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን፣ ናይጄሪያ ላይ ለሚካሄደው የአፍሪካ ወጣቶች አትሌቲክስ ቻሜፒዮና ፌዴሬሽኑ ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶችን የሚመርጠው አንደኛ ስለወጡ ብቻ እንደማይሆን ያስረዳል። በMRI ጭምር ምርመራ ተደርጎ እንደሚመረጡ የጠቆመው ስለሺ ስህን፣ ፌዴሬሽኑ በቅርቡ የጀመረው የፋይዳ መታወቂያ ምዝገባም በተለይ ወደፊት ይሄንን ችግር ያቀላል የሚል ተስፋ አለው። የዓለም አትሌቲክስም ወደፊት እየተስተካከለ ይሄዳል የሚል ምክረ ሃሳብ ስለሰጠ ችግሩን ለማስወገድ ፌዴሬሽኑ ጠንክሮ እንደሚሠራ ቃል ገብቷል። መገናኛ ብዙኃንም በመቀስቀስ፣ በማስተማር ችግሩ እንዲወገድ የማገዝ ትልቅ ሥራን አብሮ እንዲሠራ ጥሪውን አቅርቧል።

በቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You