”የፌዴራል መንግሥት የፕሪቶሪያውን ስምምነት በተመለከተ ከሚጠበቅበት በላይ ተጉዟል‘ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነትን አንደኛ ዓመት በተመለከተ ከኢፌዴሪ መንግሥት የተሰጠ መግለጫ ሙሉቃል

 የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ለሰላም ባላቸው የጸና አቋም የተነሣ የውጭም ሆኑ የውስጥ ጠላቶች በተነሡ ጊዜ ሁሉ እየተጠቁም ቢሆን አስቀድመው የሰላምን አማራጭ ይፈልጋሉ። የፈሩ፣ አቅመ ቢሶችና ደካሞች መስለው እስከሚታዩ ድረስ ችግሮችን በሰላም ለመፍታት እስከጥግ ድረስ ይሄዳሉ።

መንግሥት የሰላም አማራጭን አብዝቶ የሚፈልገው ጦርነት የኢትዮጵያን ሕዝብ ወደ ሰላም፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እና ብልጽግና ስለማያመጣ ነው። እነዚህ የሰላም አማራጮች ተሟጥተው ማለቃቸውን ሲመለከቱ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት እንደ አራስ ነብር ተነሥተው ጠላቶቻቸውን አደብ ያስገዛሉ። የጥንትም የቅርብም ታሪካችን ይሄንን ይመሰክራል።

በትግራይ ከሁለት ዓመታት በፊት የተፈጠረው ሁኔታ ወደ ጦርነት ከማምራቱ በፊት መንግሥት የሰላም አማራጮችን ሁሉ ሞክሯል። የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ሞክረዋል። እናቶች እያለቀሱ ለምነዋል። የጦርነት ነጋሪት ከልክ በላይ እየተጎሰመ እንኳን ከትግራይ ክልል ጋር የነበረው ግንኙነት እንዳይቋረጥ ትዕግሥት አስጨራሽ መንገድ መንግሥት ተጉዟል። የተለያዩ ወገኖች መንግሥት በብቸኝነት ኃይል የመጠቀም ሕገ መንግሥታዊ መብቱን እንዲጠቀም እየወተወቱት እንኳን ለውይይትና ለፖለቲካዊ ንግግር ቅድሚያ በመስጠት ከልክ በላይ ትችቶችን አስተናግዷል።

በተለያዩ ጊዜያት መንግሥት የኃይል የበላይነት እንዳለው እያረጋገጠ እንኳን ለትግራይ ሕዝብ ሲል ጦርነትን ለማቆምና ከጦርነት ቦታዎች ለመውጣት ቆራጥ ውሳኔ ወስኖ ተግባራዊ አድርጓል። በጦርነት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ርዳታ ለትግራይ ሕዝብ እንዲደርስ መንገዶችን ከፍቶ አሳልፏል። ርዳታ የጫኑ መኪኖች በሄዱበት እየቀሩ እንኳን ከሕዝብ የሚበልጥ የለም በሚል ችግሩን ተቋቁሞ ርዳታ እንዳይቋረጥ አድርጓል።

ይህ ሁሉ ተደርጎ የሚፈለገው ሰላም ባለመምጣቱ ወደ ግጭት ተገባ። በዚህም የተነሣ ሕግ የማስከበር ሥራውን እንዲፈጽም መንግሥት ተገድዷል። መንግሥት ተገድዶ በገባበት በዚያ ጦርነት የደረሰውን ኪሣራ ከትግራይ ሕዝብና ከክልሉ መንግሥት በላይ የሚያውቀው የለም።

ጦርነትን ብቸኛ አማራጫቸው ያደረጉ ኃይሎች የትግራይን ወጣቶች ለእሳት ማግደዋቸዋል። የኢትዮጵያን እናቶች በኀዘን እሳት ጠብሰዋቸዋል። የክልሉን ብሎም የሀገርን ኢኮኖሚ አውድመዋል። የትግራይ ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር የነበረውን ዘመናት የተሻገረ ወገናዊነት አበላሽተዋል።

በጦርነቱ መጨረሻ የፌዴራል መንግሥት ሁሉን ነገር በኃይል ለመፈጸም የሚያስችል ወታደራዊ ቁመና ነበረው። ነገር ግን ጦርነቱ በሰላም ስምምነት ቢቋጭ ሀገርን አትራፊ የሚያደርግ መሆኑ ስለታመነበት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እንዲፈረም አድርጓል።

ይሄንን ያደረገበት ከመርሁ የመነጨ ምክንያት ነበረው፤ በምንም መልኩ ለትውልድ ቂምና በቀልን ማውረስ የለብንም፤ ጦርነት አሸናፊና ተሸናፊን ይፈጥራል፤ ሰላም ግን ሁሉንም አሸናፊ ያደርጋል፤ መጪው ትውልድ በአሸናፊና ተሸናፊ ትርክት ውስጥ ከሚያድግ ሁሉንም አሸናፊ በሚያደርገው የሰላም ትርክት ውስጥ ቢያድግ ይሻላል በሚል የተደረገ ነው።

ለተጎዱ የተለያዩ ማኅበረሰቦች የሚያገግሙበት ፋታ ለመስጠት የተሰጠ ዕድልም ነው። ይህ ውሳኔ ሀገርን ለመገንባትና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት ሲባል የተከፈለ መሥዋዕትነት ነው።

ከሰላም ስምምነቱ በኋላ መንግሥት በሆደ ሰፊነትና ቁስሉ እንዲሽር ካለው ፍላጎት ረጅም ርቀት ተጉዟል። ከስምምነቱ መፈረም በኋላ የጥላቻውን ጉም በመግፈፍ ወደ ትግራይ በግንባር ቀደምነት የተጓዘው በአፈ ጉባዔው የተመራው የፌዴራል መንግሥቱ ልዑክ ነበር። ይህ ልዑክ ከተጓዘ በኋላ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የባንክና የአውሮፕላን አልግሎቶች በፍጥነት እንዲጀምሩ ተደርገዋል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በተመሠረተ ጊዜ መሳሳብና መጓተትን ለማስቀረት ሲባል የአመራሩን ድርሻ ክልሉ እንዲወስድ በማድረግ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ፋታ አግኝቶ ፊቱን ወደ ሰላምና ልማት እንዲያዞር ተደርጓል።

የግብርና ሥራውን ለማገዝ የሚመለከተው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በክልል ደረጃ ከሚጠበቅበት በላይ ሠርቷል። ዩኒቨርሲቲዎችንና ትምህርት ቤቶችን ወደ አገልግሎት ለመመለስ የትምህርት ሚኒስቴር ከተልዕኮ በላይ ተጉዟል።

የመከላከያ ሠራዊት የሕዝቡን ችግር ለመፍታት ከራሱ በጀት ቀንሶ አያሌ ተግባራት አከናውኗል። የሰላም ስምምነቱን እንደ ዕድል በመጠቀም ሕዝብን ከችግር በማዳን፣ መንግሥታዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በማስመጀር ኃላፊነቱን ተወጥቷል።

አንዳንድ ነገሮችን እያገዘ፤ አንዳንድ ነገሮችን ችሎ እያለፈ፤ አንዳንድ ነገሮችን እየመከረ፤ አንዳንድ ነገሮችንም ራሱ እየሠራ የሰላም ስምምነቱ በተሟላ ልኩ በሂደት እንዲፈጸም ለማድረግ ሞክሯል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በአንዳንድ ነገሮች ወደኋላ እየቀረና ስምምነቱን በተሟላ ሁኔታ ሳይፈጽም እያነከሰ እንኳን ለክልሉ የሚደረገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ የፌዴራል መንግሥቱ አላቋረጠም። ከፌዴራል መንግሥቱም አልፎ ክልሎች ከአነስተኛ በጀታቸውና ገቢያቸው በመቀነስ የትግራይ ክልልን ደግፈዋል። አከራካሪ የሚባሉ አካባቢዎችን በተመለከተ የፌዴራል መንግሥቱ አቋም ወስዶ ሠርቷል።

የፌዴራል መንግሥት በዚህ ረገድ ያለው አቋም ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋግጥ፣ ሁሉንም ወገን በሚጠቅም መንገድ ፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ብልጽግናን በሚያረጋግጥ መንገድ መፍትሔ መሰጠት አለበት። ክረምት ደርሶ የእርሻ ሥራ ከመጀመሩ በፊት ተፈናቃዮች ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ፤ የአካባቢ ነዋሪዎች በመረጧቸው አካላት እንዲተዳደሩ፤ በመጨረሻም ደረጃ በደረጃ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ አቅጣጫ ተቀምጧል።

ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል። እነዚህን ሁሉ አቋሞችና ተግባራት የኢትዮጵያ ሕዝብና ዓለም አቀፉም ማኅበረሰብ በሚገባ ያውቃል።

ይህ ሁሉ ቢደረግም እንኳን በዚያኛው ወገን እግር የመጎተት አዝማሚያ ይታያል። ይህ ግን ዘላቂ ሰላምን፣ ብልጽግናንና የሕዝቦችን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት አያረጋግጥም።

የፌዴራል መንግሥት የፕሪቶሪያውን ስምምነት በተመለከተ ከሚጠበቅበት በላይ ተጉዟል። በዚህም ለሰላም ያለውን ጽኑ አቋም ደጋግሞ አሳይቷል።

የፕሪቶሪያው ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲከበር መንግሥት አሁንም ቁርጠኛ አቋም አለው። ሁሉም አካላት ተመሳሳይ ቁርጠኝነት በማሳየት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል።

ጥቅምት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

አዲስ አበባ

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/2016

Recommended For You