ሀገር የሀገርነት ልዕልናዋን የምትጎናጸፈው በዜጎቿ ሃሳብ ውስጥ ነው። እያንዳንዱ ዜጋ በውስጡ ያለው እሳቤ ሀገርን የመገንባት አልያም የማዳከምና ብሎም የማፍረስ ኃይሉ ጉልህ ነው። ቀና አስቦ ለሀገር ባለው አቅም ሁሉ አበርክቶውን የሚያደርግ ዜጋ ያላት ሀገር ሰላሟም፣ ሁለንተናዊ ዕድገቷም በዜጎቿ መልካም እሳቤና ተግባር ልክ ይረጋገጣል።
በአንጻሩ ስለ ሀገሩ ሳይሆን ስለ ግላዊና ቡድናዊ ጥቅሙ ብቻ የሚያስብ፣ የሚኖርና የሚተጋ የግለሰቦች ስብስብ ባለበት ሀገር ውስጥ ሀገር የሀገር ልዕልናዋ በግለሰባዊ ጥቅምና መሻት ልክ እያሽቆለቆለ ሰላሟ መናጋቱ፤ ዕድገቷም መጓተቱ፤ አለፍ ሲልም ሕልውናዋ ጥያቄ ውስጥ መግባቱ አይቀሬ ነው።
በዚህ ረገድ ደግሞ ምሁራን እና ተቋማት የሀገርን ሰላምም፣ ሁለንተናዊ ዕድገትም እውን እንዲሆን ከማገዝ አኳያ ያላቸው ሚና እጅጉን የጎላ ነው። ምሁር ሃሳቡ ብቻ ሳይሆን እውቀቱ ለሀገር በእጅጉ ያስፈልጋል። ተቋምም ተቋማዊ አቅምና ተልዕኮው በሀገራዊ ልዕልና እውን መሆን ላይ ቀጥተኛ አስተዋጽኦ አለው። ምሁራንም ሆኑ ተቋማት ደግሞ በሀገር ሀብት የተገነቡ፤ ለሀገርም ብዙ እንዲያበረክቱ የሚጠበቅባቸው ናቸው።
ለአብነት፣ ኢትዮጵያ ካላት ላይ ቀንሳ ያስተማረቻቸው፤ ያሳወቀቻቸው፤ ለዕድገትና ብልጽግናዋ እንዲሰሩላት የእውቀት ማዕድ ያቋደሰቻቸው፤ በፈለገቻቸው ጊዜ ሁሉ የአዕምሯቸውን ቀመር ለችግር መፍትሄ በሚሆን መልኩ አበጅተው እንዲያቀርቡ በብዙ የምትጠብቅባቸው ልጆቿ ናቸው።
ታዲያ እነዚህ ምሁራን ሀገር ያስተማረቻቸው ብቻ ሳትሆን፤ ካሳወቀቻቸው የእውቀት ማዕድ በችግሮቿ ጊዜ አለሁልሽ ሊሏት የተገባ ነው። ምክንያቱም እነዚህ ምሁራን በሀገር ሀብት የተማሩ፤ ሀገር ከእነሱ ብዙ የምትጠብቅባቸው ናቸውና። ከእነሱ የምትጠብቀው ደግሞ የሰላም መንገድን እንዲያመላክቱ፤ ምርጥ ሃሳብ እንዲያዋጡ፤ የዕድገትና ልዕልናዋን መዳረሻ በዕውቀታቸው አድማስ እንዲተልሙ ነው።
ከዚህ ውጪ ሀገር ከምሁራኗ የምትጠብቀው ጉዳይ አይኖርም። መማራቸው ለሰላም ሃሳብ ማዋጣት ካልቻለ እና በተቃራኒው ግጭትና ቁርሾን የሚዘሩ ከሆነ ይሄ ለሀገር የሚከፈልን ዋጋ መዘንጋት ነው። ስለ ልማትና ዕድገቷ መክረው የተሻለ መንገድን መተለም ካልቻሉ እና በተቃራኒው የልማትና እድገቷ መንገድ አወሳሳቢ የሚሆኑ ከሆነ፣ ይሄ የሀገርን ከፍ ያለ አደራ መብላት ነው።
በመሆኑም ምሁራን ከንትርክ ይልቅ የውይይት መስመርን ማሳየት፤ ከግጭት ይልቅ የእርቅ ሃሳብን ከፍ አድርጎ መግለጥ፤ ከጥፋት ይልቅ የልማትና ዕድገት ጎዳናን ለሕዝቦች በሚገባ መልኩ ከእውቀት ማዕዳቸው አፍልቀው ማቋደስ ይኖርባቸዋል።
ከምሁራን ባሻገር ሀገር የገነባባቸው ተቋማት ይሄን መሰል ኃላፊነት ሊወጡ የሚገባቸው ቀዳሚዎቹ አካላት ናቸው። እነዚህ ተቋማት ሀገር ከዜጎቿ በምትሰበስበው ግብር የሚተዳደሩ፤ ካልሆነም ከሌላት ላይ ቀንሳ ከምትከፍለው የብድር ገንዘብ የሚደጎሙ ናቸው። ሀገር ደግሞ ይሄን የምታደርገው ተቋማት እንደየተቋቋሙበት ዓላማ እና እንደተሰጣቸው ተልዕኮ ለሰላሟም፤ ለልሟቷም ጠብ የሚል ነገር ማበርከት እንዲችሉ ነው።
ከዚህ ውጪ እነዚህ ተቋማት የሰው ኃይል ይዘው፤ በጀት ኖሯቸው፤ በተዋበ ሕንጻ እየሠሩ ለታይታ ብቻ ያሉ ከሆነ፤ የተቋቋሙበትን ዓላማ የዘነጉ፤ የተሰጣቸውንም ተልዕኮ መወጣት የማይችሉ መሆናቸው አይቀሬ ነው።
በዚህ ረገድ በተለይ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና ሌሎችም ለሀገር የሚሆን የሰው ኃይልን ከማፍራት በተጓዳኝ፤ ችግር ፈቺ የሆኑ ሃሳቦችንና የምርምር ውጤቶችን በማፍለቅ ለሀገርም ለሕዝብም የሚበጅ አንዳች ነገር ማበርከት ይኖርባቸዋል።
በመሆኑም ሀገር እንደ ሀገር ሰላሟ የተረጋገጠ፤ ልማትና ዕድገቷም የፈጠነ ይሆን ዘንድ፤ መንግሥት እንደ መንግሥት፣ ሕዝብም እንደ ሕዝብ ከሚያደርጉት ያላሰለሰ ጥረት በተጓዳኝ፤ ከፍ ያለ የሀገር እዳ ያለባቸው ምሁራን እና ተቋማት ለዚህ የሚሆን አበርክቷቸውን ሊወጡ የተገባ ነው!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/2016