የባህር በር ጥያቄ የነበረ ያለና ተገቢውን ምላሽ እስኪያገኝ የሚቀጥልም ነው !!!

 ከሰላሳ ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ሁለት የራሷ ወደቦች የነበሯት ሀገር ነበረች። በየትኛውም ዘመን የነበሩ የኢትዮጵያ መንግሥታት በወደብ ጉዳይ የሄዱበት ርቀት ቢለያይም ኢትዮጵያ ወደብ አያስፈልጋትም ወይንም የወደብ ታሪኳ ተዘግቷል ብለው አያውቁም። ዛሬም በወደብ ጉዳይ የተነሳው እንወያይበት እንምከርበት የሚለው ሃሳብ የዚሁ እውነታ አንድ አካል ነው።

በወደብ ጉዳይ ከግማሽ ምእተ ዓመት በፊት የነበረውን እንቅስቃሴ ብቻ እንኳን ብንመለከት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በሚያዝያ 25 ቀን 1950 ዓ.ም ከዩጎዝላቪያ መንግሥት በብድር በተገኘ በ26 ሚሊየን አንድ መቶ ሺህ ብር ወጪ «ፖም ግራድ» በተባለ የዩጎዝላቪያ ኩባንያ የአሰብ ወደብ ግንባታን መሠረት አስጥለው ማስጀመራቸው ይታወሳል።

የወደቡ ግንባታም ከአራት ዓመታት በኋላም ተጠናቆ ራሳቸው በተገኙበት ለመመረቅ በቅቷል። ይህ የንጉሱ ተግባር በወቅቱ አንድ ሀገር ከአንድ በላይ ወደብ እንደሚያስፈልጋት ተረድተው እንጂ የምጽዋ ወደብ በእጃቸው እንደነበር ልብ ሊባል ይገባል።

በተመሳሳይ ወቅት ማለትም ታኅሣሥ ዘጠኝ ቀን 1954 ዓ.ም ንጉሱ ቤተመንግሥታቸውን ለአሁኑ አዲስ አበባ የኒቨርሲቲ በቀድሞ ስሙ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ለሚባለው ለሕዝባቸው ያበረከቱበት ጊዜ ነበር። ይህ የሚያሳየን ንጉሱ ለሀገሪቱ ብቸኛ የሆነውን ዩኒቨርሲቲ ከመክፈት በፊት ለባህር በር ትልቅ ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀሳቸውን ነው።

ለዚህ ኅዳር 23 ቀን 1954 ዓ.ም የአሰብ ወደብ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ንጉሰ ነገሥቱ ባደረጉት ንግግር ነው። « …..በ1916 ዓ.ም ወደ ኤሮፓ የሔድንበት ዋናው ጉዳይ ፤ ኢትዮጵያ በማናቸውም ዓይነት በጭሰኝነት እንኳ ቢሆን የባህር በር እንዲኖራት በነበረን ብርቱ ምኞት ተመርተን ስለነበር፤ በዚያው ጊዜ የኢጣልያ መሪ ከነበሩት ጋር ተነጋግረን በኮንሴሺን ሊሰጠን ታስቦ የነበረው ከጥቂት ሺህ ሜትር ካሬ መሬት የማይበልጥ ነበር። አሁን ግን በእግዚአብሔር ቸርነት ኢትዮጵያ የራሷን ባህርና የራሷን ወደብ ገዥ በሆነችበት፤ ከኢትዮጵያ ተወስዶ የነበረው ተመልሶ የኢትዮጵያ በሆነበት ታሪክ፤ ተመልሶ ታሪክ በሆነበት በዛሬው ጊዜ ከዚህ ቦታ ተገኝተን ይህንን አዲስ የተሰራውን የአሰብን ወደብ ለኢንተርናሽናል ንግድ መርቀን ስንከፍት እጅግ ደስ እያለን ነው። …. »።

በወቅቱ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የአሰብ ወደብ ተመርቆ ሥራ መጀመርን አስመልክቶ ኅዳር 25 ቀን 1954 ዓ.ም «ወደብ» በሚል ርዕስ ያስነበበው ርዕሰ አንቀጽ የመጨረሻ አንቀጽ እንዲህ ይል ነበር።

«….ለሥልጣኔ መሠረቱ ትምህርት እንደመሆኑ መጠን በአንድ ፊት ዩኒቨርሲቲው፤ በአንድ ፊት ወደቡ፤ ከዚህም በላይ መንገዱ፤ ሕክምናው፤ ኢንዱስትሪውና ፋብሪካው በየቦታው ተደጋግፈው መብቀልና ማደግ ሲጀምሩ ለሥልጣኔአችን ጣዕም በየዕለቱ ለምናደርገው የጋራ ትግል አላማና ፍቺ እያስገኙልን ይሄዳሉ። ….»

ኢትዮጵያ ወደብ እንደሚያስፈልጋት ከታመነና ይህ ሃሳብም በዓለም አቀፍ ሕጎች የሚደገፍ ከሆነ ጥያቄ መነሳቱ የማይቀር ጉዳይ መሆኑ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል። በመወራቱም ግርታ ሊፈጥር አይገባም። ምክንያቱም ሀገሪቷ ካለ ወደብ ጥገኛ ሆኖ መኖርን መምረጥ አይኖርባትም ና ነው።

ከዚህ ውጭ ግን አንዳንድ ዓለም አቀፍ ሕጎችና ስምምነቶችም መዳኘት ያለባቸው ወቅቱን ባገናዘበ መልኩ እንጂ የአንድን ወገን ጥቅም ብቻ በሚያስከብር መልኩ መሆን የለበትም። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ከሕዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ የገጠማትን ችግር ማስታወስ ያስፈልጋል።

በግድቡ ግንባታ መጀመሪያ ዓመታት የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በተለይም ግብጻውያን ሲዘምሩ የነበሩት ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ በቅኝ ግዛት ዘመን የነበረው ስምምነት እንዲተገበር ነበር። በወቅቱም ሆነ አሁንም ድረስ ይህ አግላይና አድሏዊ የሆነን ስምምነት ኢትዮጵያ ተቀብላው ቢሆን ኖሮ የህዳሴው ግድብና ከሱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ በሀገሪቱ ያለው ሁኔታ ምን ሊመስል እንደሚችል መገመቱ አያዳግትም።

በመሠረቱ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኙ የተጎራበቱ ሀገራት የሚያገናኛቸው በርካታ ነገሮች እንዳሉ ይታወቃል። ዘመኑ ደግሞ ለማንም ቢሆን ድንበር አጥሮ ለመኖር የሚፈቅድ አይደለም። እንኳን ስደተኛ የምንቀባበል እኛ የአፍሪካ ሀገራት እንቅርና ሌሎቹም ቢሆኑ ድንበራቸውንም ሃሳባቸውንም ለድርድር አልዘጉም።

ኢትዮጵያም ብትሆን ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት በብዙ ምስቅልቅል ውስጥ ሆና እንኳን ከኤርትራ፤ ከሶማሊያ፤ ከደቡብ ሱዳንና ሌሎች ሀገራትም የተሰደዱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን እጇን ዘርግታ ስትቀበል መኖሯ መዘንጋት የለበትም። ይህ አርቴፊሻል ድንበር ለግንኙነት አልፋ እና ኦሜጋ ለመሰላቸው አንዳንድ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ አካላት ጥሩ ማሳያ ነው።

እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባውና እኛም ሆንን ጎረቤቶቻችን ሊገነዘቡት የሚገባው እነሱ ችግራችን ፍላጎታችን ባሉት ነገር ላይ ብቻ ሳይሆን እኛም በምናነሳቸው ጉዳዮች ላይ ለመወያየት በርን ክፍት ማድረግ መሸነፍ ሳይሆን መሰልጠን መሆኑን ነው።

የታሰቡና የተወሩ ነገሮችን በሙሉ ከጦርነትና ነገር ጫሪነት ጋር ማያያዝም ተገቢ አይደለም። በኢትዮጵያ በኩል መንግሥት ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ያሉትን የሰላም አማራጮች በሙሉ አሟጦ እንደሚጠቀም ይታወቃል።

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በእርግጥም ኢትዮጵያም ኢትዮጵያውያንም ወደብ ያስፈልገናል ይገባናልም። በመሆኑም ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘቷ ጥያቄ ትላንት የነበረ ዛሬም ያለ ወደፊትም የባህር በር እስክታገኝ ድረስ በትውልድ ቅብብሎሽ የሚቀጥል መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

 ሰውመሆን መልካም

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You