የመንግሥት የግብርናው ዘርፍ ቁርጠኝነት ሌሎች መገለጫዎች!

 የግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት እያደገ መጥቷል፡፡ ሀገሪቱ ግብርናው የኢኮኖሚው መሠረት መሆኑን በመገንዘብ ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ መሥራቷን ተከትሎ ነው ይህ ዕድገት ሊመዘገብ የቻለው፡፡ በዘር የሚሸፈነው ማሳ እየጨመረ መምጣት፣ የኩታ ገጠም እርሻና ሜካናይዜሽንና የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት መስፋፋትና የመንግሥት ድጋፍና ክትትል ለምርትና ምርታማነቱ እያደገ መምጣት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች መካከል ይገኙበታል፡፡

በዘርፉ እየተመዘገበ ያለው የምርትና ምርታማነት እድገት ሀገሪቱ በዘርፉ ካላት እምቅ አቅምና ፍላጎት አኳያ ሲታይ በቂ ተብሎ የሚወሰድ አይደለም፡፡ እየተተገበረ በሚገኘው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያም የግብርናው ዘርፍ ከአምስቱ የኢኮኖሚው ምሰሶዎች አንዱ እንደመሆኑ ከዘርፉ ብዙ ይጠበቃል፡፡ በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው የአስር ዓመቱ እቅድ ከግብርናው ዘርፍ ብዙ ይጠበቃል፡፡ የምርትና ምርታማነት መጨመር አንድ ነገር ሆኖ፣ እንደ ቤተሰብም እንደ ሀገርም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ለኢንዱስትሪው ልማት የሚሆን አቅም ከግብርናው ማግኘትና ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በሀገር ውስጥ መተካት አልፎም ተርፎ ስንዴ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ከግብርናው ዘርፍ የሚጠበቁ ተግባሮች ተደርገው እየተሰራባቸው ናቸው፡፡

እንደሚታወቀው መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት ምርትና ምርታማነት የበለጠ እንዲያደግ እየሠራ ይገኛል፡፡ መንግሥት ለዘርፉ የሚያደርጋቸውን የተለያዩ ድጋፎች አሁንም አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ከድጋፎቹ አንዱ የአፈር ማዳበሪያ ማቅረብ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በ2014/15 የምርት ዘመን ለማዳበሪያ ግዥ 15 ቢሊየን ብር ያወጣው መንግሥት፣ በ2015/16 የምርት ዘመን 21 ቢሊየን ብር አውጥቷል፡፡ ዘንድሮ 23 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ እንዲቀርብ እያደረገ ነው፡፡

የፋይናንስ ተቋማት ለግብርናው ዘርፍ ትኩረት እንዲሰጡ ሲወተውት ቆይቷል፡፡ መንግሥት የፋይናንስ ተቋማት ከአርሶ አደሩ ይልቅ በሕንጻ ግንባታ ለተጠመዱ ባለሀብቶች ብድር እየሰጡ ካሉበት ሁኔታ ወጥተው ለገንዘቡ ባለቤት ለአርሶ አደሩ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያደርጉ በተደጋጋሚ አስገንዝቧል፡፡ ይህ የመንግሥት ማሳሰቢያ በፋይናንስ ተቋማቱ ተደምጦ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተቋማቱ አርሶ አደሩን ተደራሽ ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ለግብርናው ዘርፍ የሚቀርቡት ፋይናንስ እየጨመረ መምጣቱን መንግሥትም አረጋግጦታል፡፡

መንግሥት ለዘርፉ እድገት ማነቆ የሆኑትን ችግሮች ፈጥኖ መፍታቱን ቀጥሎበታል፡፡ ለእዚህም በቅርቡ በአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ላይ የወሰደው ርምጃ ይጠቀሳል፡፡ ባለፈው ዓመት በአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እና ሥርጭት ላይ ክፍተት ታይቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ መንግሥት ይህን ክፍተት ለመድፈን ዘንድሮ በማዳበሪያ ግዥና አቅርቦት ላይ አስቀድሞ መሥራት ጀምሯል፡፡ በእዚህም ለ2016/17 የምርት ዘመን 23 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ እየሠራ ይገኛል፡፡ ከዚህ ውስጥም አንድ ሚሊየን 327 ሺ 574 ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ግዥ የተፈጸመ ሲሆን፣ የቀሪው ግዥም በሂደት ላይ ነው፡፡

ዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ የጫነችው የመጀመሪያዋ መርከብም በቅርቡ ጅቡቲ ወደብ መድረሷን ተከትሎ በግብርና ሚኒስትሩ የተመራ የልዑካን ቡድንም ማዳበሪያ ለማጓጓዝ እየተደረገ ያለውን ጥረት ሰሞኑን በጅቡቲ ተገኝቶ ተመልክቷል፡፡ ይህም መንግሥት የማዳበሪያ ግዥ በወቅቱ ከመፈጸም በተጓዳኝ የማጓጓዝ ሂደቱ የደረሰበትን ደረጃ እየተከታተለ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ በአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ክትትል ላይ እየወሰደ ያለው ይህ ሁሉ ርምጃ፣ ለግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት እድገት ያለውን ቁርጠኝነት በተጨባጭ ያረጋገጠበት ሌላ ወሳኝ መንገድ ነው፡፡

መንግሥት ቀደም ሲልም ይህን ቁርጠኝነቱን በሰብል ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ተባዮችን በወቅቱ ለመከላከል እንዲያስችል በኬሚካል መርጫ አውሮፕላኖች አቅርቦት ላይ አሳይቷል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እንደ አንበጣ፣ ግሪሳ ወፍ የመሳሰሉት ጸረ ሰብል ተባዮች በቡቃያና በደረሰ ሰብል ላይ ጉዳት ሲያደርሱ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ረጅም ጊዜ ሲወስድና ትልቅ አጀንዳ ሆኖ ሲያነጋግር እንደነበር ይታወሳል፤ ጸረ ሰብል ተባዮቹን ለመከላከል የኬሚካል መርጫ አውሮፕላኖችን በትብብር ለማግኘት የተለያዩ ሀገሮችን እስከ መጠቀም መደረሱ ይታወቃል፡፡ ለሰብል ተባይ መከላከሉ ሥራ አርሶ አደሩ ብቻ ሳይሆን የከተማ ነዋሪዎችን፣ የመከላከያ ሠራዊትንና የመሳሰሉትን የኅብረተሰብ ክፍሎች በማስተባበር ይሠራ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተለያዩ አካባቢዎችና ወቅቶች የተከሰቱ የተምች፣ የአንበጣና የግሪሳ ወፍ መንጋዎችን በቅድሚያ በአርሶ አደር ደረጃ በመከላከል ከዚህ ያለፈውን ደግሞ በአውሮፕላን ኬሚካል በመርጨት መከላከል እየተቻለ ነው፡፡ ጸረ ሰብል ተባዮች በሰብል ላይ ያደርሱ የነበረውን ጉዳት መቀነስ መቻሉ ለምርትና ምርታማነቱ ማደግ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ መንግሥት በእዚህ በኩል ሀገሪቱ አቅም ማጎልበት የቻለችበትን ሁኔታ በፍጥነት መፍጠሩ ለግብርናው ዘርፍ ያለው ቁርጠኝነት ሌላው መገለጫ ነው፡፡

መንግሥት የግብርናውን ዘርፍ ዋና ዋና ማነቆዎች በተለይም አነጋጋሪ ሆነው የቆዩ ችግሮችን ለመፍታት የሄደባቸው ርቀቶችና የተገኙት ተጨባጭ ውጤቶች የቁርጠኝነቱ መገለጫዎች ናቸው፡፡ ችግሮች ዳግም ችግር እንዳይሆኑ ማድረግ መቻልም በራሱ በርግጥም ቁርጠኛ መሆንን ያመለክታል!

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You