ሀገራዊ ምክክሩና ፖለቲካ ፓርቲዎች

ሀገራችን ካላት ረጅም ዕድሜ አንጻር ጥቂቷን 100 ዓመት ብቻ ወደኋላ ዘወር ብለን ብንመለከት ፖለቲካችን መገፋፋትና መጠፋፋት የሰለጠነበት ነው፡፡ በእያንዳንዱ ፖለቲካዊ ሽግግር ብዙዎች ሕይወታቸውን፣ አካላቸውን፣ ንብረታቸውን አጥተዋል፡፡

ጥያቄዎችን ሠላማዊ በሆነ መንገድ ከማንሳት፤ በጠረጴዛ ዙሪያ ከመፍታት፤ በሰከነ መንገድ ለችግሮቻችን መፍትሔን ከመፈለግ ይልቅ ጎራ ለይተን ጦር እየተማዘዝን፤ ሰብዓዊና ቁሳዊ ዋጋ እየከፈልን አለን፡፡ ኢኮኖሚያችንንም እያዳከመው ይገኛል፡፡

የመጣንበትን መንገድ ለልጆቻችን ላለማውረስ፤ ለዘመናት አንድ ቦታ ደጋግመን እንድንረግጥ ካደረገን የጦርነት አዙሪትና የቁርሾ ፖለቲካ መውጣት ይገባናል፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ፣ በችግሮቻችን ላይ በመምከር፣ ልዩነቶቻችንን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት ስንችል ነው፡፡

እንደ ሀገር መግባባት ባልቻልንባቸው፣ አቋም ይዘን ጎራ በለየንባቸው ጉዳዮች ላይ መምከር እንደሚያሻን በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ዘንድ ታምኖበት ሀገራዊ ምክክሩን ይመራ ዘንድ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሟል፡፡

ኮሚሽኑ ዓላማዎቹን ከግብ ለማድረስ ለብሔራዊ ምክክሩ ስኬት አስፈላጊ የሆኑ ቅድመ ዝግጅቶችን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ሠላምን የሚሻው የኢትዮጵያ ሕዝብም ምክክሩ «ሀገራዊ ችግሮቻችንን ይፈታልናል» «ያቀራርበናል» «ያግባባናል» ብሎ ትልቅ ተስፋን ጥሎበታል፡፡ በምክክር ኮሚሽኑ ለሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር የፖለቲካ ፓርቲዎች ከባለድርሻዎች መካከል ይገኙበታል፡፡

አቶ ሙባረክ ረሺድ፣ በነፃነትና እኩልነት ፓርቲ አመራርና የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት አባል ናቸው። ሀገራችን ካሳለፈችውና ካለችበት ፖለቲካዊ ሁኔታ አኳያ ብሔራዊ ምክክሩ ከአስፈላጊም በላይ ነው ብለው ያምናሉ፡፡

በሀገራችን ለረጅም ጊዜ ቁርሾ የነበሩ እንደ ሀገር ልንስማማባቸው ሲገባ በልዩነት የቆምንባቸው ብዙ ጉዳዮች መኖራቸውን ያነሱት አቶ ሙባረክ፣ ባለፉት ጊዜያት በሀገራችን የሀገራዊ ምክክር ጉዳይ ትኩረት ሳይሰጠው የቆየ ቢሆንም፣ አሁን ግን ሀገራዊ ምክክር የማካሄድ አስፈላጊነት ላይ መንግሥትም አምኖበት በኮሚሽን ደረጃም ራሱን የቻለ ተቋም ተቋቁሞ ምክክሩን ለማካሄድ እየተሄደበት ያለውን ሂደት ፓርቲያቸው በተስፋ እንደሚያየው ገልጸዋል፡፡

ተከተል አጋፋሪ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ሶሻሊስት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሲሆኑ፣ ፓርቲያቸው ለሀገራችን መፍትሔ የሚያመጣው ሀገራዊ ምክክር እንደሆነ ከሌሎች ይህን ሃሳብ ከሚጋሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመሆንና በተናጠልም በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያነሳ እንደቆየ አንስተው፣ ፓርቲያቸው ምክክሩ ለሀገራችን ትልቅ መፍትሔ ያመጣል ብሎ ተስፋ እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡ ሀገራችን ከገባችበት አለመረጋጋት፣ ጥርጣሬ፣ አለመተማመንና እርስ በእርስ አለመከባበር ሊያወጣት የሚችለው ውይይት ነው የሚል አቋም እንዳለውም ያነሳሉ፡፡

እርሳቸው እንዳሉት፣ ሀገራችን ያለችበት ሁኔታ ተስፋ የሚያስቆርጥ ቢመስልም፣ የሰው ልጅ ከፈጣሪ ዘንድ የመመካከርና ችግሮቹን በራሱ የመፍታት ተፈጥሯዊ ባህርይ የተሰጠው ነውና የኢትዮጵያ ሕዝብም ይህን ተጠቅሞ መፍትሔ ማምጣት ይችላል የሚል አቋም አላቸው፡፡

የፖለቲካ ፍላጎቶች ሕዝቡ መፍትሔ ከሚሻባቸው ጉዳዮች ጋር ፈጽሞ መቀላቀል የለባቸውም በማለት፣ ይህ ካልሆነ ግን፣ ምክክሩ የተፈለገውን መፍትሔ ሊያመጣ እንደማይችል ለዚህም መንግሥትና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሕዝቡን ሊያስቀድሙና ከታችኛው ማኅበረሰብ የሚነሳውን ጥያቄ ወደ መድረክ እንዲያመጡ፤ አጀንዳ ሊሆኑ የሚገባቸው ጉዳዮች ሳይደመጡ እንዳይቀሩ በማድረግ በኩል ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተከተል(ዶ/ር) ጠይቀዋል፡፡ ምክክሩ በተገቢ መልኩ ከተያዘና አካታችና አሳታፊ ሆኖ ከተመራ ውጤታማ የማይሆንበት ምክንያት እንደሌለም አበክረው ይናገራሉ፡፡

የምክክሩን አሳታፊነት በተመለከተ አቶ ሙባረክ፣ መላው ኢትዮጵያውያን፣ መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ሌሎችም አካላት ይህንን ምናልባትም መልሰን ልናገኘው የማንችለውን ዕድል ሊያበላሹ ከሚችሉ ነገሮች መጠበቅና ለጋራ መፍትሔ በንቃት መሳተፍ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ከምክክር ኮሚሽኑ አባላት አመራረጥ ጋር ተያይዞ ቅሬታዎች ቢኖሩንም እንደ ሀገር ለሀገራዊ ምክክር ሂደት አዲስ መሆናችንን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በሂደት እየተማርንና እየለመድን እንሄዳለን በሚል መርህ የምክክሩን ሂደት ለማገዝና በሂደቱም ለመሳተፍ እንደ ፓርቲ ቁርጠኛ አቋም እንዳላቸው የገለጹት አቶ ሙባረክ፣ በተግባርም እንደ ፓርቲ ሂደቱ ላይ ያሉ እንከኖችን ከመንገር ጀምሮ፣ በሌሎችም ተግባሮች ሂደቱን እያገዙ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ፣ (ኢሶዴፓም) እንደ አንድ ባለድርሻ አካል ምክክሩን በተስፋ እንደሚጠባበቅ የተናገሩት ተከተል (ዶ/ር)፣ በተግባርም ፓርቲው ኮሚሽኑ በሚጋብዛቸው መድረኮች ሁሉ ከየአደረጃጀቱ ሰዎችን በመወከል እያሳተፈ እንደሚገኝና፤ ለተሳታፊዎችም ሥልጠናዎችንም በመስጠት አቅም እየገነባ እንደሚገኝ ገልጸው፤ በግልም እንደ ፓርቲም ለሀገራዊ ምክክሩ ያላቸውን ዝግጁነት ገልጸዋል፡፡

ሀገራዊ ምክክር የሚካሄደው በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ነው ያሉት አቶ ሙባረክ፤ በሀገሪቱ ውስጥ ነፍጥ ያነገበ አካል እያለ እንደ ሕዝብ ምክክር አደርጋለሁ ማለት ይከብዳል፤ ችግሮችን በነፍጥ ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ ሁለቱም ወገኖች ልዩነታቸውን ወደ ሀገራዊ ምክክሩ ማምጣት መፍታት ይገባቸዋል፡፡ እርሳቸው እንዳሉት፣ ውይይት የሚካሄደው ነፍጥ ያነገቡ ጉዳዮች ላይም ሆደ ሰፊ ሆኖ በመቀራርብ ለመፍታት ነው፡፡

አቶ ሙባረክ እንደተናገሩት፣ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘንድም የጦርነት አጀንዳን ትቶ ችግሮች የሚፈቱልኝ በጦርነት ሳይሆን በውይይት ነው ብሎ ማመንና፣ ሜዳውንም ለዚህ ዝግጁ ማድረግ ይጠበቃል፡፡

አቶ ሙባረክ፣ ምክክሩ የሁሉንም ትብብር የሚሻ እንጂ የተቋቋመው ኮሚሽን ብቻውን ሊያሳካው የሚችል እንዳልሆነ አስምረውበታል፤ ኮሚሽኑ ሀገራዊ ምክክሩን አመቻች ሲሆን፣ ስኬታማነቱ ግን በሁሉም ባለድርሻ አካላት እጅ ነው የሚለውንም አክለዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በአንድ ወቅት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት ሃሣብ፣ እንደ ብልጽግና ፓርቲ በሀገራችን ሀገራዊ ምክክር እንዲደረግ ሙሉ ቁርጠኝነት እንዳለው በማንሳት፣ ኮሚሽኑን ከሚመሩ ሰዎች ጥቆማ ጀምሮ ኮሚሽኑን በማዋቀር እና በማደራጀት ሕዝብን አሳታፊ ባደረገና ተጠሪነቱም ለሕዝብ ተወካዮች ሆኖ እንዲቋቋም የተሄደበት ሂደት ለዚህ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

በቀጣይም እንደ ገዢ ፓርቲ በምክክር ሂደቱ የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማድረግ ትልቅ ቁርጠኝነት እንዳለውም ገልጸዋል፡፡ አቶ አዲሱ፣ በምክክር ሂደቱ የሀገራችን ፖለቲካ ከሁከት፣ ከጎዳና ላይ ነውጥና ከጠብመንጃ አፈሙዝ ተላቆ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ እንደሚመጣና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደቱም ወደ ተሻለና ወሳኝ ወደ ሆነ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግረው ያላቸውን ጽኑ እምነት ገልጸዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋው እውን ይሆን ዘንድ ከዚህኛውና ከዚያኛው ጫፍ እንድንቆም ባደረጉን ጉዳዮቻችን ላይ ለመምከር እንትጋ፤ ብሔራዊ አንድነታችንን በማጠናከር ልጆቻችን ሠላም ወጥተው የሚገቡባት፤ አዛውንቶች የሚጦሩበት ከጦርነት ተላቃ ሠላም የሰፈነባት ሀገርን ለትውልድ እናውርስ!

ዮርዳኖስ ፍቅሩ

 አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You