በቱሪዝም ሀብቶች – የአዲስ አበባ ከተማ ድርሻ

የኢትዮጵያ መንግሥት ቱሪዝም ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት የሚኖረውን ድርሻ ለማሳደግ ልዩ ልዩ ስልቶችን በመንደፍ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል። በዚህ መነሻም በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዋና ዋና ምሰሶ ከሆኑ ዘርፎች አንዱ ቱሪዝም ተደርጓል። አዳዲስ ማስፈፀሚያ ሕጎችን፣ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን እና የልማት እቅዶችን በማውጣትም የዘርፉን አቅም ለማሳደግ እየተሠራ ስለመሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በዋናነትም ኢትዮጵያ ያላትን የመስህብ ሀብቶች በማስተዋወቅ፣ የመዳረሻ ልማት ፕሮጀክቶችን በማስፈፀም ከዓለም አቀፍ የቱሪስት ፍሰት ድርሻ ተጠቃሚ ለመሆን እየተሠራ ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመንግሥት በኩል በዘርፉ እየተተገበሩ ያሉ የመዳረሻ ልማት ሥራዎችም የዚሁ እቅድ አካል ናቸው።

የኢትዮጵያን የቱሪዝም መስህቦች ከማልማትና ከመጠበቅ ባሻገር የማስተዋወቅ ተግባር በእጅጉ አስፈላጊ ነው። ሀብቶቹን ከሀገር ውስጥ ጀምሮ ለመላው ዓለም ማስተዋወቅ የቱሪስት ፍሰትን ጭምሮ ኢኮኖሚያዊ አቅምን ለማሳደግ ይረዳል። በዚህ ረገድ መንግሥት ተገቢ ያላቸውን ስልቶች ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል። ከእነዚህ ውስጥም በዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽኖች፣ ኮንፍረንሶች እና ልዩ ልዩ መድረኮች ላይ በመገኘት የኢትዮጵያን የቱሪዝም የመስህብ አማራጮች ማስተዋወቅ አንዱ ነው::

ከዚህ በተጨማሪም በሀገር ውስጥ ትላልቅ ዓውደ ርዕዮችን፣ ኮንፍረንሶችን እና የንግድና የባዛር ትርኢቶችን በማዘጋጀት የገበያና ትውውቅ ሥራ ያከናውናል። እነዚህን መድረኮች በዲጂታል አማራጭና በመገናኛ ብዙኃን በማሰራጨትም ኢትዮጵያ ያሏትን የቱሪዝም ሀብቶች ተደራሽ በማድረግ የጎብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግ እየተሠራ ነው።

በያዝነው የ2016 በጀት ዓመት የቱሪዝም ሀብቶችን ከማስተዋወቅ አንፃር ልዩ ልዩ መድረኮች ተካሂደዋል፤ እየተካሄዱም ይገኛሉ:: ከእነዚህ ውስጥ የቱሪዝም ሚኒስቴር በሳይንስ ሙዚየም እያካሄደ ያለው ለአንድ ወር የሚዘልቅ ዓውደ ርዕይ አንዱ ነው። በመላው ሀገሪቱ ያሉ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሀብቶችን በአንድ መድረክ ላይ በማምጣት ሲያስተዋውቅ የቆየው ይህ ዓውደ ርዕይ የፊታችን ጥቅምት 28 ይጠናቀቃል።

ከዚህ በተጨማሪ ባሳለፍነው መስከረም ወር ላይ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን በስካይ ላይት ሆቴል ያዘጋጀው ዓውደ ርዕይ በአፍሪካ ሀገሮችና በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የቱሪዝም ባለድርሻዎች የተሳተፉበትና በዲጂታል ማስተዋወቅ ረገድ ውጤት የታየበት ነበር። እነዚህ መድረኮች አገሪቱ በተፈጥሮ፣ በታሪክ፣ በባሕልና በልዩ ልዩ የመስህብ ሀብቶች ያላትን አቅም ለማሳየት አስችለዋል።

ከላይ ካነሳናቸው የቱሪዝም ሀብት ማስተዋወቅ (visibility) ተግባሮች በተጨማሪ ተከታታይነት ያላቸው ተመሳሳይ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው። ከእነዚህ ውስጥ ተጠቃሽ የሆነው ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማን የቱሪዝም ሀብቶች የሚያሳየውና የዓለም የቱሪዝም ሳምንትን ምክንያት በማድረግ በመስቀል አደባባይ ለሦስት ቀን የተዘጋጀው መርሐ ግብር ነው።

ይህ መድረክ ኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ አዲስ አበባ ያላትን የቱሪዝም ሀብቶች ከማስተዋወቅ ባሻገር ሀብቶቹን ወደ ኢኮኖሚያዊ አቅም “እንዴት ማሳደግ ይቻላል” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የሞከረ ስለመሆኑ ተመልክተናል። በተለይ በአዲስ አበባ ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት በዘርፉ የተመዘገቡ ስኬቶች እንዲንፀባረቁበት ተደርጓል። የዛሬው የባሕልና ቱሪዝም አምዳችን በዛሬው ባሕልና ቱሪዝም ዓምዱ በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ዓመታት የተገኙ ውጤቶች ምን እንደሚመስሉ ይመለከታል።

የአዲስ አበባ ከተማን የቱሪዝም ሀብቶችና እየተሠሩ ያሉ ተግባራት ለማሳየት በማሰብ በመስቀል አደባባይ በቱሪዝም ሳምንት ዝግጅት ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የሥራ ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር ዓባይ ከተማዋ አያሌ የቱሪስት መዳረሻዎች ባለቤት መሆኗን ጠቅሰው፣ መስህቦቹን በአግባቡ በመለየት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ ከተማ እና የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የሁሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅ አመልክተዋል። ኢትዮጵያ ካሏት ሰው ሰራሽ፣ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መስህቦች በተጨማሪ አዲስ አበባ ከተማ ወደ ቱሪስት መስህብነት እየተለወጠች እንደሆነና ከነበረችበት በእጥፍ ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውንም ይገልፃሉ።

እየተከናወኑ ከሚገኙ የልማትና የማስተዋወቅ ሥራዎች መካከል በምሳሌነት አዲስ አበባ የነበራትን የአረንጓዴ ሽፋን ከሁለት ነጥብ ስምንት በመቶ ወደ 15 በመቶ በማሳደግ ከተማዋን ከአየር ንብረት መዛባት በከፍተኛ ሁኔታ መታደግ የሚቻልበት ሁኔታ መፈጠሩን ይገልፃሉ። በዚህም ልዩ ልዩ መዳረሻዎችንና ፓርኮችን በማልማት ውጤታማ ሥራ መከናወኑንም ተናግረዋል:: በቱሪዝም ዘርፍ ብዙ ያልተሠራና እምቅ አቅም እንዳለ በማንሳት ሃብቶቹን ማወቅና ማልማት እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ቡዜና አልቃድር አዲስ አበባን ከቱሪስት መተላለፊያነት ወደ ቱሪስት መዳረሻነት ለመቀየር በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውንና እየተሠሩም እንደሚገኙ ይናገራሉ። አገልግሎት እየሰጡ ያሉ የአንድነት ፓርክ፣ የእንጦጦ እና የሸገር ፓርኮች እንዲሁም ግንባታው በፍጥነት እየተጠናቀቀ ያለው የአዲስ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽንና ኤግዚቢሽን ማዕከል የዚህ ማሳያ መሆናቸውን ያነሳሉ። በከተማችን ብሎም በሀገራችን ያሉትን እምቅ የቱሪዝም አቅሞችን በማልማት ወደ ቱሪዝም መስህብነት ለመቀየር፣ የለሙትን የቱሪዝም መስህቦችን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ጎብኚዎች በማስተዋወቅ ወደ ውጭ ምንዛሪ ለመቀየር የእያንዳንዱ ባለድርሻ አካልን ንቁ ተሳትፎ እንደሚጠይቅም ይገልፃሉ።

እንደ አፈ ጉባኤዋ ገለፃ፤ በከተማችን የሚገኙ የቱሪስት መስህቦችን በማልማት፣ የውጭ ጎብኚዎች በከተማዋ ያላቸውን የቆይታ ጊዜ በማራዘምና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ ይገባል። በተጨማሪም የከተማዋ ነዋሪ በቂ የመናፈሻና የመዝናኛ ስፍራ እንዲኖር እየተሰሩ ባሉ ስራዎች በመሳተፍ፣ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ለትውልድ የሚተርፍ አሻራ ለማሳረፍ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የአዲስ አበባ ባሕል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሣው በበኩላቸው “የከተማችንን የቱሪዝም ሃብቶች በማስተዋወቅ ሁላችንም የዘርፉ ባለቤቶችና አምባሳደሮች መሆን ይጠበቅብናል” ብለዋል:: ዶክተር ሂሩት እንደሚሉት፤ መላው የከተማዋ ነዋሪ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ የቱሪዝም ሀብቶችን ጠንቅቆ በማወቅ ሁሉም የከተማዋ የቱሪዝም አምባሳደር በመሆን አዲስ አበባ ጽዱ፣ ውብና ለጎብኚዎች የተመቸች ከተማ እንድትሆን አበክሮ መሥራት ይጠበቅበታል።

በርካታ ሀገሮች ቱሪዝምን የውጪ ምንዛሪ ምንጭ በማድረግ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግርና ለውጥ ለማረጋገጥ የሚያስችል ከአገልግሎት ዘርፍ ውስጥ ቀዳሚውን ድርሻ የሚወስድ ኢንዱስትሪ አድርገውታል ሲሉ ጠቅሰው፣ ይህንን አቅም መጠቀም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል::

የአዲስ አበባ ባሕል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሃፍታይ ገብረእግዚአብሔር የአዲስ አበባን እምቅ የቱሪዝም ሀብቶች ለማስተዋወቅና እየተሠራ ያለውን ሥራ ለማሳየት የተዘጋጀውን መድረክ አስመልክቶ እንዳሉት፤ የቱሪዝም ዘርፍ በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ውስጥ ከኬሚካል እና ነዳጅ ቀጥሎ ሦስተኛው ዋነኛ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ኢንዱስትሪ ነው። ቱሪዝም የውጪ ምንዛሪ ምንጭ በመሆን የበርካታ ሀገራት መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግርና ለውጥ ለማረጋገጥ የሚያስችል ከአገልግሎት ዘርፍ ውስጥ ቅድሚያ ድርሻ የሚወስድ ኢንዱስትሪ ነው:: በመሆኑም ኢትዮጵያም ያላትን ይህን ሀብት በማስተዋወቅና በማልማት ከዘርፉ ተጠቃሚ ልትሆን ይገባል።

“ከተማችን አዲስ አበባ የበርካታ ተፈጥራዊ እና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም መስህብ ፀጋዎች ባለቤት ነች” የሚሉት አቶ ሃፍታይ፤ ከዚህ ባሻገር ያሏትን እምቅ የቱሪዝም ሃብቶች አልምቶ በከተማዋ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ፋይዳ ሊያመጣ በሚችል መልኩ መጠቀም የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ ተደርሷል ነው ያሉት:: ይህንንም በመረዳት እንደተቋም የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን በማከናወን ውጤት እየተመዘገበ መሆኑንም ይገልፃሉ:: በዚህ መሠረት ባለፉት ሦስት ዓመታት በተከናወነ ተግባር ለአምስት ሺህ 112 የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አዲስ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ፣ ለ14 ሺህ760 ተቋማት ደግሞ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት እድሳት ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል። ይህ ተግባር በቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ከአገልግሎት አሰጣጥ አንፃር የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲሻሻሉ የራሱን አስተዋፅዖ እንደነበረው ይናገራሉ::

የሀገር ውስጥ እና የውጪ ጎብኚዎችን ብዛት በቁጥር አስደግፈው የሚናገሩት አቶ ሃፍታይ፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት (2013-2015ዓ.ም) የአገር ውስጥ ጎብኚ ቁጥር 14 ሚሊዮን 484 ሺህ 381 እንደደረሰ ይገልፃሉ። ወደ ከተማዋ የገባው የውጪ አገር ጎብኚ ቁጥርም አንድ ሚሊዮን 085 ሺህ 129 መሆኑን ያነሳሉ።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ከውጪ ቱሪስቶች ወደ ከተማው ኢኮኖሚ 64 ነጥብ 06 ቢሊዮን ብር ፈሰስ ተደርጓል:: ለዚህ ስኬት መመዝገብ የከተማው አስተዳደር አዳዲስ የመዳረሻ ልማት ፕሮጀክቶች ትኩረት መስጠቱ፤ በከተማችን ያለው ሰላም እና የኅብረተሰቡ እንግዳ ተቀባይነት በጉልህ ይጠቀሳሉ::

“ትኩረት ተደርጎ ከተሠሩት ሥራዎች መካከል ለከተማችን ኅብረተሰብ በዘርፉ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ላይ ነው” የሚሉት ኃላፊው፣ በዚህም ለ34 ሺህ 143 የከተማዋ ሥራ አጥ ወጣቶች በቋሚና በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉን ይገልፃሉ::

አቶ ሃፍታይ እንዳስታወቁት፤ ቱሪዝም በባሕሪው ሰው ተኮር ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በቀጣይም የከተማዋን ሕዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮክቶችን በመቀየስና ተግባራዊ በማድረግ፣ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ጎብኚን ቁጥር በመጨመርና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራቱን በማሻሻል አዲስ አበባ ከዘርፉ በሚፈለገው ልክና ደረጃ መጠቀም እንድትችል ትኩረት በመስጠት በጋራ መሥራት ይጠበቃል:: በተለይ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ የቱሪስት መስህቦችና የመዳረሻ ቦታዎችን ዜጎች እንዲጎበኙ ለማድረግ በማስተዋወቁ ረገድ አምባሳደር ሆነው መሥራት ይጠበቅባቸዋል::

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የቱሪዝም ዘርፍ በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ውስጥ ከኬሚካል እና ነዳጅ ቀጥሎ ሦስተኛው የዓለማችን ዋነኛ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ኢንዱስትሪ ነው። ከዘርፉ ሰው ተኮር ባሕርይ የተነሳ ከ10 ሰዎች ለአንዱ የሥራ እድል በመፍጠር 319 ሚሊዮን የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ይነገራል። የዓለምን ሰባት በመቶ የውጭ ንግድና 760 ቢሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ይሸፍናል። በጥቅሉ 10 በመቶ ለሀገራዊ ምርት (GDP) አስተዋፅዖ በማበርከት በተለይም በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት የውጭ ንግድ ሚዛን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ድርሻ እየተጫወተ ይገኛል::

ይህንን ከከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ድርሻ በማስመልከትና የሚፈጥረውን በጎ ተፅዕኖ በማሰብ በየዓመቱ የዓለም የቱሪዝም ሳምንት ይከበራል። ዘንድሮም በዓለም ለ44ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ36ኛ ጊዜ “ቱሪዝም ለአረንጓዴ ልማት:: አረንጓዴ ልማት ለቱሪዝም” (Tourism and Green Investment) በሚል መሪ ቃል ከመስከረም — ጀምሮ እየተከበረ ይገኛል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በመተባበር ለሦስት ተከታታይ ቀናት ይህንን ቀን በልዩ ልዩ ዝግጅቶች አክብሮታል።

 ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You