መኅልዬ መኅልዬ ዘ ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጄታ፤

መኅልዬ መኅልዬ ዘሰሎሞን ከሁሉም የሚበልጥ የሰለሞን መዝሙር ማለት ነው:: የሁለት ፍቅረኛሞች ንግግር ተደርጎም ይወሰዳል:: የፍቅረኞች ንግግር በግጥም ነውና ምት፣ ዜማ አለው:: ሰለሞን ስለ ሙሽራውና ሙሽሪት፣ ስለፈጣሪና ስለ ቤተ ክርስቲያን የዘመራቸውን 1005 መዝሙሮችን ይመለከታል:: ሙሽራው ልዑል እግዚአብሔርን ሲወክል ሙሽራይቱ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት:: መኅልይ ለዘብ ያለ ወረብ አይነት በፍጥነት የሚዘመር ጥዑም ዜማ ነው ::

መዝሙሮቹ በተለያየ ስልት ዜማ ቢደጋገሙም ያው ስለፈጣሪና ቤተ ክርስቲያን ክብር፣ ቅድስና የሚመስክሩ ናቸው:: ይህ መጣጥፍ ታላቁን “የማሽላውን አባት” የሚዘክር፣ የሚያወድስና የሚያከበር ሆኖ ስለአገኘሁት “መኅልየ መኅልይ ዘ ፕሮፌሰር ገቢሳ እጄታ” ማለትን መርጫለሁ ::

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ብሔራዊ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ዘርፍ ሜዳልያ በዋይት ሐውስ ካበረከቱላቸው አንዱ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጄታ ናቸው። ሽልማቱ የተሰጠው ባጠቃላይ ለ21 አሜሪካውያን ተመራማሪዎች ነው። ሽልማቱ በሳይንስ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ላበረከቱ የሚሰጥ ነው ይለናል የእንግሊዙ ዜና ማሰራጫ ቢቢሲ።

ከዘንድሮው ተሸላሚዎች መካከል አነስተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ንጹሕ የመጠጥ ውሃ በማቅረብ እንዲሁም በረሃን የሚቋቋሙ ዕፅዋት በማብቀል የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ እንደሆኑ ፕሬዚዳንት ባይደን በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተናግረዋል። “የሰው ልጆችን አኗኗር የሚያሻሽሉ ግኝቶች ናቸው። እንደ ካንሰርና ፓርኪንሰንስ ያሉ ሕመሞችን ለማከም አስተዋፅዖ ያበረከቱም ይገኙበታል” ብለዋል።

ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊው ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጀታ የተሸለሙት በዕፅዋት ዘረ መል ምሕንድስና ሲሆን፣ የበረሃን የአየር ንብረት የሚቋቋሙ ዝርያዎች በማግኘታቸው ሽልማቱ ተበርክቶላቸዋል። ይህ ግኝት የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጥ ነው። ፕሮፌሰር ገቢሳ በአሜሪካ ኢንዲያና በሚገኘው ፕሪዲዩ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ ናቸው። በዩኒቨርስቲው የዓለም አቀፍ ምግብ ዋስትና ክፍል ዋና ዳይሬክተር ሲሆኑ፤ በዕጽዋት ማርባት፣ በዕፅዋት ዘረ መል እንዲሁም ዓለም አቀፍ ግብርና አንቱታን ያተረፉ ጉምቱ ሊቅ ናቸው።

ተሸላሚዎቹ በግኝታቸው ለሳይንሳዊ እመርታ ፈር ቀዳጆች እንደሆኑ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በዋይት ሐውስ ንግግራቸው ጠቅሰዋል። “ሁላችሁም ተሸላሚዎች ስለ ጀግንነታችሁ እናመሰግናለን”። ከተሸላሚዎቹ መካከል ከተለያዩ አገራት አሜሪካ የሄዱ ሳይንቲስቶች እንደሚገኙበት በመጥቀስም “አሜሪካ የሚገልጻት አንድ ቃል ቢኖር ዕድሎች ነው” ብለዋል ፕሬዚዳንቱ። ከዚህ ዕድል ተቋዳሽ ከሆኑት ሳይንቲስቶች መካከል አንዱ ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጄታ ናቸው። ተወልደው ያደጉት ኢትዮጵያ ነው። በዓለም በዘረ መል ምርምር አሉ ከሚባሉ ባለሙያዎች ግንባር ተጠቃሽ ናቸው። ከዚህ ቀደም የዓለም ምግብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በዋናነት ምርምር የሚያደርጉት በማሽላ ላይ ነው።

አሜሪካ በሳይንስ ዘርፍ የመሪነት ሚና እንደምትጫወት፤ ተሸላሚዎቹ የዚህ አካል እንደሆኑም በንግግራቸው ጠቅሰዋል። “እዚህ የተገኛችሁት ተሸላሚዎች አሜሪካውያን ውጤት ሳይገኝ የሚረቱ ወይም ጥረት የሚያቆሙ እንዳልሆኑ ማሳያ ናችሁ” ብለዋል። ፕሮፌሰር ገቢሳ የዕፅዋት ዘረ መል፣ የዘረ መል ለውጥና ዘር ሐረግ በሚያጠናው ዘርፍ (Plant Genetics) ነው ምርምር የሚያደርጉት። ሽልማቱ የተበረከተላቸው ድርቅ መቋቋም የሚችል የማሽላ ዝርያ በማዋቀር ነው። “ለሚሊዮኖች የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጥ ግኝት ነው” በሚል በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል።

በሳይንስና ፖሊሲ ዘርፍ እንዲሁም በምጣኔ ሀብት ማሻሻል ረገድ ፕሮፌሰር ገቢሳ ያበረከቱት አስተዋፅዖ ለአርሶ አደሮች የተሻለ ሁኔታ መፍጠር የቻለ እንደሆነ ተገልጿል። “ሀገራትን የሚያጠናክርም ነው” በማለት ስለ ምርምራቸው በዋይት ሐውሱ የሽልማት ሥነ ሥርዓት ተገልጿል። እአአ በ2009 ‘ወርልድ ፉድ ፕራይዝ’ የተሸለሙት ማሽላን በማዳቀል ድርቅ እና አረም የሚቋቋም ለማድረግ ባደረጉት ምርምር ነበር። ይህ ጥናታቸው ከሰሐራ በታች ባሉ ሀገራት በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለመመገብ ማስቻሉን ፕሪዲዩ ዩኒቨርስቲ በድረ ገጹ ላይ አስፍሯል።

ፕሮፌሰር ገቢሳ“ውጤት መር ምርምር በማድረግ ነው የሚታወቁት። በታዳጊ አገራት ከ500 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን የሚመግበውን ማሽላ ድርቅ የሚቋቋም ማድረግ ችለዋል” ይላል ድረ ገጹ። ማሽላ በምርት ወቅት ሊገጥመው የሚችለውን ችግር በመፍታት የተመጣጠነ ይዘት እንዲኖረው እንዲሁም ድርቅና ቅዝቃዜንም እንዲችል በማድረግ ምርምራቸው ይታወቃሉ። ማሽላው ከአረም በተጨማሪ የዕፅዋት ሕመምን መቋቋም የሚችልም ነው። ዘረ መላቸው የተሻሻለ የማሽላ ዓይነቶችን በአሜሪካ እንዲሁም በአፍሪካ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ተመራማሪው አስችለዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን በአሜሪካ የመንግሥት ተቋማትን በሳይንስና ፖሊሲ በማማከር አገልግለዋል። የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እአአ በ2010 የአፍሪካ የሳይንስ ልዑክ አድርገው ሾመዋቸው ነበር። በ2013 በቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ባንኪ ሙን የሳይንስ አማካሪ ቦርድ ሆነው ተሹመው ነበር። ከሮኬፌለር ፋውንዴሽን፣ ከፋኦ እና ሌሎችም ተቋማት ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።

የዓለም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሠሩት ሥራ በዓለም መድረክ ስማቸውንና የሀገራቸውን ስም ያስጠሩ ፀሐፊ፣ አርታኢ፣ መምህር፣ አማካሪ እና ተመራማሪ የዓለም ሎሬት ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጀታን ከረዥሙ የሕይወት ጉዞአቸው በጥቂቱ ይዘንላችሁ ቀርበናል ይለናል አዲስ ማለዳ:: ሎሬት ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጀታ ከአዲስ አበባ 62 ኪሎሜትር በስተምዕራብ ርቀት ላይ በምትገኘው ኦሎንኮሜ በምትባል መንደር በ1950 እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር ተወለዱ:: የቄስ ትምህርታቸውን በአካባቢያቸው ሲከታተሉ ቆይተው የአንደኛ ደረጃ ትምህርት በአካባቢያቸው ስላልነበረ 20 ኪሎሜትር በእግራቸው ተጉዘው ተከታትለዋል::

የዓለም ሎሬት ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጀታ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጅማ የግብርና ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ የተከታተሉ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በዕፅዋት ሳይንስ ከዓለማያ ኮሌጅ በ1973 ዓ.ም ወስደዋል:: እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በ1976 በዕፅዋት ሳይንስ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን እንዲሁም በ1978 በዕፅዋት ማዳቀል እና ዘረመል ኢንጂነሪንግ አሜሪካ ከሚገኘው ፔድሩ ዩኒቨርስቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል::

ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጀታ ከሁለት መቶ በላይ የጥናት ጽሑፎችን ለኅትመት ያበቁ ሲሆን፤ አራት መጽሐፎችን የአርትዎት ሥራ ሠርተዋል:: ላለፉት 28 ዓመታት በአሜሪካ በሚገኘው ፔድሩ ዩኒቨርስቲ ያገለገሉት የዓለም ሎሬት ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጀታ ዩኒቨርሲቲው አሉኝ ከሚላቸው ተመራማሪዎችም አንዱ ናቸው:: ዶክትሬታቸውን ከተመረቁ በኋላ ወደ ሱዳን በመሄድ ማሽላ ላይ ምርምራቸውን ቀጥለዋል:: በምርምራቸውም ድርቅን መቋቋም የሚችል የማሽላ ዝርያ ለዓለም ማኅበረሰብ ማበርከት ችለዋል::

በ150 እጥፍ ምርታማነትን የሚጨምር የማሽላ ዝርያን ለዓለም አበርክተዋል:: ድርቅን መቋቋም የሚችል የማሽላ ዝርያ ላይ ባስገኙት ውጤት ከአምስት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ አፍሪካውያን የምግብ ዋስትንን ማረጋገጥ ችለዋል:: ጥናታቸው በዚህ ሳያበቃ በአፍሪካ ምርታማነትን በ40 በመቶ የሚቀንሰው እስትራጋ የሚባለውን አረም መቋቋም የሚችል የተሻሻለ የማሽላ ዝርያን ኢትዮጵያን ጨምሮ ለ12 አፍሪካ ሀገሮች ማቅረብ ችለዋል:: ለእነዚህ እና መሰል የምርምር ሥራዎቻቸው ከ17 በላይ ዓለም አቀፍዊ፣ አህጉራዊ እና ሀገራዊ ሽልማቶችን አግኝተዋል:: እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2009 World Food Nobel Prize የተሸለሙ ሁለተኛው አፍሪካዊ ለመሆን በቅተዋል:: African Nationality Science Hero Award ከተሸለሙ አፍሪካዊ ሰባት ተመራማሪዎችም አንዱ መሆን ችለዋል::

ከሰባ በላይ በሚሆኑ ዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ ተቋሞች ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ላይ የሠሩት የዓለም ሎሬት ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጀታ የዓለም ሕዝብ ቁጥር በጨመረ ቁጥር የምግብ ፍላጎት እየጨመረ ይመጣል ይህን ለመቋቋም ሳይንስ ፣ ቴክኖሎጂ እና የምርምር ፈጠራ ውጤቶች በመጨመር ይሄንን ችግር መቋቋም የግድ የሚል ነው ይላሉ:: ፕሮፌሰር ገቢሳ ኤጀታ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2011 በፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የዓለም አቀፍ የምግብ እና ግብርና ልማት ቦርድ ውስጥ እንዲሁም ከ2014 ጀምሮ በዩናይትድ ኔሽን ሴክሬተሪ ጄነራል ባኒኪሞን የ UN የሳይንስ አማካሪ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ::

ነገርን ነገር ያነሳዋልና እግረ መንገዴን ስለአልተዘመረላቸው የመቀሌው ዩኒቨርሲቲው የግብርና ፕሮፌሰር ላነሳ ወደድሁ። የምማረው ከገበሬ ነው ስለሚሉት ተመራማሪ ፕሮፌሰር ምትኩ ኃይለ። ፕሮፌሰር የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መሥራች እና የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ዓለም አቀፍ የግብርና ሽልማት አሸናፊ እንደነበሩ ይታወሳል። ዓለም አቀፍ የግብርና እና ላይፍ ሳይንስ ከፍተኛ ተቋማት ማኅበር (GCHERA)ፕሮፌሰር ምትኩ ኃይለ እና የጌንት ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ማርክ ቫን ሞንታጉ የ2021 የዓለም ግብርና ሎሬቶች በማለት ሸልሟቸዋል።

የሽልማቱ ሥነ ሥርዓትም፣ በቻይና ውስጥ በበይነ መረብ የተካሄደ ሲሆን፣ ፕሮፌሰር ምትኩ በአፈር እና ግብርና ልማት፣ በዕፅዋት መዓዛ፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ በሠሯቸው ሥራዎች መታጨታቸው ተገልጿል። መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ባዘጋጀው የእንኳን ደስ አለዎት ፕሮግራም ላይ፣ ፕሮፌሰሩ በኢትዮጵያ “በግብርና፣ የሳይንስ ትምህርት እና ሳይንሳዊ ጥናቶች ላይ ከፍተኛ አስተዋፅዖ” አድርገዋል ብሏል።

በወቅቱ የስልክ እና ኢንተርኔት አገልግሎት በተቋረጠባት የትግራይ ክልል ውስጥ ይገኙ የነበሩት ፕሮፌሰር ምትኩ ኃይለ፣ ‘የ2021 የዓለም ግብርና ሎሬት በመሆን አሸንፈሃል፤ ሽልማቱን የምትቀበል እንደሆን አሳውቀን’ የሚለው የኢሜይል መልዕክት እስከደረሳቸው ዕለት ስለ ሽልማቱን እንደማያውቁ ይናገራሉ። ይሄንን መልዕክት ሲያዩ ‘ማጭበርበር ይሆን?’ ብለው ተጠራጥረው እንደነበር እና መደነቃቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ኢንተርኔት በማይገኝበት ሁኔታ ውስጥ ምን እየተካሄደ እንዳለ ማወቅ አይቻልም፤ መልዕክቱም ከማላውቀው ሰው ስለሆነ የደረሰኝ ማረጋገጥ ነበረብኝ። አሁን ባለንበት ሁኔታም እንደዚህ አይነት ነገር ስለማልጠብቅ ሽልማቱ አስደንቆኛል”ሲሉ በወቅቱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከ20 ዓመታት በፊት በላቲን አሜሪካ የሚገኘው ኧርዝ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት የነበሩ እና አሁን የጂሸራ ሊቀመንበር እና ፕሬዚዳንት የሆኑትን ጆሴ ዛግሉል፣ ሽልማቱ ላይ ፈርመውበታል። ይህንን ሲመለከቱ እውነት ነው ብለው ማመን እንደቻሉ የሚናገሩት ፕሮፌሰር ምትኩ “ወደ ቤት ሄጄ ባለቤቴ እና ልጄን ሳሳያቸው ሁላችንንም አስደነቀን” ይላሉ ፕሮፌሰሩ፣ እስከ አሁን በግል እና ከሌሎች የሙያ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን የሠሯቸው ከ200 በላይ የምርምር ሥራዎችን አሳትመዋል። ፕሮፌሰር ምትኩ፣ በ1993 ዓ.ም የመቀሌ ግብርና ኮሌጅ እንዲቋቋም ያደረጉ ሲሆን፣ ከ2000 እስከ 2011 ባሉ ዓመታት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት በመሆን አገልግለዋል።

ላለፉት ለ30 ዓመታት በኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አስተዳደር እና የሰው ኃይል ግንባታ እንዲሁም በተፈጥሮ ሃብት እና የአፈር ልማት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያላቸው ፕሮፌሰር ምትኩ ማን ናቸው?ፕሮፌሰር ምትኩ ዕፅዋት እና አረንጓዴ አካባቢን ስለሚወዱ የተፈጥሮ ተሟጋች ናቸው። በሆነ አጋጣሚ ሰዎች ለጥርስ መፋቂያ ነው ብለው ሲቆርጡ፣ ወይም የመንገድ ዳር ማስዋቢያ የሆኑ ሳር እና አበባዎችን ረግጠው አልያም ቀንጥሰው ሲሄዱ፣ ውሃ በቸልተኝነት ሲፈስ ካዩ ይቆጣሉ፤ ይጣላሉ።

የፕሮፌሰሩ የምርምር ሥራዎች የአፈር ለምነትን ማረጋገጥ ላይ ትኩረት ያደርጋሉ። አብዛኛዎቹ ሥራዎቻቸው ትግራይ ላይ ትኩረት ያደረጉ ሲሆኑ፣ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የሚገኘውን የአፈር አይነት በማጥናት መጀመራቸውን ይናገራሉ። ሕዝቡ ለረጅም ዘመናት ኑሮው ግብርና ላይ ተመሥርቶ ስለኖረ ሰፋፊ የግብርና አካባቢዎች ተሸርሽረው እና ይዘታቸውን ቀንሶ ነበር።

ባለፉት 30 ዓመታትም በተፈጥሮ ሃብት ልማት ከገበሬው ጋር በመሥራት የግብርና ምርትን ማሳደግ፣ የአፈር ለምነት እና የውሃ ምንጮች እንዲጎለብቱ፣ የከርሰ ምድር ውሃ መጠን ከፍ እንዲል፣ የመስኖ እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም እንዲያድግ እና የደን ሽፋን እንዲጨምር ማድረግ ተችሏል ብለዋል። ፕሮፌሰር ምትኩ እነዚህ ሥራዎችን ወደ ዓለም አቀፍ መድረኮች በመውሰድ እውቅና እንዲያገኙ ማድረግ ላይ ትልቅ ሥራ አከናውነዋል።

ለዚህም ከአምስት ዓመት በፊት ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል በረሃማነት በማጥፋት ላይ በተሠሩ ሥራዎች ተሸላሚ ሆናለች። “እኔ የገበሬን ችግር በማየት ከገበሬው ነው የምማረው፤ እነዚህ ሥራዎችን ከእሱ ተምረን ሳይንስ ጨምረን ስንሰጠው ኑሮውን የሚያሻሽል ለውጥ ማምጣት እንደሚችል አሳይተውኛል። ለውጥ ካላመጡ ደግሞ እኔ የተጠያቂነት ኃላፊነት ይሰማኛል” በማለት ምሑራን የሚሠሯቸው ጥናቶች ኅብረተሰቡን ያሳተፉ መሆን አለባቸው ይላሉ።

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)

አዲስ ዘመን ጥቅምት 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You